ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ወደ ቡና አቅራቢነት

‹‹ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ከሚሰጥ ቤተሰብ ነው የተገኘሁት፤ ይሁን እንጂ ቤተሰቡ በሚፈልገው ልክ በትምህርት አልገፋሁም›› ይላል የዛሬው የስኬት ገጽ እንግዳችን። እሱ እንደሚለው፤ የራሱን ፍላጎት ማሳካት ባይችልም፣ የቤተሰቡንም ፍላጎት ባያሳካም፣ የነብሱ ጥሪ በሆነው መንገድ ግን ተጉዞ ውጤታማ መሆን ችሏል።

እግር ኳስ ‹‹የልጅነት ህልሜ ነው›› በሚል ገና ከልጅነቱ ጀምሮ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በጥረቱም ከትምህርቱ ጎን ለጎን በእግር ኳስ ተጫዋችነቱ የትውልድ አካባቢውን ማስጠራት ችሏል። የእግር ኳስ ተጫዋችነቱን ገታ በማድረግም አሁን ላይ ቡና አቅራቢ ነጋዴ ሆኗል።

ከትምህርቱ ጎን ለጎን በእግር ኳስ ጨዋታ ውጤታማ የነበረውና በአሁን ወቅት ደግሞ በቡና አቅራቢነት በአካባቢው የሚታወቀው የዕለቱ እንግዳችን አቶ ማቲዮስ ቃሚሶ ‹‹የማቲዮስ ቃሚሶ ቡና›› ‹‹የቅዱስ ዱቄት ፋብሪካ›› መስራችና ባለቤት ነው።

ከሁሉም በፊት ለትምህርት ትኩረት መስጠት እንዳለበት እየተነገረው ያደገው አቶ ማቲዮስ፤ ቤተሰቦቹ በተለይም ወላጅ አባቱ በትምህርት ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ ምኞታቸው ነበር። ምኞታቸው ዕውን እንዲሆን ታዲያ ‹‹ያልተማረ ሰው ወደፊት ከብት እንኳን ማገድ አይችልም›› እያሉ ትምህርት ያለውን ትልቅ ዋጋ ሊያስረዱት ሞክረዋል። ይሁንና የወላጅ አባቱን የሁልጊዜ ምክር ወደ ጎን በመተው ውስጣዊ ፍላጎቱን በማዳመጥ ከእግር ኳስ ጨዋታ ባለፈ ቡና አቅራቢ ነጋዴ ሆኗል።

በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ገተራ ቀበሌ ተወልዶ ያደገው አቶ ማቲዮስ፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ አካባቢው ተከታትሏል። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ከመጓዝ ይልቅ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ለመግፋት ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው በመሆኑ ትምህርቱን ወደጎን በመተው በእግር ኳስ ተጫዋችነት ለተከታታይ አምስት ዓመታት አካባቢውን በመወከል ለአለታ ወንዶ ከነማ እግር ኳስ ቡድን ጥሩ ውጤት ሲያስመዘግብ መቆየቱን አጫውቶናል።

እግር ኳስ ተጫዋች በመሆኑ ከብዙ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ያገኘበትና ከሀገር ሀገር መንቀሳቀስ የቻለበት በመሆኑ ደስተኛ እንደሆነና ወቅቱን ሲያስታውስ ብዙ ትዝታዎች እንዳሉት ሲገልጽ፤ ‹‹ኳስ አንዱ የሕይወት መስመሬ ሆኖ ብዙ ነገር እንዳውቅና እንድረዳ እንዲሁም ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት እንዲጠነክር አድርጓል›› በማለት ነው። ለኳስ ያለው ፍቅር ምንም እንኳን ጥልቅ ቢሆንም ታላቅ ወንድሙ የሚሰራውን የቡና አቅራቢነት ሥራ በማየት ቀስ በቀስ ወደ ሥራው ተስቧል። ለማገዝ በሚል የተጠጋው ሥራም ኳስ ተጫዋችነቱን አስጥሎ ዛሬ ላይ የሶስት ድርጅት ባለቤት አድርጎታል።

የንግድ ሥራን ‹‹ሀ›› ብሎ ሲጀምር ከቤተሰብ ጋር እንደነበር ያነሳው አቶ ማቲዮስ፤ ታላቅ ወንድሙ ይሰራ የነበረውን የቡና አቅራቢነት ሥራ ቀረብ ብሎ በማገዝና በኃላፊነት ጭምር በመሥራት ሥራውን ተቀላቅሏል። ከጥቂት ዓመታት በኋላም በግሉ ቢሰራ ተመራጭና አዋጭ እንዲሁም ውጤታማ እንደሚሆን በማሳብ የቡና መፈልፈያ ድርጅቶችን በኮንትራት እየወሰደ መሥራት ጀምሯል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቡና መፈልፈያ ጣቢያዎችን በማፈላለግ ኮንትራት ወስዶ ሲሰራ እንደነበርና በዚህም ውጤታማ እንደነበር ያስታውሳል።

ከታላቅ ወንድሙ ጋር የጀመረው ሥራ በቂ ዕውቀትና ልምድ መቅሰም እንዳስቻለው የሚናገረው አቶ ማቲዮስ፤ በወቅቱ ሥራውን በከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት ሲሰራ እንደነበር ያስታውሳል። በፍላጎትና በተነሳሽነት መሥራት መቻሉም ዘርፉን ለማወቅና ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። በጊዜ ሂደት ያገኘውን ዕውቀትና ልምድ ተጠቅሞ ሥራውን በግሉ ቢሰራ አዋጭና ተመራጭ እንደሆነ በማሰብ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ በግሉ መሥራት ችሏል። ለዚህም ትልቅ መሠረት የጣለለት ከወንድሙ ጋር በጋራ መሥራት መቻሉ እንደሆነ ይናገራል።

ከእግር ኳስ ጨዋታ ወጥቶ ከወንድሙ ጋር የንግድ ሥራን የጀመረው አቶ ማቲዮስ፤ በአሁን ወቅት በኮንትራት ሲወስዳቸው የነበሩ የቡና መፈልፈያ ድርጅቶችን በግሉ ማቋቋም ችሏል። በመሆኑም በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያውን ማቲዮስ ቃሚሶ ቡና አቅራቢ ድርጅት አለታ ወንዶ ጩኮ ወረዳ ላይ ማቋቋም ችሏል። ድርጅቱ እሸት ቡና መፈልፈያ ሲሆን፤ ቡናውን ከአካባቢው አርሶ አደር በመግዛት ፈልፍሎ፣ አጥቦ፣ አድርቆና አበጥሮ የታጠበ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ቡና ለላኪዎች ያቀርባል።

ሥራውን እያሰፋና እያሳደገ ሄዶ ቁጥር ሁለት ቡና ማዘጋጃ ጣቢያ ያቋቋመው አቶ ማቲዮስ፤ ከትውልድ አካባቢው ወጣ በማለት፤ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ላይ ሁለተኛውን እሸት ቡና መፈልፈያ ጣቢያ አቋቁሟል። ድርጅቱ በተመሳሳይ እሸት ቡና ከአካባቢው ቡና አምራች አርሶ አደር አሰባስቦ ፈልፍሎ፣ አጥቦ፣ አድርቆ፣ ቀሽሮና አበጥሮ የታጠበ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ቡናን ለላኪዎች እያቀረበ ይገኛል። አራት የሚደርሱ ቡና ላኪዎችም ከማቲዮስ ቃሚሶ ቡና አቅራቢ ድርጅት የታጠበ ደረጃ አንድና ሁለት ቡና እየገዙ ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ።

በሁለቱ ቡና ላኪ ድርጅቶች ለውጭ ገበያ የሚዘጋጀው ቡና በጥራትም ሆነ በመጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ የመጣ ሲሆን፤ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና ጥራቱም የተጠበቀ እንዲሆን ከአርሶ አደሩ ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ማቲዮስ፤ በሁለቱም አካባቢዎች 300 ከሚደርሱ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግሯል። ለአርሶ አደሮቹ ከሚያደርገው ድጋፍ መካከልም ኮምፖስት ወይም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ ማቅረብ አንዱ ሲሆን ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችንም ያደርጋል። በዚህም ለላኪዎች የሚቀርበው ቡና ከዓመት ዓመት የተሻለ ጥራትና መጠን ያለው በመሆኑ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ይናገራል። ቡና የማቅረብ አቅሙን በተመለከተ አቶ ማቲዮስ ሲናገር፤ በዓመት እያዳንዱ መኪና 10 ሺ ኪሎ ግራም ቡና መያዝ የሚችል 20 መኪና ደረጃ አንድ እና ሁለት የታጠበ ቡና ለውጭ ገበያ በማዘጋጀት ለላኪዎች ያቀርባል።

ማቲዮስ ቃሚሶ ቡና አቅራቢ ድርጅት በአሁን ወቅት እያቀረበ ያለው የቡና አይነት ኮሜርሻል የሚባለው ነው። በቀጣይ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን የገለጸው አቶ ማቲዮስ፤ ለዚህም በዘንድሮ በጀት ዓመት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል። እሱ እንደሚለው ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ ነው። ምክንያቱም ስፔሻሊቲ ቡና በዓለም ገበያ በስፋት የሚፈለግና ከፍተኛ ገቢ ማምጣት የሚችል ነው። ስለሆነም በቀጣይ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። በአሁን ወቅት ግን ደረጃ አንድ እና ሁለት የታጠበ ቡና ለላኪው እያቀረበ ነው።

ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ወጥቶ ቡና አቅራቢ መሆን የቻለው አቶ ማቲዮስ ቡና የማቅረብ ሥራው በፈጠረለት ዕድል የንግድ ሥራውን እያሰፋ ሄዷል። በመሆኑም ከቡና አቅራቢነቱ በተጨማሪ አለታ ወንዶ ከተማ ላይ ዱቄት ፋብሪካ በማቋቋም የዱቄት ምርት ለአካባቢው ማህበረሰብ እያቀረበ ይገኛል። ይህም በአካባቢው ያለውን ክፍተት በመመልከት የጀመረው ሥራ እንደሆነ ጠቅሶ፤ ቅዱስ ዱቄት ፋብሪካ በአሁን ወቅት በቀን 420 ኩንታል ዱቄት ያመርታል።

በቀጣይም ሥራውን የማስፋት እቅድ ያለው በመሆኑ የቡናውን ዘርፍ ከአቅራቢነት ወደ ላኪነት የማሳደግ እንዲሁም ዱቄቱ ላይ እሴት በመጨመር ፓስታና ማካሮኒ የማምረት ዕቅድ አለው። እቅዶቹን ዕውን ለማድረግም የዝግጅት ሥራውን ከወዲሁ የጀመረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል ተናግሯል። በቡናው ዘርፍ ላይ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራት ያለበት መሆኑን ያነሳው አቶ ማቲዮስ፤ በተለይም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር እንዲሁም በቡና ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቃሚና ወሳኝ ነው ይላል።

እሱ እንደሚለው፤ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች መካከል አንዱ ቡና እንደመሆኑ ቡና ላይ ብዙ መሥራት የግድ ነው። በአሁን ወቅት የሲዳማ ቡና በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ ይህን ዕድል አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሲቻል የኢትዮጵያ ቡና አሁን ካለው ተፈላጊነት በእጥፍ ማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ በማድረግ በዘርፉ የታቀደውን ማሳካት ይቻላል።

የሥራ ዕድልን አስመልክቶ አቶ ማቲዮስ ሲናገሩ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለና በቀጣይም የሥራ ዕድል ቁጥሩን ከፍ እንደሚያደርግ ነው የገለጸው። እሱ እንደሚለው፤ በሁለቱ የቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎች ብቻ 40 ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በጊዜያዊነት ደግሞ ከ200 እስከ 500 ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ከቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎቹ በተጨማሪ በቅዱስ ዱቄት ፋብሪካ በቋሚነት ለ40 ሰዎች በጊዜያዊነት ደግሞ ለ17 ሰዎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፤ በድምሩ ለ80 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

‹‹የልጅነቴ ሕልሜ ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር። ያም ቢሆን አሁን በምሰራው ሥራ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ›› የሚለው አቶ ማቲዮስ፤ ማንም ሰው በውስጡ የሚመላለስ ነገር ካለ አውጥቶ ሊሞክረው እንደሚገባና በሙከራ ውስጥ ደግሞ መውደቅ መነሳት መኖሩን ያነሳል። እሱ እንደሚለው ቡና አቅራቢ በሆነ ጊዜ ገና ከጅምሩ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውት ነበር። ነገር ግን ለሚገጥሙት ችግሮች ሁሉ እጅ ሳይሰጥ በብርቱ ትግል ዛሬ ላይ ደርሷል። የሰዎችን ድርጅት በኮንትራት ወስደው በሚሰራበት ወቅት ከባድ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ እንደነበርና ከዜሮ ተነስቶ ማንሰራራት እንደቻለም አጫውቶናል።

አሁን ላይ የቡናውም ሆነ የዱቄት ፋባሪካ ሥራው በጥሩ ሁኔታ ላይ እየተንቀሳቀሰ ያለ ሥራ እንደመሆኑ በቀጣይ እሴት በመጨመር ሥራውን የማስፋት ዕቅድ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ለዚህ ዕቅድ ተግባራዊነትም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሰራ እንደሆነ ያስረዳው አቶ ማቲዮስ፤ በቀጣይ በተለይም በቡና ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቡና በድርጅቱ ስም ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቋል። በዱቄት ፋብሪካውም እንዲሁ እሴት በመጨመር ፓስታና ማካሮኒ ለማምረት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሰራ ሲሆን፤ የዱቄት ማምረቻ ማሽኑን ወደ ፓስታና ማካሮኒ ማምረቻ ከፍ ለማድረግ እየተሰናዳ ይገኛል።

ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ድጋፍ የሚያደርግ እንደሆነ የገለጸው አቶ ማቲዮስ፤ በቋሚነት የሚረዳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ስለመኖራቸውም ተናግሯል። ከዚህ በተጨማሪም በማንኛውም ጊዜና ቦታ መንግሥታዊ ለሆኑ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

ወጣቶች ማንኛውንም ሥራ ሲሰሩ መሥራት ስላለባቸው ብቻ ሳይሆን አምነውና ፈልገው መሥራት ይኖርባቸዋል። የሚለው አቶ ማቲዮስ፤ ሥራውን ሳይሰሩ ስለሚያገኙት ገንዘብ ካሰቡ ውጤታማ መሆን አይችሉምና ሥራ ጠባቂ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ በመሆን ማንኛውንም ሥራ ወደው፣ ፈልገውና አክብረው መሥራት ከቻሉ ውጤታማ መሆን ይችላሉ በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You