እየሩስ አበራ
የአንድ እናት ልጆች ባህሪና በመልክ ተመሳሳይ አይደለም። እንደ የባህሪያቸው ሥራቸውን በዚያው ልክ የተለያየ ነው። አንደኛው ለፍቶ አዳሪ ሆኖ እራሱን ለውጦ እናቱን ለመለወጥ ዘወትር የሚጥር ሲሆን፤ ሌላኛው በተቃራኒው መሥራት የማይወድ የእናት እጅ ጠብቆ አዳሪ ይሆናል። እነዚህ ሁለቱም ልጆች ለእናታቸው ቢጠቅሟትም ባይጠቅሟትም ልጆች በመሆናቸው ለእርሷ እኩል ናቸው። አሁን አሁን በአገር ዙሪያ በተለያየ ጽንፍ የሚቆሙ የሀገሬን ሰዎች ስመለከታቸው በእነዚህ በሁለት ልጆች ጋር የሚያቆራኝ ታሪክ ያላቸው ይመስ ለኛል። በተለይ ኑሯቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ በሁለት ጎራ የቆሙ ወገኖች ድርጊትን ስመለከት ልክ መሆኔን አስባለሁ።
እነዚህ በባዕድ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድሮ ስለእነሱ ፍቅር ስሰማው የነበረውን ታሪክ ሳሰታወስ ይገርመኛል። በሚኖሩበት የባዕድ አገር ተፈላልገው ‹‹የሀገር ልጅ የማር እጅ›› እየተባባሉ የሚላላሱበት ያ ደግ ጊዜ በትውስታ ብቻ በነበረ መቅረቱ ያሳዝነኛል። ያኔ በሁሉም ዘንድ ለአገር የሚሰጠው ክብር ከሁሉ በላይ ይልቅ ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን በዓለም አደባባይ የሚታየውና የሚሰማው በተቃራኒው ሆኗል።
አሁን አሁን ከአገራቸው በተቃራኒ ጎራ የቆሙ አንዳንዶች የበሉበትን ወጭት ሰባሪ ሆነው በሀገር ሲቀልዱ ማየት እየተለመደ መጥቷል። በባእድ ሀገር ሆነው በሀገር ላይ ማላገጥ የዘወትር ሥራቸው የሆነ ይመስላል። ሀገር በዋዛ በፈዛዛ የምትገኝ እየመሰላቸው በሰው ሀገር ላይ እየኖሩ የራሳቸው ሀገርና ህዝብ ህልውና የሚነካ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ይገኛሉ። እኔን የሚገርመኝ ለዛሬ ማንነታቸው መሠረት የሆነችውን እትብታቸው መቀበሪያ ምድር መርሳታቸው ሳይሆን የሰው ሀገር ቁጭ ብለው የራሳቸውን ሀገር ለመክዳት ያነሳሳቸውን እብደት ነው። አሁን በሚኖሩባት ሀገር ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው ሆዳቸው ሲጠግብ ሲንደላቀቁ ሀገር የሚለው እሳቤ ጠፍቶባቸው ክህደታቸውን በአደባባይ እወቁልኝ እያሉ መሆኑ ያስገርማል።
የራሳቸውን ጎራ ፈጥረው እዚያ ሆነው እዚህ እንድትኖር የሚፈልጓት ዓይነት ሀገር ለመፍጠር መጣራቸው እጅግ የሚደንቅ ነው። የሁለት ዓለም ሰው ሆነን እኛ እየኖርንባት ያለችው አገር፤ እነሱ ሳይኖሩባት ከሩቅ ሆነው ሊያኖሩን ማሰባቸው የሚደንቅ ነው። እጃቸውን ለማስረዘም እንደዚያ ወርድ ብለው በዓለም አደባባይ ሀገራቸውን አሳልፈው ለመስጠት ያስባሉ የሚል እምነት አልነበረኝም። እየሆነ ያለው ግልጽ እውነት ግን ይሄው ነው።
የእነዚህ ከሀዲዎች መነሻ ጁንታው በህይወት በነበረበት ወቅት ‹‹አጣብቂኝ ውስጥ ስገባ ማስተንፈሻ ይሆነኛል›› ብሎ ያዘጋጃቸው ጀሌዎች ስለመሆናቸው ብዙ ርቀት ሳይሄዱ ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ ቡድን የዘረፈውን የህዝብ ሀብት በዶላር ቢባል በዩሮ እየመዠረጠ በአውሮፓና በአሜሪካ ላሉ ዘመዶቹ ብቻ ሳይሆን ነገ ይጠቅሙኛል ብሎ ላሰባቸው መበተኑ ለዚህ ጊዜ ያገዘው ይመስላል። እነዚህኞቹም ልክ አገር ውስጥ እንደነበረው ጁንታ የሀገራቸው ጉዳይ ተቆርቋሪ መስለው በሚሽሩበት ተንኮልና በሚጎነጉኑት ሴራ ወገኖቻቸውን ለከፋ ችግር የሚዳርጉ ናቸው። እነዚህ በበሉበት የሚጮሁት ውሾች ለጌታቸው የገቡት ቃል እያስጨነቃቸው ለሀገሩ ጀብዱ እንደሠራ ሰው በየሀገራቱ አደባባይ እየወጡ ጌታዋ እንደጠፋባት ውሻ መሬት ላይ እየተንከባለሉ አባሪ ተባባሪ ፈለጋ በአውሮፓ ህብረትና በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በመቆም ዘወትር ያላዝናሉ። በሠሩት ሥራ አፍረው አንገታቸውን ይደፋሉ ብዬ ስጠብቅ፤ ጭራሽ ዓይናቸውን በጨው አጥበው እርፍ አሉት።
የጁንታው መሞትና መቀበር አልዋጥ ብሏቸው፤ የሚያደርጉት ጠፉቶባቸው፤ ከራሳቸው ውጪ ሌላ ሰው ያለ የማይመስላቸው በምቾች የሰከሩት እንደልባቸው እየተደላቀቁ ለመኖር እያለሙ በራሳቸው ወገኖች ላይ መቀለድ ይፈልጋሉ። ዛሬም በድህነት አረንቋ ውስጥ ያለውን ወገናቸውን በማሰብ ፋንታ በወገናቻቸው ቁስል እንጨት የመስደድ ጨዋታ የሚጫወቱት በባእድ ሀገር ጉያ ተሸሽገው ሀገራቸው ላይ ጣታቸውን እየቀሰሩ ደባ ያሴራሉ። የጌቶቻቸው መቃብር አፈሩን ከላዩ እያረገፉ መኖሩን ቢሰብኩም ሰሚ ጆሮ በማጣታቸው ፤ ያልሆነውን ያልተፈጠረውን ሆነ ተፈጠረ እያሉ በማደናገር ተሰሚነትን ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ታዲያ በእነሱ አንገት ሰባሪ ድርጊት ቢሆንም እነሱ ምንም ሳይመስላቸው ቀጥለዋል። ይልቁን ድርጊታቸው በሀገርና በህዝብ ዘንድ ለትዝብት ዳረጋቸው እንጂ አይጠቅማቸውም።
ከሰሞኑ እነሱ በቆሙበት ቆመው ለሀገር አለኝታ መሆናቸው ያሳዩንን ወገኖቻችንን ዓይተናል። ለሀገራቸው ዘብ የቆሙ ኢትዮጵያውን እነዚህን ውሽታሞች አፍ የሚያስዝ ጀብዱ ሲሠሩ ከማየት በላይ የሚያስደስት ምን ጉዳይ ሊገኝ ይችላል። እውነትና ንጋት ጊዜውን ጠብቆ ይፋ ይሆናል ብለው ዝም ያሉ የሀገሬ ጀግኖች በእነዚሁ ከሀዲዎች ጎን ወጥተው፤ ሃሳባቸውን ተቃውመው ‹‹አለሁልሽ ሀገሬ›› ማለታቸውን ስሰማ እጅግ ተደስቻለሁ። ለካ ሀገሬ መኖሯን የሚሹ የቁርጥ ቀን ልጆች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም አሏት ለማለት በቅቻለው።
በናፍቆትና በሰቀቀን ውስጥ የአገራቸውን መጥፎዋን ሲሰሙ የሚያማቸው፣ ክፉዋን ማየት የማይፈልጉ፤ በባዕድ አገር እየኖሩ የሀገራቸውን መፃኢ ተስፋ ሰንቀው ለሀገራቸው ምን ላድርግልሽ የሚሉ መኖራቸው ተስፋዬን አለምልሞታል። መአት መአቱን እያዘነቡ ሀገ ርን ለማጥፋት ቀን ከለሊት ሥራዬ ብለው በሚሠሩት ተንኮለኞች የደማው ልቤ፤ በእነዚህኞቹ ወገኖቼ ካሳ ያገኘ ያህል በልቤ ውስጥ ያደረው ደስታ የተለየ ሆኖብኛል።
የዓለም ሀገራት ዓይናቸው ወደ ኢትዮጵያ ባነጣጠረበት በአሁኑ ወቅት ሰላሟ ደፈረሰ የሚል ዜና ለመስማት ያሰፈሰፉ ብዙ ናቸው። እነዚህ ለራሳቸው ጥቅም የኢትዮጵያን መፍረስ የሚሹ ሌሎች አገሮች በኢትዮጵያዊያን መካከል በመግባት ግድግዳ ለመሆን የሸረቡት ሴራ በወገኖቻችን በሩን ተዘግቷል። ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው፤ ለሀገራቸው ዘወትር የሚጨነቁ የሀገሬ ልጆች ዝምታቸውን ሰብረዋል። በዓለም አደባባይ የሀገራቸውን ሀቅና እውነት ሊያወጡላት አለሁ ብለው የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን አሳይተዋል። ወትሮም በአጠገባቸው ተቀምጠው የሚያላዘኑትን እያዩ ዝም ያሉት፤ የውሾችን መጨረሻ ስለሚያውቁ መሆኑ የገባኝ አሁን ነው። ሀገር አፍርሰው ህዝቡን ሀገር አልባ ለማድረግ ያቀዱ አካላት፤ ያንን ሁሉ ድንፋታና ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጨሃል ዓይነት ቢሂላቸውን ትተው ከሀገራቸው ጎን መቆም ይሻላቸዋል።
የወገናቸው ጭንቀትና መከራ ገብቷቸዋል። ባሉበት በዚያው በባእድ ሀገር ሆነው ያለውን እውነት አጥርተው የገባቸውን ሐቅ ይዘዋል። ዛሬም ነገም ለሀገራቸውና ለወገናቸው አለኝታ ምስክር ነን እያሉ ፍቅርቸውን አሳይተዋል። እውነትም ሀገር ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን እሰየው የሚያሰኝ ነው። እንደነዚህ ዓይነት የሀገራቸውን እድገት እንጂ ክፉዋን ማየት የማይፈልጉ ሀገር ወዳዶች ለነገ የሀገር ተስፋ ናቸው። ገና ለሀገራቸው ብዙ ለመሥራት ያቀዱ የባይተዋር ሀገር ኑሮ ቢቸግር እንጂ ‹ማን እንደሀገር› የሚሉ አገር ወዳድ ስለመሆናቸው አልጠራጠርም። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ያብዛልን ዘንድ የሁላችንም ፀሎት ይሆን ዘንድ ተመኘሁ። ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013