በጋምቤላ ክልል ሰላም በመስፈኑ የተሻለ ግብር መሰብሰብ እንደተቻለ ተገለጸ

ጋምቤላ፡- የጋምቤላ ክልል ያለበትን የጸጥታና ሰላም ችግሮች መቅረፍ በመቻሉና ሰላም በመስፈኑ የተሻለ ግብር መሰብሰብ ተችሏል ሲል የጋምቤላ ክል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

የጋምቤላ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኮት ዴቪድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ክልሉ የፀጥታ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ አሁን ላይ የክልሉ ችግር እየተፈታ ይገኛል፡፡ ይህም የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ አስችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ 11 ወራቱ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል፡፡ በቀጣይ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የክልሉ ጸጥታና ሰላም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ገቢ ለሀገር መሠረተ ልማት ግንባታዎች ዋነኛ የጀርባ አጥንት መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ግብርን ጠንክሮ መሰብሰብ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 11 ወራት ሁለት ነጥብ 81 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ እንደቻለ ጠቅሰው፤ በዚህም የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት የእቅዱን 94 ነጥብ 95 ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

አምና ሁለት ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር ገቢ መብሰቡን አስታውሰው፤ የዘንድሮው በጀት ዓመት የ11 ወራት አፈጻጸም ብቻ ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ652 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰቡን አመልክተዋል።

በክልሉ ከቀጥታ እና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች ገቢ እንደሚሰበሰብ ጠቁመው፤ በክልሉ አኙዋክ ዞን እና መጃንግ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎች በማዕድን ላይ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑንና ከዚህም 50 በመቶ ገቢው ለክልሉ 10 በመቶ ማዕድኑ ለተገኘበት አካባቢ መልሶ ልማት ላይ የሚውል ነው ብለዋል።

በወረዳዎች ገቢ የሚሰበሰብባቸውን ደረጃ-ሀ፣ ደረጃ-ለ እና ደረጃ-ሐ ግብር ከፋዮች በአግባቡ ለመከታተል አቅም ያለው የተደራጀ እና በእቅድ የሚመራ ባለሙያ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ቸንኮት፤ ይህንንም ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ከሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አቶ ቸንኮት ዴቪድ ጠቁመዋል። ቢሮው ከክልሉ ፋይናንስ ቢሮ፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ፣ ፕላንና ልማት ቢሮ እንዲሁም ጉምሩክ ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You