በግቢው ውስጥ የማንጎና ሌሎች ተክሎች ይገኛሉ።ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ በግቢው የለም።በጓሮውም አረንጓዴና ንጹሕ ነገር ነው የሚያዩት።በዚህ ግቢ ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች በዓይነህሊናዬ ሳልኳቸው።ጤናቸው ከመኪና በሚወጣ ጭስ፣በየቱቦው ውስጥ ከተጠራቀመ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ከሚወጣ መጥፎ ጠረን፣ከኢንዱስትሪዎችና ከግንባታ ከሚወገድ ጭስና ብናኝ አይታወክም።ከድምፅ ብክለትም ነፃ ናቸው።ለደቂቃ እንዲህ የተደመምኩበት በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ዳራማሎ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ከሼ ፀሐ ግቢ ውስጥ ሆኜ ነበር።አጋጣሚውን አግኝቼ በእርሳቸው ግቢ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ የታዘብኩትን እንዲህ አካፈልኳችሁ እንጂ የአብዛኖቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ግቢ በተመሳሳይ ንጹሕና አረንጓዴ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡
ከሰሞኑ ወደ ደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ጉዞ ባደረኩበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ተነስቼ አርባምንጭ ከተማ እስክምደርስ የገጠራማውን ልምላሜ ትኩረቴን ስቦኝ እየተደመምኩ ነበር መንገዱ ሳይሰማኝ የደረስኩት።ጉዞው ደግሞ በዚህ ሙቀታማ ወቅት በመሆኑ ይበልጥ አስደሳች አደረገው።ልምላሜው እንደገጠሩ ስፋት ባይኖረውም በከተሞችም ለንጹሕ አየርም ለውበትም የሚሆኑ እይታን የሚስቡ የተለያዩ ተክሎች በየጎዳናው ተተክለዋል።በተለይ ወደ አርባምንጭ ከተማ ሲቃረቡ ከመግቢያው በር ጀምሮ ከመንገድ አካፋዩ ዳርና ዳር የተተከሉት ደማቅ ብርቱካማ ቀለም አበባ ያላቸው ተክሎች ወደ ከተማዋ ለሚገባው እንግዳ አቀባበል የሚያደርጉ ይመስላሉ።ጎላ ባለ ጽሑፍ ‹‹እንኳን ወደ አርባምንጭ ከተማ ደህና መጣችሁ›› ተብሎ በትልቅ ሰሌዳ ላይ ከሚነበበው በላይ ጥሩ ስሜት ነበር የፈጠረብኝ።ሥራቸው የሰፋው ተክሎች ዕድሜ ጠገብ እንደሆኑም ያስታውቃል፡፡
እንዲህ ደስ በሚል ስሜት ነበር አርባምንጭ ከተማ የገባሁት።ከተማዋ ሴቻና ሲቀላ በሚል ስያሜ ትጠራለች።ከተማዋ በግንባታ ብዙ የተጨናነቀች ባለመሆኗ ተስማሚ አየርና እይታ አላት።ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ የተገነቡት ሎጆች(ባህላዊ ሆቴልቤቶች)ጀርባ ያለው ጥብቅ ደን የሚስብ በሚል ቃል ብቻ የሚገለጽ አይደለም።ከእጅግም በላይ ቃል ቢኖር ይገባዋል።የገጠራማ አካባቢው ልምላሜ ተዳምሮ በከተማውም ያየሁት ለተክል የተሰጠው ትኩረት በተክሎች ምትክ ሕንፃዎች የከበቧትን አዲስ አበባ ከተማን እንዳስታውሳት አደረገኝ።በአረንጓዴ ልማት ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡
እንዲህ በልምላሜው በአድናቆት የገለጽኩላችሁ ጋሞ ዞንና አካባቢው ልምላሜውን ጠብቆ እንዲቆይ የማያስችሉ ክፍተቶችንም አስተውያለሁ።በአረንጓዴ ልማቱ ዛሬ እንዲህ መንፈሳዊ ቅናት ያሳደረው አካባቢ ከተማ ሲስፋፋ አርንጓዴን አብሮ ታሳቢ ማድረጉ ስለሚዘነጋ አርባምንጭ ከተማ እንዲህ ያለው ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
አርባምንጭ ከተማ ከመድረሴ በፊት ከመንገድ ማዶ ባየሁት ጥቅጥቅ አረንጓዴ ደን ውስጥ አልፎ አልፎ ከፍተኛ የሆነ ጭስ ይጨሳል።በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ደግሞ የሚቦገቦግ እሳትም ነበረ።ጫካው ይነድ ይሆን የሚል ስጋት ያደረብኝ እኔ እንጂ ለካስ የተለመደ ነው።በአስፓልት ዳር ላይ በተለያየ መጠን በማዳበሪያ ተሞልቶ ለሽያጭ የቀርበው ከሰል ከዚያ ከተደመምኩበት ደን ውስጥ የከሰለ እንደሆነ ከሌላ ሰው ማረጋገጥ አላስፈለገኝም።እንዲህ በግልጽ በደን ውስጥ ከሰል እየከሰለ በአደባባይ ላይ ለገበያ ሲቀርብ የሚከታተልና የሚቆጣጠር፤ ሀይ ባይ አስተዳዳሪና ተቆርቋሪ የለውም ያስብላል።የአካባቢው ነዋሪም ለጊዜያዊ ጥቅሙ ብሎ ለዘለቄታው የሚጠቅመውን ደን ማውደሙ የሚቆጭ ተግባር ነው፡፡
ሌላው በአንድ በኩል መልካም ነገር፤በሌላ በኩል ደግሞ ጥፋት ሆኖ ያገኘሁት በአባያ ሐይቅ ዳርቻ እየተከናወነ ያለው የአትክልት ልማት ነው።በዚህ አካባቢ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችና የአካባቢው አርሶአደሮች ከሐይቁ ውሃ በመጥለፍ በመስኖ ያለማሉ።በተለይ ለወጣቶች በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል መፈጠሩ በመልካም የሚወሰድ ተግባር ነው።በማህበር ተደራጅተው የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በልማቱ ከተሳተፉት መካከል አብዛኞቹ የትምህርት ውጤታቸው ከ10ኛ ክፍል በላይ ለመዝለቅ ያላስቻላቸው እንዲሁም በትምህርታቸው ዩኒቨርሲቲ የደረሱና በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡
በሚያለሙት አትክልትና ፍራፍሬ ውጤታማ ሆነው ዕድገት ለማስመዝገብ የተዘጋጁ ተስፋ የሰነቁ ናቸው። ከራሳቸው አልፈው በአካባቢው ላይም ለውጥ እንዲያመጡና ለሌላው አርአያ እንዲሆኑ ይጠበቃል። በሐይቁ ዳርቻ ላይ ሲያለሙ ያገኘኋቸው ወጣቶች በልማቱ ረጅም ጊዜ ባለመቆየታቸው ያመረቱትን ቲማቲም ገበያ ላይ አውለው ያገኙት ትርፍ ገና ነው።ግን ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶቹ ቀድመው ወደ ልማቱ ከገቡ ከአካባቢው አርሶአደሮች ጋር የሚወዳደሩ በመሆናቸው ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው አይጠራሩም።የነገ ህልማቸውን እንዳጫወቱኝ ከቻሉ በጋራ፣ካልቻሉ ደግሞ በግላቸው አንቱ የተባለ ነጋዴ መሆን ነው ፍላጎታቸው፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራው ዓላማም ወጣቶቹ ደክመው ውጤታማ እንዲሆኑ ነው።ነገር ግን በሐይቁ ዳርቻ ልማት የሚያከናውኑት ብቻ ሳይሆኑ አደራጅቶ ወደ ሥራ ያስገባቸው አካልም በሐይቁ ውስጥ ያለውን ብዝሐ ሕይወት ላይ በአሁን ወቅት እየደረሰ ያለው ጉዳት ቀድመው የተገነዘቡት አይመሰልም፡፡
በተለይም አልሚዎቹ የሚጠቀሙት የተለያየ ኬሚካል በሐይቁ ህልውና ላይ ከባድ ስጋት ደቅኗል።ከሁሉ በላይ ሐይቁ ሞልቶ ልማቱን እስከ ማጥለቅለቅ የሚደርስበት ጊዜ ጉዳቱም ሆነ ጥፋቱ የከፋ እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ።ባለፈው ክረም ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ እንደነበርና በዚሁ አደጋ የአትክልት ልማቱን ጨምሮ የብዙ አርሶአደሮችን ማሣ ማጥፋቱ ይታወሳል፡፡
ከልማቱ ጋር ተያይዞ በአባያ ሐይቅ ውስጥ ባሉ ብዝሐህይወት ላይ እየደረሰ ስላለው ጉዳት የደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስማማው አዋሽ እንደሚገልጹት፣በአባያ ሐይቅ ውስጥ የሚገኘው የዓሣ ሀብት በሁለት መንገድ ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል።ህገወጥ ዓሣ አስጋሪዎች እና ህገወጦቹ ጫጩት ዓሣ አጥማጆችም ሀብቱን በከፍተኛ መጠን አመንምነውታል፡፡
ሌላውና በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እያደረሱ ያሉት ደግሞ አትክልት አልሚዎች ናቸው።በተለይም ቲማቲም ሲያለሙ ወደ 12 ዓይነት ኬሚካል ይጠቀማሉ።ኬሚካሉ ወደ ሐይቁ እየገባ ዓሣዎችን በመጉዳቱ በሐይቁ ዳርቻ ላይ የሞቱ ዓሣዎችን ማየት እየተለመደ ነው፡፡
‹‹የአካባቢው ነዋሪም የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ጽህፈት ቤት የለም እስከማለት ደርሰዋል።በተለይም የአትክልት ልማት በስፋት የሚካሄድባቸው ወረዳው የሚገኙ ቆርጋ፣ ያቄ፣ፉራ፣ቆራሙለቱ ቀበሌዎች ችግሩ የከፋ ሆኖ ይታያል›› ያሉት ወይዘሮ አስማማው ልማቱ ወደ ሐይቁ መቅረቡ አልሚዎችንም ተጎጂ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።ባለፈው ዓመት ሐይቁ ሞልቶ በሦስት አልሚዎች የልማት ማሳ ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡
ወይዘሮ አስማማው ጽህፈትቤታቸው ችግሩን ቢገነዘበውም ለብቻው ውጤት አያመጣም ይላሉ። እንደርሳቸው ገለጻ የልማቱ ሥራ ከሐይቁ ዳርቻ በተወሰነ ደረጃ ራቅ ብሎ እንዲከናወን ጽህፈትቤቱ ከእርሻ ተፈጥሮ ሀብት ልማትና ከአካባቢ ጥበቃ አመራሮች ጋር ምክክር አድርጓል።ምክክሩ አልሚዎቹ ስለሚደርሰው ጉዳት ግንዛቤ ኖሯቸው የራሳቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስችል ትምህርት እንዲሰጥ የሚያደርግም ጭምር በመሆኑ በቀጣይ ለሚወሰደው ዕርምጃ ያግዛል፡፡
ህገወጥ የዓሣ ማስገርንም በመከላከሉ ረገድ በተመሳሳይ ማህበራትን ከሚያደራጀው ህብረት ሥራ ማህበር፣ንግድና ገበያ ማዕከል፣ ግብርና ጽህፈትቤትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በጋራ ለመንቀሳቀስ ጥረት ተደርጓል።ከተቻለ የልማት ሥራው ብዝሐ ህይወትን በማይጎዳ እንደ ሙዝ ያሉ ኬሚካል የማይጠቀሙ ልማቶች ቢከናወኑ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ኃላፊዋ እምነታቸው ነው።የግድ ከሆነ ደግሞ አንዱ ሌላውን በማይጎዳ መልኩ መከናወን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የኡጋዩ ቀበሌ ግብርና ጽህፈትቤት ባለሙያ አቶ አሰፋ አይዛ፣ በሐይቁ ላይ የተጋረጠውን ችግር ይጋራሉ።እርሳቸው እንደሚሉትም ከልማቱ በሚወጣው ኬሚካል በሐይቁ ውስጥ የሚገኘው ብዝሐ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በሐይቁ አካባቢ ሳር የሚግጡና ውሃ የሚጠጡ የቤት እንስሳትና በአቅራቢያው በሚገኘው ኡጋዩ ፓርክ ውስጥ የሚኖሩ የዱር እንስሳት ሳይቀር ተጎድተዋል።የሞቱም አጋጥመዋል፡፡
እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፣በቀበሌው የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው እያንዳንዱ ማህበር አምስት አባላት ያለው ስድስት ያህል ማህበር በሐይቁ ዙሪያ በአትክልት ልማት ተሰማርተዋል።ይሁን እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹም ሆኑ አርሶአደሮች በኬሚካል አጠቃቀም ላይ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ነው፡፡
ለሁሉም የአትክልት ዓይነት ጥቅም ላይ መዋል ያለበት የተለያየ የኬሚካል ግብአት ነው።ኬሚካሎቹም ለአትክልቶቹ ተስማሚ መሆናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል።ሆኖም ልማቱ ይሄን ሁሉ ማዕከል ያደረገ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ጽህፈትቤታቸው ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጋር ተናብቦ ለምን እንዳልተንቀሳቀሰ አቶ አሰፋ ለቀረበላቸው ጥያቄም ጽህፈትቤቱም ሆነ ባለሙያውም ምክር ሳይጠየቅ የተጀመረ የልማት ሥራ በመሆኑ ነው ችግሩ የተፈጠረው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ግን መረጃው ወደ ጽህፈትቤቱ መድረሱን ገልጸዋል።ልማቱ ሳይስተጓጎል ችግሩ የሚስተካከልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በጽህፈትቤቱ በኩል ለአልሚዎቹ ስለኬሚካል አጠቃቀምና ወደ ኬሚካሉ ወደ ሐይቁ ታጥቦ እንዳይገባ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ትምህርት በመስጠት ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።ግንዛቤው ሲዳብር ችግሩ እየተፈታ ይሄዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አባያ ሐይቅ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ሐይቆች በስፋት አንደኛ ሲሆን፣በውስጡም 54 የሚሆኑ ብዝሐይወት ይዟል።በዓመት አራት ሺ ቶን አሣም ይመረታል።አዞን ጨምሮ በነጭ ሳር ቤሄራዊ ፓርክ የሚገኙ የዱር እንስሳት ህልውናቸው አባያ ሐይቅ ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሐይቁ ከሚገኘው ብዝሀሕይወት የአካባቢው ማህበረሰብ የሚተዳደር በመሆኑ የተፈጠረው ችግር ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ያዳክመዋል።አባያ ሐይቅ 180 ሄክታር የሚሆነው የውሃ ክፍል በእምቦጭ አረም የተጎዳ መሆኑም በአንድ ወቅት መገለጹ ይታወሳል።አሁን በኬሚካል እየደረሰ ያለው ተጨማሪ ጉዳት ሐይቁን ለከፋ ጉዳት እንዳያጋልጠው ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2013