የታዳጊዎችን የፈጠራ ክህሎት የሚያጎለብተው ስቲም ማዕከል

ዘመነ ቴክኖሎጂ ተማሪዎች በሳይንስና በሒሳብ ትምህርቶች ጎልብተው የህብረተሰቡን ችግር በሚፈቱ የፈጠራ ሥራዎች ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠርን ይጠይቃል። ለዚህም ነው በሳይንስ፣ በሒሳብ፣ በኢንጂነሪግ እና በሮቦቲክ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ እንደ ስቲም ፓወር አይነት ድርጅቶች ማዕከላትን በማቋቋም ተማሪዎችን በማሰልጠን ወጣቶች ወደ ቴክኖሎጂው ጠልቀው እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ናቸው።

የስቲም ፓወር በኢትዮጵያም በሀገሪቱ ለሚገኙ ለ65 የስቲም ፓውር ማዕከላት ድጋፍ ያደርጋል። በእነዚህ ማዕከላት ከመጀመሪያ ደረጃና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች በሮቦቲክስ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስና በሌሎችም መሰረታዊ ሳይንስ በሚባሉት በሂሳብ፣ በፊዚክስና በሌሎችም ዘርፎች ይሰለጥናሉ።

በስቲም ፓወር ከተቋቋሙ ማዕከላት መካከል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማዕከል አንዱ ነው። ይህ ማዕከል ከተቋቋመበት ጀምሮ በርካታ ተማሪዎች እያሰለጠ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል አስተባባሪ አቶ አለምሰገድ ሞረዳ እንደሚለው፤ በዩኒቨርሲቲው ሥር የሚገኘው ስቲም ማዕከል በ2008 ዓ.ም የተመሠረተ ነው። ማዕከሉ የተለያዩ ላብራቶሪዎች እና የራሱ የሳይንስ ሙዚየምም አለው። አሁን ስልጠናዎችን ይሰጣል። ከስልጠናዎቹ መካከል ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት /ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ/ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ይሰጣል። ይህ ስልጠና የሚያካትታቸው የኬሚስትሪ፣ የሒሳብና የፊዚክስ ትምህርቶችን ሲሆን፣ በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር በላብራቶሪ የተለያዩ ሙከራዎች እንዲያደርጉ በማስቻል የሚሰጥም ነው።

የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች ስልጠናውን በበጋው መርሃ ግብር ለሁለት ወራት እንዲወስዱ ይደረጋል። ስልጠናውን ከወሰዱ ከሁለት ወራት በኋላም ለመመዘኛ ፈተና ይቀመጣሉ። ፈተናውን ካለፉ ወደ ሁለተኛ ዙር ስልጠና እንዲገቡ ይደረጋል። በሁለተኛው ዙርም እንዲሁ አራት የስቲም ፕሮጀክት የትምህርት ዓይነቶችን ይማራሉ። ከእነዚህ ውስጥም ኤሌክትሮኒክስ፣ ሮቦቶችንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች መሥራት የሚያስችላቸው ‹‹ኢንቤድድ ሲስተም›› እንዲሁም ፕሮግራሚንግ እና ሶሊድ ዋርክ ናቸው። ሶሊድ ዋርክ የኮድ ሶፍትዌር አይነት ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ሥራቸውን በራሳቸው ዲዛይን እንዲያደርጉ ያስችላል። ይህ ሶፍትዌር ተማሪዎቹ የሚሰሯቸውን ሮቦቶች እና ሌሎችንም ቴክኖሎጂዎች ኮምፒዩተር ላይ መፍጠርና ራሳቸው በቀላሉ ዲዛይን እንዲያደርጉ ያስችላል።

አራቱን ኮርሶች ለመውሰድ ሁለት ወር ያህል ይፈጃል። ሁለተኛውን ዙር ካጠናቀቁ በኋላ ፈተና ይሰጣቸዋል። ፈተናውን ካለፉ ወደ መጨረሻ ዙር ይሸጋገራሉ። የመጨረሻው ወይም ሦስተኛው ዙር ፕሮጀክት የሚሰራበት ነው። ስለሮቦቲክስ የሚሰለጥኑበት እና ኢንጂነሪንግ ወይም ስቲም ፕሮጀክት የሚሰሩበት ነው። ተማሪዎቹ ሦስተኛው ዙር ላይ ሲደርሱ በሁለት ቡድን ተከፍለው የመጀመሪያ ‹‹ፕሮጀክት ኤ›› እና ሁለተኛው ‹‹ፕሮጀክት ቢ›› ተብለው ይሰየማሉ።

የመጀመሪያው ቡድን በ‹ፕሮጀክት ‹‹ኤ›› ያሉት ለሁለት ወር በሮቦቲክ ላይ ስልጠና ይሰጣቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሚኒ የሚባል ፕሮጀክትም ይሰራሉ። ይህንን ፕሮጀክት እንዲሰሩ የሚደረግበት ዋና ዓላማ በቡድን ሆነው ስለሚሰሩ ከመጀመሪያው ዙር እስከ ሁለተኛው ዙር የተከታተሏቸውን የስቲም ፕሮጀክቶች ተግባራዊ አድርገው ቴክኖሎጂ እንዲሰሩ ለማስቻል ነው ሲል አቶ አለምሰገድ ያብራራል።

ተማሪዎቹ ይህንን ቴክኖሎጂ እንዲሰሩ መደረጉ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስተባባሪው አቶ አለምስገድ ጠቅሶ፤ ወርክሾፕ ገብተው ቁሳቁስን በሚጠቀሙበት ወቅት እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል ይላል። ለአብነትም በወርክሾፑ መቁረጫ፣ መበየዳ እና መብሻ ማሽኖች መጠቀም እንደሚለማመዱበት መሆኑን ጠቅሶ፣ በራሳቸው መሥራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል ብሏል። በኤሌክትሮኒክስ የሙከራ ክፍል እንዲሁ ከኤሌክትሮኒክስ ጋር የተያያዙ ቁሳቁስ እየተጠቀሙ በራሳቸው ስለሚሰሩ የስቲም ትምህርቶች በይበልጥ ወደ ተግባር የሚለወጡበትና በብዛት ክህሎት የሚያዳብሩበት እንደሆነ ይገልጻል።

አቶ አለምሰገድ እንደሚለው፤ ተማሪዎቹ በዚህ ዙር የሰሯቸውን ሥራዎች ከሁለት ወር በኋላ ለውድድር አቅርበው ይወዳደሩባቸዋል፤ የተሻለ የሰራ ቡድንም ይሸለማል። እነዚህ ተማሪዎች ወደ ሶስተኛ ዙር ሲገቡ ለሁለት በቡድን የተከፈሉት የፕሮጀክት ‹‹ኤ›› ተማሪዎች ናቸው።

እነዚሁ ተማሪዎች ቀጥሎም በዚሁ ሦስተኛ ዙር ላይ ፕሮጀክት ‹‹ቢ›› ወይም አድንቫንስድ ፕሮጀክት ቡድን ተብለው እንዲገቡ ይደረጋል። እነዚህ በየዓመቱ በኅዳር ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የሮቦቲክና ኢንጂነሪንግ ውድድር የሚቀርቡ ናቸው፤ በዓለም አቀፉ የሮቦቲክ ውድድር ላይ የሚሳተፉም ይሆናሉ። ዘንድሮ በቱርክ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ሮቦት ኦሎምፒያድ ውድድር ኢትዮጵያ ለመወከል በተዘጋጀ ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።

ስቲም ማዕከሉ በቅርብ ጊዜ የልጆች የሳይንስ ሙከራ (ኪድስ ሳይንስ ኤክስፐርመንት) የተሰኘ ፕሮግራም ማካሄድ ጀምሯል ሲሉ አቶ አለምሰገድ ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህ ፕሮግራም ለሰባተኛ ክፍል እና ለስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች በተለየ መልኩ ፊዚክስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ፕሮግራሙ በክረምት መርሃ ግብር የሚሰጥ ሲሆን፣ ከተጀመረ በኋላ ውጤታማ መሆኑን መመልከት ተችሏል።

‹‹ስልጠናው ልጆቹን በሚመጥን መልኩ ስለሚሰጥ እነሱም በጣም ተቀብለውታል። በየጊዜው እየፈተሸን ማሻሻያዎችን እናደርጋለን፤ ከዚህም በኋላ ኮርሶቹ ታይተው ሥርዓተ ትምህርቱ በደንብ ተጠንቶ እነርሱን በሚመጥን መልኩ ተዘጋጅቶ ስልጠናው ይቀጥላል›› ሲል አቶ አለምሰገድ ተናግሯል።

ማዕከሉ ከዚህ ሌላ እሴት ጭመራ የተሰኘ ላብራቶሪም እንዳለው ጠቅሶ፣ በዚህ ላብራቶሪ የሳሙና፣ የዘይት እና የወረቀት አሰራር ሰልጠናዎች እንደሚሰጡ አመልክቷል። ባዮ መካኒክስ የተሰኘ ላብራቶሪም እንዳለው በማንሳት፤ በዚህም ተማሪዎቹ ለአንድ ወር ያህል ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ማዕከሉ ለተማሪዎች ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ሌላ ተጨማሪ ስልጠና ለመምህራን እንደሚሰጥ አስተባባሪው አስታውቋል። ማዕከሉ ተማሪዎችን ከየትምህርት ቤቱ ስለሚሰበሰብ እነዚህ ተማሪዎች የተመረጡባቸው ትምህርት ቤቶች መምህራን ተማሪዎቻቸው ስለሚወሰዱት ስልጠና ግንዛቤ ኖሮቸው ተማሪዎቹን ወደ ስልጠና ማዕከል እንዲልኩና እንዲተባበሩ የሚያስችል ስቲም የመምህራን ስልጠና (ስቲም ቲቸር ትሪንግ) እንዲኖር መደረጉን ያስረዳል።

‹‹በዚህ ፕሮግራም ከየትምህርት ቤቶቹ የሳይንስ መምህራን በመምረጥ ስልጠና እንሰጣለን፤ እያንዳንዱ ስልጠና ለአንድ ሳምንት ያህል ይሰጣል፤ የኬሚስትሪ፣ የሒሳብ፣ የፈዚክስ፣ የኤሌክትሮኒክስና ፕሮግራሚንግ ትምህርቶች በስልጠናው ይሰጣሉ›› ሲል አስታውቋል።

አቶ አለምሰገድ እንዳለው፤ የዩኒቨርሲቲው ማዕከል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኝ እንደመሆኑ፣ በዚህ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ተማሪዎች ቅድሚያ እድል ይሰጣል። ከሌላ አካባቢ ወደ ማዕከሉ መምጣት የሚፈልጉ ተማሪዎችንም ይቀበላል። ማዕከሉ ሁሉም ተማሪዎች የተቀመጠውን መመዘኛ መስፈርት እስካለፉ ድረስ የሚቀበላቸው ሲሆን፣ በአቂቃ ቃሊቲ ዙሪያ ብቻ የትራንስፖርት /ሰርቪስ/ አገልግሎት በነጻ ይሰጣል፤ የትራንስፓርት አቅርቦት አለመኖር ለሌሎች አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ከሌላ ቦታ ወደ ማዕከሉ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ሌላ አማራጭ ተቀምጦላቸዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት ባሉበት ቦታ መስጠት ባይችልም ተማሪዎቹ ማዕከሉ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በሚሰጥባቸው አቂቃ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች መምጣት ከቻሉ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ።

ማዕከሉ አሁን በአንድ ዙር እስከ 300 ተማሪዎች እያሰለጠነ ይገኛል። ስልጠናው ዓመቱን በሙሉ ይሰጣል። የስልጠና መርሃ ግብሩ በጋ ቅዳሜና እሁድ፣ ክረምት መደበኛ ተማሪዎች ስለማይኖሩ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በሥራ ሰዓት ይሰጣል። በየሁለት ወሩ ሦስት መቶ ተማሪዎችን አሰልጠኖ ያስመርቃል።

በቱርክ ለሚካሄደው ሮቦቲክ ኦሎምፒያድ በየማዕከላቱ በሮቦቲክ የሰለጠኑ ሁሉም ሰልጣኞች በሮቦቲስ የሰሩትን እንዲያቀርቡ መደረጉን ያስታወሰው አቶ አለም ሰገድ፤ 27 የማዕከሉ ተማሪዎች የሮቦቲክ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ሦስት ሦስት ሆነው በቡድን ፕሮጀክቶችን እንዲሰሩ መደረጉን ይገልጸል። ከእነዚህ መካከል የተመረጡ አራት ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን አስታውቆ፣ አስራ ሁለት ተማሪዎች በየፕሮጀክቱ ሦስት ሦስት ተማሪዎች የሰሩት ፕሮጀክት ለውድድር አቅርበዋል ብሏል። እነዚህ አስራ ሁለት ተማሪዎች በተለያየ መመዘኛ መስፈርት መሰረት ተወዳደረው ስለተመረጡ ፕሮጀክቶቹ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እንዲቀርቡ መደረጉን አብራርቷል።

አስተባባሪው እንደሚለው፤ ስቲም ፓወር ኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶቹ ግብዓት የሚሆኑ የቁሳቁስ ድጋፍ ለማዕከሉ አድርጓል። የተቀሩት ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ ግብዓቶች በዩኒቨርሲቲው ተሟልተው ሥራዎች ተሰርተዋል። በተለይ ወደ ማዕከሉ መጥተው ስልጠናውን ከወሰዱ 12 ተማሪዎች መካካል በፆታ አንጻር ሲታይ 7ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ የተቀሩት አምስቱ ወንዶች ናቸው። እነዚህ ተማሪዎች ናቸው አራት ፕሮጀክቶች ሰርተው ለውድድሩ ያቀረቡት።

ለዓለም አቀፉ ውድድር የቀረቡት አራት ፕሮጀክቶች ሁሉም ሮቦቶች ናቸው። ፕሮጀክቶቹ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ወይም ከተፈጥሮ ጋር ተሰማምተው አካባቢ ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተፅእኖ ሳይፈጥሩ የሚሰሩ ሮቦቶች የተሰሩባቸው ናቸው። አንደኛው ፕሮጀክት የሃይድሮ ፎኒክ ሲስተም/ ለግብርና ሥራ የሚውል/ ፋርሚንግ ሲስተም/ ነው። ይህም አፈር ሳያስፈልግ ለአትክልቶቹ የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች ብቻ አትክልቶቹ ወደ ተተከሉበት ፕላስቲክ የሚያስገባና መጠነ ሙቀት፣ በውሃ ውስጥ ያለውን የጨው መጠን፣ የአሲድ ወይም የቤዝ መብዛት እና አለመብዛቱን እየለካ የሚያመጣጥን ሮቦት ነው።

ሁለተኛው ፕሮጀክት ለአሣ እርባታ የሚያገለግል ሮቦት ነው። ሮቦቱ በኩሬ ውስጥ በተሞላው ውሃ አሞኒያ የተሰኘው ንጥረ ነገር መኖሩን አረጋግጦ ካለ እንዲወጣ ያደርጋል። አሞኒያ አሳዎችን ስለሚገድል በሮቦቱ ሴንሰር አማካኝነት የአሞኒያ ጋዙ ከውሃ ውስጥ እንዲወጣ ያደርጋል። በተለያየ ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን ጨው መኖር አለመኖሩን እንዲሁም በምን ያህል መጠን እንዳለ በማረጋገጥ እንዲወገድ ያደርጋል።

የአሲድም(ቤዝ) ጥንካሬ እየጨመረ ሲመጣ አሳዎችን ይገድላል ወይም ለእድገታቸው ምቹ ያልሆነ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል ያሉት አቶ አለምሰገድ፣ ይህንን እያረጋገጠ ውሃው ንጹህ እንዲሆን ያደርጋል። ሌላኛው አሳዎቹን በሰዓት እየጠበቀ ይመግባቸዋል። ያለምንም አጋዥ ራሱን በራሱ መቆጣጣር የሚችል ሮቦት ነው።

ሦስተኛው ፕሮጀክት ሆስፒታል ውስጥ ለታካሚዎች ሰዓት ጠብቆ ምግባቸውን እንዲወስዱ ትዕዛዝ የሚሰጥ ሮቦት ነው። አራተኛውና የመጨረሻው ሮቦት ዓይነሥውራን የሚያግዘው ነው። የብሬል ፊደሎች በሁሉም ቤት የለም ያለው አቶ አለምሰገድ፣ ተማሪዎች ብሬል ሊያገኙ የሚችሉት ትምህርት ቤት ብቻ ነው፤ አንደኛ ደረጃ ላይ ያሉ ተማሪዎች ይህን ለማግኘት ረዳት ወይም አጋዥ ይፈልጋሉ፤ ይህንን ድጋፍ የሚሰጥ ሮቦት ነው የተሰራው። ፊደሉን ሲነኩ፣ ምን ፊደል እንደሆነ የሚነግር ሮቦት ነው።

ማዕከሉ እነዚህን አራት ፕሮጀክቶች ለዓለም አቀፉ የሮቦቲክ ኦሎምፒያድ ውድድር ይዞ የቀረበ ሲሆን፤ ከአራቱ ፕሮጀክቶች አንደኛው አሣ እርባታ ላይ የሚያገለግለው ሮቦት ሦስተኛ ደረጃ በመውጣት አሸናፊ ሆኖ ተሸልሟል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You