ጌትነት ተስፋማርያም
የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መሠረት ያደረገ እና ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ምርምር እና ጥናት በማድረግ የሀገርን ልማት ማፋጠን ይቻላል። ኢትዮጵያ ለሳይንስ ትምህርቶች ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቷ ጋር ተያይዞ መንግሥት ለዘርፉ የሚያደርገውን ትኩረት እንዳሳደገ መሆኑን በተለያየ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል።
ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የሳይንስና ምርምር ዘርፎች በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሚከናውኗቸው ስራዎችን በተመለከተ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፤ ሳይንስና ኢትዮጵያ ያላቸው ዝምድና እስከምን ድረስ ነው?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ:- ሳይንስ ማለት በዘመናዊ መንገድ ዕውቀትን የመፈለግ ሂደት ማለት ነው። ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ሀገር እንደመሆኗ የሳይንስ ስራዎቿም ቀደምት ናቸው። ኢትዮጵያ እና ሳይንስ፤ ኢትዮጵያ እና እውቀትን ፍለጋ ትስስራቸው የሰው ዘር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተያያዘ ነው፤ አሁን ላይ እያደገ መጥቶ ወደ ደረስንበት ደረጃ አድርሶናል።
ምድረቀደምት እንደመሆናችን የጥንት አባቶቻችን አዕምሮ ውስጥ የሳይንስ አሰራሮች ነበሩ፤ እራሳቸውን ከአካባቢ ጋር አስተሳስሮ እና አሸንፎ ለመኖር ብዙ ሃሳቦች ውስጥ ገብተው መፍትሄ እያመጡ ኖረዋል። ለመኖር ደግሞ ቴክኖሎጂያዊ አስተሳሰቦችን እየተገበሩ ዘመናት አሳልፈዋል።
በዘመናዊው አስተሳሰብ ይህንን ተግባር ጥናትና ምርምር ነው የምንለው። ምክንያቱም ወረቀት ላይ አስፍረነው አሰራር ስርዓት ብለን ስለምንከተለው ማለት ነው። ይህ እውነታ በየጥንታዊ መዛግብቶች ውስጥ ተመላክቷል።
የድሮዎቹ መዛግብት በቤተክህነት ውስጥ እንዲሁም በመስጂዶች በአጠቃላይ በቤተ ዕምነቶች ውስጥ ያሉት ጽሁፎች እና በአርኪዎሎጂ ጥናት ተቆፍረው የሚወጡ ሰነዶች ሳይንስና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁርኝት እንደነበራቸው የሚያሳዩ ናቸው።
ኢትዮጵያ እና ሳይንስ የረጅም ጊዜ ትስስር ነበራቸው፤ አሁን ደግሞ በደረስንበት ደረጃ በባህላዊም ይሁን በሳይንሳዊ መንገድ ተግባራዊ የሚደረጉ በተለይም በህክምናው እና በስነፈለግ ዘርፍ ጥቅም የሚሰጡ የሳይንስ ውጤቶችም ከኢትዮጵያ በብዛት ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን:- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሳይንስና ምርምር ስርጸት ደረጃ አነስተኛ መሆኑን ጥናቶችም ጭምር አሳይተዋል። ይህ ከምን የመነጨ ነው? እንደሀገርስ መፍትሄ ለማምጣት ምን ያስፈልጋል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ:– ቀድሞ በጥንታዊነት ስንጠቀምባቸው የነበሩ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች በወቅቱ ዓለም ሁሉ የሚደመምበት ትልቅ ስልጣኔ ነበር። በሂደት እንደሃገር ያለፍንባቸው ታሪካዊ ሁነቶች የጀመርናቸውን ሳይንሳዊ ስራዎች ከፍ አድርገን እንዳንጠቀም የራሳቸውን ችግር ፈጥረዋል።
አሁን በደረስንበት ደረጃ ግን የቀድሞውን እውቅና ሰጥተን ከዓለም እኩል መራመድ መቻል አለብን። ባለ ነገር ላይ እየጨመሩ መሄድን ሀገራዊ ባህል ማድረግ ይገባናል። ሳይንስ ላይ ያሉንን መሰረት የያዙ ጉዳዮችን ይዘን የጎደሉትን ደግሞ እየጨመርን መሄድ ይጠበቅብናል።
ያላስተካከልናቸውን አሰራር ስርዓቶች እያስተካከልን መሄድ አለብን። ለዚህ ደግሞ የእኛ ዘመን ምሁራን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፤ ምሁራኑ ይህን ኃላፊነት እንዲወጡ እና በቁጭት እንዲሰሩ መንግሥት የሚመራውን ዘርፍ ሀገራዊ አሰራር ስርዓቶች ለማስተካከል ሞክሯል።
አዲስ ዘመን:- የሳይንስ ስርጸቱ አነስተኛ መሆን ከተመራማሪዎች ቁጥር ማነስ ጋር አይያያዝም?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ:- የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ስራዎች አጥኚ እና ተመራማሪዎችን ይፈልጋል። እንደሃገር ደግሞ የአጥኚዎችና የተመራማሪዎች ቁጥር ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር እንኳን ብናነፃጽረው ዝቅተኛ ነው።
እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፤ ባህልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) መረጃ መሰረት ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ጥቂት ተመራማሪዎች ካሏቸው ሀገራት ተርታ ተመድባለች። እንደመረጃው ከሆነ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ 87 ተመራማሪ ብቻ ነው ያለን። ኬንያን ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ 313 ተመራማሪዎች አሏት። ደቡብ አፍሪካን ብንወስድ ደግሞ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ 900 ተመራማሪ አላት፤ ቁጥሩ ከኢትዮጵያ 10 እጥፍ በላይ ነው።
የኬንያን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጥር ብናነፃጽር በእጥፍ ኢትዮጵያ ትበልጣለች፤ በተመራማሪ ግን ኬንያ በአራት እጥፍ ነው ኢትዮጵያን የምትበልጠው። ይህ ትልቅ ስራ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። የሳይንስና ጥናት ልማት ስራዎችን በብቃት እና በስፋት ለማከናወን በርካታ ተመራማሪዎችን እንደሃገር ማፍራት ይጠበቅብናል። ለዚህም ስራ በሀገር ውስጥ እና በውጭ በርካታ ተመራማሪዎችን ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል። በየዓመቱ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እና ተመራማሪ መሠረታዊ እውቀት እና ልምድ እንዲያገኝ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን:- ባለሙያዎችን ከማፍራት ጎን ለጎን ምቹ ያልሆነውን የምርምርና ጥናት መሠረተ ልማት ከማሳደግ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ:- በርካታ ተመራማሪዎችን ካፈራን በኋላ ደግሞ ለተመራማሪው ምቹ የሆነ አካባቢን መፍጠር ያስፈልጋል። ምቹ ስራ አካባቢ ውስጥ አንዱ ጥናትና ምርምርን የሚደግፍ አሰራር ስርዓት ነው። አሰራሩ ውስጥ ፖሊሲ፣ መመሪያ እንዲሁም የድጋፍ ገንዘብን ያጠቃልላል። ምርምር ከፍተኛ ገንዘብ ይፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥም ለዘርፉ የሚሆን የሃብት ቋት ያስፈልጋል።
በርካታ ሀገራት ውስጥ የምርምር እና የሳይንስ ፈንድ ተቋቁሞ ወደስራ ገብቷል። ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው የመንገድ ፈንድ ተቋም ሁሉ የምርምር እና የሳይንስ ፈንድ ተቋም በመመስረት በቋት የሚሰበሰብ በጀትን ለጥናትና ምርምር መጠቀም ያስፈልጋል። ጥናትና ምርምር የሚደረግባቸው የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት እና ተመራማሪዎችን በማስታወቂያ በመጥራት መልምሎ ፈንድ እያቀረቡ መስራት ቢቻል ሀገራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ምርምሮች በየመስኩ መስራት ይቻላል።
ምቹ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር ደግሞ የምርምር መሠረተ ልማቶችን ማደራጀት ያስፈልጋል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ምስረታ በኢትዮጵያ 70 ዓመታት አስቆጥሯል። ሀገራችን ውስጥ እንደሚታወቀው አንድ ብለን የጀመርነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነበር። በ70 ዓመት ጊዜ ውስጥ አሁን ላይ የመንግሥት ብቻ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 52 ደርሰዋል፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዛሬ 30 እና 40 ዓመት ላይ ምንም አልነበሩንም፤ አሁን 278 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉን።
ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርና ምርምር ዘርፍ ብንመለከት የዛሬ 55 ዓመት ነው ተቋሙ የተመሰረተው። አሁን ላይ ግን በዘርፉ ብዙ ማዕከላት በኢትዮጵያ ተከፍተዋል፤ በሁሉም ዞን አስተዳደሮች ስር የምርምር ማዕከላት ተፈጥረው ችግር ፈቺ ስራዎችን በሰብል፣ በእንስሳት አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች እየተሰሩ ይገኛል።
በጤናውና በማህበራዊ ሳይንስም ብዙ አይሁኑ እንጂ ተቋማት አሉን። ይሁንና ተቋማቶቹ ጠንካራ የምርምር መሰረተ ልማት የላቸውም። አላቸው ተብለው የሚታሰቡትም ቢሆኑ ለአብነት ዩኒቨርሲቲዎች ለብቻው የጥናትና ምርምር ላቦራቶሪ እና ወርክሾፕ በአብዛኛው የላቸውም።
ምሁራኑ ምርምርና ጥናት የሚሰሩት ለቅድመ ምረቃ ተብለው በተደራጁ ወርክሾፖች ውስጥ ነው። ይህ ከአገራዊ አቅም ጋር የሚሄድ ነው ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፤ ግን ከዚያ ከፍ ብለን መሄድ መቻል አለብን። አሁን ላይ በርካታ የሁለተኛ እና የዶክትሬት ዲግሪ መስኮችን ከፍተን እየሰራን ስለሆነ የድህረ ምረቃ የምርምር መርሐ ግብሮች ልዩ ላብራቶሪ ያስፈልጋቸዋል።
ልዩ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ እውቅና ያላቸው እና ፍተሻቸው የተረጋገጡ ላብራቶሪዎች እንዲሁም መስክ ላይ ምርምር የሚሰራባቸው ወርክሾፖችም ጭምር መገንባት ይጠይቃል። በግብዓት የተሟሉ ዘመናዊ ላብራቶሪ እና ወርክሾፖች መኖራቸው ለምርምር ስራ ማደግ ወሳኝነት አላቸው።
በሌላ በኩል እንደሀገር የምርምር ግብዓቶች እንደተፈለገው አይገኙም፤ በአብዛኛው ከውጭ ሀገር ገበያ ነው የሚመጡት። ይህ ደግሞ በአገራዊ የግዥ ስርዓቱ ጋር በተገናኘም ሆነ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ ግብዓቶቹ በሚፈለገው ደረጃ እየቀረቡ አይደለም። በዚህ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎቻችን ቅሬታ ያቀርባሉ።
ስለዚህ ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል። እንደአጠቃላይ ብቁ ሰው፣ የአሰራር ስርዓት ፤ የምርምር ድጋፍ እና መሰረተ ልማት እንዲሁም ግብዓት በማሟላት እንደሀገር ያለውን የምርምርና ጥናት ደረጃ ከፍ ማድረግ ይቻላል። በዚህ ውስጥ የጥናት ውጤቶቹ ለሚፈለገው አካል ተደራሽ የሚሆኑበትንም መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ያለውን አነስተኛ የምርምር በጀት ለማሳደግ በመንግሥትም ሆነ በሚኒስቴሩ ደረጃ ምን ይጠበቃል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ ሀገራት ከዓመታዊ አጠቃላይ ጥቅል ምርት (GDP) ውስጥ ለምርምርና ጥናት የምንመድበው ባጀት ቢያንስ አንድ በመቶውን መሆን አለበት የሚል ስምምነት አድርገዋል። ወደአፍሪካ ስንመጣ አንድ በመቶ የደረሱ ሀገራት ጥቂት ናቸው።
ኢትዮጵያ ደግሞ ከጂዲፒዋ 0 ነጥብ 27 በመቶውን ብቻ ነው ለምርምርና ጥናት ስራዎች የምታውለው። ይህ በጣም አነስተኛ በመሆኑ መንግሥት ወደፊት ማሳደግ ይኖርበታል።ሀገራዊ ኢኮኖሚው ሲያድግ ባጀቱም እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል።
ከዚያ በፊት ግን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር ተቋማት የሚመድበው ባጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ወይ የሚለውንም ማየት ተገቢ ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችንም ከኦዲተሮች እና ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር ይህን ክትትል እያደረገ ቁጥጥር ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች የተቀናጁ አይደለም፤ አንዱ ጋር የተሰራውን የመድገም ችግር አለ፤ አሊያም የአንዱን ወስዶ ለማሳደግ የሚያስችል ቅንጅት አልዳበረም፤ ይህን ለመቅረፍ ምን ታስቧል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ ምርምር ሀብት ይፈልጋል። ያሉን ጥቂት ተመራማሪዎች የሚሰሯቸው ስራዎች ሃብት ይወስዳሉ። አንዱ የሰራውን ደግሞ ሌላው ከፍተኛ ተቋም ላይ የሚደግም ከሆነ የሃብት ብክነትም ያስከትላል፤ ድምሩም ኪሳራ ነው የሚሆነው። በመሆኑም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የቅንጅት ስራ ነው የሚያስፈልገው።
በየተቋሙ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች በተቋማት ድረ ገጽ ላይ መረጃ ሆነው ሊቀመጡ ይገባል። የተጠናቀቁት ብቻ ሳይሆን በስራ ላይ የሚገኙ ተብሎ በግልጽ መቀመጥ አለበት። እንደአጠቃላይ ግን በሀገርአቀፍ ደረጃ የምርምር ቋት ያስፈልጋል። መረጃዎቹን ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን እንዴት ጥቅም ላይ ይውላሉ የሚለውንም በቀላል መንገድ የሚያሳይ እና ለትግበራውም መሪ የሆነ አጠቃቀም ያስፈልጋል።
አንድ ሰው ኢንተርኔት ላይ ገብቶ ስለባህር ዛፍ የተጠኑ ስራዎችን ሲፈልግ ከዚያ ቋት በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶችን ከማግኘት ባለፈ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እችላለሁ የሚለውንም የሚመልስ የመረጃ ቋት ያስፈልገናል። ይህ ከሆነ የተሰራውን ስራ መልሶ ላለመድገም፤ ሃብትንም በአግባቡ ለመጠቀም ፤ በምርምር ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን ለመመልከት እድል ይሰጣል።
አንድ ዩኒቨርሲቲ በጥምረት ከሌላው ጋር በህብረት ምርምሮችን ማካሄድ እንዲችሉ እና ከኢንዱስትሪዎች ጋርም በትስስር እንዲሰሩ የመረጃ ቋት እና ትግበራ መምሪያ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ በርካታ ጊዜያት የተጠኑ ስራዎች እና ምርምሮች ተግባራዊ አይደረጉም፤ ሚኒስቴሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስር የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ተግባራዊ እንዲደረጉ ለማስቻል የተጠያቂነት አሰራር ከመተግባር አኳያ ምን ታስቧል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ አስገዳጅ ከማድረጋችን በፊት ተግባራዊ የሚሆኑ ምርምሮችን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። ሁለት አይነት ምርምሮች አሉ። አንደኛው መሰረታዊ ምርምሮች ናቸው። እነዚህ ዕውቀትን ለማግኘት ታስበው የሚሰሩ ናቸው።
ሀገራችን ላይ ብዙ ጊዜ ዓለም ላይ የማይገኙ ዕውቀቶች በመኖራቸው ሊፈተሹ፣ ሊደራጁ እና ሊተነተኑ ይገባል። ለአብነት ማህበራዊ ሳይንስ ላይ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ። እያንዳንዱ የተለየ እውቀት አላቸው። ልዩ እውቀቶቻቸው በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንተው ለሌላውም ተደራሽ መሆን አለባቸው። መሰረታዊ ምርምሮች አላማቸው ዕውቀቶቹን ተደራሽ ማድረግ ነው፤ እነዚህ ይደገፋሉ እየተሰሩ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ናቸው።
በሁለተኛነት ግን ለኢትዮጵያ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ተብሎ በፖሊሲም የተመላከተው ችግር ፈቺ ምርምር ነው። ችግር ፈቺው ምርምር ተግባራዊነትን ይጠይቃል። በሁሉም መስኮች ዙሪያ ችግር ፈቺ ምርምሮች ይሰራሉ። ወደትግበራ የሚተላለፉት ደግሞ ጥናታቸው ተጠናቆ ተተንትነው እና ምክረሃሳብ ቀርቦላቸው የተደራሹን አሊያም የተጠቃሚውን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።
ዩኒቨርሲቲዎቻችን በተልዕኮ ጥናትና ምርምር አከናውነው፤ የመማር ማስተማር ስራ አከናውነው እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሰጥተው ነው ተልዕኳቸውን የሚወጡት። እነዚህ ያስጠኗቸው ችግር ፈቺ ምርምሮች ውጤት እንዲያመጡ እንደድልድይ ሆኖ መተግበር ያለበት ጉዳይ አለ። ይሄውም በአጥኚው በአቅራቦት እና በተቀባይ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ነው። ይህ ድልድይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ አይደለም።
በርካታ ጠቃሚ እና ችግር ፈቺ ምርምሮች አሁንም ይሰራሉ፤ ለታለመ አላማቸው እንዲውሉ የሚያስችለው ኢንዳስትሪው ሊሆን ይችላል፤ ማህበረሰቡን ለልማት የሚያንቀሳቅሱ አካላት ሊሆኑ ይችላል፤ ሴክተር መስሪያቤቶች አሊያም ማህበራት ሊሆኑ ይችላል።
እነዚህ አካላትን ከዩኒቨርሲቲዎች የሚፈልቁ ምርምሮችን ተቀብሎ ስራ ላይ የማዋል ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን ማጠናከር ቀጣይ ስራችን ነው። ብዙ ጥናቶችና ምርምሮች ተሰርተው ተደራሽ ካልሆኑ ውጤት አልባ ናቸው። ህብረተሰቡን ታሳቢ ካደረገ በመገናኛ ብዙሃን አሊያም በአካል መቅረብ አለባቸው።
ምርምሮቹ ኢንዱስትሪዎችን ታሳቢ ካደረገ ደግሞ ኢንዱስትሪ ባለቤቶቹ በወቅቱ ጥናቱን ማግኘት አለባቸው። ዘመኑን የሚመጥን የማሰራጫ ስርዓት በመጠቀም የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ እየተከናወኑ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም የምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር የማህበረሰብ አገልግሎት እና የትስስር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደስራ ገብቷል። በህዝብ ገንዘብ የሚሰራ ስራ ውጤታማ ሊሆን ይገባል። ዩኒቨርሲቲዎች ዘንድ ያለውን የምርምር ስርዓት ተጠያቂነት አሰራር በመተግበር ዩኒቨርሲቲዎቻችን ምርምሮች እንዴት ተደራሽ መሆን ይችላሉ የሚለውን የእቅዳቸው አንድ አካል አድርገው እንዲሰሩ በመመሪያው ተመላክቷል።
ይህን ተመራማሪዎችም ሆነ ዩኒቨርሲቲዎች በአግባቡ እንዲገነዘቡት ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየሰጠን ይገኛል። በሚቀጥሉት ጊዜያት የተሻለ የምርምር ስራዎች ተደራሽነት ተጠያቂነት ይሰፍናል ብለን እንጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፦ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ስራዎችን ሳይንሳዊ አድርጎ ከመምራት አኳያ ያለውን ክፍተት ለመሸፈን ምን አይነት ስራ ያስፈልጋል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ መንግሥትም ይህንን ጉዳይ ታሳቢ አድርጎ ነው የዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ያቋቋመው። ተቋሙ ሲጀራጅ በጥልቅ እውቀት ላይ ተመስርቶ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ የሳይንስና ምርምር ስራዎች የሚከናወኑት በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ውስጥ ነው በአብዛኛው። ምሁራንም ወጣት ተመራማሪዎችም በአብዛኛው ያሉት እነዚሁ ተቋማት ውስጥ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም ከጥግ እስከጥግ የሚመጡ ተማሪዎች ላይ የሚተገበረው የሳይንሳዊ አስተሳሰብ ስራ ሁሉም ቤተሰብ ዘንድ ይደርሳል። ልጆች ወላጆቻቸው ጋር ሲደውሉም ሆነ ለእረፍት ሲሄዱ እንኳን በአቅማቸው ያንን እውቀት ያደርሳሉ።
በሌላ በኩል በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ውስጥ ያሉት ባሉት ተመራማሪዎች እና መምህራን አማካኝነት ሳይንሳዊ አሰራሮች ወደህብረተሰቡ ይተላለፋሉ። ይህን የሚመራ ሀገራዊ የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሚኒስቴራችን አዘጋጅቷል። ከ10 ዓመት ሀገራዊ እቅድ ላይ በማስተሳሰር ምን አይነት ሳይንሳዊ አሰራሮች ሊተገበሩ ይገባል የሚል ስምንት አቅጣጫዎች ይዟል።
ከዚህ ውስጥ አንዱ የሰው ሃብት ልማት ነው፤ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶችን አቅም የመገንባት ስራ ሌላኛው አቅጣጫ ነው። ሃብት የማፈላለግ እና ከውጭ ሀገራት ግንኙነት የመፍጠር እና የአስተዳደር ስርዓትም ተካቷል። ይህ ግብ ተዘጋጅቶለት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ወደየራሳቸው እቅድ ውስጥ አካተው እንዲተገብሩት መግባባት ላይ ተደርሷል፤ አሁን ላይ ወደትግበራ በመግባት ላይ ነው።
ፖሊሲና ስትራቴጂ አለን፤ ፕሮግራሞች እና እቅዶች አሉን። እነዚህ ሁሉ በአግባቡ እንዲተገበሩ በመከታተል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሳይንስ መሰረት ይዞ የሀገርን ልማት እንዲደግፍ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ሀገራዊ የምርምር ስራዎችን ከውጭ ሀገራት ተቋማት ጋር አስተሳስሮ በመጓዝ ረገድ ያለውን አነስተኛ እርምጃ ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ ኢትዮጵያ የምርምርን ዓለም አቀፋዊነት ትደግፋለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ እውቀት ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን፤ ዓለም ላይ ያለው ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት በፖሊሲም ደረጃ ተቀምጧል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂም ሆነ በሳይንስ ምርምር ያከናወነችው ስራ ጅምር በመሆኑ ሌሎች አገራት ውስጥ ፈልቀው ፤ ስራ ላይ ወጥተው ተፈትነው ያለፉ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት አምጥቶ ለልማት ማወል ይገባናል። እነዚህን እውቀቶች ለማምጣት ተቋማዊ ትስስር ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል የምርምር መሰረተ ልማቶችን እና የገንዘብ ምንጭ ለማግኘት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነትን ማጠናከር ጠቃሚ ነው። ለዚህም የምርምር ተቋማት ከውጭ ሀገራት የምርምር ተቋማት፤ ዩኒቨርሲቲዎችም ከዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተሳስረው መጠቀም አለባቸው፤ ለዚህም በየጊዜው ለውጦች እየታዩ ነው።
ዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነት በመፍጠር የሰው ሃብት ልማት ላይ እየሰሩ ነው፤ ተመራማሪዎች ውጭ ሀገራት በመሄድ ልምድ አግኝተው ይመለሳሉ፤ የውጭዎቹም መጥተው በጋራ የምርምር ስራ አከናውነው ይሄዳሉ።
ይሁንና የሚፈለገውን ያክል ትስስር ተፈጥሯል ማለት አይቻልም። በኢትዮጵያ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የውጭ ምሁራን ስራዎችን ሰርተው ወደየሀገራቸው የመመለስ ልምድ አላቸው። አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ሰፊ ስራ መከናወን አለበት። አሁንም በኢትዮጵያ ትስስር ፈጥረው ሰፊ የምርምር ስራ ማከናወን የሚፈልጉ ተቋማት በርካታ ናቸው።
የምንቸገረው ግን ጠንካራ አሰራር ስርዓት ባለመፈጠሩ ለግንኙነቱ ማነቆ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ወደሌላ ሀገራት አልፈውም ምርምራቸውን የሚያከናውኑ አሉ። ለዚህ መፍትሄ የሚሆን የአሰራር ስርዓቱን ቀላል የሚያደርግ እና የውጭ ተመራማሪዎች ከኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ይበልጥ የሚያመቻች የአሰራር ስርዓት እየዘረጋን ነው።
ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋሞቻችንም ይህንን አውቀው ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም ይህንን የሚደግፍ ሀገራዊ የሳይንስ ካውንስል አቋቁመናል። በሰጥቶ መቀበል መርህ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ሃብት በማይጎዳ መልኩ እንዲሁም የምርምር ስነምግባርን በተከተለ መልኩ ሀገራዊ የምርምር ስራዎችን ከውጭ ሀገራት ተቋማት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ የሚያስችለውን ስርዓት አደራጅተን እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፦ በሳይንስ ዘርፍ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ስራዎች ውጤት እንዲያመጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ምን አይነት ስራ አከናወናችሁ?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ በየዘርፉ ተስፋ ሰጪ ምርምሮች ይከናወናሉ፤ ትልቁ ችግር እነሱን አደራጅቶ ለትግበራ ማብቃቱ ላይ ነው። ለአብነት ልዩ ምርት የሚሰጡ የሰብልና የአዝርዕት ዝርያዎች በየጊዜው ይፈልቃሉ።
ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ አለኮ ወይም ሞሪንጋ ተክል ላይ የተሰሩ ተስፋ ሰጪ ምርምርች አሉ። በጤናውም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ ምርምሮች አሉ። እነዚህን አሰባስቦ እና አደራጅቶ ማዘጋጀቱ ላይ ነው ውስንነት ያለው።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስራቸው የሚፈልቁ አያሌ አመርቂ የሳይንስና ምርምር ስራዎችን አደራጅተው ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ በየጊዜው የምክክር እና የመመሪያ ማሳወቂያ መድረኮች እየተካሄዱ ይገኛል።
ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቴክኖሎጂ፤ ሳይንስና ጥናት ስራዎቻቸው አስፈላጊው ፍተሻ ተደርጎባቸው በቀጥታ ወደሀገራዊ ልማት እንዲገቡ የሚያስችል ሙያዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን እየተሰጠ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ሳይንስና ምርምር መፍትሄ ያመጣል ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ እንደአገር ምን አይነት ስራ ይጠበቃል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ በቅርቡ በወጣው መረጃ በዓለም በርካታ አማኝ ካላቸው ሃገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ አንዷ ኢትዮጵያ ነች። አንድ ሃያል ፈጣሪ አለን ብሎ የሚያምን 99 በመቶ ህዝብ ስላለ፤ አማኝ ነን። ስለዚህ ሳይንስም መፍትሄ ያመጣል ብሎ የሚያምን ህብረተሰብም እንዲሁ እንዲፈጠር ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መድረኮች ያስፈልጋሉ።
ሳይንስ ችግር ፈቺ ነው፤ ቴክኖሎጂ ሃብት አመንጪ ነው የሚለውን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፤ እስከዛሬ በግብርናውም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች በገጠሩ ክፍል ጨምሮ የተከናወኑ ሰርቶ ማሳያዎች የእራሳቸው ለውጥ አምጥተዋል። ከዚህ በበለጠ ደግሞ ህዝብ እንዲረዳው በመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ጭምር አመርቂ ስራ መስራት ይጠበቅብናል።
ድሮ በደርግ ዘመን ህብረተሰቡ የወቅቱን ፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲረዳ በግዳጅ ጋዜጣ እንዲያነብ ይደረግ ነበር። አሁንም ሳይንስ የሚባለው የእውቀት ፍለጋ ስርዓት ለዕለት ተዕለት ስራዎች መሻሻል ጠቃሚ ነው ብሎ እንዲያምን በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በተገኙት አማራጮች ሁሉ ሊተላለፍ ይገባል። ሳይንሳዊ አመለካከት እና አሰራር ባህል እንዲሆን የሁሉም አካላት ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013