አዲሱ ገረመው
ጉዞ ወደ “የበረሃዋ ገነት
ክፍል ሦስት
ጸሐይዋ ንዳዷን እየጨመረች ነው። ረጅሙን የስምጥ ሸለቆ ጉዞ ተያይዘነዋል። ግራና ቀኙን ካጀበን በተለምዶ የወያኔ ዛፍ በሚል ከሚጠራው ተክል ጋር እየተፋጠጠን፣ እየታከክን በመጓዝ ወደ መተሐራ ተቃርበናል።
“ድንገት ከኋላዬ አየኸው ይሄ እኮ የወያኔ ዛፍ የሚባለው ነው” ሲባል ሰማሁ። ታዲያ ወሬው ብዙ ነገሮችን ሊያስፈትሽ እንደሆነ ሲገባኝ በንቃት መከታተል ጀመርኩ። ተክሉ የወያኔ ዛፍ ተብሎ እንዴት ሊጠራ ቻለ? ምን ባህሪ አለው የሚለውንም ማወቅ እፈልግም ነበርና ወደ ሃሳቡ ጎራ ተቀላቀልኩ።
ተክሉ የመንገዱን ግራና ቀኝ ተከትሎ በሰፋፊው የስምጥ ሸለቆው መሬት ላይ የተንሰራፋ ሲሆን፤ በተሽከርካሪዎች የፍጥነት እንቅስቃሴ ነፋስ ሲያገኘው እየሰገዱ እንግዳ የሚቀበሉ አስተናባሪዎችን ይመስላል፤ ማቆሚያ የለውም፤ መነሻውና መድረሻ አይታወቅም፤ ለአይን ይታክታል።
የመኪና ውስጥ ወሬው ሲደራ አካባቢውን በውል እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ስለተክሉ ምንነት መናገር ጀመሩ። ተክሉ በዚህ ሥፍራ የታወቀው ወያኔ አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው የሚል መረጃ አለ። ወያኔ የሚባሉ የቤት መኪናዎችም ነበሩ፤ የዚህ ስያሜም መነሻው ያው የወያኔ የሀገሪቱን ስልጣን መቆናጠጥና መስፋፋት ይመስለኛል።
ይህ ተከል ሌሎች ሀገር በቀል ዛፎችን እና ተክሎችን እየገፋ የአፋር ክልልንና አጎራባች አካባቢዎችን ማጥለቅለቁ እና ለቁጥጥርም አዳጋች መሆኑ ይነገራል። አፋሮች ዛፉን “ወያኔ ዛፍ” ይሉታል። በሳይንሳዊ መጠሪያው ደግሞ ፕሮፌሲስ ኒውፎራ በሚል ይታወቃል።
ተክሉ ትልልቅ እሾሆች አሉት። ቅጠሉን ግመሎችም ሆኑ ሌሎች እንስሳት ለመብላት ይቸገራሉ። ይህን አካላዊ ባህሪውን ካለፈው የህወሓት መንግስት ስልጣን ተስፋፊነትና ተንኮል ጋር በማዛመድ ስሙ ሳይወጣለት እንዳልቀረ አንዱ ተጓዥ በፖለቲካ ቋንቋ ነገረን። ይህን ዛፍ የአካባቢው ሰዎች ለከሰልነት ቢያውሉትም ከሰሉ ግን እስከዚህም ነው እንደሚባል ከጨዋታው ተረዳን።
አረንጓዴነቱን ላስተዋለ ግን ወያኔ ዛፍ ያምራል። ዛፉ በስሙ እንዲጠራ ያልፈለገው ወያኔ ግን የግብርና ባለሙያዎቹን እያሰማራ የዛፉ ስም “ደርጊ ሃራ” ነው ማስባል ጀምሮ እንደነበር ይገለጻል። አፋሮች እና ዛፉ በሚበዛበት አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦች ግን ይህን ዛፍ እና ወያኔን የምናውቀው በተመሳሳይ ወቅት ስለሆነ የደርግ ሳይሆን “የወያኔ ዛፍ ነው!” ማለቱን ቀጠሉበት ሲሉ ነገሩን ውስጥ አዋቂዎች። ተክሉ ግን ስለምን በአንድ ጊዜ ይሄን ሁሉ በረሀ እንዳዳረሰ ተጨማሪ ጥናት ቢደረግበት አንዳች ፋይዳ ይኖረው ይሆናል በሚል ተግባቦት ጉዞአችንን ቀጠልን።
ሰዓቱ የቁርስ ባይባልም ቁርስ ልንበላ መተሐራ ከተማ ላይ እረፍት አደረግን። “እዚህ ግቡ” የሚሉ የሆቴል አስተናጋጆች ከተረባረቡብን በኋላ አንዱ ሆቴል በረንዳ ላይ ተሰየምን። ወጭ ወራጁ፣ ነጋዴው፣ የመኪና ትርምሱ ብቻ ውክብክብ ያለ ነገር ይታያል። እዚህ አካባቢ ማስክ ብሎ ነገር የለም። እንደውም ከሌላ አካባቢ የመጣ ሰው የሚለየው ማስክ በማድረጉ ነው። የአካባቢው ሰው ያለማስክ መንቀሳቀሱ ይቺ ናት ኮቪድ መከላከል እንድል አረገኝ።
ሁሉም የሻውን ከበላና ከጠጣ በኋላ ጉዞአችን ቀጠለ። ጸሐይዋ መሀል አናታችንን ስታልፍ አዋሽ ላይ ከተምን። የነፍስ እርካታዬ የሆነው የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን አዋሽ የተሰኘው ግጥም ትዝ አለኝ። በአይነ ስጋዬ አዋሽን በቅርብ ርቀት እየቃኘሁ በህሊናዬ የጸጋዬን “አዋሽ” ግጥም ማነብነብ ጀመርኩ። በትካዜ በተመስጦ ከገጣሚው ጋር ተከዝኩ።
ግጥሙ ታማኙን የኢትየጵያ ወንዝ “አዋሽን” ይዘክራል። ይሁንና በውስጡ በቀላሉ ተመርምረው የማይደረስባቸው ጥልቅ ምስጢሮችን ያዘለ ሳይሆን አይቀርም። በእውነቱ ይህንን ስነ ግጥም ለመተንተን ጥልቅ ምልከታን ይጠይቃል። በቀላሉም ሊደረስበት የሚችል አይደለም።
እንደ ግጥሙ እንደ ነባራዊ እውነታውም አዋሽ እናት ኢትዮጵያን የውሃ ማማ ካሰኟት ታላላቅ ወንዞቿ አንዱ ነው። ግጥሙን ወይም ገጣሚውን ያስተከዘው ግን የወንዙ ታላቅነት ብቻ አይመስለኝም።
“እነ ዋቢ ሸበሌማ…
እነ ግዮን ወርደው አልፈው…” ይላል ከስንኞቹ መሀል አንዱ፤ አንዳች ልጁን ከሌላ ሰው ጋር እያነጻጸረ በቁጭት የሚበግን ሰው የሚያንቆረቁረው እሮሮ ይመስላል። አዋሽ ወንዝን እንደ የአገር ፍቅር ምልክት ፣ የህዝቦች ማንነት የትስስር ሰንሰለት ፣ የአንድነት ማስተሳሰሪያ ገመድ ሆኖ አየሁበት። እውነታውም ያው ነው።
“የሸዋ የእምብርትሽ ላቦት
………………መጫ ምንጩ
ዳዳ ጽንሱ ሸዋ ፍንጩ
……………………………..
የሰባት ቤት ጉራጌ አድባር
የከረዩ ቅቤና ማር
…………………………..
ከከረዩ መተሐራ፤ ከኢቱ እስከ አፋር አምጬ” ሲል የኢትዮጵያውያን የትስስር ውል መሆኑን ያሳየናል።
ከአዋሽ በቀር ሌሎች ወንዞች ድንበር አልፈው የሚሰደዱ መሆኑ፤ ግዛታቸውን ብቻ ሳይሆን ስማቸውንም የሚቀይሩ ሆኖ ሳለ፤ ምስኪኑ አዋሽ ብቻ ከእነ ስሙ በረሃ አሸዋ ውስጥ ኩርምት ብሎ ሰምጦ መቅረቱ የአንዳች ሌላ መልዕክት ምልክት ነው ማለት ይቻላል። ይህም የት ይደርሳል ተብሎ በጉጉት ሲጠብቁት ባክኖ የሚቀር ማንነት ምሳሌ ነው። ይህን ህልውና፣ የከሸፈ ማንነት ጠለቅ ብለን ስንመረምረው የመላው የሰው ዘር እውነታም ነው ማለት እንችላለን። መጨረሻው መቀመቅ የሆነ ከንቱ ልፋትና ጥረት በአዋሽ ወንዝ ተመስሎ ሳይቀርብ የቀረ አይመስለኝም። የሆነው ሆኖ እኔ አሁን አዋሽ ላይ ሆኜ ነው የማወጋችሁ።
አዋሽ ልብ ላይ ቢፈስም ህይወቱ በአሸዋ ውስጥ ትቀሰፋለች። ግና እንደሌሎች አልከዳንም። እዚሁ ተጸንሶ እዚሁ ተወልዶ እዚሁ አድጎ እዚሁ የሞተ የአገር ዋርካ ነው።
ህይወቱ ሞቶ የመቅረት ብቻ ሳይሆን በብዙም አገልግሎናል። የሀገራችን ስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ ሲወሳ አዋሽ አብሮ ይነሳል። እነ ወንጂ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች፣ እነ ኑራኤራ እና መርቲ የብርቱካንና የቲማቲም እርሻዎች በማን ላይ እንደቆሙ ይታወቃል። ወሬው ብቻ በዛ እንጂ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካስ አዋሽ ላይ አይደለም የቆመው። ሌሎችም ሌሎችም የመስኖ ሥራዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ።
እንዲያው አዋሽን በዝምታ ከማልፈው ብዬ እንጂ ስንክሳሩማ መች ተነግሮ ያልቃል። “ምነው መለየት ባልነበረ” አለ ዘማሪው። መኪናችን ቆሞ ቢሆንና አዋሽን ዞር ዞር ብለን እንድናይ ቢፈቀድልን ስንቱን ባነሳሁ። የሆነው ሆኖ አዋሽን በአይን ተሰናብትን። ድልድዩን ከወዲያ ማዶ እያየን እልም ያለው የአፋር በረሃ ንዳድ ውስጥ ገባን። አሁን ዋናው ቅኝት ተጀመረ። አፋር እንዴት ናት? የሳምንት ሰው ይበለን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013