ታምራት ተስፋዬ
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች። የህዝብ ቁጥሯም ከመቶ ሚሊየን በላይ ልቋል። በመሆኑም ለዘላቂ ልማት ሁሉን አቀፍ የሆነ የትራንስፖርት ሥርዓት ያስፈልጋታል። በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲሆን የተሟላ የመሰረተ ልማት መታገዝ እንዳለበት አሁን የሚታዩት ችግሮች ያስገድዳሉ።
እንደ መንገድ ያለው መሠረተ ልማት በቂ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በከተሞች ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ እያጋጠመ ይገኛል። የትራፊክ መጨናነቁ ጫና በዕለት ተዕለት የሰዎች እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ ነው። ሰራተኞች ወደ ስራ፣ ተማሪዎችም የትምህርት ገበታቸውን ላይ በሰአት እንዳይገኙ በማድረግ ችግሩ ይገለጻል። አምቡላንስ እንኳን የታመሙ ሰዎችን በፍጥነት ወደ ህክምና ለማድረስ እንቅፋት እየሆነ ነው። ችግሩ ተባብሶ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ማረፉ አይቀሬ ነው። መንግስት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ሥራዎችን ቢሰራም ችግሩ አልተቃለለም።
በተለይ አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ዋና መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ እና የዓም አቀፍ ተቋማት መናገሻ እንደመሆኗ መጠን በቂ ሽፋን ወይም ተደራሽ የሆነ፣ ጥራቱን የጠበቀና አማራጭ ያለው መንገድ ሊኖራት እንደሚገባ አያጠያይቅም። ከተማዋ ካላት የተሽከርካሪ ብዛት እና የመንቀሳቀስ ፍላጎት አንፃር ከፍተኛ የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎት እየጨመረ መምጣን መመልከት እንችላለን።
ምንም እንኳን ከሌሎች ሀገሮች አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቁጥር አለው የሚባል መኪና ባይኖርም ቀድሞ ከነበረው የመኪና ቁጥር ጨምሯል። መሰረተ ልማቱ ሳይስፋፋ የመኪናው ቁጥር መጨመር ችግሩን እንዳባባሰው ይነገራል።
የችግሩን አሳሳቢነት በሚመለከት አስተያየታቸውን የሚያጋሩ ነዋሪዎችም ሆነ ምሁራንም በከተማዋ የሚታየው የመንገዶች መዘጋጋትና መጨናነቅ ዘላቂ መፍትሔ በሚሰጥ ልማት የመጣ ቢሆንም አማራጭ መንገዶችን ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ የማድረግ ስራም አብሮ ሊታሰብ እንደሚገባም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በመዲናዋ ችግሩን ያቃልላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት በመከናወን ላይ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተለይም በመዲናዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ላይ ትራፊኩን ለማሳለጥ የሚያስችሉ የውስጥ ለውስጥ አቋራጭ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶችን ገንብቷል።
በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን እየተገነቡ ከሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ከአሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ ተነስቶ ጎተራ ማሳለጫ የሚዘልቀው ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ስራ ይጠቀሳል።
ይህ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክት በሁለት በኩል 320 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ (Tunnel) እና 100 ሜትር ርዝመት ያለው ተሻጋሪ ድልድይ እንዲሁም የፈጣን አውቶብስ መተላለፊያ መስመር (Bus Rapid Transit) እና ስድስት ሜትር የሚረዝም የእግረኛ መንገድን ያካትታል።
ይህ ፕሮጀክት 320 ሜትር ርዝመት ያለው የዋሻ ግንባታ፣ መንገዱ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 45 ሜትር የሚሆን የጎን ስፋት አለው። የግንባታ ስራውን ቻይና ፈርስት ሀይ ዌይ ኢንጂነሪንግ የተባለ የስራ ተቋራጭ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባው ሲሆን፣ የግንባታ ቁጥጥሩንና የማማከር ስራውን ደግሞ ቤስት አማካሪ ድርጅት እያከናወነው ይገኛል።
የመንገድ ፕሮጀክቱን የግንባታ ስራ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ውለታ ቢያዝለትም አሁን ላይ ካለው የፕሮጀክቱ የስራ አፈፃፀም አንፃር ከተያዘለት የጊዜ ገደብ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ያሳያል። ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ማህበራዊ ድረገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ አጠቃላይ ከአሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ ተነስቶ ጎተራ ማሳለጫ የሚዘልቀው ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ 65 ነጥብ 4 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም ላይ ደርሷል።
በዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ 320 ሜትር ርዝመት ያለው የዋሻ ግንባታ ስራ 92 በመቶ የሆነ የግንባታ አፈፃፀም ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ 100 ሜትር ርዝመት ያለው ተሻጋሪ ድልድይ እንዲሁም የፈጣን አውቶብስ መተላለፊያ መስመር እና ስድስት ሜትር የሚረዝም የእግረኛ መንገድን ያካተተ ነው።
አሁን ላይ በተሻጋሪ ድልድዩ ላይ የሚከናወኑ የቋሚ ምሶሶዎችን የማቆም ስራዎች በመገባደድ ላይ ሲሆኑ ከአጠቃላይ ከመንገድ ርዝመት ውስጥ አንድ ኪሎ ሜትር በሚሆነው የግንባታ ክፍል ላይ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ስራ ተከናውኗል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከቂርቆስ፣ ከጎተራ፣ ከጎፋ፣ ከሳር ቤት፣ ከሜክሲኮ እና ከቄራ የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን ከማሳለጡም ባሻገር ለአካባቢውና አጠቃላይ ለከተማዋ የተለየ ገጽታን ያላብሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የፑሽኪን አደባባይ ጎፋ ማዞሪያ -ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም የከተማዋ ምክትል ከንቲባን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የስራ ተቋራጮች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013