መላኩ ኤሮሴ
ምንም እንኳን “ስማርት ሲቲ” የሚለው ቃል ለሀገራችን አዲስ ቢሆንም ሃሳቡ ግን አዲስ አይደለም። አስርታትን አስቆጥሯል። በተለይም እ.አ.አ በ2008 የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የስማርት ሲቲ ሃሳብ እየተስፋፋ መጥቷል። የብዙ ሀገራት መሪዎችን ቀልብም መሳብ ችሏል። ብዙ ሀገራት ሃሳቡን በተግባር በመሞከር ላይ ናቸው።
ስማርት ሲቲ አገልግሎት ለመስጠት እና የከተማ ችግሮችን ለመፍታት ቴክኖሎጂን የምትጠቀም ከተማ ናት- ስማርት ሲቲ። የከተሞች ህይወት እጅግ ውስብስብ ከመሆኑም ባሻገር በከተሞች የሚኖሩ ህዝቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣትን ተከትሎ የነዋሪዎች ጥግግት፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ ፍላጎት መጨመር፣ የህክምና አገልግሎት ፍላጎት መጨመር ተጠቃሽ ናቸው። በመሆኑም በከተሞች የሚስተዋሉ የችግሮች ውስብስብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እየመጣ ነው። እየጨመረም ይሄዳል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ነው የስማርት ሲቲ ሃሳብ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው። ስማርት ሲቲዎች ከተሞች የሚያጋጥማቸው የተለያዩ ችግሮችን ቀላል የማድረግ ጽንሰ ሃሳብ ነው። አንዳንድ ሀገራት በአንድ በኩል ነባር ከተሞችን ወደ ስማርት ሲቲ የማሳደግ በሌላ በኩል አዳዲስ ስማርት ሲቲዎችን እየገነቡ ነው።
ስማርት ሲቲ የሚያጋጥሙ ችግሮችን አርቲፊሻል ኢንተልጀንስ በመጠቀም መፍታትም የስማርት ሲቲ ሃሳብ አንዱ አካል ነው። ስማርት ሲቲ ሃሳቡ የተሻለ የትራንስፖርት እና የማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲሁም ዘላቂ ልማት እና በከተሞች የሚከወኑ በነዋሪዎች ተሳትፎ የሚተገበር ነው።
ሀገራት ስማርት ሲቲዎችን የሚገነቡበት ዋና ዓላማም የከተሞችን እድገት በማስፋፋት፣ ቴክኖሎጂን በማነቃቃት እንዲሁም የኑሮ ጥራትን ለማሻሻል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ተግባር ላይ በማዋል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስፋፋት እና የሰዎችን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል ነው።
ስማርት ሲቲ አራት ሁለገብ ልማቶች አካቶ የሚይዝ ሲሆን፣ እነርሱም ተቋማዊ ፣ አካላዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ናቸው። በረጅም ጊዜ ሂደት ከተሞች እነዚህን በመሳሰሉ ሁለገብ መሰረተ ልማት በማደግ ዘመናዊነታቸውን እየጨመሩ ሲሄዱ ወደ ስማርት ሲቲ ያድጋሉ።
የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ስማርት ሲቲዎች ከሌሎች ከተሞች ከሚለዩባቸው በርካታ ነገሮች አንዱ የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ ጉዳዮች ዙሪያ የሚኖራቸው ሚና ነው። ስማርት ሲቲዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸው ናቸው ከተማዋን የሚፈጥሩት። ከተማዋን በመቅረጽ እና እንዴት እንደምትሰራ አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ ነዋሪዎች ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው።
ስማርት ሲቲዎችን ከመደበኛ ከተሞች የሚለያቸው በርካታ ነገሮች አሉ። አንዳንድ ጊዜ በመደበኛ ከተሞች ውስጥ ያሉ የከተማው ባለስልጣናት አንድ ችግር ስለመኖሩ እና ችግሩ መቀረፍ እንዳለበት እንኳ ላያውቁ ይችላሉ። ግን ስማርት ሲቲ በሆነ ከተማ ውስጥ ከከተማዋ ባለስልጣናት ባሻገር የከተማዋ ነዋሪዎች ስለ ጉዳዩ ማወቅ ከመቻላቸው ባሻገር ለችግሩ መፍትሄዎችን በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
ኢንተርናሽናል ማኔጅመንት ፎር ዴቪሎፕመንት (አይ ኤም ዲ) የተሰኘ ተቋም ከሲንጋፖር ዩንቨርሲቲ ጋር በመሆን በ2019 የሰሩት ጥናት እንደሚያመላክተው በዓለም ላይ 102 ስማርት ከተማዎች የሚገኙ ሲሆን፣ የከተሞቹ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።
በዓለም ላይ የተለያዩ ሀገራት ስማርት ሲቲ ሃሳብን በመጠቀም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የጥበቃ ስራ የማከናወን፣ በሰው አልባ መኪናዎች የትራፊክ አደጋ የመቀነስ፣ በከተሞች ውስጥ የሚከናወኑ እያንዳንዱ ነገር ግልጽነት ያለው እንዲሆን በማድረግ ሙስናን መከላከል ችለዋል።
ኢትዮጵያም ስማርት ሲቲዎችን የመገንባት እቅድ ይዛ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በሚተገበረው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፈ መሪ እቅድ ቢያንስ አንድ ‹‹ስማርት ሲቲ›› እንዲኖራት ታስቧል።
ሀገሪቱ በሁለት መንገድ ስማርት ሲቲዎችን የመገንባት ውጥን ይዛ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። አንድም አዳዲስ ስማርት ሲቲዎችን መገንባት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ባሉት ከተሞች ያለውን አሰራር በማዘመን ወይም ዲጂታላይዝ በማድረግ ወደ ሰማርት ሲቲነት ከፍ ማድረግ ነው።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከዓምና ጀምሮ ሀገሪቱ ቢያንስ አንድ ስማርት ሲቲ እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከተማውን የመገንባት ስራ የአንድ ተቋም ብቻ ሃላፊነት እንዳልሆነም ያምናል። የሁሉም ወገኖችና የመንግስት ሃላፊነት መሆኑንም ጠቁሟል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ እንደተናገሩት፤ አንድ ሀገር ብልጽግና ማማ ወይም የሚያስበው ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሎ የሚለካው ስማርት ሲቲዎችን በመገንባት እና ሌሎች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ማደግ እና ወደሚፈለገው የብልጽግና ማማ መውጣት ካለባት ስማርት ሲቲዎችን ከወዲሁ ማሰብ አለብን ሲሉ ጠቁመዋል።
በተለይ የከተማነት ደረጃ አንዱ መለኪያ ብልጽግና ነው፤ የመሰልጠን መለኪያ ጭምር ነው ያሉት ኢንጂነሯ፤ የሰለጠኑ ከተሞች ስማርት አገልግሎቶች እንዳሏቸው ጠቅሰው፣ ኑሮ እና እንቅስቃሴ ቀላል የሚሆንባቸው፣ ሰላማዊ ከተሞች ሊኖሩን ይገባል የሚል እምነት መያዙን ነው ያብራሩት።
ከተማው የት መሆን አለበት፣ ለምን ይቋቋማል ከሚለው አንስቶ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉም ጠቁመው፤ ይህን አውን የማድረጉ ስራ አንደ ሀገር አጠቃላይ የማህበረሰብና የመንግስት ቅንጅትንና ጥረትን እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
‹‹ደፍረን ልንሰራው የሚገባ ጉዳይ ነው። ስማርት ሲቲ እንዲኖረን ማድረግ አለብን ›› ሲሉ ያስገነዘቡት ሚኒስትሯ፤ ክልሎችም ከተሞቻቸውን ስማርት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አዋጭ በሆነበት ላይ ሁላችንም እንደ መንግስት ተረባርበን እንዲህ አይነቱ ከተማ እንዲኖረን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ የመጣው ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጅያዊ እድገት የሰው ልጅ ታላላቅ ግኝቶችን ያነሳሳ ቢሆንም፤ ግኝቶቹ ግን ለአዳዲስ ችግሮች ምንጭ ሲሆንም ተስተውሏል። ስማርት ሲቲዎችም ለሰው ልጆች በርካታ እድሎችን የሚያጎናጽፍ ቢሆንም የራሱ የሆኑ ተግዳሮቶች አሉት። ከነዚህ ተግዳሮቶች መካከል በስማርት ሲቲዎች አብዛኛው ስራ በበይነ መረብ የሚከናወን በመሆኑ ለመረጃ መንታፊዎች እድል እንደሚከፍት የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። በተጨማሪም ውስብስብ እና እጅግ ውድ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ግንባታ የሚያስፈልገው በመሆኑ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል።
ሁሉም ሰው የበለጠ ምቹ ፣ ሰላማዊና ጤናማ አካባቢን የሚፈልግ ቢሆንም ፣ ማንም ሰው ሁል ጊዜ ክትትል የሚደረግበት ሆኖ ሊሰማው አይፈልግም። በእያንዳንዱ የጎዳና ጥግ ላይ የተጫኑ ካሜራዎች ወንጀልን ለማስቆም ሊረዱ ይችላሉ። ነገር ግን በዚያው ልክ ህጉን በሚያከብሩ ዜጎች ላይ ፍርሃትንና ስጋትን ሊፈጥሩ ይችላሉ።
በማንኛውም ከተማ ውስጥ በሕይወት ጥራት እና በግላዊነት መካከል ሚዛን ሊኖር የሚገባል። ቢሆንም ስማርት ሲቲዎች ግን የህይወት ጥራት የሚጨምር ቢሆንም የግለሰቦች ግላዊ መረጃዎች በአላስፈላጊ ሁኔታ አሳልፎ ይሰጣል በሚል ይተቻል።
እውነተኛ ስማርት ሲቲ በእውነት እንዲኖር እና እንዲበለጽግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ እና በንቃት የሚጠቀሙ “ብልህ” ዜጎች ያስፈልጉታል። በማንኛውም አዲስ ከተማ አቀፍ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክት የአተገባበሩ አካል አንድ አካል ህብረተሰቡን ስለ ጥቅሞቹ ማስተማርን ሊያካትት ይገባል። በመሆኑም የከተማውን ነዋሪዎች ስለ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በየጊዜው ማስተማር እና ግንዛቤውን ከፍ ማድረግ አዳጋች ተግባር ይሆናል።
በሌላ በኩል ስማርት ሲቲዎች መስፋፋትን ተከትሎ ከሚነሱ አንዱ የአካታችነት ጥያቄ ነው። መሰል ከተሞች የሞባይል መተግበሪያዎችን በመጠቀም አብዛኛውን ተግባራት መፈጸምን ትኩረታቸው የሚያደርጉ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የማይችሉትን በተለይም የሞባይል መሳሪያዎችን ወይም መተግበሪያዎችን መጠቀም የማይችሉትንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ያለውን አረጋውያንን አካታች አለመሆኑ ሌላኛው ተግዳሮት ነው።
ስማርት ሲቲዎች ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ግድ ይላል። በተለይም ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመታት ስማርት ሲቲዎችን ለመገንባት እቅድ የያዘች ሀገር እንደመሆኗ መጠን ተግዳሮቶቹን በቅድሚያ መቅረፍ የምትችልበትን አቅም ጭምር ልትገነባ ይገባል። በተለይም የስማርት ሲቲዎች ዋነኛው ተግዳሮት የሆነውን የመረጃ ምንተፋን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል አቅም መገንባት ይጠበቅባታል።
የመረጃ ምንተፋን የመሳሰሉ ህገ ወጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ አካላትን አደብ ሊያስገዛ የሚችል የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ ከተሞቹ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚችል ብቁ እና ንቁ ዜጎችን የሚፈልግ በመሆኑ የዜጎችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎች መከወን ያስፈልጋል።
የስማርት ሲቲ ግንባታ በመንግስት አካል ብቻ ሊሳካ እንደማይችል በዘርፉ ጥናት ያካሄዱ ልሂቃን ያብራራሉ። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በምትመራበት የከተማ ልማት ፖሊሲ ስማርት ሲቲዎች ግንባታ ለማሳካት አዳጋች ነው። በመሆኑም ሀገሪቱ በቀጣይ አስር ዓመታት የወጠነችውን ግብ ለማሳካት የከተሞቹ ልማት በአዳዲስ የከተማ ልማት ፖሊሲዎች እና የመንግስት የግል ሽርክናዎች መመራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013