አቶ ይከፈለው ወልደመስቀል የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር
አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች የመጣች ከተማ ናት። ዘመናዊ ሕንጻዎች፤ ሆቴሎች፤ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች በርካታ ፋብሪካዎች አቅፋ ይዛለች። እነዚህ ተቋማት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አደጋን በመከላከልና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅበታል። የዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን የአደጋ ቅድመ መከላከል፤ በመዲናዋ የሚደርሱ አደጋዎችን የመቆጣጠርና የመከላከል የዝግጁነት ደረጃ፤ አደጋ ከደረሰ በኋላ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በምን መልኩ አደጋን የመከላከል ዝግጁነት ምን እንደሚመስል የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽን ኮሚሽነር ይከፈለው ወልደመስቀል ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ምንባብ!
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ አደጋን ከመቀነስና ከመከላከል አኳያ ምን ታቅዶ ምን ተሰራ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- በኮሚሽናችን የሚከናወነው የአደጋ የመከላከል ሥራ ሶስት ደረጃዎች ያሉት ነው። የመጀመሪያው አደጋ ከመድረሱ በፊት ቀድሞ የአደጋ ስጋትን በማጥናት የማቅለያ ርምጃ እንዲወሰድ ለማህበረሰቡ የማስጠንቀቂያ መልዕክት እንዲደርስ ማድረግ ነው። ሁለተኛው አደጋ ከደረሰ በኋላ ምላሽ የመስጠት ሥራ ነው። በሶስተኛ ደግሞ በአደጋ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ነው።
እኔ የምመራው የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ የአደጋ መከላከል ሥራ ብቻ የሚከናወንበት ነው። አደጋ ከመድረሱ በፊት ስጋቶችን በማጥናት አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ርምጃዎች በተቋማት እንዲወሰዱ፤ በማህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲደረግ በእቅድ የማስተማር ሥራ ሰርተናል። በዚህ መሠረትም ከነበሩን ዋና ዋና እቅዶች አንዱና ዋነኛው ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት ነው። የግንዛቤ ሥራው በሕትመት ሚዲያው፤ በበራሪ ወረቀቶች፤ ብሮሸሮች፤ እንዲሁም በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሁሉን የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ዕለት ከዕለት በምንሰጠው መረጃና የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ይሰራል።
አደጋ ሲያጋጥም ከአደጋው ህብረተሰቡ ሊማር በሚችልበት ደረጃ ዘገባዎችን በመሥራት ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ እና ጥቃቄ እንዲያደርግ ይደረጋል። ቤት ለቤት የማስተማር ሥራ እንሰራለን። በስልክ “ስቲከር” በመለጠፍ የተቋሙ አድራሻ እንዲኖራቸው እና አደጋን በመካከል ሂደት እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል። ከዚያ ውጭ በመድረክ ሌሎች ተቋማት በሚፈጥሯቸው የተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ በመገኘት የማስተማር ሥራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- በኮሚሽኑ የሚሰራው የግንዛቤ ሥራ ማህበረሰቡ ስለ አደጋ ያለው ግንዛቤን ማሳደግ ተችሏል ብለው ያስባሉ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- የግንዛቤ ደረጃው አሁንም ገና ብዙ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። ማህበረሰቡ ጋር ያለው የግንዛቤ ሁኔታ በተሰራው ልክ ለውጥ መጥቷል፤ በሚፈለገው ልክ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥንቃቄ እየተወሰደ ነው ለማለት አይቻልም።
የግንዛቤ ሥራዎችን ከማከናወን ባለፈ ለማንኛውም ሕንጻ ላለው ግለሰብ የሙያ ምክርና የቴክኒክ ድጋፍ እናደርጋለን። የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጥም ሆነ ለመኖሪያም ቢሆን ሕንጻው ማሟላት የሚገባው የደህንነት መስፈርቶች እና መሟላት ስለሚገባቸው መስፈርቶች የሙያ ምክርና የቴክኒክ ድጋፍ እናደርጋለን። ከዚህ አለፍ ሲልም፣ የፍተሻ ሥራ ይሰራል። የደህንነት መስፈርት ስለማሟላታቸው ምርመራ በማድረግ ግብረ መልስ ይሰጣቸዋል። ብቁ ሆነው የሚገኙ ተቋማት ሲኖሩ የምስክር ወረቀት ይሰጣሉ።
የምስክር ወረቀት ከሚሰጣቸው ተቋማት መካከል ሆቴሎች፤ ጋራዦች፤ ኢንዱስትሪዎች፤ ነዳጅ ማደያዎች፤ ፋብሪካዎች እና የተለያዩ ተቋማት ሲሆኑ ብቁ ሆነው ከተገኙ የደህንነት መስፈርትን ማሟላታቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል። የደህንነት መስፈርት የማያሟሉ ሕንጻዎች የምስክር ወረቀት መውሰድ አይችሉም። በከተማችን የደህንነት መስፈርት የሚያሟሉ ሕንጻዎች ትንሽ በመሆናቸው ተቋማችን ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ የሚያስችል አሠራር ዘርግታችኋል? በማያሟሉት ላይ የእርምት ርምጃ ትወስዳላችሁ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- ችግሩን ለማስተካከል የከተማ አስተዳደሩ ከሰኔ ሁለት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደንብ አውጥቷል። ደንቡን ማስፈጸም የሚያስችል መመሪያ በተቋሙ ተዘጋጅቶ ለፍትህ ሚኒስቴር ተልኳል። ጸድቆና ምዝገባ አልፎ ሲመጣ ከማስተማር ባለፈ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ ይጀመራል። ምናልባትም ይህ ተግባራዊ ሲደረግ ሁኔታው ሊቀየር ይችላል። በሌላ በኩልም ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በጋራ በመሆን በቅርበት እየሰራን ነው።
ከዚህ በፊት ቱሪዝም ሚኒስቴር ለሆቴሎች ሰጥቶት የነበረው የኮከብ ደረጃ በመጪው መስከረም ላይ ይከልሳል። ነባሩን በመሰረዝ በአዲስ መልክ ሰርተፊኬት ይሰጣል። የእሳት አደጋ የደህንነት መስፈርትን ያላሟላ ሆቴል በሙሉ የኮከብ ደረጃ እንዳያገኝ በማድረግ ቱሪዝም ሚኒስቴር እየተባበረ ነው። ስለሆነም ይህ አፈጻጸም ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል።
የት አካባቢ ምን ዓይነት አደጋ ሊከሰት ይችላል? በሚል እሳቤ የአደጋ ጥናት እንሰራን። አሁን የምንገኝበት ወቅት ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት የሚችልባቸው ቦታዎች በእሳት አደጋ ኮሚሽን ተለይቷል፤ የመሬት መንሸራተት ሊከሰትባቸው የሚችሉ እና ሰፋ ያለ የትራፊክ አደጋም ጉዳት ይደርስባቸዋል የሚባሉ አካባቢዎች እንዲሁ ተለይተዋል።
በአጠቃላይ በአራቱ የአደጋ ዓይነቶች 505 የሚሆኑ ቦታዎች በጥናት የተለዩ ሲሆን ከነዚህ ቦታዎች ውስጥ በጎርፍ አደገኛ ናቸው ተብለው ከተለዩት 135 በቦታዎች ላይ በቶሎው የመፍትሔ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል። ችግሩ ከመድረሱ በፊት ቅድመ መከላከል እንዲኖር ኮሚሽኑ ለስምንት ተቋማትና ለ11ዱ ክፍለ ከተማ አስተዳደሮች በማሰራጨት መነሳት የሚገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከቦታው እንዲያስነሱ ተደርጓል።
ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩት አካባቢዎች በአጋጣሚ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ዘመናዊ ለማድረግ በሚከናወነው የኮሪደር ልማት መቀነስ ተችሏል። ከዚህ በፊት የፍሳሽ መሠረተ ልማት አልነበረም። የኤሌክትሪክ መስመሮችም በብዙ ቦታዎች በአየር ላይ የተዘረጉና የተጠላለፉ እና አደጋን የሚያስከትሉ ነበሩ። ወንዝ አካባቢዎች በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ይኖሩ የነበር ሲሆን አሁን ላይ ችግሮቹን በኮሪደር ልማት ሥራው መቅረፍ ተችሏል።
ቀበናን ጨምሮ ከቤተ መንግሥት እስከ እንጦጦ እየተደረገ ባለው የማልማት ሥራ የአደጋ ስጋት ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው። በወንዙ ግራና ቀኝ ሰፍረው የነበሩ፤ ተንጠልጥለው የነበሩ ቤቶች በሙሉ ተነስተው ነዋሪዎቹ በምትኩ የተሻለ የመኖሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ከአደጋ ቦታ በመራቃቸው ችግሩ ተወግዷል።
መንገድ በጣም ጠባብ የነበረባቸው የመኪና አደጋ በተደጋጋሚ ይከሰትባቸው በነበሩ ቦታዎች ላይም መንገድ እየሰፋ የእግረኛ መንገድና ዋና መንገድ እየተለየ በመሄዱ አደጋ እየቀነሰ ነው። በአየር ተጠላለፍው የሚሄዱት የቴሌ፤ የመብራት መሠረተ ልማት በኮሪደር ልማቱ ከመሬት በታች እየተቀበሩ እየሄዱ በመሆኑ መሠረታዊ ለውጥ እየመጣ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተቋማትና የድርጅቶች አደጋን የመቀነስ ልምድ ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሚያስተዳድሩት ሕንጻ ላይ አደጋ ይከሰታል ብለው ቀድመው የመዘጋጀት ችግሮች አሉ። ብዙ ሕንጻዎች የአደጋ መከላከያ መስፈርት የላቸውም። የደህንነት መስፈርት አያሟሉም።
አዲስ አበባ እያደገች ነው፤ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እየተገነቡ ስለሆነ ይህን የሚመጥን የአደጋ ደህንነት መስፈርት ማሟላት እየቻሉ አይደለም። የኮንስትራክሽን ሥራ ሲሰራ ሊደረግ የሚገባቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አሉ። የሕንጻ የአደጋ የመከላከል ሕግ አለ። በዚህ መሠረት በዲዛይን ውስጥ አካትተው የግንባታ ፈቃድ ሲወስዱ የደህንነት መስፈርት ማሟላት ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ከግንባታ ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት ለመሥራት ሙከራ እየተደረገ ነው።
ብዙ ሕንጻዎች ኮሚሽኑ ለፍተሻ ሲሄድ ያዘጋጃሉ። ነገር ግን እውነታ ላይ የተመሠረተ ሥራ አይሰሩም። ደህንነት ለራስ ነው፤ የራሳቸው ተቋም እና ሠራተኛ ለመጠበቅ የሚሰራ በየስድስት ወሩ በባለሙያ ታይቶ የሚሞላ እሳት ማጥፊያ ሊኖራቸው ይገባል። እሳት ሲነሳ መልዕክት በቶሎ እንዲደርስ የሚያደርግ ‹ዲቴክተር›› መሳሪያ ሊኖራቸው ያስፈልጋል። አንድ ሕንጻ አደጋ ቢያጋጥመው እሳት አደጋ እስከሚደርስ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲከላከል የሚያደርግ ዝግጁነት ሊኖር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማችን ምን ያህል ሕንጻዎች የደህንነት መስፈርት አላቸው ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- ባለፉት ዓመታት በተሰራው የቁጥጥር ሥራ ከ20 ሺ በላይ ሕንጻዎችን ፈትሸናል። በዚህ ዓመት ለ200 ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት ታቅዶ ለ43 ድርጅቶች ብቻ ሰርተፊኬት ተሰጥቷል። በተቋማችን ከታዩ ከ20 ሺህ ሕንጻዎች የእሳት መከላከያ መስፈርቱን ያሟሉና እውቅና የተሰጣቸው 43ቱ ብቻ ናቸው ። ከእዚህ ውጭ ያሉ ድርጅቶች የደህንነት መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው ሰርተፊኬት አላገኙም። አንዳንዶች መስፈርቱን ቢያሟሉም ሰርተፊኬት ያልወሰዱ አሉ። ለምሳሌ በቅርብ እየተገነቡ ካሉ ተቋማት መካከል ዓድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የጠበቀ ግንባታ ነው። የደህንነት መስፈርት ማሟላቱን የምስክር ወረቀት ሊወስድ ይገባል የሚል አቋም አለን። ኃይሌ ግራንድ ሆቴል ደረጃው የጠበቀ ነው። ነገር ግን እስካሁን የደህንነት ስርተፊኬት አልወሰደም። መስፈርቱን አለማሟላት የሚስተዋልባቸው እንደ ማደያዎች፤ ፋብሪካዎች፤ የገበያ ማዕከላት፤ ሞሎች፤ መኖሪያ ሕንጻዎች፤ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ናቸው።
በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወር ውስጥ በተደረገው ግምገማ ከስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት በአደጋ ወድሟል። ይህ ሀብት ለዚች ሀገር ትልቅ ሀብት ነው። ባለን ውስን ሀብት ከአደጋ ራሳችን ካልጠበቅን የውድመት መጠኑ በጣም ከፍተኛ ነው። ከዚህ በላይ በገንዘብ የማይተመን የሰው ሕይወት ይጠፋል። በኮንስትራክሽን ሂደት ላይ ከሕንጻ ላይ ወድቀው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች አሉ። መርካቶ አካባቢ በመደርመስ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች አሉ፡ በማሽነሪ ሊቆፈር የሚገባው በሰው በማስቆፈር ተንዶ ሕይወታቸውን ያጡ አሉ። በጎርፍ ጭምር በዚህ ዓመት ሰባት የሚሆኑ ሰዎች ተወስደዋል። በተለያየ መንገድ ሕይወታቸው እያጡ ያሉት ወጣቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በገንዘብ የሚተመን ንብረት ወድሟል፤ የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። ነገር ግን ከውድመትና ከጥፋት የታደጋችሁት ሀብት እና የሰው ሕይወት የለም?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- የምናድነው የሰው ሕይወትና ንብረት ከሚጠፋው በብዙ እጥፍ ይበልጣል። በዘጠኝ ወር ብቻ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከውድመት መታደግ ተችሏል። ከሚጠፋው የሚድነው ይበልጣል። የተቋሙ ሠራተኞች ብዙ ያልተመቻቹ ነገሮች እያሉ ንብረትና ሕይወትን አድነዋል።
የከተማችን የትራፊክ ፍሰት ሁኔታ አሁን የሚሰራው መንገድ ያለው ነገር ተስፋ ሰጭ ሁኔታ ቢኖርም በጣም አስቸጋሪ ነው። እሳት አደጋ ተከስቶ በቦታው ለመድረስ መንገድ ይዘጋል። አደጋው በተከሰተበት ቦታ ከደረስን በኋላም ኤሌክትሪክ ካልተቋረጠ ርምጃ መውሰድ አይቻልም። ውሃ ሲረጭ ኤሌክትሪክ ካለ አደጋ ሠራተኞቹ ጉዳት ውስጥ ይወድቃሉ።
የከተማው እድገት እና ከሕዝብ ብዛት ከተቋሙ አቅም አንጻር ሥራችንን ፈታኝ እያደረገው ነው። በከተማዋ የሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅም በሥራችን ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ እያሳደረበን ነው። በሀገራችን ለእሳት አደጋ መከላከያ የተሽከርካሪዎች ብቻ ጥቅም የሚሰጥ መስመር ስለሌለ የሚፈጠረውን አደጋ በአጭር ሰዓት ደርሶ ለመከላከል አያስችልም። በሌሎች ሀገራት የእሳት አደጋ ተሽከርካሪ የሚጓዘው በራሱ መስመር ነው። በመሆኑም በሚፈለገው ፍጥነት አደጋው በተፈጠረበት ቦታ ደርሶ መከላከል ያስችለዋል።
በሌሎች ሀገራት የእሳት አደጋን ለመከላከል ድሮኖችን ይጠቀማሉ። ድሮኖች ካሉ አደጋ በደረሰበት ቦታ በሰከንዶች ውስጥ በመድረስ እሳቱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ማዋል ይቻላል። እኛም ከድሮን ጋር ተያይዞ ለከተማ አስተዳደሩን ጥያቄ አቅርበናል።
ከድሮን በተጨማሪ ተቋማችን ለማዘመን እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ ለመሥራት የተለያዩ ርምጃዎችን ጀምረናል። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አደጋዎች በደረሱ ወቅት ጥሪዎች በተገቢው መንገድ እኛ ጋር እንዲደርስ ማድረግ የሚያስችል ነው። ይህን ቴክኖሎጂ ከመጠቀማችን በፊት ደዋዮች ራሱ በቀጥታ ሊያገኙን የሚችሉበት እድል ጠባብ ነበር።
ሌላው ተቋማችን የተጠቀመው ቴክኖሎጂ ደግሞ ሀሰተኛ ጥሪዎችን መለየት የሚያስችል ነው። ይህን ቴክኖሎጂ መተግበር ከመጀመራችን በፊት በአንድ ቀን ውስጥ እስከ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ሀሰተኛ ጥሪዎች እናስተናግድ ነበር። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በሰራነው ሥራ ሀሰተኛ ጥሪዎችን መለየት የምንችልበት በመፈጠሩ ሀሰተኛ ጥሪዎችን መቀነስ ተችሏል።
ሌላው ተቋማችን በዘንድሮው ዓመት ለመተግበር ከጫፍ ላይ የደረሰው ቴክኖሎጂ ተሽከርካሪዎች ላይ በሚገጠም ካሜራ አማካኝነት የአደጋ ቦታዎችን እና አጠቃላይ ሁኔታዎችን ቢሮ ላይ ሆነን መከታታል የሚያስችል ነው። ለምሳሌ የመንገድ አማራጭ፣ አደጋው የት ጋር ነው? አደጋው ስፋቱ ምን ያህል ነው? ስንት መኪና ያስፈልገዋል? በየት በኩል መኪና መላክ እንችላለን? ትራፊክ መጨናነቅ የሌለው በየት በኩል ነው? የሚለውን እና መሰል ጥያቄዎችን መፍታት የሚያስችል ነው። አሁን ላይ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ የምናደርግበት ሥርዓት እየዘረጋን ስለሆነ የምናሻሽለው ነገር ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ቴክኖሎጂው መቼ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- ሁለተኛው የቴክኖሎጂው ፌዝ በዚህ በጀት ዓመት ሁለት ወራቶች ውስጥ ተጠናቆ በመስከረም ወር አካባቢ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል። መኪና ላይ የምንገጥመውን ካሜራ በተመለከተ በኢኖቬሽን ቢሮ አማካኝነት በውጭ ድርጅት እየተሰራ ነው። ሂሊኮፍተር እና ድሮን የምንታጠቅበትን ጊዜ መቁረጥ አንችልም። ነገር ግን ሂሊኮፍተር እና ድሮን ለመግዛት ከተማ አስተዳደሩ ቃል ገብቶልናል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ቢሮ ከስትራቴጂክ እቅድ አንጸር ሂሊኮፍተር እና ድሮን መቼ ለመግዛት እቅድ ይዛችኋል?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡– እኛ የአምስት ዓመት የሪፎርም እቅድ አለን። በሪፎርም እቅዳችን ውስጥ ሂሊኮፍተር እና ድሮን በተመለከተ ታሳቢ አድርገናል። ይህን መሠረት አድርገን ባለፈው ዓመት ጀምሮ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርበናል። ክብርት ከንቲባዋም ቃል ገብተዋል። አሁን ላይ ያለው የኮሪደር ልማት ከፍተኛ የበጀት አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የመጀመሪያው ትኩረት እዚያ ላይ ነው። በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ግን ይሟላል ብለን እናስባለን። እሱን ስናገኝ አስተማማኝ የሆነ የመከላከል ሥራ እንሰራለን። ነገር ግን ምንም ነገር ቢኖር ደግሞ ከአደጋ በፊት የሚሰራውን ሥራ አይተካም። ሰው አደጋ ሊያስከትሉ በሚችሉ ነገሮች ላይ እስካልተጠነቀቀ ድረስ ሁሌም እየሄድን እሳት ማጥፋት ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛው የአደጋ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- ባለፈው ዓመት ፖሊስም ባደረገው የምርመራ ሥራ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት አደጋዎች የወንጀል ምልክት ያላቸው ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ ሰዎች ኢንሹራንስ ለማግኘት ተብለው እሳት የሚያስነሳባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። 80 እና 90 በመቶ የሚሆነው ግን ከጥንቃቄ ጉድለት የሚያመጣቸው አደጋዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አደጋን ለመቀነስ ጥናቶች እንደሚደረጉ ይነገራል። ካለፉት ዓመታት አንጻር ያለው ሁኔታ ሲታይ አሁን ላይ አደጋዎች ጨመሩ ወይስ ቀነሱ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- አደጋ የመቀነስ ሁኔታው ብዙ አይደለም። ይህ ማለት ግን የአደጋ ቅነሳ ሥራ ስላልተሰራ ነው ማለት አይደለም። የሀገር እድገት፣ የሕዝብ ብዛት፣ የአየር ንብረት ለውጡ የሚፈጥራቸው ሁኔታዎች አሉ። የባለፈው ዓመት የአየር ሁኔታና የዘንድሮው ዓመት የአየር ሁኔታ ከአስር ዓመት በፊት ከነበረው የአየር ሁኔታ የተለየ ነው። አሁን ላይ ያለው የሰዎች የአኗኗር ሁኔታ እንዲሁ የተለየ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚመጣው ሕዝብ ብዛት እየጨመረ ነው። ይህ ሕዝብ ደግሞ የሚሰፍርበት ቦታ ይፈልጋል። በሕጋዊም ሆነ ሕገ ወጥ መንገድ ወንዝ እና ገደላማ ቦታዎች አካባቢ ጭምር ይሰፍራል። ይህ ደግሞ ለአደጋ ይጋለጣል። በእነዚህ እና መሰል ምክንያቶች በከተማችን አደጋ የመቀነስ ነገር አይታይበትም። ነገር ግን አደጋን የመቀነስ ሥራ ባንሰራ ኖሮ ሊደርስ ይችላል ብለን የምንገምተው እና የሚደርሰው በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ አለው። ስለሆነም የመከላከል ሥራችን ውጤታማ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሌሎች ሀገራት የአደጋ ተሽከርካሪዎች የራሳቸው የሆነ መስመር አላቸው። አሁን እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት የአደጋ ተሽከርካሪዎች የራሳቸው የሆነ መስመር እንዲኖራቸው ለማስቻል ከከተማ አስተዳደሩ እና ከመሠረት ልማት ሚኒስቴር ጋር ተናባችሁ ከመሥራት አንጻር ያለው ነገር ምን ይመስላል?
አቶ ይከፈለው፡- የዘለቄታ መፍትሔ የሚሆነው አስቻይ አሠራሮችን መዘርጋት ነው። በሪፎርማችን ውስጥ ብዙ ጉዳዮች አንስተናል። ከዚህ ውስጥ በትራፊክ ማኔጅመንት ለማስተናገድ እድል እንዲያገኙ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች እንደ ፖሊስ እና መከላከያ የተለየ ታርጋ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየሰራን ነው። ለምሳሌ አምቡላንስ የሚጠቀሙ ተቋማት የራሳቸው የሆነ መለያ ድምጽ ይኖራቸዋል። በተመሳሳይ ለእኛ ተሽከርካሪዎችም የራሱ መለያ ድምጽ ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን አሁን ላይ ለእሳት አደጋ ተብሎ የተለየ መንገድ የለም። በሂደት ግን ታሳቢ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ 20 ሺህ ሕንጻዎች የእሳት መከላከያ መስፈርቱን እንዲያሟሉ መዝግባችሁ ነበር። ነገር ግን መስፈርቱን ያሟሉ እና እውቅና የተሰጣቸው ለ43 ብቻ ነው። መስፈርቱን ባላሟሉ እና እውቅና ባልያዙ ሕንጻች ላይ ምን ርምጃዎችን ወሰዳችሁ? ያንን ማስፈጸም የሚያችል የሕግ ማዕቀፍ አላችሁ?
አቶ ይከፈለው፡- የሕንጻዎችን የእሳት የመቆጣጠር አቅም የምንለካባት ሕግ አለን። ይህም ሰኔ 2014 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ ያወጣው ነው። ሕጉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ የሆኑ ተቋማትን ያስገድዳል። የአደጋ ደህንነት መስፈርት ያላሟላ ተቋም ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ ተቋሙ አገልግሎት እንዳይሰጥ እስከ ማድረግ ድረስ ርምጃ ይወስዳል።
ነገር ግን ሕጉ ማስፈጸሚያ መመሪያ አልነበረውም። አሁን ላይ ለሕጉ ማስፈጸሚያ የሚሆነው መመሪያ እንዲጸድቅ ለፍትህ ሚኒስቴር ተልኳል። መመሪያው ተመዝግቦ እና ተቀባይነት አግኝቶ ሲመጣ ተግባራዊ ማድረግ እንጀምራለን። ከችግር መውጫ መንገድ ይሆናልም ብለን እንጠብቃለን። ሕጉን መስከረም ላይ ወደ ትግበራ እናስገባለን ብለን እንጠብቃለን።
መመሪያው ባይወጣም ሕጉን ተንተርሰን የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። ሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የጸደቀው ሕግ የደህንነት መስፈርት በማያሟሉ ሕንጻዎች እና ሆቴሎች ላይ መጀመሪያ እስከ መቶ ሺህ ብር ድረስ እንደሚቀጣ እና ከስህተቱ የማይመለስ ከሆነ ደግሞ የንግድ ፍቃዱ ይሰረዝና በመጨረሻም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እስከ መዘጋት እንደሚደርስ ይደነግጋል።
ይሄንን ሕግ ለፋብሪካዎች፤ ለሆቴሎች እና ለነዳጅ ማደያዎች ሰብስበን ላለፉት ሁለት ዓመታት እያስተማርን ቆይተናል። መስከረም ላይ ወደ ትግበራ እንገባለን። በሕንጻ ፈቃዱ በኩል ዲዛይኑ ውስጥ ማካተት አለበት። ሕንጻ ሳይጠናቀቅ ወደ ትግበራ በማስገባት ከሕንጻ ቁጥጥር እና ፈቃድ ባለስልጣን ጋር ሕጋችንን ለማጣጣምና በጋራ ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከአዲስ አበባ ውጭ በሆኑ ከተሞች ላይ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ አኳያ ያሏችሁ ሚና ምን ይመስላል?
አቶ ይከፈለው፡- የእኛ ተልዕኮ አዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ከተሞች የሚፈጠሩ አደጋዎችን መከላከል ነው። ከአደጋ ደህንነት አንጻር እስከ ዞን ድረስ ሰፋ ያደርገዋል። ከዚያ ውጭ ግን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጥያቄ ሲቀርብልን ከአዲስ አበባ ውጭም የምንሰራበት አግባብ አለ። ለምሳሌ ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር አብረን ስለምንሰራ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ሆቴሎች እውቅና ስልጠና የሰጠናቸው ሆቴሎች አሉ።
የሰብዓዊ ጥያቄ ስለሆነ የትም ቦታ ቢሆን እኛ ስንጠየቅ አገልግሎቱን እንሰጣለን። በዚህ ዓመት አደጋ ያጋጠማቸው ክልሎች ላይ በዋናተኞቻችን አስክሬን ያወጣበት ሁኔታ አለ። ኦሮሚያ ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ አደጋ ሲከሰት በቦታው ተገኝተን እንከላከላለን።
አዲስ ዘመን፡- ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ እና አደጋን ለመከላከል ቁርጠኛ አመራር እንዲኖር ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በምን መልኩ ተናባችሁ እየሰራችሁ ትገኛላችሁ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- እስካሁን ቁርጥ ያለ ርምጃ መውሰድ ያልቻልነው የሕግ ማዕቀፉ ክፍተት ስለነበረ ነው። በሕንጻ ሕጉ ጅምር ሕንጻዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ይፈቅዳል። የእኛ ተቋም ደግሞ በጅምር ሕንጻዎች ችግር ሊፈጠር ስለሚችል አገልግሎት እንዳይሰጡ አቋም አለን። ይህ የአሠራር ልዩነት ለአደጋዎች መፈጠር በር እየከፈተ ይገኛል።
በግንባታ ወቅት ለሚደረግ ጥንቃቄ ላይ ሕጉ ክፍተት የለበትም። ርምጃ መውሰድ ያለበት ተቋም ርምጃ ያለመውሰድ ክፍተት ነው። ይህንን ተጠያቂ የማድረግ ያስፈልጋል። ርምጃ በማይወስዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ተጠያቂ የሚደረግብት አግባብ በእኛ ተቋም ሕግ ወጥቶለታል። ማስፈጸሚያ መመሪያው በእጃችን ሲገባ፤ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አንድ ሕንጻ በግንባታ ላይ እያለ ተገቢውን ቁጥጥር ሳያደርጉ ቀርተው አደጋ ቢያጋጥም እና የሰው ሕይወት ቢያልፍ የመጀመሪያ ተጠያቂ የምናደርገው የመንግሥት ተቋም የሆነውን የግንባታ ፈቃድ እና ተቆጣጣሪውን ነው።
ክትትል ሲያደርጉ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መወጣጫ ላይ ሲያሰራ የሚገኝ ሕንጻ ላይ ያለ ምህረት ርምጃ መውሰድ አለባቸው። ይህንን ካላደረጉ እነሱ ተጠያቂ ይሆናሉ። በማሽነሪ የሚቆፈረውን ጉድጓድ በሰው ጉልበት የሚስቆፍር ኮንትራክተር ሲያገኙ ርምጃ መውሰድ አለባቸው። ይህንን ካላደረጉ እኛ የምንጠይቀው እነሱን ነው።
ሕጉ ወደ ሥራ ሲገባ ቆራጥ ርምጃ ለመውሰድ ያስችለናል። እኛ እስከ ዛሬ ከማስተማር እና ከመምከር ባለፈ ሕግ ለማስከበር የሚስችል ስልጣን አልነበረንም። ሕጉ የወጣው ሰኔ 2014 ነው። ሕጉን በደንብ አስተምሮ በመመሪያ ተደግፎ ወደ ሥራ መግባት ውጤታማ ያደርጋል። የአደጋን ጉዳይ ከኛ በላይ የሚገነዘብ የለም፤ እኛ በተግባር አይተናል። ስለሆነም ሕግ በማያከብሩ እና በማያስከብሩ አካላት ላይ እኛ ጠብቀን ርምጃ መውሰድ አለብን ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- የተቋማችሁ ሠራተኞች በሥራ ላይ እያሉ አደጋዎች ቢደርስባቸው ካሳ ከመክፈልስ አኳያ አሰራራችሁ ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡– በእኛ ተቋም የሚሠሩ ሠራተኞች እንደ ማንኛውም ሲቪል ሰርቫንት መታየት የለባቸውም። ምክንያቱም ሕይወታቸውን ሰጥተው በመስጠት ሕይወት ያድናሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተማ አስተዳደሩ እያየው ያለው ነገር አለ። በሥራ ላይ እያሉ ጉዳት ቢደርስባቸው እና በጉዳት ምክንያት ከሥራ ቢወጡ መቋቋም የሚያስችል የተሻለ የደሞዝ እና የተለያዩ የጥቅማ ጥቅም የክፍያ ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል።
አሁን ላይ የአካል ብቃት የሚሰሩበት የስፖርት ጅምናዚየም፣ የተሻለ ካፍቴሪያ፣ ተገቢው ደምዝ እና ጥቅማ ጥቅም፣ ተገቢ የአደጋ ጊዜ አልባሳት እንዲኖራቸው ለማድረግ የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ። ከተማ አስተዳደሩም እያገዘን ነው። በዚያ መንገድ ሪፎርም ሠራውን ለማሳካት እየሰራን ነው።
በርግጥ ሠራተኞቻችን የመድህን ዋስትና አላቸው። ነገር ግን አካል ቢጎድላቸው ፤ ሕይወታችውን ቢያጡ የካሳ ክፍያው ምን መሆን አለበት የሚለውን ግን አሁንም ገና ብዙ ማሰብ ይጠይቃል። ከኢንሹራንስ ካምፓኒዎችም ጋር የተለየ ስምምነት ይጠይቃል። ደሞዛቸውን እና ጥቅማ ጥቅማቸውን ከማሻሻል ባለፈ የመድህን ዋስትናቸውን ማሰብ ይጠይቃል።
ከዚህ በፊት ተቋሙ የሚመራው በሲቪል ሰርቪስ ሕግ ነበር። አሁን ራሱን የቻለ “የፓራ ሚሊታሪ” ደንብ ወጥቶለት እድገታቸውንም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው። በቂ አይደለም በሌላው ዓለም አደጋን የሚከላከሉ ሰዎች በማህበራዊ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል። የአደጋ ሠራተኛ ነው ከተባለ ባቡር ላይ ተነስቶ ጭምር ሰው ያስቀምጠዋል። ያለ ወረፋ እና ሰልፍ አውሮፕላን እንዲሳፈር ይደረጋል። ይህን ክብር ወደሀገራችን ለማምጣት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለቀይ መስቀል ወይም ተመሳሳይ ተቋማት ከመንግሥት ሠራተኞች እና ዜጎች የሚቆረጥ ገንዘብ አለ። ከዚህ አግባብ የድርጅቱን ገቢ ለማሳደግ ምን እየሰራችሁ ነው ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- ይህን ለማድረግ ሃሳቡ ስላለ በሪፎርም እቅዳችን ውስጥም አለ። ለዚህ ደግሞ ሕግ ማዘጋጀት ይኖርብናል። ይህ ዓይነት አሠራር ሌላው ዓለም ላይ አለ። አሁን ላይ ድጋፍ እንኳን የጠየቅናቸው ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና ባንኮች ብዙም የሚያጠግብ ምላሸ አልሰጡንም። መሆን የነበረበት ግን በቋሚነት ለእሳት አደጋ ካሚሽኑ መቁረጥ ነበረባቸው ይህን ለማድረግ ሕግ ያስፈልጋል ብለን ሥራ እየጀመርን ነው። በቀጣይ ዓመት በርግጠኝነት እሱን እናጸድቃለን ብለን እናስባለን። በሕግ የሚመራ ድጋፍ እና ገቢ ይኖረናል። ያ ሲሆን ልዩ ክፍያ እና ልዩ ጥቅማ ጥቅም ማሟላት ያስችለናል።
አዲስ ዘመን፡- በሰው ኃይል እና በመሳሪያ ከተማዋን የሚመጥን የተደራጀ ሥራዎችን ለማከናወን የያዛችሁት እቅድ ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- እቅድ አለን። በአምስት ዓመት ውስጥ ምን ያህል ተጨማሪ የአደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ እና አምቡላንስ ለመጨመር፤ አንድ ሄሊኮፕተር እና አንድ ድሮን ለመግዛት በስትራቴጂክ እቅዳችን ላይ ይዘናል። ይህም ከከተማው ገቢ ጋር እየተጣጣመ እና እየታየ የሚሰራ ይሆናል። ቅርንጫፍ በመስፋትም ረገድ አሁን ላይ 26 ቅርንጫፎች ያስፈልጉናል። ባለፈው ዓመት ሪፎርሙን ስንጀምር ዘጠኝ ቅርንጫፎች የነበሩ ሲሆን አሁን 11 ደርሰናል። በሚቀጥሉት ዓመታት ነገሮችን እያየን ቅርንጫፎችን የምንከፍት ሆኗል።
አንድ ቅርንጫፍ ሲጨመር ታሳቢ የሚደረጉ በርካታ ነገሮች አሉ። የሰው ኃይል፣ ተሽከርካሪ፣ የሥራ ቦታ እና ሌሎች ነገሮች ያስፈልጋሉ። እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት አቅማችንን እያየን ስታንዳርድ ማሟላት አለብን። አደጋ መከላከል ጋር ተያይዞ ዓለም ላይ ስታንዳርድ አለው። ለምን ያህል ሕዝብ እና ለምን ያህል የቆዳ ስፋት ስንት “ፋየር ፋይተር”? ፣ ስንት የእሳት አደጋ ተሽከርካሪ? ስንት አምቡላስ መኖር እንዳለበት ዓለም አቀፍ ስታንደርድ አለ። እኛም በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አስጠንተን ስታንዳርዱን ለማሟላት እቅድ ይዘን እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማሰልጠኛዎቻችሁን በማዘመን፤ የውጭውን ዓለም ተሞክሮ ለሰልጣኞቻችሁ ከመስጠት አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው ?
ኮሚሽነር ይከፈለው፡– የውጭው ዓለም የደረሰበትን የአደጋ መከላከል ሥርዓት በሀገራችን እንዲኖር እና ሰልጣኞቻችንም የተሻለ እውቅት እንዲኖራቸው ለማስቻል የውጭ ሰዎች እዚህ ድረስ መጥተው ስልጠና እየሰጡ ነው። እድሉ ሲገኝም ሠራተኞቻችንን ወደ ውጭ ሀገር ልከን እናስተምራለን። በርግጥ አሁን አሁን እንደዚህ ዓይነቱ አሠራር እየቀነሰ ነው። በቀደመው ጊዜ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰልጣኞች በብዛት ወደ ውጭ ሄደው እውቀት የሚያገኙበት አግባብ ነበር። አሁን ላይ አንድ አመራር እና 10 ባለሙያዎች ለስልጠና ኮሪያ ሀገር ናቸው። ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም። ተጨማሪ ሥራን ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
ኮሚሽነር ይከፈለው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም