
በዓለማችን እጅግ ተነባቢና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነው የ”Foreign Affairs” መጽሔት ሰሞነኛ ዕትሙ “The Committee to Run the World” ወይም “ዓለምን የሚመራ ደርግ ወይም ኮሚቴ” በሚል ይዞት የወጣው ዕትም ድፍን ዘረ አዳምን እያነጋገረ ነው። በነገራችን ላይ ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። በምድራችን በተመሳሳይ ጊዜ ለሲአይኤም፣ ለኋይታወስም፤ለዳውኒግ ስትሬትም፣ ለኤም አይ ፋይፍ፤ ለሞሳድም፣ ለቤት ሀናሲ፤ ወዘተረፈ እንደ “ፎሪን አፊርስ”መጽሔት ቤተኛ መሆን የቻለ የለም።
የዓለማችን መሪዎች፣ ታዋቂ ልሒቃንና ተመራማሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የስለላው ዓለም ተዋንያን እይታቸውንና አመለካከታቸውን ስለሚያጋሩበት ብስራቱም ሆነ ሟርቱ ጠብ አይልም። እኤአ ከ1922 ዓ.ም ወደ አንባቢዎቹ መድረስ የጀመረው ይህ ታሪካዊ መጽሔት የፖሊሲ ጉዳዮችን ይሁን ጂኦፖለቲካን አልያም ዓለማቀፍ ጉዳዮችን ያንሳ ባላየና ባልሰማ የሚያልፉት መጽሔት አይደለም።
የልዕለ ኃያላን ሀገራት መሪዎች፣ ታዋቂ ምሁራን፣ ጄነራሎች፣ የቲንክታንክ መሪዎች እና የዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ አባላት ሀሳብ የሚሰናዘሩበት እና በገለልተኛነቱ በሚወሳው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነቶች ምክር ቤት የሚታተም መሆኑ አመኔታን ያተረፈለት ስለሆነ የአሜሪካ ልዕለ ኃያልነት ማክተሙንና ዓለማችን ከዚህ በኋላ በሶስትዮሽ ማለትም ቻይናንና ራሺያን ባካተተ መንገድ እንደምትመራ ሲነግረን በሌላ በኩል የአሜሪካ የዓለም ፖሊስነት ማክተሙን ይነግረናል።
ታዋቂው ፓንአፍሪካኒስት ፕሮፌሰር ሉሙምባ አፍሪካውያን ዓለምን ለመከተል ሳይሆን ለመምራት “ፎሪን አፊርስ”ን ማንበብ አለባቸው ያሉት ለዚህ ነው። “ፎሪን አፊርስ”ን ዕይታው ምዕራባውያን ተኮርና በሊህቃን የሚዘወር ነው የሚል ትችት ቢቀርብበትም፤ ሁልጊዜም ከቻይና፣ ከራሺያ፣ ከአፍሪካና በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ጸሐፍትን ይጋብዛል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ታዋቂ ልሒቃን እንደ ፖሊሲ፣ ጂኦፖለቲክስና የዓለማቀፍ ጉዳዮች መመሪያ የሚቆጥሩት የ”ፎሪን አፊርስ” መጽሔት የአሜሪካ የ80 ዓመታት የልዕለ ኃያልነት ዘመን አብቅቶ፤ ዓለማችን ሶስት አባላት ባሉት ኮሚቴ ወይም ደርግ መመራት ጀምራለች።
የአሜሪካ ልዕለ ኃያልነት አብቅቶ ዓለም በሶስት ማዕዘናዊ መሪዎች እየተመራች ነው። አዎ! ምድራችን በቻይና፣ በራሺያና በአሜሪካ በኮሚቴ እየተመራች ነው። አሜሪካ እንዳሻት የምትፈነጭበት ዓለም ላይመለስ ተሸኝቷል። አሁን ጥያቄው ቻይና ልዕለ ኃያልነቱን መቼ ጠቅልላ በመዳፏ ስር ታደርጋለች የሚለው። ላለፉት 80 ዓመታት ማለትም የድህረ 2ኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ መር አሰላለፍ ፍጹም እየተገለባበጠ ነው። በዚህ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ፣ በርዕዮተ ዓለም ክፍፍልና በተከሰቱ ቀውሶች የተነሳ ቻይናንና ራሺያን ያካተተ አዲስ ዓለምአቀፉ ሥርዓት እየተፈጠረ ነው።
ከዚህ በኋላ የዓለም ሥርዓት በሶስቱ ኃያላን ማለትም አሜሪካ፣ ቻይና እና ራሺያ በትብብር ይሁን በፉክክር አልያም በግጭት ይመራል። ለዚህ ደግሞ ሕጋዊ ያልሆነ ተቀባይነት ወይም እውቅና ያልተሰጠው ነገር ግን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ራሳቸውን እንደ ኮሚቴ ቆጥረዋል ወይም የዲፋክቶ ኮሚቴው አባል አርገው ሹመዋል። በአሜሪካ ይመራ የነበረው የሊበራል የዓለም ሥርዓት ከመንኮታኮቱ ባሻገር መረጋጋት ተስኖታል። በዚህ ሥርዓት ምትክ በመንግሥታቱ ድርጅት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው፤ ግዙፉ ኢኮኖሚና ወታደራዊ ኃይል ያላቸው ቻይናና ራሺያ የዓለምን ሥርዓት እንደ አዲስ እየበየኑት ይገኛል።
ይህ ኮሚቴ አሜሪካ መር ከነበረው የሊበራል አሰላለፍ ፍጹም የተለየ ነው። የጋራ መለያም ሆነ ርእይ የለውም። በምትኩ ከአሜሪካ ልዕለ ኃያልነት ወደ ባለብዙ ኃያላን ወይም መልቲፖላር እየተቀየረ ያለውን ዓለም ሚዛን ያስጠብቃል። በታሪክ ባለብዙ ኃያላን የዓለም አሰላለፍ ሁለት ወይም አንድ ልዕለ ኃያል ከሚመራው አሰላለፍ በባሰ የአለመረጋጋትና የግጭት ምንጭ ነው።
አሁን ባለማችን እየሆነ ያለው ይህ ነው። አንድ ልዕለ ኃያል ሀገር የለም ማለት ኃያላኑ ፍላጎታቸውን ለመጫን፤ የዓለም ሥርዓትንና አሠራር በሚፈልጉት መንገድ ለመበየን ሽኩቻ ውስጥ ይገባሉ። በአሜሪካ፣ በቻይና እና በራሺያ መካከል ያለውን ትንቅንቅ ልብ ይሏል። እነዚህ ኃይላት ለዓለማችን ሰላምና መረጋጋትም ሆነ ለትርምስ የሚሆን ኃይል እጃቸው ላይ አለ።
የዛሬን አያድርገውና አሜሪካ የሊበራሉን አሰላለፍ ላለፉት 80 ዓመታት ወታደራዊ ኃይሏን፣ ዲፕሎማሲንና አኮኖሚዋን በመጠቀም፤ ኔቶን፣ የዓለም ባንክን፣ ዓለማቀፉን የገንዘብ ተቋም ወይም IMFን ከነጻ ገብያና ዲሞክራሲያዊ እሴት ጋር በማጃመል ዓለምን መርቷል። ዛሬ እድሜ ለትራምፕ አሜሪካ ትቅደም ! በሚል ስጋት ውስጥ ገብቷል። በአሜሪካ ውስጥ በተፈጠረ ውጥረት፣ ኢፍትሐዊ ኢኮኖሚ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ እምነት መታጣቱ የአሜሪካንን የቅስም ወይም የሞራል ልዕልና ክፉኛ ጎድቶታል።
በኢራቅና በአፍጋኒስታን የተካሄደው ጦርነት ስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ እንዲያደርግ ማስገደዱ እንዳለ ሆኖ የተፈጠረው የመነጠል ስሜት የአሜሪካን ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንዲቀንስ አድርጓል። አሁን አሁን አሜሪካንን እያስጨነቀ ያለው ከቻይና ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት AI፣ በኳንተም ኮምፒውቲንግ እና በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ የተገባው ፉክክር ነው።
ይሁንና ዛሬም ፍላጎትን ለመጫን የሚያስችል ኃይልና አሰላለፍ አለ። ኔቶ፣ የአውስትራሊያ፣ የእንግሊዝና የዩኤስ AUKUS፣ ሕንድን ጃፓን አውስትራሊያንና ዩኤስን ያቀናጀው Quadrilateral Security Dialogue ወይም QUAD እና የጃፓን የደቡብ ኮሪያና የአውሮፓ ሕብረት ትብብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የዶላርና የወል ስትሬት የበላይነት ሲሊካን ቫሊ የፈጠራውን ዓለም ዛሬም በፊታውራሪነት እየመራ መገኘቱ፤ ሆሊውድ፣ ዓለማቀፍ ሚዲያው እና ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ሌላው የአሜሪካ ተጽዕኖ መገለጫ ናቸው። ወዲህ በሺ ጂንፒንግ በአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራ ግን ደግሞ ነጻ ገበያን የሚያቀነቅነው የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ዓለማቀፉን
አሰላለፍ ለመፐወዝ ሌት ተቀን እየተጋ ነው። የትራምፕን የታሪፍ ፖለቲካ እንዴት አፈር ድሜ እንዳበላው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ኢኮኖሚያዊ ውህደትን በማካሄድና ጦሯን በማዘመን፤ እነ ዓለም ባንክን የሚገዳደር እንደ የእስያን የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ Asian Infrastructure Investment Bank በምህጻረ ቃሉ AIIB የተሰኘ ትይዩ ተቋም እና የቀበቶና መንገድ ልማት the Belt and Road Initiative (BRI) በመተለም በዓለም ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እየፈጠረች ነው። በደቡባዊ ፓሲፊክ በኢንዶ ፓሲፊክ
እና በደቡብ ቻይና ባሕር እንዲሁም በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድና የውሃ ክልል በሌሎች አዋሳኝና አጎራባች ሀገራት ተጽዕኖ በማሳደር ቀጣናውን ለመቆጣጠር ሌት ተቀን እየሠራች ነው። አንዳንድ ጊዜም ትንኮሳ እየፈጸመች ነው።
ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እንደ ቻይና የመከላከያ ኃይሉ ላይ በየዓመቱ በመቶ ቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር በማፍሰስ እየተጠናከረ የመጣ የለም። የዘመኑ የኃያልነት መገለጫ በሆነው የቴክኖሎጂ ዘርፍም ማለትም በG5፣ በኳንተም ኮምፒውቲንግ፣ በAI፣ በሴሚ ኮንዳክተር፣ በታዳሽ ኃይል እና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻይና አሜሪካን እየመራችና እየተገዳደረች ነው። ሆኖም ለቻይና ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ነው ማለት አይደለም። የአረጋውያን መብዛትና የሰራተኛ እጥረት ወይም የሕዝብ ጽፋዊ ወይም Demographic Crisis ቀውስ ፈተና ሆኖባታል። ሌላው የቻይና የራስ ምታት ኢኮኖሚዋ የምዕራባውያን ገበያ ጥገኛ መሆኑ እና ነገረ ሥራዋ በአውሮፓ በአሜሪካና በሕንድ አለመታመኗ እንዲሁም እስያውያን ቻይናን እንደ ስጋት መቁጠራቸው ነው ይለናል ፎሪን አፊርስ መጽሔት።
ቻይና በአጠቃላይ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ያለፈችበትን የውርደት ታሪክ እንደገና ለመጻፍ ሌት ተቀን እየሰራች ነው። የአሜሪካንና የአጋሮቿን ከበባ መስበር፤ የደቡባዊ ቻይና ባሕርን ወታደራዊ መናኸሪያዋ ማድረጓ፤ የ2008 ኦሎምፒክ እና በ2025 በቻይና የተመረተ
ዕቅዷ ታሪክን እንደገና የመጻፍ ግቧ አካል ነው። የጠርማሿ ራሺያ ነገር ግን ከሁለቱ ኃያላን በተለይ ኢኮኖሚዋ ተፎካካሪ አይደለም። ሆኖም የኒውክሌር የጦር መሳሪያ የታጠቀች፤ ሰፊ የነዳጅ ሀብት ያላትና ተገማች አለመሆኗ ከልዕለ ኃያላኑ ጎን አሰልፏታል።
የድህረ 2ኛው የዓለም ጦርነትን አሜሪካ መር አሰላለፍ እና የኔቶን መስፋፋት አምርራ መቃወሟ፤ ጆርጂያን ክሬሚያንና ዩክሬን መውረሯ፤ የተዘባ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሟ፤ የሳይበር ጥቃቷና በሀገራት ምርጫ የምትፈጽመው ጣልቃ ገብነት ሌላው የተጽዕኗዋ መገለጫ ነው። ራሺያ በዓለም ላይ ከባድ ተጽዕኖ መፍጠር ብትችልም እራሷም ለተጽዕኖ መጋለጣ አልቀረም። ኢኮኖሚዋ በ10ሺዎች የሚቆጠር ማዕቀብ የተጣለበት መሆኑ እና ኢኮኖሚዋ የነዳጅና የኢነርጂ ጥገኛ መሆኑ ለተጽዕኗ ተጋላጭ አድርጓቷል። ራሺያ ከቻይና እና በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ውጭ ዲፕሎማሲያዊ መገለል ላይ መሆኗ ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው። መሪዎቿ በዓለማቀፉ የጦር ወንጀል መከሰሳቸው ዕንቅስቃሴያቸውን ገድቦታል።
የሶቪየት ሕብረት መበታተን የዛሬዋን ራሺያ እንደ ጥላ እየተከተለ ያባንናታል። ፑቲን በዚህ የዞረ ድምር ወይም ሀንጎቨር ነው ለሕዝባቸው ሶቪየት እንደፈረሰችው ራሺያም አደጋ ላይ እንዳትወድቅ ስልጣኔዋን መጠበቅ፤ የምዕራባውያንን መስፋፋት ማስቆም አለብን የሚሉት። ኮሚቴው ወይም አሜሪካ፣ ቻይና እና ራሺያ የርዕዮተ ዓለም እና የስትራቴጂክ ልዩነት ቢኖራቸውም በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዮች አሉ ይለናል “ፎሪን አፊርስ”መጽሔት።
የኒውክሌር ጦር መሳሪያን መስፋፋት በመቆጣጠር እና የጦር መሳሪያ እሽቅድምድምን በማስቆም ለዓለም ሰላም በጋራ በመሥራት ሊተባበሩበት የሚገባ ዋናው ጉዳይ ነው። ሌላው ሊተባበሩበት የሚገባው የጋራ አጀንዳ የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ሶስቱም ሀገራት ከፍተኛ ካርቦን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ይታወቃሉ። በዓለማቀፍ ደረጃ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ፤ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፤ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል እና የሕዋ ምርምርን ለማቀናጀት የእነሱ ተሳትፎ የግድ ነውና ይለናል መጽሔቱ።
ሆኖም በማዕቀብ፣ በታሪፍና በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለመበጠስ በሚደረግ ትንቅንቅ የተነሳ፤ በታይዋንና በቻይና ያለው ፍጥጫ፤ በደቡባዊ ቻይና ባሕር የቻይና ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደገ መምጣት እና የኔቶ መስፋፋት፤ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ውጥረት መከሰቱ አይካድም። ሌላው የሀገራቱ ውጥረት መነሻ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ነው። ሊበራል ዲሞክራሲ ወይስ በአምባገነናዊ አገዛዝ የሚመራ ካፒታሊዝም ይሻላል የሚል ውዝግብ እና በሶሪያ፣ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚያካሂዱት የውክልና ጦርነቶች ውጥረቱን አባብሰውታል።
ይህ መደበኛ ያልሆነ ኮሚቴ የሚሠራው የቅንጅት ሥርዓት አብጅቶ እና ተማምኖ አይደለም። ሥልጣንን ለመጋራት ሲባል ድንገት የተፈጠረ መዋቅር እንጂ ሆን ተብሎ የተመሰረተ አሰላለፍ አይደለም ይለናል የ”ፎሪን አፊርስ”መጽሔት። እያንዳንዱ አባል የተቀሩትን እንደ አስፈላጊ ተቀናቃኙ ነው የሚያቸው። አሰላለፉ አለመረጋጋትን የሚጎነቁል ቢሆንም አንድ ልዕለ ኃያል ሀገር እንዳይፈጠር በማድረግ ደግሞ ሚናውን ይጫወታል።
መጽሔቱ በመጨረሻም የዚህን ኮሚቴ እድል ፈንታዎችን ወይም ቢሆኖችን አልያም ሊሆኑ ይችላሎችን ወይም scenarios ያስቀምጣል። ከቁጥጥር ውጭ ያልሆነ ጠላትነት የመጀመሪያው ሴናሪዎ ሲሆን ሌላው አሰላለፉ አሜሪካና አጋሮቿ በአንድ ወገን ቻይናና ራሺያ በሌላ ወገን ሊሆኑ ይችላል የሚለው ነው። ሌላው እድል ፈንታ ባለ ብዙ የልዕለ ኃያላን አሰላለፍ የአውሮፓ ሕብረት፣ ሕንድ፣ ብራዚልና የአፍሪካ ሕብረት ወደ ፊት ከመጡ የኮሚቴውን ስልጣን ከንቱ ሊያደርጉት የሚለው ሌላው ሴናሪዎ ነው።
አስፈሪውና አስደንጋጩ ሌላው ሊሆን ይችላል ወይም ሴናሪዎ በድንገት ወይም ሆን ተብሎ ሊከሰት የሚችል ግጭት ዓለምን 3ኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ እንዳይዘፍቃት የሚለው ነው። የ”ፎሪን አፊርስ” ሌላው ሲናሪዎ ሲቀጥል ወረርሽኝን ወይም የከባቢ አየር ሙቀትን ለመቀነስ ለሚደረግ ጥረት ትብብር ሊፈጠር ይችላል የሚል ነው።
የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አካል የሆኑ ተቋማትን ማለትም የመንግሥታቱ ድርጅትን፣ G20ን፣ የዓለም ንግድ ድርጅትንና ሌሎች ተቋማት ላይ ማሻሻያ ማድረግ ወይም እንደ አዲስ ማቋቋም ምን አልባት ሁሉንም የሚያግባባ አሰላለፍ በዓለማችን ሊያነብር ይችላል የሚለው የመጨረሻው ሴናሪዮ ሆኖ በመጽሔቱ ተተንብይዋል። “ፎሪን አፊርስ”፤”The Committee to Run the World” በሚለው በዚህ ገራሚና አነጋጋሪ ዕትሙ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል። የመጀመሪያው አሜሪካ፣ ቻይናና ራሺያ ዓመታዊ ምክክር የሚያደርጉበት መድረክ ቢፈጠር የሚል ነው።
ሁለተኛው ምክረ ሀሳብ ደግሞ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ በማድረግ ሕንድ፣ ብራዚልና አፍሪካ አባል ቢሆኑ በኮሚቴው የሚስተዋለውን መሳሳብ ሊያስቀርና ውጥረት ሊያረግብ ይችላል የሚል ይገኝበታል። መጽሔቱ በማጠቃለያው ዓለማችን ከዚህ በኋላ አንድ ልዕለ ኃያል የላትም። በምትኩ በሚፎካከሩና እርስ በርስ በጥርጣሬ በሚተያዩ የአሜሪካ፣ የቻይና እና የራሺያ መሪዎች ትመራለች።
በ21ኛው መክዘ አሜሪካ፣ ቻይናና ራሺያ ዓለማችንን እስከወዲያኛው የሚቀይርና ተጽዕኖው ለነገው ትውልድ የሚተላለፍ ውሳኔዎችን በየፊናቸው እየወሰኑ ይገኛል። ይህ ኮሚቴ ተብዬ ጦርነት ይከላከል አልያም ሰላምን ያዝለቅ ወይም ድንበር ዘለል ተግዳሮቶችን ይፍታ አይፍታ የሰውን ልጅ መጻኢ እድል ግን መወሰኑ አይቀርም። ይሁንና ካልተሳካላቸው ግን በዓለማችን ላይ ቀውስን ከማዋለድ ባሻገር ዘመናዊው የዓለማችን አሰላለፍም ያከትምለታል።
የአሜሪካን የልዕለ ኃያልነትን ዘመን ፍጻሜን ትራምፕ እያፋጠኑት። የተሳሳተው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አሜሪካን ያለአጋር እያስቀሯት ነው በሚል እየተተቹ ነው። ዩክሬንን በተመለከተ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት መንግሥታቸው ከምዕራባውያን በተቃራኒ ከራሺያ ጎን መቆሙ ላለፉት 80 ዓመታት አጋር የነበሩ ሀገራት አቋማቸውን መለስ ብለው እንዲያጤኑ አድርጓል። በኔቶ አባላት እና በአሜሪካ መካከል ንፋስ መግባቱን የታዘቡት ቻይናና ራሺያ ደግሞ አጋጣሚውን በመጠቀም ተገዳዳሪ ኃይል ሆነው እንዲወጡ እያደረጋቸው ነው። ስሁት የሆነው የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ከዓለም ጋር የከፈቱት የንግድ ጦርነት አሜሪካን ለራሺያና ለቻይና ተጽዕኖ አጋልጧታል።
ሻሎም !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም