በጤናው ዘርፍ በተሠሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ በተሠሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሀረላ አብዱላሂ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ ያስተናገደችው ዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባዔ “ኢኖቬሽን ለሁለንተናዊ የጤና ሽፋን” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ እንዳሉት፤ የኢኖቬሽን የጤና ክብካቤ፣ ጥራት፣ የጤና ፍትሃዊነት ፣ የህሙማን ደህንነት እና የጤና አመራር ጉዳይ የማንደራደርበት ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያ እነዚህን ፕሮግራሞች የጤና ትራንስፎርሜሽን መሠረት አድርጋ እየሠራች ነው። በዚህም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአብዛኛዎቹ ክልሎች በጤና ተቋማዊ የወሊድ መጠን ሽፋንን ከ80 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ኢትዮጵያ የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዷን አመልክተው፤ የክትባት ሽፋን ተደራሽነት ከ90 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። ባለፉት 10 ዓመታት የወባ ሞት ከ60 በመቶ በላይ መቀነስ ተችሏል። ውጤቱ ሊገኝ የቻለውም በዋናነት ፈጠራን እንደ ስትራቴጂ ችግር መፍቻ በመቀበላችን ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሚከናወኑ የጤናው ዘርፍ አገልግሎቶች ተደራሽነት ማስፋት እንደተቻለ ጠቁመው፤ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በቴሌሜዲስን እና በጤና ኤክስቴንሽን የታገዘ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው። የጤና ዘርፉን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅም በትልቅ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ በሰው ኃይል ልማትና ሌሎች ዘርፎች ለውጥ መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ጉባዔው ከእውቀት ልውውጥ ባለፈ የጋራ ተግባር መድረክ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

በቀጣይነትም በዘልማድ የሚሠሩ ሥራዎችን በማዘመን ያልተሻገርናቸውን ችግሮች ለመፍታት ኢኖቬሽንንና ጥራት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መሥራት ይኖርብናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለዚህም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ አጋርነት ያስፈልገናል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎት ጥራትን፣ የታካሚ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና በችግሮች የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት ኢኖቬሽን ቅንጦት ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለድርሻ አካላት ኢኖቬሽንን ባህል በማድረግ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እያደገ የመጣውን የጤና ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ በዘርፉ የኢኖቬሽን ሥራዎችን ለማስፋት በትብብር እየተሠራ ይገኛል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው የስታርት አፕ ረቂቅ አዋጅ ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ የኢኖቬሽን ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል። የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ኦውን ካሉዋ(ዶ/ር)፤ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በኢኖቬሽን መደገፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የጤና ተደራሽነትን ለማስፋፋት በርካታ ሥራዎችን እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ፈጠራን (ኢኖቬሽን) በመጠቀም ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት መሥራትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ በእናቶች ጤና፣ በወባ እና ሌሎች ብሔራዊ የጤና መርሃ ግብሮች ላይ በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በጤናው ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና ዘርፉን ለማሳደግ ፈጠራ፣ ጥራትና ደህንነትን ያካተተ ዘላቂ የጤና ሥርዓትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጠንካራና ፍትሃዊ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽን እና ጥራት ጉባዔ ኢትዮጵያ እና የዓለም ጤና ድርጅት በትብብር ያዘጋጁት ሲሆን፣ በጤና ኢኖቬሽን፣ በታካሚ ደህንነት፣ በአገልግሎት ፍትሃዊነት እና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጎ እስከ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።

ፋንታነሸ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You