ዓለማየሁ ገብረ ማርያም
የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንጀር “አሜሪካ ቋሚ ጓደኞች ወይም ጠላቶች የሏትም፣ ቋሚ ጥቅሞች ብቻ ነው ያሏት” ብለው ነበር። የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ህወሓት) ለ 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የአሜሪካ “ቋሚ ጓደኛ” ነበር። አሁን ግን እንደ ኪሲንጀር አነጋገር በኢትዮጵያ ውስጥ “ከማያውቁት መልአክ ይልቅ የሚያውቁት ዲያብሎስ ይሻላል” የሚል አቋም አሜሪካ የወሰደች ይመስላል።
ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል የአሜሪካ “የቋሚ ጥቅም” በዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት ጦርነት ላይ የሚቀላቀል ጓደኛና ግብረአበር ማግኘት ነበር ። ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ. በ 2015 ባደረጉት ጉብኝት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ኢትዮጵያን “የላቀ አጋር” ብለው የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት “ቁልፍ አጋር” ብለው የሰየሟት ስትሆን “ከአፍሪካ ከማንኛውም ሀገር የበለጠ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች በማበርከት” ኢትዮጵያን አድንቀዋል ።
እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2021 የባይደን አስተዳደር “የላቀ አጋርነት” እንደሞተ እና ኢትዮጵያም ወደ አሜሪካ “ቋሚ ጠላት” ሞፈር ውስጥ እንደገባች የማያጠራጥር ጥቆማ ይሰጣል።
ሆኖም የአሜሪካ “ቋሚ ጥቅሞች” በኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል ምንድን ናቸው?
አምስት “ቋሚ ጥቅሞች” አሉ እላለሁ።
የመጀመሪያው የህወሓትን ቅሪት (ህወሓት) ወደ ስልጣን መመለስ ነው ። እ.ኤ.አ. ህዳር 3 ቀን 2020 በትግራይ ክልል በሰሜን እዝ ጣቢያ (ሰእጣ) ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ የህወሓት ጦር በፌዴራል መከላከያ በመቅጽበት ተደመሰሰ ፡ እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 2020 አጋማሽ ጀምሮ የሱዛን ራይስ ፣ የአንቶኒ ብሌንከን እና ጄክ ሱሊቫን (የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ሹማምንት የሆኑት) በማሕበራዊ ሜድያ ላይ የውሸት ትርክት ዘመቻቸውን ጀመሩ፣ “ኢትዮጵያ እርስ በእርስ ጦርነት ልትጠፋ ነው፣ ዘር ተኮር ግድያ እየተካሄደ ነው፣ የጦር ወጀል እየተፈጸመ ነው፣ የቀጠናው ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ እየወደቀ ነው “ ወዘተ ።
የኢትዮጵያ መከላከያ የህወሓትን ጦር ዶጋ አመድ አድርጎ ህወሓት ወደ ጫካ ሲያፈገፍግና ድል ለኢትዮጵያን መሆኑን ሲገነዘቡ እነዚህ የአሜሪካን ባለሥልጣኖች የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር “መደራደር” እና “መወያየት” አለበት የሚል ዘመቻ በይፋ ጀመሩ።
የ “ውይይቱ” ግባት ለህወሓት የሥልጣን መጋራት ስምምነት እንዲኖር፣ በብሔራዊ መንግሥት ውስጥ ማዕከላዊ ሚና እንዲኖራቸው ዋስትና ለመስጠት እናም ላለፉት 27 ዓመታት በፈፀሙት ማናቸውም ወንጀሎች፣ የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀሙትን እና የማይ ካድራ ጭፍጨፋዎችንም ጨምሮ፣ የህግ ተጠያቂነት እንዳይኖርባቸው ለማድረግ ነበር።
ጥሩ ስራ ሲሰራ እውቀት መስጠት ተገቢ ነውና ምንም የትራምፕ አስተዳደር የተሳሳተ አቋም በኢትዮጵያ ላይ ቢኖረውም እ.ኤ.አ ኖቬምበር 4 ቀን 2020 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የወያኔን ጥቃት በማውገዝ “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመቆም ለሰላም ፣ ለብልፅግና ፣ ለዴሞክራሲ እና ለህግ የበላይነት ከፀኑ ሁሉ ጋር ትሰራለች” ብለዋል ።
እ.ኤ.አ ኖቬምበር 15 ቀን 2020 የአሜሪካ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጂ ህዳር 14 በኤርትራ ላይ የወያኔ ሕገ ወጥ ጥቃቶችን እና በትግራይ የተፈጠረውን ግጭት ዓለም አቀፍ ለማድረግ ህወሓት ያደረገውን ጥረት አጥብቀው አውግዘዋል ።
እ.ኤ.አ. ታህሳስ 1 ቀን 2020 ናጂ በቢቢሲ ቃለ-ምልልስ ውስጥ ስለ ህወሓት ማጥቃት ሲናገሩ “እዚህ ላይ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ማስታወሱ አስፈላጊ ነው ። በአንድ እጅ ሉዓላዊ የኢትዮጵያ መንግሥት እና በክልል አስተዳደር ያለ ግጭት ነው ። በመሠረቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግጭት የጀመረው የትግሬ ክልል አመራር ነው… በመሰረታዊነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን ለማውረድ እና በዚያው ውስጥ ተሽሎክሉኮ ላለፉት 27 ዓመታት የያዙትን ስልጣን ለመጨበጥ ነበር… ”
የዱሮው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ስለ ኒካራጓዊው አምባገነን መሪ አናስታሲዮ ሶሞዛ ሲናገሩ “ሶሞዛ የምናውቀው ወሮበላ ነው፣ ቢሆንም የእኛው ግርፍ ወሮበላ ነው”ብለው ነበር።የህወሓት ጉዳይም ይሄው መሆኑ ነው።
እንዲሁም አሜሪካ ህወሓት የወሮበላ ስብስብ መሆኑን ታውቃለች ግን አሜሪካ ኮትኩታ ያሳደገቻቸው ወሮበሎች ናቸው ።
አሜሪካ ህወሓትን ወደ ሥልጣን ለመመለስ ሦስት ምክንያት አላት-1) ምንም ጥያቄ የማይጠየቀውን ትእዛዛቱን የሚያከናውን የአሳላፊ (“የባንዳ” መንግሥት) አገዛዝ እንደገና ማቋቋም; 2 ኛ) ቀዳሚነትን የሚሰጥ እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጠብቅ አገርና ሕዝብ ወዳድ መንግሥት እንዳይነሳ መከላከል እና 3) ኢትዮጵያ በምንም መንገድ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የአሜሪካን አምባገነንነት ሊያዳክም የሚችል አካባቢያዊ ኃይል እንዳትሆን ማድረግ ነው ።
ሁለተኛው የአሜሪካ “ዘላቂ ጥቅም” በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን የቻይና መቃብር ማድረግ ነው ። አሜሪካ ከቻይና ጋር በኢትዮጵያ ምድር አተካሮ ለመፍጠር ጣቶችዋን እያከከች ነው ። ቻይና ለአሜሪካ ዓለም አቀፍ አምባገነንነት ጠንካራ ፈተና ታቀርባለች ። አሜሪካ አፍሪካን የ“ዓይነ ምድር መጣያ” ሀገሮች ስብስብ ብላ በመደምደሚያም አፍሪካ ለዘላለም ለማኞች አህጉር ሆና ትቆያለች የሚል መርሖ ሲከተሉ፣ ቻይና የተለየ ዕርምጃ ወስዳ ለአፍሪካውያን ከምዕራባዊ ሊበራል ካፒታሊዝም ጋር የሚፎካከር ብቻ ሳይሆን ቻይና እራሷን ያየችውን የድርብርብ እድገት ተስፋ የሚሰጥ የኢኮኖሚ ሞዴል ታቀርባለች ። ሂላሪ ክሊንተን እና ሌሎች የአሜሪካን ባለሥልጣናት ቻይናን ለአፍሪካውያን አማራጭ ማቅረብን እንደ ኒኦኮሎኒያዊ ኃይል አርገው ይሞግቱታል። የኒዎኮሎኒያዊ ክስ በቻይና ላይ እውነት ከሆነ ፣ ድስቱ ምጣዱን ጥቁር ነህ ብሎ እንደተናገረው አባባል ይሆናል።
አሜሪካ የቻይናን ሚና እና ተዓማኒነት በኢትዮጵያ ውስጥ ማጥፋት ከቻለች ይህ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ለአስርተ ዓመታት የዘለቁትን ጥረቶች፣ ግንኙነቶች እና ስኬቶች በአንድ ጊዜ ያወድመዋል የሚል እምነት የአሜሪካን ባለስልጣኖች አላቸው። እውነታዎች እንደሚያሳዩት ቻይና በኢትዮጵያ እና በተቀረው አፍሪካ ውስጥ መንገዶችን ፣ የባቡር መስመሮችን ፣ ድልድዮችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች ።
ቻይና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ አትገባም፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሮት አትጥስም ወይም እርዳታ በመቁረጥ ኢትዮጵያን ለመቅጣት አትሞክርም፣ ብድሮችን በመከልከል እና በማስፈራራት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ አትሞክርም። የኢትዮጵያን መንግሥት እንደ ሎሌ ታዛዥ መንግሥት አታዋክብም።
ደግሞም የኢትዮጵያን ታላቅ መከበሪያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በቦምብ አፈርሳለሁ እያለች አትዝትም። አሜሪካ ቻይናን ኢትዮጵያ ውስጥ በጡጫ ብትዘርር በአፍሪቃ ላይ አዲሱን ፓክስ አሜሪካና ወይም አሜሪካ በአፍሪቃ የምታዝበት የሰላም ዘመን ይመጣል ብለው ያምናሉ ባለስልጣኖቹ።
ግን ቻይና የድሮውን አባባል በስራ ላይ እያዋለች የምትሄድ ይመስላል ። “የቁርጥ ቀን ጓደኛ በእውነት ጓደኛ ነው ።”
ሦስተኛው የአሜሪካ “ዘላቂ ጥቅም” በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን በ 2021 ማደናቀፍና ማንቋሸሽ ነው። እ.ኤ.አ. በሰኔ 2021 በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ከተካሄደ — እንደማምነው ይካሄዳል – ይህ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ያላትን የሻጥር ስትራቴጂ ያበላሸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዶ የሚፈልገውን መንግሥት ከመረጠ የህወሓት የሬሳ ሣጥን ላይ የመጨረሻው ምስማር ይሆናል። በኢትዮጵያ የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በሁሉም በአምባገነንነት አገዛዝ ለሚኖሩ የአፍሪካ አገራት ከፍ ያለ ተምሳሌት ይሆናል።
ኢትዮጵያዊው ወጣት ትውልድ ትክክለኛው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መፍጠር ከቻለ የሁሉም የአፍሪካ አገራት ወጣቱ ትውልድ እንዲሁ መፍጠር ይቻሉ የሚል መንፈስን ይፈጥራል። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ የሰው ልጆች ምንጭ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ፀደይ እምብርት ልትሆን ትችላለች ።
አራተኛው የአሜሪካ “ቋሚ ጥቅም” በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የመጨረሻ “ንጉስ አንጋሽ ” መሆን ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እጅዋን ማስገባት ትፈልጋለች ። አሜሪካ የምትመርጠውና የምታፀድቀው መሪዎች ብቻ ወደ ስልጣን ላይ መውጣት እና መቆየት ይችላሉ ። ያኔ እ.ኤ.አ. በ 1991 ያ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ ሄርማን ኮሄን በለንደን ውስጥ የውሸት “ውይይት” እና “ድርድር” አድርጎ በመቀጽፈት ህወሓትን በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ አስቀመጠ። ይህን ለመድገም ነው ያሁኑ መፍጨርጨር።
በቀጣዮቹ 27 ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ዕርዳታ ለወያኔ ድጋፍ ሰጥታ በዓመታዊው የአሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርቶች በሰፊው እንደተዘገበው ጭፍጨፋዎቻቸው፣ በጅምላ እስር፣ ስቃይና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ዓይኔን ግንባር ያርገው ብላ ኖራለች።
ዛሬ አሜሪካ ያስተባበረችው የምዕራባዊያን የገደል ማሚቱ ሚድያዎች ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብዬዎች ፣ ቲንክ-ታንክ የጥናት ተቃውሞች እና ሌሎችም የሚጠነስሱት ሴራ የአሁኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በ “የጦር ወንጀሎች” እና በሰብአዊ መብቶች ለመወንጀል የሚያደርጉት ጥረት ነው።
አሜሪካ እርዳታ የምትሰጠውን በመቁረጥ ወይም በማቆም፣ የዓለም ባንክ ብድሮችን በማሳገድ፣ በአሜሪካ ኢንቨስትመንቶች ኢትዮጵያ ላይ ገደቦች በማድረግና የተባበሩት መንግሥታትንና የራሷን ማዕቀቦች ኢትዮጵያ ላይ በመጣል የኢትዮጵያ መንግሥት “እባክህ ጌታየ አሜሪካ የዛሬን ብቻ ማረን ” ብሎ እንዲለምን ነው ።
አምስተኛው የአሜሪካ “ዘላቂ ጥቅም” ኢትዮጵያ የአሜሪካንን አምባገነንነት የሚፈታተን ቀጠናዊ ኃይል ሆና እንዳትነሳ ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ ትልቅ የሆነውን ህዳሴ ግድብ እየገነባች ነው ። ያም ደግሞ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ባለቤት ሊያደርጋት ይችላል ።
በአሁኑ ጊዜ ሰባ ከመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል የለውም ። በአንፃሩ መቶ በመቶ የሚሆነው የግብፅ ህዝብ ተደራሽ ነው ። የኢትዮጵያ ብዙ የወጣት ብዛት ኢትዮጵያን ወደ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ሀይል እንድትመራ ሊያደርጋት ይችላል ። የትላቛ ኢትዮጵያ ታላቅነት በአፍሪቃ ለአሜሪካ ትልቅ ራስምታትዋ ነው።
ኮቪድ -19 እና ትራምፕ አሜሪካን የከሰረች (ፌልድ ስቴት) ሀገር መሆኗን አሳይተዋል። በዜጎቹ ላይ ለሚደርሰው ሥቃይ ደንታ ቢስ በሆነው የአሜሪካ አመራሮች ስብስብ ውጤታማ ስራ ስላልተሰራ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን በኮቪድ ሞተዋል ። እ.ኤ.አ. በ2019 34 ሚሊዮን አሜሪካውያን በድህነት ላይ ሲገኙ ከ 35 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በረሃብ ይገረፋሉ። ዛሬ ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በምግብ ባንኮች ላይ እንደ የኔ ቢጤ ዝክር ይለምናሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ “በምድር ላይ ከሁሉም በላይ ታላቅ አገር” ውስጥ ተስፋ የመቁረጥ ሕይወት ይኖራሉ ።
ሆኖም ብሊንኬን እና ግብረ አበሮቹ በዓለም መድረክ ላይ በእብሪት ተሞልተው ትዕዛዝ በጩኸት ይደነፋሉ። በረሃብ ለሚሞቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም የአዞ እንባም ያፈሳሉ። በጎ አድራጎት በቤት ውስጥ ቢጀመር አይሻልም? አሜሪካ ኢትዮጵያን ከማዳን በፊት እራስዋን ብታድን አይሻልም ?
ኢትዮጵያውያን የአሜሪካንን ጉልበተኝነት፣ ማስፈራራት፣ ስም ማጥፋት እና የውሸት መረጃ ማስፋፋትን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይችላሉ?
መጀመሪያ ፣ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ እንደ ሉዓላዊ ሀገር ከእነሱ ጋር ግንኙነት መቀጠል ግዴታ እንዳለባት አጥብቀው ማስረዳት አለባቸው ። ከዚህም ጋር ኢትዮጵያ ከ1787 (አሜሪካ ሳትፈጠር) በፊት በሺ ዓመታት የኖረች መሆንዋን ማስረገጥ ያስፈልጋል። አሜሪካ ኢትዮጵያንና መንግሥትዋን ማክበር ግዴታዋ እንደሆነና ኢትዮጵያም ሎሌና “የዓይነ ምድር መጣያ አገር” እንዳልሆነችና ፍርጥርጥ ባለ መንገድ ማስረገጥ አለባቸው። በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ክብራቸውን እንዳትነካ ቁርጥ አቛማቸውን ማስረገጥ አለባቸው።
ኢትዮጵያን እንደ ለማኝ ልያመናጭቛት እንደማይችሉም ማሳወቅ አለባቸው። ኢትዮጵያን ማክበር ካልፈለጉ ድጎማቸውን ወስደው ገሃነም ይግቡ ። ሦስተኛ ፣ ኢትዮጵያ -አሜሪካ ግንኙነቶች ወደ ፊት መሄድ የሚችሉት ዓለም አቀፍ ህግ በሚያዘው ድንጋጌ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 2 ያገር ውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት (ነን ኢንተርቨንሽን) መሰረት ብቻ ነው።
የዛሬ 125 ዓመት ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት ከጣሊያን ኃያላን የቅኝ ገዥ ጦር ጋር ሲፋለሙ ጎራዴ ፣ ቀስትና አንዳንድ የጦር ብረቶች ይዘው የህልውና ፈተና ውስጥ ገብተው ነበር። ግን ጣሊያኖች ከ 24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተደመሰሱ። ከዚያም ትልቅ ትምህርት ተምረዋል። የነጮች አነጋገር ስናሻሽለው “አሸናፊው በውጊያው ውስጥ ያለው የጅብ ግዙፍነት ሳይሆን የትንሽዋ ኣአበሳ ውስጥ ያለው አልበገሬነት ነው።”
በሌላ አገላለጽ አንድነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በጭራሽ ሊሸነፉ አይችሉም! ምክንያቱም አልበገሬ ኢትዮጵያውያንን ማንም የዓለም ሃይል ሊያሸንፋቸው አይችልም!
ዓለማየሁ (አል) ገብረ ማርያም ፣ ዶ/ር በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ሳን በርናርዲኖና የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር እና የሕግ ጠበቃ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013