ከአንድ ወዳጄ ሻይ ቡና እያልን ስንጨዋወት አንተ ሰው! ዘንድሮም ጉድ ተሰራሁ አለኝ።የዛሬ ዓመት ሁዳዴ ሊገባ ሲል የቅበላ እለት ጉድ ተሰርቶ እንደነበር አስታወሰኝ፤ ለቅበላው ስጋ መግዛት ይፈልግና ለአይን ሳይዝ ( ኸረ ቀን ነው ) ስጋ ሊገዛ ይወጣል።እዚያም ስጋ ቤት ቢሄድ እዚያ ሁሉም ቤት ስጋ ያጣል።
እንዲያውም የተመለከታቸው ስጋ ቤቶች በሙሉ በተለይ ዓርብና እሮብ ማታ ስጋ ሊቀበሉ በራቸውን ከፍተው እንደሚጠባበቁት አይነት ስጋ ቤቶች ይሆኑበታል። አራት አምስት ቤት አይቶ አልሆን አለውና ወደ ቤቱ ይመለሳል።
ሞኝ አውሬ ነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ሁለቴ የሚወጋ ያለው ይሄ ወዳጄ፣ምኔ ሞኝ ነው ፣ዘንድሮስ አልሞኝም ብሎ ባለፈው እሁድ የቅበላ እለት ስጋ ሊገዛ አስር ሰዓት ላይ ይወጣል፤በእሱ ቤት ጥሩ ሰዓት ላይ መውጣቱ ነው፤ እዚያም ቢሄድ እዚያ የስጋ ጠረኑን ያጣል፤ ያምናውን ታሪክ ደገመው። እኔም ተመሳሳይ ቁስል ነበረብኝና ለከርሞ እንዳትቦነስ ከወዲሁ አስብበት ስል ቀለድኩበት።
ወዳጄን ልጆች እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ጧት ነበር እንጂ መውጣት ፤ከልብህ አልነበርክም ፤ወዘተ እያሉ ሰቅዘው ይይዙታል። እዚያ ስጋ ቤት ሄደሃል? እዚህ ስጋ ቤት ሄደሃል? እያሉ ስጋ ቤቱን ሁሉ እያደረሱ ይጨቀጭቁታል።
በመጨረሻም አንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳል።ሲያስበው ለካስ ልጆቹን በርገር ሊጋብዝ ቃል ገብቶ ነበር፤ ቢያንስ የልጆች ጥያቄ ይመለስ ይልናም ወጪው ቢያሳስበውም በርገር ላይ ወስኖ ጉዞ ወደ በርገር ቤት ሆነ።
እዚያም የሰው ብዛት የዋዛ አልነበረም፤ወንበር የለም፤ሁኔታው ሰው ነቅሎ የወጣ ያስመስለዋል። ገበያውን ላለማጣት ያሉት የካፌው አስተናጋጆች እነዚያን ሰው ሲበዛ የሚበተኑ፣ ሰው ሳይኖር ተሰካክተው የሚቀመጡ ወንበሮች መንገድ ዳር ላይ አፈሰሷቸው፤ ሁሉም እዚያ ላይ ተቀመጡ።በርገሩ ታዘዘ፤እሱስ በዋዛ ሊመጣ ነው፤እልህ አስጨርሶ መጣ።
የሚጎለው አለ፤ ይቅርታ ሌላ ጊዜ እንክሳለን ብሎ አስተናጋጁ አስቀምጦ ሄደ፤በእርግጥም ብዙ ጎሎታል፤ስፔሻል የተባለው በርገር ተራ የሚባለውንም አያህልም።በርገር እንደነገሩ፤ ልጆች ቀማመሱ፤ በስሱም ቢሆን ቅበላው በበርገር ሆነ ፤ችግር በቅቤ ያስበላል ይሏል ይሄ ነው።
እኔ የምለው ግን ስጋውን አሟጦ የጨረሰው ማነው? ጾመኛ ከሆነ እሰየው ነው።ጾም የእምነት ነው፤ ከብዙ መጥፎ ነገር ይጠብቃልና ትልቅ ተስፋ ከፊት ይኖራል፤ መልካም ነው።
እንደዚያ ግን አይመስለኝም።ጧሚው እኮ ብዙ አይደለም፤መች አጣነው፤ታዲያ ስጋውን ማን ጨረሰው? የሚይዝ ይዞት እንጂ ለስጋ የማይበረታ ኢትዮጵያዊ እኮ የለም። ጾም ሊያዝ ሲል እና ጾም ሲፈታ ያለስጋ አይኑ የማይገለጥ ብዙ ነው።
የየቤቱን ትተን የስጋ ቤቱን፣የሆቴል ቤቱን፣ካፌውን ብቻ ብንመለከት ግርግሩ አያድርስ ነው፤ይህን ለመቀላቀል የማይሞክር የለም፤ሰርቶም ፣ተጠግቶም ተበድሮም፣ አዋጥቶም አጋጭቶም ፣ሰርቆም ቢሆን ግርግሩን ይቀላቀላል።ግርግሩን ለተመለከተ ከዚህ በኋላ ስጋ የለም የተባለ ነው የሚመስለው።
የገበያ ዛር የቆመላቸው ስጋ ቤቶች ታዲያ ከወትሮው በተለየ መልኩ ነው ስጋ የሚያስገቡት፤ ዋጋ ላይም እንዲሁ ከፍተኛ ጭማሪ ያደርጋሉ።ሲሮጥ የመጣን አህያ አጥብቀህ ጫነው እንደሚባለው ስጋ ፈላጊውን በዋጋም በቅሸባም ይበሉታል።
ይህ ሁሉ ሆኖም ስጋ ፍለጋ የወጣው ሁሉ ያሰበውን ስጋ በሚጠብቀው ዋጋ አያገኝም።በዋጋ ጭማሪው እና ቅሸባው በጾሙ ወቅት ሲዘጉ የሚያጡትን ሂሳብ ላለማጣት የሚሰሩበት ወቅት አንዱም ይህ ጊዜ ይመስለኛል።
ጾመኞች እንደምንም ብለው ለቅበላ ጊዜ ስጋ ቢያገኙ ይፈልጋሉ፤ትክክል ናቸው።ተጨማሪ ሥራ ሰርተውም፣ ቆጥበውም፣ለክፉ ቀን ካሉት ላይ ቀንሰውም ቢሆን ይህን ፍላጎታቸውን እንደ ዘመኑ ያደርጋሉ።ኑሮ ውድ እየሆነ ስለመጣ እንደ ፊቱ አይሸምቱም። ሩብም ግማሽም ሙሉ ኪሎም እያሉ ይገዛሉ፤ ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም ያሉት ደግሞ ቅንጣቢም ቢሆን ፈልገው ጾሙን ይይዛሉ ።
በእዚህ ቀን የመግዛት አቅሙ የሌላቸው እናቶች እና አባቶች አስቀድመው ይዘጋጃሉ፤ለዚህች ቀን የምትሆን ነገር ለማዘጋጀት አይሰንፉም። ልጆች አባትና እናቶቻቸውን ፆም ለማስያዝ አስቀድመው ይዘጋጃሉ፤ይህን ማድረግ ወግም ስርአትም ነውና የገቡበትም ገብተው ቢሆን እናት አባታቸውን ጾም ያስይዛሉ፤በዚህም ይመረቃሉ።
የሞላላቸው ደግሞ ከስጋ ተለይተው ባያውቁም ይህን ቀን ሜዳ ሳይገቡ በዋዛ አያልፉትም፤ለነገሩ ሆድም አየሁ አይልም፤በአዲስ መንፈስ ይሰለፋል።
ጾሙ የማይመለከታቸውም የዚህ ግርግር አካል ይሆናሉ።በጾም መያዣ እና መፍቻ ወቅት የሚቀርበው ስጋ ጥሩ ነው የሚሉ በርካታ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እንደ ጥንቱ ኮሶ ጠጥተው ጭምር ሳይሆን አይቀርም ይህን ግርግር የሚቀላቀሉት።
በዚህ ወቅት በስጋ ቤቶች፣ ሆቴል ቤቶች፣ካፌዎች ጭምር በስጋ ላይ የሚታየው ትርኢት የሆነ የስጋ ፌስቲቫል የተከፈተ ነው የሚመስለው። ስጋ ጥሬው ፣ጥብሱ ፣ክትፎው ፣ወጡ ፣ቅቅሉ፣ወዘተ በአይነት በአይነት ይበላል፤የአንዳንዶቹ አበላል ደግሞ ለመጪው ሃምሳ አምስት የጾም ቀናት /ሁዳዴ/ ስንቅ የሚቋጥሩ ያስመስላቸዋል። አንድ ቤት ተቀምጠው ወይም ቤት እየቀያየሩ እየጠጡ እየደጋገሙ መብላት ተለምዷል፤አንዴ ጥሬውን ፤ሌላ ጊዜ ጥብሱን ፣ደሞ ክትፎውን። እንብርት እስከሚንጣጣ መብላት እንደሚሉት አይነት። እስከሚሰባበሩ ድረስ መብላትና መጠጣትን እንደ ትልቅ ነገር የሚያዩም አሉ።
ይሄስ በእጅጉ ሊታረም ይገባዋል።ጾሙ በቅጡ የሚመለከታቸው እናቶች አባቶች ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ለወጉ እንኳ ስጋ ቀምሰው ጦም መያዝ እያቃታቸው ባለበት ይህን አይነቱ አመጋገብ በእውነት ሊታረም ይገባል።ለህብረተሰቡም ለበላተኞቹም አይጠቅምም።
በአባቶችና እናቶች ዘንድ ቅበላ ትልቅ ትርጉም አለው።እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በእድሜያቸው ብዙ ያዩ ናቸው።ቅበላ ሲመጣ ብዙ ነገር ይታወሳቸዋል።አመጋገብን በልክ በማድረግ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች /ጧሚዎች/ ምንም ሳያማርሩ ጾም እንዲይዙና እንዲፈቱ ለማድረግ ለቅበላ እንዲሁም ለጾም ወቅት የሚያስፈልግ ድጋፍ ማድረግ ላይ ማሰብ ይገባል።
በበዓላት ወቅት ለበዓላት በሚል ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚሰራ ሁሉ ጾም ለሚይዙ ሰዎች /ለቅበላ/ ሰዎች ተሰባስበው ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር ያለበት ይመስለኛል። በየስጋ ቤቱና በመሳሰሉት አለአግባብ ከሚወጣው ሀብት የተወሰነው ለእነዚህ ችግረኞች ግማሽ ኪሎ ስጋ መግዣ ቢውል ውለታው ብዙ ይሆናል።
ጧሚዎች በጦም ወቅት የሚደገፉበት ሁኔታም ቢፈጠር መልካም ነው። ሰው ከፈጣሪው ጋር ለመቀራረብ ሲጥር ሆዱ ሊያስቸግረው አይገባም።ለእኛም ጭምር ነውና የሚጸልዩት በምግብ መደገፍ ያስፈልጋል።ይህን ሁሉ ማድረግ ለኢትዮጵያውያን ብዙም አይገድም፤ ለስማችንም ለጤናችንም የማይመጥን አመጋገብ ውስጥ ከምንገባ አለግባብ እያወጣን ካለነው ሀብት ላይ ለእነዚህ ወገኖች አከፋለን ለመንፈሳዊና ሰብአዊ ማንነታችን የሚጠቅም ድጋፍ ላይ ማሰብ ይኖርብናል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2013