(ከጁንታው . . .)
Mኣr
“ተዋከበና” እንዲል ዜማው በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ያለችው ዓለም ሁሌ እንደተዋከበች አለች። ከመዋከብም ባለፈ እየተንገላታች ነው ያለችው።
ከእነዚህ እንደ ማዕበል ከሚንጧት ነውጠኞች አንዱ ደግሞ ውዥንብር ነው። ለዛውም ከድሮው ለየት ያለና በዘመናዊ ቴክኖሎጂና የቴክ እውቀት የተደገፈ፣ የተጠናከረና የሚሰራጭ ውዥንብር።
ውዥንብር ድሮም ያለና የነበረ ሲሆን የአሁኑን ዘመን ለየት የሚያደርገው የራሱ ልዩ ባህርይ ያለው ሲሆን ከላይ ከጠቀስነው በተጨማሪ የሰው ሀይል፣ በጀትና ጊዜ ተመድቦለት መሰራቱ ነው። (ከሴራ ንድፈ-ሀሳብ (Conspiracy theory) ጋር ያለው ትስስር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።)
ከላይ በርእሳችን “ከፓንደሚኩ ኢንፎደሚኩ . . .” ብለን የተነሳነው ያለምክንያት ሳይሆን በአሁኑ ዘመን፣ በተጨባጭና በተረጋገጠ መረጃና ማስረጃ ላይ ለመመስረት በመፈለግና ወደ አሁኑ አለማችንንም ሆነ በተናጠል እኛን እያመሰን ወዳለው ሰሞንኛ፤ ሲበዛም እኩይ ተግባር ለመምጣት እንደመንደርደሪያ ለመጠቀም በማሰብ ነው።
ይህ ብቻም አይደለም፤ የአሁኑን ዓለም አቀፍ ቀሳፊ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) መከሰትን ተከትሎ አንድ አለማችንንና እኛን እያመሰን የነበረውና አሁንም ያልተፋታነው ችግር ቢኖር የመረጃ ወረርሽኝና ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት “Infodemic” ሲል የሰየመው፤ ከድርጅቱ አቋም በተፃራሪ የቆመ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው።
በቅድመ ወረርሽኙ (ኮቪድ-19) በነበሩት ውትወታዎች በተለያዩና ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደርሱ የህዝብ ለህዝብ ግጭቶች፣ በሀሰት መረጃ ስርጭት (አሉባልታ) አማካኝነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች፣ የስነ-ልቦና ጦርነቶች፣ የሰው ልጅ ውድ ህይወት መቀጠፍ፣ የሀብትና ንብረት መውደምና የመሳሰሉት ሁሉ የተወሰኑ አገራት ችግሮች ተደርገው በመወሰዳቸው እሪታው የጥቂቶች፤ በተለይም የታዳጊና ዲሞክራሲ በንቃተ-ህሊና ካልተደገፈባቸው አገራት ጋር ብቻ (ባብዛኛው) ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ በድህረ ወረርሽኙ ግን ሳይታሰብ ድንገት በተከሰተው ኮቪድ-19 እና በተለይ ባደጉት አገራት ላይ እያስከተለ ባለው ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ችግሩ የጋራ፤ የሁሉም ለመሆን በቅቷል።
ይህም ጉዳዩን ከኮቪድ ባልተናነሰ ሁኔታ የመነጋገሪያ ርእሰ-ጉዳይ ከማድረጉም አልፎ የዓለም ጤና ድርጅትን በእሮሮና ሳግ የታጀበ መግለጫ እስከማውጣት እንዲደርስ አድርጎታል። በወቅቱ ባወጣው መግለጫም ከኮቪድ በላይ አስቸጋሪና የዓለማችን ፈተና እየሆነ ያለው የመረጃ ወረርሽኝ (Infodemic)ና ያስከተለው የተዛባ መረጃ መጥለቅለቅ ነው።
በወቅቱ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም (ዶ/ር) ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደ ተናገሩት ከሆነ ድርጅታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነውና ወረርሽኙን የመከላከልና መቆጣጠር ስራው ላይ እንዳያተኩር እያደረገ ያለ ክፉ ጋሬጣ ቢኖር የሃሰት መረጃ ጎርፍ ሲሆን ከድርጅቱ የሚወጡም ሆኑ ከመንግስታት ለህዝቦቻቸው የሚተላለፉ ቫይረሱን መከላከልና መቆጣጠርን የተመለከቱ መረጃዎች በትክክልና ተገቢው መንገድ ህብረተሰቡ ጋር ማድረስ፤ ህብረተሰቡ እራሱንም ሆነ ሌላውን እንዲጠብቅ ማድረግ በፍፁም አልተቻለም። “በአሁኑ ሰአት እየተዋጋን ያለነው ከወረርሽኙ በበለጠ ከመረጃ ወረርሽኝ/ኢንፎደሚክ ጋር ነው። የሀሰት መረጃዎች፣ የተፈበረኩ ዜናዎች፣ ሳይንሳዊ ያልሆኑና ያልተረጋገጡ ትርክቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጠራረጉን ነው።” ሲሉም ነበር ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ዶክተሩ “እባካችሁ ማናችንም ብንሆን ማህበራዊ ሚዲያውን በሀላፊነት እንጠቀም፤ የሚዲያ ተቋማቱ ሀላፊዎችም በሃላፊነት አስተዳድሩት” ከማለትም ባለፈ “እባካችሁ ይህንን አደገኛ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ሁላችንም አንድ ሆነን በጋራ እንስራ። ሁላችንም በሀላፊነት እንንቀሳቀስ፤ ሁላችንም ሀላፊነትና ተጠያቂነት ያለብን በመሆኑ በዛው ልክ እንስራ። ይህን ካላደረግን ከልክ ባለፈ የመረጃ ወረርሽኝና ጎርፍ፤ መሰረተ ቢስ በሆነ የመረጃ ማዕበል፤ በሀሰት ዜናዎችና ሴራዎች ተጠራርገን መጥፋታችን ነው” ሲሉ ነበር በወቅቱ መልእክታቸውን ያስተላለፉት። (በዛን ወቅት በቀን ከሶስት እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርሱና ህዝቡ እራሱን ከወረርሽኙ እንዳይከላከል የሚያደርጉ መረጃዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ይለቀቁ ነበር።) የ”ከፓንደሚኩ ኢንፎደሚኩ” ጉዳይ ዝርዝሩ ብዙ ነውና በዚሁ አብቅተን ወደ ጁንታው እንሂድ።
የዘንድሮ የአገራችን አቢይ አጀንዳ ሆኖ የነበረውና አሁንም ያለው ህግን ለማስከበር ሲባል በጁንታው ላይ የተወሰደው የማያዳግም እርምጃ ነው። እርምጃውም እጥር ምጥን ባለ መልኩ በአስራ አምስት ቀናት የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን አካባቢውንና የክልሉን ማህበረሰብ ወደነበረበት ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ከነበረበት ወደ ተሻለ ህይወት ለማምጣት ሰብአዊና ፖለቲካዊ ስራዎች በመስራት ላይ ይገኛሉ። እነዚህን ተግባራት ዓለም እንዲያውቃቸው በማሰብም መንግስት በሩን ለሚመለከታቸው ሁሉ ክፍት አድርጓል። በቃ እውነታው ይሄው ነው።
የክልሉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉም ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ ያረጋገጡት ይህንኑ ሲሆን “በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተላለፉ ያለ ያልተረጋገጡና የሀሰት መረጃዎች የጥፋት ሀይሉን ሀሳብ የሚያንሸራሽሩ፣ በእውነታ ላይ የተመሰረቱ፣ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የሚገልፁና መሬት ያለውን የሚያመላክቱ አይደሉም። በመሆኑም ህብረተሰቡ በተሳሳተ መረጃ እንዳይዘናጋ፤ ይህን የሚያደርጉ አካላትም ከዚህ አይነቱ አስነዋሪ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ” በማለት ነበር ክልሉንና ህዝቡን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያው የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎችንና የተዛቡ፤ ለጁንታው የወገኑና ጁንታውን ብቻ ማዕከል ያደረጉ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን የገለፁት።
ተግባሩ “ውሻ በበላበት ይጮሀል” እንደሚባለው ነው። ጁንታው በህይወት እያለ 22 እና 23 አካባቢ የነበሩት የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች የጁንታው ግብአተ መሬት ከተፈፀመ በኋላ ባንድ ጊዜ ወደ 300 እና በላይ መስፈንጠሩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳው ዘመቻ ምን ያህል በገንዘብ፣ በሰው ሀይልና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተደግፎ፤ አስፈላጊው አመራር ሁሉ እየተሰጠበት፣ አጀንዳ እየተቀረፀለት . . . እንደሚከናወን ከግልፅም በላይ ፍንትው ያለ እውነት ሲሆን፤ ከሚሰራጨው ወረርሽኝም መረዳት የሚቻለው ይህንኑና “ውሻ በበላበት …” የሚጮህ መሆኑን ነው።
እርግጥ ነው፤ ዛሬ ሁሉ ነገር በእጅና ጣታችን ጫፍ ላይ ነው። ቅለቱ እዚህ ድረስ ሲሆን በዚህ አይነቱ ወቅት ትልቁ ጉዳይ ሚዲያውን በሀላፊነትና በእውቀት፤ ከሁሉም በላይ አገርና ወገንን ባይጠቅም እንኳን በማይጎዳ መልኩ የመጠቀሙ ሁኔታ ነው። በቃ ይህን የዜግነት፣ የሰውነትና የተጠቃሚነት ሀላፊነትን መወጣትን ብቻ ነው የሚጠይቀው። ይህን ካደረግን እዳው ሁሉ ገብስ ነውና አያሳስብም።
ባጭሩ፤ ጁንታው የተደመሰሰው በስራው፤ በሀጢያቱ ነው። ተረቱ “ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው” እንዲል ነውና የእጁን፣ የአሻራውን ነው ያገኘው። መደምሰስ ስለነበረበት ተደመሰሰ። በቃ። ከዛ በኋላ ያለው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉትና እንዳሉት ብቻ ነው።
እባካችሁ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በእውቀትና በኃላፊነት እንጠቀም!!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013