በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
በዲሲና በኒውዮር የተንጣለሉ አስፋልቶች እጅግ ውድ በሆኑ እንደ ላምቦርጊኒ፣ ጂፕ ቼሮኬ ፣ ጂፕ ራንግለር፣ ኦዲና ቼቭሮሌት ኮርቬቴ ያሉ ቅንጡ ተሽከርካሪዎችን በመንዳት የከሀዲውን ትህነግን እርዝራዦች ለመደገፍ እምዬ ኢትዮጵያን በውሸት ለማጠልሸት የተደረገው ሰልፍ እጅግ አሳፋሪ ነበር።ሰልፉ በቅንጠቱ መኪናዎች የታጀበ ስለነበር አይደለም እኛን አሜሪካውያንን ሳይቀር በጣም ያስገረመ ነበር።እነዚህን ዘመናይ ተሽከርካሪዎችንም ሆነ ቅንጡ አፓርታማዎችን በመረጠው ጎዳና ሲገዛ ያለምንም እዳ ከእኔና ከአንቺ በጠራራ የተዘረፈ ዶላር ሆጭ አርጎ እጅ በእጅ መሆኑን ስንሰማ የሀገራችን እዳ 30 ቢሊዮን ዶላር የደረሰበት ምክንያት ይገለጥልናል። ታዲያ ለትህነግ ወሬሳ ገዥ ቡድን ቆርጦ በሚጥል ቅዝቃዜ አስፋልት ላይ እንደ በርሚል ቢንከባለሉለት ያንሰዋል እንጂ ይበዛበታል። ለሰዓታት ሰልፍ እንኳ ከቀኝ እጁ የስታር ባክስ ካፑቺኖ ከግራው የማክዶናልድ በርገር የማይለየው የእነ አቦይ ዓይን ያወጣ የዘረፋ ቅምጥል ልጅ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማትችል በርሀብ አለንጋ የምትገረፍ እናት ዕርዳታ አትቀበይ ሲል መስማት ምን ያህል ከነባራዊ ሁኔታው እንደራቀና በራሱ የቅዠት ዓለም ሆኖ እንደሚያስብ ቁልጭ አርጎ ያሳያል። የአረመኔነት ጥግም ነው።
አውሮፓና አሜሪካ ሆነው የትግራይ ሕፃናትን ለእሳት መማገዳቸው ሳያንስ እኛ ካልገዛን እምቦቃቅላ ልጆችሽም ሆኑ እናቶች በርሀብ ይርገፉ ማለት የየትኛው የፖለቲካ ፓርቲ የትግል ስትራቴጂ እንደሆነ እነሱ ይንገሩን። እንዲህ ባለ ጭካኔና አረመኔነት ጅዋጅዌ የሚጫወተው የዲያስፖራ ጭፍራ በትግራዋይ ስም የተሰበሰበ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ለግል ጥቅሙ ቢያዎለው ምኑ ይገርማል። በ77 ዘግናኝ ድርቅ ዜጎች እንደ ቅጠል እየፉ የእርዳታ እህል ካሮቱም ላይ ሽጦ የጦር መሳሪያ መግዣና ድል ያለ የድርጅት ጉባኤ ማካሄጃ አይደል ያደረገው። የትህነግ ዲያስፖራ እርዝራዥ የሀገሪቱን ገጽታ ለማጠልሸት እንደ ጠላት ገንዘብ (ለነገሩ ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቡ ጠላቶቹ ናቸው።) የዘረፈውን ረብጣ እየበተነው ነው።
ትህነግ /ህወሓት ስሟን ለመጥራት እንኳ የሚጠየፋትን ኢትዮጵያ “ሀገሪቱ” በሚል የባይተዋርና የባዳ ስም እየጠራ፤ በመካከለኛ ዘመን በወረራ እንዳስገበረው ሕዝብና ሀገር ወይም እንደነ ፖርቱጋል፣ ስፔን ፣ እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ ፣ ወዘተረፈ ቅኝ እንደሚገዛት ሀገር ሀብትና ንብረቷን ለ30 ዓመታት በጠራራ በአደባባይ እየዘረፈ ወደ አረብ ሀገራት ፣ አውሮፓና አሜሪካ ፣ ቻይና ፣ ሲንጋፖር ፣ ኳላሉፑር ፣ ጃካርታ ፣ ወዘተረፈ ሲያሸሽ ኖሯል። የትህነግን ስግብግብ ኃይል የስስት ጥግ ስናስተውል ዘረፋው ፣ ዘግቶ በልነቱና አልጠግብ ባይነቱ ከቅኝ ገዥዎችም ሆነ ከወራሪዎችም በእጅጉ የከፋ ነው። ቅኝ ገዥዎች የሚገነቡት የሚሠሩት አንድ ቀን ለቀውት መሄዳቸው እንደማይቀር እያወቁ ነው። ሀብትና ንብረት የሚያሸሹትም ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን ለሀገራቸውና ለመንግሥታቸው ነው። የቀን ጅቡ ትህነግ ገዥ ቡድን የሚዘርፈው ከገዛ ሀገሩና ሕዝቡ ለዚያውም በርሀብና በእርዛት ከተጎሳቆለው ወገኑ መሆኑ ነው ዳፋውን የከፋ የሚያደርገው። በኢትዮጵያውያን ስም የተለመነ ከ30ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታና ብድር ዘርፎ ለግል ጥቅሙ አሽሽቷል። ስድስት ታላላቅ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቦችን ዘርፎ እብስ ብሏል። በግንባታ ላይ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተያዘለት በጀት 5ቢሊዮን ዶላር ነውና። 36ሺህ ሜጋዋታ ምንአልባትም በመቶ ሺዎች ሔክታር የሚገመት የመስኖ ልማት መሠረተ ልማት አጥቦናል። ይህ ግዙፍ ሀብት ለታለመለት ልማት ቢውል ኖሩ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ምን ያህል አስተዋፅኦ ይኖረው እንደነበር ለመረዳት የግድ የኢኮኖሚ ሳይንስ ባለሙያ መሆን አይጠይቅም። የከሀዲው ትህነግ ገዥ ቡድን ለቀደሙት 30 ዓመታት በጠራራ ሲዘርፍ የኖረው በስሙ ሲምልለትና ሲገዘትለት ለኖረው የትግራይ ሕዝብ አልነበረም። ወደ አገዛዝ ከመጣ በኋላም በፌዴራል ለ27 ዓመታት በትግራይ ለሦስት ዓመታት ሲቀማና ሲዘርፍ የኖረው የግል ካዘናውን ለማድለብ ነበር። ይህ መዥገር የሆነ ቡድን ለሀገራችንና ለሕዝባችን ከነበረው ጥላቻና ከማፊያነት ባህሪው አንጻር መለስ ብሎ ለገመገመው በግዙፍ ወይም ሜጋ ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ወለድ እየተበደረና እጁን ወደ ኋላ ሸርቦ በኢትዮጵያውያን ስም የሚለምነው ለሀገርና ለሕዝብ አስቦ ሳይሆን የሚዘርፈውን እያሰላና እንደ ትዕምት / ትካል እግሪ ምትካል ትግራይ ወይም EFFORT / Endowment Fund For the Rehabilitation of Tigray ያሉ የንግድ ኢምፓየሮችን ለመገንባት ነው።
አቦይ ስብሀት በተደጋጋሚ ያለአንዳች ዕፍረት በኩራትና በጀብደኝነት ደረታቸውን ነፍተው እንደተናገሩት “ በሀገሪቱ ካሉ ኩባንያዎች ግዙፉ ኤፈርት ነው።“ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በይፋ የሚታወቀው ሀብቱ ከሀገሪቱ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከ30 በመቶ በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በዚህ ስሌት ሀብቱ ከትርሊዮን ብር በላይ ነው ማለት ይቻላል። ኤፈርት በመንግሥት ውስጥ ያለ ሌላ መንግሥት ነበር። በግዛት ውስጥ ያለ ሌላ ግዛት ነበር። ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያ የኤፈርት ምስ እና የስግብግብነት ከርስ መሙያ ነበሩ። ሀገርና ሕዝብ የእነ አቦይ ስብሐት አንጡራ ሀብት ነበሩ። ሀገሪቷን ወደ ዘረፋ ዋሻነት ቀይረዋት ነበር። በሰው ልጅ ታሪክ ካላት ሀብትና ከድህነቷ አንጻር ላለፉት 30 ዓመታት እንደ ሀገራችን የተዘረፈ ፤ በቁሙ እርቃኑ ፣ አጽሙና መለመሉ የቀረ ሀገር የለም። እንደ ታዋቂው ፎርብስ መፅሔት ዘገባ ፤ ባለፉት 20 ዓመታት ብቻ ከሀገራችን በሕገ ወጥ መንገድ 30 ቢሊዮን ዶላር ሸሽቷል።ኢኮኖሚውንና ገብያውን በአብዮታዊ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በተሰኘ የዘረፋና የአምባገነናዊ አገዛዝ ማስፈጸሚያ አዚም እና ልማታዊ መንግሥት በተባለ ማደናገሪያ ከሀዲው ትህነግ ተቆጣጥሮት ስለነበር ከሀገር ይሸሽ የነበረው ሀብት ሙሉ በሙሉ የስብሐት ስረወ መንግሥት ነበር። እንዲህ በጠራራ በአደባባይ እየተዘርፈ የሸሸ ብድር ነው እዳ ሆኖ በሀገሪቱ አናት ላይ እየጨፈረ ያለው። እዳው ከጥቅል የሀገር ውስጥ ምርቷ 60 በመቶን ተሻግሯል። እዳው ከሀገሪቱ ተዘርፎ ከሸሸው መሳለመሳ ይሆናል። ሀገሪቷ ምንም እርህራሄ በሌላቸው ጅቦች መቆርቆዙ፣ ሕዝብ በድህነትና በኋላቀርነት መማቀቁና ባለዕዳ ማድረጋቸው ሳያንስ ሀገሪቷን ቅርቃር ከመክተቱ ባሻገር በአበዳሪ ተቋማት እንደ ውጋት ተቀስፋ ተይዛለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ዕዳ ያለበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለአውሮፓ የቦንድ ገበያ በተሸጠ ዩሮ ቦንዶ የተገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላር በውጭ የግል አበዳሪዎች ዘርፍ ውስጥ የሚገኝ ዕዳ ነው። የዚህ የብድር መክፈያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2024 የሚጠናቀቅ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያ በገባችው ስምምነት መሠረት አንድ ቢሊዮን ዶላሩን ከነወለዱ በተባለው ጊዜ ውስጥ መመለስ ይጠበቅበታል። ከዚህ በተጨማሪም ለአዋሽ ወልዲያ ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ተመሳሳይ መጠን ያለው ብድር ከውጭ የግል አበዳሪዎች አግኝታለች። ከእነዚህ የውጭ የግል አበዳሪዎች የተገኘ ብደርን የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ፣ አገሪቱ አሁን ካለባት ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ሸክም አንፃር አስፈላጊ መስሎ ቢታይም ፣ ይህንን ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕዳዋን መክፈል የማትችል አገር አድርጎ ሊያሰይም እንደሚችልና ይህም የወደፊት የውጭ ብድር ፍላጎት ላይ በር የሚዘጋ በመሆኑ ፣ መንግሥት ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአማርኛው ሪፖርተር ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይህንን አዝማሚያ በማየትም ሙዲስ የተባለው ዓለም አቀፍ የውጭ ዕዳ ገምጋሚ ቡድን ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት ፣ ኢትዮጵያን ዕዳ በመክፈል ረገድ ጥንቃቄ ሊደረግባት የምትገባ አስጊ አገር ብሎ እንደፈረጃት ማሳያ በማቅረብ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
የስግብግቡ ትህነግ ዳፋ እንደ ጥላ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚከተለን ሌላው ማሳያ በኮሚሽን ሲበደረው የኖረ እዳ ነው። የትህነግ ማፍያ ባለስልጣናትና ተላላኪ ደላሎቻቸው ከብድር ፈርቅ ይይዙና ኮሚሽን ይበሉ ነበር። ፕሮጀክት ሀ የተባለ ፕሮጀክትን ለመገንባት 250ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ከሆነ የትህነግ ማፍያዎችና ደላሎች ፋይናንሱን ያፈላልጉና ሲያገኙ ለፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገው 250 ሚሊዮን ዶላር በላይ 50 ወይም 100 ሚሊዮን አልያም በእጥፍ ጨምረው ብድሩንና ፕሮጀክቱን ያገናኙና ጨረታውን ከሚያሸንፈው ኩባንያ ልዩነቱን ይቀበላሉ።
ሕገ መንግሥታዊ ማፊያ የነበረው የትህነግ ገዥ ቡድን የሀገሪቱንና የሕዝቡን ጀርባ በእዳ ያጎበጠው ለሀገር ልማትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ቀናኢ ሆኖ አይደለም። ከእያንዳንዱ ብድርና ዕርዳታ የሚዘርፈውን ረብጣ ዶላር እና ለንግድ ኤምፓየሩ ኤፈርት በብቸኝነት የሚፈጥረውን ገብያ እያሰበ ነው ያለ ምንም ኃላፊነት ሲበደር የኖረው። በዚህ ማፊያ ቡድን ብድር የተነሳ ሀገሪቱ የገባችበትን ቅርቃር ከፍ ብለን ተመልክተናል። የሚያሳዝነውና የሚያስቆጨው ብድሩም ሆነ ዕርዳታው አየር ባየር ሲዘረፍ ኖሮ ሀገርና ሕዝብ እዳን ታቅፈው መቅረታቸው ነው። የእፉኝቱ ትህነግን ሀገርና ሕዝብ ጠልነት ጥግ ለተመለከተ በብድርም ሆነ በዕርዳታና በበጀት የሚያካሄዱ ማንቸውም የልማት ሥራዎች በቅንነት ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ታስበው ነው የሚል እምነት አይኖረውም። የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፣ የስኳር፣ የማዳበሪያ የባቡር ፣ የአስፋልት ፣ ወዘተረፈ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውጥንም ሆነ ሴራ ለዘረፋውና ለኤፈርት ኤምፓየር መናጆ ( አሻሻጭ) እንዲሆኑ ታልሞ ነበር ማለት ይቻላል።
በሀገሪቱ የግንባታ ታሪክ በግዙፍነት የሚታወቀው ወደ 5ቢሊዮን ዶላር በሚጠጋ በጀት የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 6ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የሀገር አርማ ሜጋ ፕሮጀክት ሆኖ እያለ የትህነግ ስግብግብ ቡድን ጥርሱን ለነቀለበት ዘረፋ ሲል አደጋ ላይ ጥሎት ነበር። በትህነግ ጄነራሎቹ በሚመራው ሜቴክ ለመዝረፍ ሲል የአነስተኛ የዱቀት ፋብሪካ ኤሌክትሮ ሜካኒካል እንኳ ስለመግጠሙ እርግጠኛ ላልሆንበት ሜቴክ በጨበጣ ሰጥቶ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ የመክሸፍ አፋፍ ላይ ነበር። የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አመራር ደርሶ ባይታደገው ኖሮ ፎርሾ ቀርቶ ነበር። የማፊያው ቡድን ለማይጠረቃው ስግብግብነቱ ምስ እንጅ ለሀገርና ሕዝብ ጥቅም ደንታ የለውም የምለው ለዚህ ነው። የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን በጥራትና በብቃት ማከናወን ባለመቻሉ ሥራው ለሌላ ተቋራጭ ተሰጥቷል። ሀገሪቱን ላልተገባ ከፍተኛ ወጪ መዳረጉ ሳያንስ ፕሮጀክቱ ከተያዘለት ጊዜ በዓመታት እንዲጓተት አድርጓል።
የሲቪል ሥራውን የሚያካሂደው ሳሊኒም ሜቴክ ሥራውን በተቀመጠለት ጥራትና ጊዜ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ እሱን ስጠብቅ ሥራ ለፈታሁበት በሚል ከፍተኛ የማካካሻ ተጨማሪ ክፍያ ጠይቋል። የሜቴክ ሥራ ጥራቱን ያልጠበቀና ዲዛይኑንም ያልተከተለ ስለነበር ፈርሶ እንደገና እንዲሠራ መደረጉ ተጨማሪ ወጪ ጠይቋል። ሜቴክ ለኤሌክትሮ ሜካኒካልም ሆነ ለምንጣሮና ለሌሎች ሥራዎች የወሰደው ቅድመ ክፍያ ከሥራው ጋር የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀና እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም ገንዘቡ እምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም። የምንጠራ ሥራውን በንዑስ ተቋራጭነት ለቀድሞ ታጋዮች መስጠቱ ፤ የማሽን ኪራይን ፣ የሲሚንቶና የብረት አቅርቦቱን የቀን ሠራተኞችን ሚንስ ቤት ሳይቀር በቁጥጥሩ ስር ማድረጉ ላስተዋለ የሕዳሴው ግድብ የስብሀታውያን ገንዘብ የምትታለብ ጥገት እንጂ የሀገር ምልክት ፕሮጀክት አልነበረም።
የትህነግን ክፉ ሴራ እንደ እጅ መዳፉ የሚያውቅ ዜጋ ፤ መለስ ግድቡን ለመገንባት የተነሳው ለኢትዮጵያ ዘላለም የማይተኛ ጠላት ለመፍጠር እና በማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ለመዝፈቅ እንጂ ለልማቷ አስቦ አልነበረም ቢል ወዲያው ወደ ሴራ ኀልዮቶ ቅርጫት የሚጣል ሃሳብ አይሆንም። የስኳር ፣ የማዳበሪያና የሌሎች ፋብሪካዎች ምንም ልምድ ለሌለው ሜቴክ ያለ ጨረታ መሰጠታቸው የስብሀታውያን መዝገብ ከዘረፋው እንጂ ከሀገርና ከሕዝብ ወገን እንዳልሆነ ለመረዳት ነብይ መሆን አይጠይቅም። የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ለሜቴክ መሰጠታቸውን በጅምር በማስቀረቱ መንግሥት በሌለ የውጭ ምንዛሬ አቅሙ በየዓመቱ እስከ 280 ሚሊዮን ዶላር ለስኳር ግዥ እንዲያወጣ ከማስገደዱ ባሻገር የሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች ዕዳ ወለዱን ሳይጨምር 149 ቢሊዮን ደርሷል።እንደ መውጫ ላለፉት 30/47 ዓመታት በስግብግቡ ትህነግ ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘረፈው ሀብት የስብሀታዊ ስርወ መንግሥትን ካዘና ለማድለብ ውሏል። በትግራይ ሕዝብ ስም ያለከልካይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሲዋኝ የኖረው ኤፈርትም የአቦይ ስብሀትና ጭፍሮቹ ንብረት ነበር። የትግራይ ሕዝብ ከ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በሴፍትኔት ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የመከራ ኑሮ እየመራ ይገኛል።
የእነ ስብሐትና ጭፍራዎቹ ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማዶች ግን በዚህ ሀብት የተቀማጠለ ኑሮ ይኖራሉ። ከዚች ድሀ ሀገር መቀነት ተቆርጦ በተሰረቀ ገንዘብ በአሜሪካና በአውሮፓ ባልተለመድ ሁኔታ የእነ አቦይ ቅምጥሎች ቅንጡ አፓርታማዎችንና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን እጅ በእጅ በመክፈል ሲገዙ መመልከት የተለመደ ነው። በእነዚህ ከተሞች ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የንግድ ድሮጅቶች ባለቤቶችም ናቸው። ልጆቻቸው ውድ በሆኑ የአሜሪካና የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ይማራሉ። የዚህ ዘበናይ ኑሮ ስፖንሰር ገዥ ኃይል ከስልጣኑ ገሸሽ ካለበት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም አንስቶ በተለይ ጁንታው በጫረው እሳት ተቃጥሎ አመድ ከሆነ በኋላ ደግሞ የተዘረፈውን ግዙፍ ሀብት በመጠቀም ከእሳቱ የተረፉ እርዝራዦችን ተጠቅሞ አለሁ ለማለት ሥራ ላይ እየዋለ ነው። የትግራይ ወጣቶች ግን በክልሉ በነበረው ጭቆና፣ አድልዎና መድልዎ የተነሳ በመማረር ለሕገ ወጥ ስደት በመዳረጋቸው የሻርክና የበርሀ ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል። ሰሞኑን በየመን የስደተኞች ጣቢያ በተነሳ እሳት ስንቶች እንደሞቱ ይታያችሁ። የእነ አቦይ ቅምጥል ደግሞ አባቱ በዘረፈው ገንዘብ በሀገረ አሜሪካ ጢምቢራው እስኪዞር ጠጥቶ ከመንገድ መብራት ምሰሶ ይጋጫል።እውነትንና ፍትሕን ይዘን እንሻገራለን !
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም