ፍሬህይወት አወቀ
የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው በሆነው የመኖሪያ ቤት ችግር ዜጎች በእጅጉ እየተፈተኑ ባሉባት አዲስ አበባ ከተማ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን ሲከተል ይስተዋላል:: ይሁንና ችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ ያገኘ ባለመሆኑ ዕለት ዕለት እየተባባሰ መጥቷል:: ይህ ነዋሪዎች ዘወትር የሚያነሱት የመኖሪያ ቤት ጥያቄን ለመመለስ በቅርቡ ከተማ አስተዳደሩ ባደረገው ጥረት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ 201 ቤቶች ተለይተው አካል ጉዳተኛ ለሆኑና እጅግ በከፋ የመኖሪያ ቤት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች በዕጣ አስተላልፏል:: ይህም ለነዋሪዎቹ ትልቅ እፎይታን የሰጠ መሆኑን ከተጠቃሚዎቹ አንደበት አድምጠናል::
ወጣት ዘቢባ ሰኢድ ትባላለች:: ኑሮዋን የመኖሪያ ቤት ችግር እጅጉን በከፋባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካደረገች በርካታ ዓመታትን አስቆጥራለች:: የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው አዲስ አበባ ከተማ የመጣችው:: ለረጅም ጊዜ የኖረችውም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ አሜሪካን ግቢ ውስጥ እንደሆነ ትናገራለች:: በምትኖርበት ቀበሌ ውስጥ የመኖሪያቤት ለማግኘት ብዙ ደክማለች:: በኪራይ ለመኖር አቅሟ አልቻለም:: የነበራት ብቸኛ አማራጭ በግለሰቦች መኖሪያቤት ጥገኝነት መጠየቅ ነበር:: ወጣቷ ችግሯን በተረዱ በጎ ፈቃደኞች ግለሰቦች ቤት ውስጥ ነው ለዓመታት የኖረችው::
ይሁንና ያስጠጓት ሰዎች የልማት ተነሺ ሆነው አካባቢውን ሲለቁ ዘቢባ መውደቂያ አጣች:: ወደ ምትኖርበት ወረዳ በመሄድ ችግሯን ታስረዳለች:: የማያቋርጥ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ የሚቀርብለት ወረዳም ችግሩ ሰፊና ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ለዘቢባና ዘቢባን ለመሰሉ ዜጎች ምላሽ መስጠት አልቻለም:: የቤት ጥያቄዋ ያልተመለሰላት ዘቢባም በአካባቢው ባገኘችበት ቦታ ለሰባት ዓመታት ሸራ ወጥራ ለመኖር ተገዳለች::
ወጣቷ የዓመታት የቤት ጥያቄዋ ከሰሞኑ ምላሽ አግኝቷል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደርሷ በቤት እጦት ሲሰቃዩ ለነበሩ በዕጣ ካስተላለፈው 201 የቀበሌ ቤቶች መካከል ተጠቃሚ መሆን በመቻሏ ዛሬ የልቧ ሞልቷል:: ለሰባት ዓመታት የኖረችበትን ሸራ አንስታ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 ውስጥ በተሰጣት የቀበሌ ቤት ጎኗን አሳርፋለች:: ቤት በማግኘቷ በእጅጉ ደስተኛ መሆኗን በሲቃ ነበር የገለጸችልን:: ከወዲሁም ብዙ ዕቅዶችን አውጥታለች:: በአዲሱ ቤቷ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ኖሮዋን ለመለወጥ ተዘጋጅታለች::
ሌላኛው ዕድለኛ ዋና ሳጅን ንጉሴ ምትኩ ናቸው:: ነዋሪነታቸው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ መርካቶ አካባቢ ሲሆን፣ በዚሁ አካባቢ ለ15 ዓመታት በፖሊስነት እያገለገሉ ይገኛሉ:: ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ናቸው:: ሳጅን ንጉሴ፤ በመኖሪያ ቤት ችግር ምክንያት አራት ልጆቻቸውን ጎንደር ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመላክ ተገደዋል:: ልጆቻቸውን ወደቤተሰቦቻቸው ለመላክ የተገደዱት በቤት ኪራይ ውስጥ ሰፊ ቤተሰብ ይዞ ለመኖር አቅማቸው የማይፈቅድ በመሆኑ ነው:: ልጆች ደግሞ ፍላጎታቸው ሰፊ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ኑሮ የማይቻል እንደሆነ አጫውተውናል::
የኑሮው መወደድ በተለይም የቤት ኪራዩ እጅግ ከባድ ነው የሚሉት ሳጅን ንጉሴ፤ ለቤት ኪራይ እስከ 1500 ብር ድረስ ይከፍሉ እንደነበር ያስታውሳሉ:: አሁን የኑሮ ጭንቀታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አቃልሎላቸዋል:: በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የርክክብ መድረክ ላይ ተገኝተው እንደነበርና በቦታውም በቤት ችግር ውስጥ ያሉ በተለይም አካል ጉዳተኞችን መመልከት በጣም አሳዛኝ እንደነበር ይናገራሉ:: ከተማ አስተዳደሩ ይህን መሰል በጎ ተግባር ማከናወኑ በእጅጉ አስደስቷቸዋል::
በቀጣይም እንዲህ ያለው በጎ ተግባር ተጠናክሮ ቢቀጥልና በየቦታው የወደቁና የተቸገሩ ዜጎችን መንግሥት በእኩል ቢመለከት መልካም ነው ይላሉ:: እርሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ዜጎች እየታወሱ ነው:: በወረዳው ውስጥ ያሉ አመራሮችም በወረዳው ውስጥ በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ለይተው የሚያውቁ በመሆኑ ሥራቸው ፍትሐዊ ነው:: የተሠራው ፍትሐዊ ሥራ ብዙዎችን ያስደሰተ እንደሆነም ያምናሉ::
የዕጣ ክፍፍሉም ከአድሎ ነፃ እንደነበርና ሰዎች እንደ ዕድላቸው ሰፊና ጠባብ እንደደረሳቸው የሚናገሩት ሳጅን ንጉሤ እርሳቸውም የደረሳቸው ጠበብ ያለ ባለአንድ ክፍል እንደሆነ፣ በዚህም እንዳልተከፉና አመስግነው መቀበላቸውን ይገልጻሉ:: በአዲሱ ቤታቸውም ኑሮ ጀምረዋል:: በሂደትም አንዳንድ ነገሮችን በማስተካከል ምቹ ለማድረግ አቅደዋል:: በቤት እጦት ወደቤተሰብ የወሰዷቸውን ልጆቻቸውን አምጥተው አብረው ለመኖርም ሃሳብ አላቸው::
በቤት ኪራይ ለ15 ዓመታት ሲኖሩ ጥሩ የሆኑና መጥፎም አከራይ እንደገጠማቸውም ሳጅን ንጉሴ ያስታውሳሉ:: የተከራዩትን ቤት ሲከፍቱና ሲዘጉ በጥንቃቄ ይሁን በማለት ‹‹ቀስ በል!›› ብሎ የተቆጣቸው አከራይ እንደነበር፣በተቃራኒው ደግሞ ሲቸግራቸው አይዞህ ብሎ ገንዘብ ያበደራቸው አከራይ መኖሩንም መልካም ጉኑን ያስታውሳሉ:: እንዲህ የተፈራረቁ ነገሮች ሲገጥሟቸው በተለይ አስከፊው ነገር ሲገጥማቸው በሀገራቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸው ያሳዝናቸዋል:: ተስፋም ይርጣሉ:: በተቃራኒው አሳቢና ገንዘብ እስከ ማበደር የሚደርስ በጎ አሳቢና አይዞህ ባይ ወግን እንዳላቸው ሲረዱ ነገን ተስፋ ያደርጋሉ:: ተስፋቸው አሁን ላይ ሰምሮላቸው የመኖሪያቤት ዕድለኛ ለመሆን በቅተዋል::
የቤት ችግር እንደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እጅግ ሰፊና ውስብስብ መሆኑን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሱ ገዙ ይገልጻሉ:: እርሳቸው እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በከፋ የመኖሪያ ቤት ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ በሠራው ሥራ በክፍለ ከተማው በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ 201 ቤቶችን በመለየትና በውስጡ ይኖሩ የነበሩትንም በማስለቀቅ ለተጠቃሚዎች ተላልፏ::
በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶች ሲባል ምን ማለት ነው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም አቶ ካሱ ሲመልሱ፤
ቤቶችን ለሦስተኛ ወገን አስተላልፈውና አከራይተው ይጠቀሙ የነበሩ፣ ቤት ሠርተው ዘመድ አስቀምጠው የሚወጡና ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው ያልወጡ እና በሌሎችም ምክንያቶች የማይገባቸውን ቤት የያዙ በማለት እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል:: በሕገወጥ ቤት ከያዙት መካከል የሚያስታውሱት በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ሺሻ የሚያጨሱ ነበሩ:: በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸውም ያላስተካከሉ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት እንዲለቁ ተደርጎ ለሚገባቸው ሊሰጥ ችሏል::
እንደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የቤት ጥያቄ የማያቋርጥ ጥያቄ ቢሆንም እንደ ችግሩ ስፋትና ጥልቀት እየታየ የቅድሚያ ቅድሚያ ምላሽ የተሰጠው:: በቅርቡም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ ለሚገባቸው ከተላለፈው 201 የቀበሌ ቤቶች መካከል በክፍለከተማው በወረዳ አንድ ብቻ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ዘጠኝ ችግረኞች ተጠቃሚ ሆነዋል:: እነዚህን ተጠቃሚዎችም ከቀጠና አስተባባሪዎች ጋር በጋራ በመሆን የችግራቸው መጠንና ስፋት በሚገባ ታይቶ በቅደም ተከተላቸው መሰረት ነው ተጠቃሚ የሆኑት::
በወረዳ አንድ ውስጥ ስድስት ነባር ቀበሌዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ቀበሌም 20 ሰዎች ተለይተዋል:: ከእነዚህ በየቀበሌው ከሚገኙ የቤት ችግር ካለባቸው ዜጎች መካከልም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ35 እስከ 40 ለሚደርሱ የቤት ችግረኞች ምላሽ መስጠት ተችሏል:: ይህ ከለውጡ ወዲህ የመጣ ውጤት በመሆኑ ትልቅ አቅም ነው:: አሁን እየተሠራ ያለው ሥራም የዚሁ አካል በመሆኑ በቀጣይም በየቀበሌው በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን እየለየ ችግሩን ለማቃለል ይሠራል::
አሁን ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር በቀበሌ ቤት ብቻ መፍታት የማይቻል በመሆኑ ሌሎች አማራጮች ለመፈለግ በክፍለከተማው አማራጭ ተቀምጧል:: ለአብነትም ሰፋ ሰፋ ያሉ ቦታዎች ያሉበትን ወረዳዎች ለይቶ ቤቶችን መገንባት ለማቃለል ጥረት ይደረጋል:: ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል:: በተጨማሪ በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወነ ባለው የቤት ልማት የጋራ መኖሪያቤት ግንባታን ማጠናከር ሌላው አማራጭ ነው::
ከተማ አስተዳደሩ እንደ ከተማ ያለውን የቤት ችግር ተረድቶ ችግሩን ማቃለል ይችላሉ ያላቸውን የተለያዩ አማራጮችን እየወሰደ ቢሆንም ከእርሱ ያለፈውን ደግሞ ህብረተሰቡ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ጥቆማዎችን ወደ አስተዳደሩ ማምጣትና በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል:: አንዳንዶች የራሳቸውን ችግር ብቻ በማየት ብሶታቸውን የሚናገሩ ቢሆኑም የሚሠሩ ሥራዎችንም መገንዘብ ይኖርባቸዋል:: ቤት መሰረታዊ ነገር በመሆኑ የህዝቡን ሮሮ ክፍለከተማው ይረዳል::
በአንድ ጊዜ ሁሉንም ሰው ማስተናገድ የማይቻል በመሆኑ ነዋሪዎች ነባራዊ ሁኔታውን ተረድተው በትዕግስት እንዲጠባበቁና ከአስተዳደሩ ጎን በመሆን ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ ካሱ ጥሪ አስተላልፈዋል:: ሌሎች አጋር አካላትም ተቋሙን በመደገፍ የተሸለ የቤት አማራጮችን በማቅረብ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ቢሠሩ መልካም ነው በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል::
የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 201 ቤቶችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እና አካል ጉዳተኛ ለሆኑ ነዋሪዎች ማስረከባቸው ይታወሳል። ችግሩ እጅግ ሰፊ በሆነበት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተገኝተው የቁልፍ ርክክብ ያደረጉት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ሀብት ያለውም በዝቅተኛ ኑሮውን የሚመራውም በጋራ የሚኖሩባት ከተማ ናት::
ሁሉንም በምታስተናግደው ከተማ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ቤቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው እና ለችግር የተጋለጡ ነዋሪዎችን በመለየት በግልጽ እና በፍትሐዊነት እየተሰጠ ነው:: በቀጣይም የሚሰጥ ይሆናል። ነዋሪዎችም ህጋዊነት እንዲሰፍን እና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የከተማዋ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ተሳትፏቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ሲሉም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013