በውሸት፣ በማስመሰል ያልተማረረ እዚች ሀገር ላይ ማን አለ? እኔ በበኩሌ ምርር ነው ያለኝ።መሽቶ በነጋ ቁጥር የምሰማው፣ የማነበው ሁሉ ውሸት ነው።በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ የህዝቦችን አንድነት የሚያላላ የጠብ ቁርሾ ማንበብ ስልችት ነው ያለኝ።ዋሽቶ ማስታረቅ እያለ ዋሽተው የሚያጣሉ የበዙበት ዘመን ላይ ቆመናል።እዛም እዚህም መሰረተ ቢስ የውሸት ትርክቶችን መስማት ጆሮአችን ሰልችቶታል።ሀገር የሚያቆም ጠፍቶ ሀገር ለማፍረስ መሽቀዳደም የብዙዎቻችን አላማ ሆኗል።ከሀገር በላይ፣ ከህዝብ በላይ ምን ደስታ እንዳለን አላውቅም።የተማረውም ያልተማረውም በየፊናው ነገር ሲፈትል፣ የሀሰት ወሬ ሲፈጥር የሚውል ነው።አብዛኞቻችን ከሀገር ግንባታ ይልቅ እውቀታችንን ለሀገር መከራ እያዋልነው ነው።ለክፋትና ለተንኮል የምንጠቀምበትን አእምሮ ሀገር ሊለውጥ በሚችል ተግባር ላይ ብናውለው ይሄኔ የት በደረስን ነበር።ሰው እንዴት ሀገር ለማፍረስ ይማራል? ሰው እንዴት ሀገር ለመጉዳት ይሰለጥናል?
በተለይም በውሸት ተወልደው በውሸት ያደጉት የጁንታው ቤተሰቦችና ርዝራዦች ዛሬ የውሸት ጅራፋቸውን ሲያጮሁ ላያቸው ግርምት የሚፈጥር ነው፡፡ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲዘርፉ፤ሲገድሉ፤ሲያስሩና ሲያንገላቱ መኖራቸው ተረስቶ ዛሬ ብጹዓን መስለው ዓይናቸውን በጨው አጥበው ቀርበዋል፡፡የሰሜን ዕዝን ከኋላው እንዳልወጉ፤በማይካድራ ሺዎችን በጅምላ እንዳልረሸኑ፤ሴት የመከላከያ አባላትን ጡት እንዳልቆረጡ ዛሬ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሆነው የአዞ እንባ እያነቡ ይገኛሉ፡፡
የህወሓት ቡድን ቤተሰቦችና ርዝራዦች ጥቅማቸው የተነካባቸው በመሆኑ ውሸት ቢያወሩ የሚያስገርም አይደለም፡፡ከኢትዮጵያውያን ጉሮሮ ተነጥቆ በአሜሪካና በአውሮፓ የተንደላቀቀ ህይወት እንዲኖሩ የተመረጡ በጹኣን ነበሩ፡፡ከድሃዋ እናት ተነጥቆ፤ከድሃ ተማሪ የእለት ጉርስ ተቀንሶ፤ከጉሊት ነጋዴዋ ተመንትፎ በአሜሪካና በአውሮፓ በቅንጡ ቤት እንዲኖሩና በቅንጡ መኪና እንዲምነሸነሹ ባረኮት የተደረገላቸው የተመረጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ችግርን ከቃላት ባለፈ ኖረውበት የማያውቁ፤ኢትዮጵያን ሃብቷን እንጂ ድህነቷን መካፈል የማይሹ ቅንጡዎች ነበሩ፡፡ስለዚህም ይህ የተንደላቀቀ እና በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የሚኖረው ዜጋ የማይኖረውን ቅንጡ ህይወት ሲያጡ እንደ እብድ ቢያደርጋቸው የሚገርም አይደለም፡፡የመጣላቸውን እንደ እብድ ሲለፈልፉ ቢውሉ ቢያንስባቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም፡፡
ለ30 ዓመታት ያህል የስብሃትና ቤተሰቡ ንብረት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ነጻ ወጥታለች፡፡በሀገሪቱ ውስጥ ለ30 ዓመታት ፈላጭች ቆራጭ በመሆን ከ30 ቢሊዮን በላይ ባለዕዳ በማድረግ፤ሃይማኖትን ከሃይማኖት ፤ብሄርን ከብሄር በማጋጨትና ህዝቡ እርስ በራሱ በጥላቻ እንዲተያይ ሴራ በመጎንጎን የተዳከመች ኢትዮጵያን በመፍጠር፤የኢትዮጵያን ለኡላዊነት ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ በመስጠት አሳፋሪ ታሪክ ጥሎ ከመቃብር በታች ውሏል፡፡ሆኖም ግን ዛሬም በውጭ የሚኖሩ የስብሃት ቤተሰቦችና የጁንታው ረዝራዦች ለ30 ዓመታት ያህል ያሳለፍነው የመከራና ስቃይ ዘመን እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡የበሬ ወለደ ውሸት በመለፈፍም ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ማደናገር ይፈልጋሉ፡፡
ሆኖም ህወሓት ላይመለስ ተሰናብቷል።ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ የ80 ቀን የሙት ተዝካሩን ለማውጣት ኢትዮጵያውያን ሽር ጉድ እያሉ ናቸው፡፡ስለዚህም እናንተ ውሸታሞች ቁርጣችሁን እወቁ ፤ህውሓት ተቀብሯል፤ላይመለስ እስከዘላለሙ ተሰናብቷል፡፡
እኔ ግን አንድ ነገር ልምከራችሁ።እስኪ ከቡድንተኝነት ወጥታችሁ እንደ ህዝብ አስቡ።እስኪ እንደ ሀገር እናስብ።እናንተ ባይርባችሁ ብዙ የተራቡ ህዝቦች ያሉባት ሀገር ናት።እናንተ ባትቸገሩ ብዙ ችግረኛ ወገኖች ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉባት ሀገር ናት፡፡ተፈጥሯችሁ አይፈቅድላችሁም እንጂ ይፈቅድልናል የምትሉና የሰው ፍጡሮች ነን የምትሉ ከሆነ እስኪ ህይወትን ካለ መልካምነት ለአፍታ አስቧት? ህይወት እኮ ያለ ጥሩነት ምንም ናት።እኛ በአባቶቻችን እንደኮራን ሌሎችም በእኛ የሚኮሩበትን እድል እንፍጠር።በእናንተ የተነሳ እኮ ሀገራችን በርካታ መስዋዕትነቶችን ከፍላለች።እየደማች..እየቆሰለች ዘመናት አልፏታል።ህዝባችንን በተሳሳተ ትርክት ፍቅሩን፣ አንድነቱን አጥቷል፡፡ብዙዎች በእናንተ የውሸት ትርክት እርስ በርስ ተገዳድለዋል፤ባልና ሚስት አፋታችኋል፤ቤተሰብ በትናችኋል፤ህጻናት እና ሴቶች በጠራራ ጸሐይ እንዲታረዱ አድርጋችኋል፤ሰዎች በማንነታቸው የተነሳ በጅምላ እንዲረሸኑ አስታጥቃችሁ አሰማርታችኋል፤እናንተን ዶላር የሚለቅሙ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንና ታዋቂ ሰዎችን በመግዛት ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ጥላሸት ለመቀባት ሞክራችኋል፡፡መቼ ነው የምትለቁን? መቼ ነው ከኢትዮጵያ ወገብ ላይ የምትወርዱት? መቼ ነው በህጻናትና ሴቶች ህይወት ላይ መወራረዱን የምታቆሙት ?
አንድ ነገር ግን ልንገራችሁ ፤እየተራገማችሁ፣ እየናቃችሁ፣ እየወቀሳችሁ በውሸት ሀገርና ህዝብ እየጎዳችሁ ከመክሰር ባለፈ የምትፈጽሙት ጀብድ የለም።ከመጉደል ባለፈ የምትሞሉት የህይወት ክፍል አይኖራችሁም፡፡ደግሞም የቀድሞው የህወሓት አገዛዝ ይመለሳል ብላችሁ የምትቃዡ ካላችሁ ቁርጡን ልታውቁት ይገባል፡፡ህወሓት መቶ አፈረስ ተጭኖበታል፡ ፡ትቢያ ሆኗል፡፡
famous mark https://www.abmahnung-filesharing-anwalt.de/unsere-rechtsanwaelte.list bought on the streets in new york city.most popular zagabriamedical for cheap sale.
በሌላ መልኩ ግን የህውሓት ቡድን የጥቅም ተጋሪ ላልሆናችሁና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የውሸት ትርክቱን ሰለባ ለሆናችሁ ወገኖቼግን አንድነገርልንገራችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችሁናት፤የእናንተም ሰላም የሚጠበቀው ሀገራችን ሰላም ስትሆን ነው፡፡ስለዚህም ስለኢትዮጵያ ሁልጊዜም መልካም ተናገሩ፤መልካም ተመኙ፤መልካም አስቡ።በህይወታችሁ ሞልታችሁ የምትፈሱት በመልካም ቃላቶቻችሁ በኩል ነው። በአሁኑ ሰዓት የሀገራችንን አንድነት እየበረዙ ያሉት ከክፉ አንደበት የሚወጡ እኩይ ቃላቶች ናቸው።ቃላት በወጉ ካልተጠቀምንባቸው ጉዳት የማድረስ ኃይላቸው ከፍተኛ ነው።ሩዋንዳ ውስጥ ያን ሁሉ የንጹሀንን እልቂት ያስከተለው ቃል ነው።ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ዛሬም ድረስ እንደ ምክንያት የሚነሳው ቃል ነው።ቃላት የጥቅማቸውን ያክል ጉዳታቸውም የከፋ ነው።በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ውስጥ እዛም እዚህም የምንሰማቸው መሰረተ ቢስ የጥላቻ ንግግሮች አሉ።በየማህበራዊ ሚዲያው የምንለቃቸው መልዕክቶች ሀገር የማፍረስ ኃይል ያላቸው ናቸው።
ህዝብን ከህዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ሥራዬ ብለው የተሳሳቱ መልዕክቶች የሚያሰራጩ ራስ ወዳድ የሆኑ ጥቅመኛ ግለሰቦች በየቦታው አሉ።በህዝቦች መከፋፈል የግል ጥቅማቸውን ለማስፈጸም ውሸት ፈብርከው፣ ያልሆነና ያልተደረገ ነገር እንደሆነና እንደተደረገ በማስመሰል ህዝብ የሚያወናብዱ ብዙዎች አሉ።ስለዚህም መልካም ቃላትን በመናገር ሀገራችሁን ታደጉ፤የውሸታሞችን ቃላት አጋልጡ፤ውሸታሞች በተሰለፉበት መድረክ አትሰለፉ፡፡ይህ ሲሆን ውሸታሞች ለአፍታም ቢሆን በእኛ ላይ ስልጣን አይኖራቸውም፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም