አቶ ኻሊድ ነስረዲን-የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የከተማዋን የመሬት ሀብት አጠቃቀም፣ ልማት እና ጥበቃን በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በከተማዋ ከመሬት ልማትና አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚወጡ ፖሊሲዎችን የመተግበር ኃላፊነትም አለበት።
ቢሮው በሕግ ተቆጥረው የተሰጡትን ኃላፊነቶች እንዴት እየተገበረ ነው? ከአሰራር ጋር ተያይዞ የገጠሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ምን ዓይነት የሕግ ማሻሻያ አድርጓል? በሚሉት እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከከተማዋ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኸሊድ ነስረዲን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በተጨባጭ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ኻሊድ፡- በ2015 አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሞ ነበር። በዚህም 16 የሚሆኑ ተቋማት ላይ ጥልቅ የሆነ ሪፎርም እንዲያደርጉ ተወሰነ። ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የመሬት ልማት አስተዳደር አንዱ ነው። ይሄን የከተማ አስተዳደር አቅጣጫ ወደ እቅድ በመቀየር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አጠቃላይ ለህብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ተቋማዊ ሪፎርም አድርጓል። ተቋማዊ ሪፎርሙ አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። እነዚህ አምስት ዋና የትኩረት መስኮች በበጀት ዓመቱ እንደ ግብ የተወሰዱ ናቸው። የአደረጃጀት ጉዳዮችም የሪፎርሙ አካል ናቸው።
የመሬት አስተዳደር ቢሮ እየሰጠ ያለው አገልግሎት የትኞቹ ማሻሻያ ይፈልጋሉ? በምን ዓይነት አደረጃጀት ውስጥ ብንሰራ ይበልጥ ውጤታማ ያደርገናል? ብለን ማሻሻያዎችን አድርገናል።
በክፍለ ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብለን ያደራጀናቸው በሪፎርሙ ውስጥ ተካተዋል። በቅርንጫፎቹ ምን ይሰራ? ምን ላይ ትኩረት ያድርጉ? ሥራዎች የት ተጀምረው የት ይለቁ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ በአደረጃጀት ውስጥ የማስተካከል ሥራ ተሰርቷል።
ሠራተኞችን የማስተዳደሩ ሁኔታ እንዴት ይሁን? ሰብዕናቸው ምን ዓይነት መሆን አለበት? ምን ዓይነት መብቶችና ግዴታዎች ሊኖራቸው ይገባል? በመደበኛው የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ብንመራ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? እንደ ገቢዎች ያለ አሰራር ብንከተል ምን ይፈጠራል? የሚለውን መርምረን ሥራ ላይ አውለናል። የቴክኒክ እና የሥነ ምግባር ፈተና ፈትነን አደረጃጀቱን አስተካክለናል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ጥሩ ውጤት እየታየ ነው። በርግጥ የመሬት አስተዳደር በየጊዜው ሪፎርም መደረግ አለበት።
ሁለተኛ ማሻሻያ ያደረግነው ከአሰራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነው። አሰራር ስንል ሕጎቻችን ላይ ማሻሻያ አድርገናል። ሁሉም ማሻሻያዎች፤ የህብረተሰቡን ጥቅምና ፍላጎት፤ ከተማዋ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
አገልግሎት ሲሰጥባቸው የነበሩ ሕጎች እና መመሪያዎች ከሁኔታው ጋር አብረው መሄድ የማይችሉ በመሆናቸው ማሻሻያዎች ተደርጎባቸዋል። በከተማ አስተዳደሩ ከ12 በላይ የተለያዩ መመሪያዎች ነበሩ። መመሪያዎቹ የተበታተኑ በመሆናቸው ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊረዳቸው የማይችሉም ነበሩ። በሪፎርሙ ያንን የተበታተነ ሕግ የመሰብሰብ እና እንደገና የማደራጀት ሥራ ተሰርቷል። ለብልሹ አሰራር በር የከፈቱን፣ ጊዜ ያለፈባቸውንና ጉድለት የነበረባቸውን የማስተካከል ሥራ ተሰርቷል።
በሪፎርሙ ላይ ባለሙያዎች ተዋያይተውበታል፤ ባለ ድርሻ አካላት አይተውታል፤ የሕግ ባለሞያዎችም ሃሳብ ሰጥተውበታል። በዚህም እንደ ተቋም ሁለት ደንቦች ተተችተው እና ውይይት ተደርጎባቸው የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔም አጽድቋቸው ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከሕግ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን አርመናል። እነዚህ የሕግ ማሻሻያዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት አንዳንዶቹ ሰርኩላሮች መመሪያን የተኩ ነበሩ። በከተማ አስተዳደሩ ሕግ እና መመሪያን ሊተኩ የደረሱ ከ140 በላይ የተበታተኑ ሰርኩላሮች ነበሩ። በሪፎርሙ ይህን የማስተካከል ሥራ ተሰርቷል።
በነገራችን ላይ ሰርኩላሮቹ መመሪያውን ለማብራራት በሚል የተቀመጡ ነበሩ። ሰርኩላር እየበዛ ከሄደ መመሪያን ወደ መተካት ይገባል። እነዚህ ላይ የማስተካከያ ሥራ ተሰርቷል። የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንብም በዚሁ ውስጥ የተካተተ ነው። በዚህም ጥሩና ግልጽ የሆነ ቢያንስ ማን ምን ይሰራል? ምን ሲያሟላ አገልግሎት ያገኛል? የሚሉትን አሻሽለን ወደ ሥራ አስገብተናል።
ሌሎች ቢሮው ማሻሻያ ያደረገባቸው ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ናቸው። ከለውጡ ወዲህ ይሄ የመሬት አስተዳደር ተቋም እንዲቀየር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረ። የመሬት ተቋም ብዙ ተዋንያንን ይይዛል።
የከተማ አስተዳደሩ ላለፉት ሁለት ዓመታት ይሄንን ተቋም ለመቀየር ከፍተኛ ሥራዎችን አከናውኗል። ከተከናወኑ አብይ ተግባራት መካከል የቢሮውን ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ ነው። ብዙ ሰው መሬት አስተዳደር ላይ ቴክኖሎጂ ቅንጦት ነው ይላል። ነገር ግን በኛም ተቋምም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው በሚል ብዙ ድጋፍ ተደርጎልናል።
ከ10 ዓመታት በፊት ተጀምረው ግን ማንም ሰው ሊተገበራቸው ፍቃደኛ ያልሆነባቸው ተግባራት ነበሩ። አሁን የተጀመረው የቴክኖሎጂ ሥራ በጣም ተስፋ ሰጭ ነው። ከኢንሳ ማረጋገጫ እና እውቅና ተሰጥቶታል።
በዚህ ቴክኖሎጂ ከበፊት ጀምሮ የነበሩ ከሰባት መቶ ሃያ ሺህ በላይ የሆኑ ከመሬት ጋር የተገናኙ መረጃዎች ‹‹ስካን›› ተደርገው ወደ ‹‹ሲስተም›› እንዲገቡ ተደርጓል። ይህ የተሰራው በራሳችን ባለሙያዎች ነው። ወደ ሲስተም የማስገባት ሥራውን ለሌላ አካል ሰጥተን ቢሆን ኖሮ ከአምስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ሊያስወጣን ይችል ነበር።
ዛሬ ላይ ቢሮው የሚሰጠው አገልግሎት ዲጂታል መታወቂያ እና ዐሻራን መሰረት ያደረገ ነው። ምናልባት ከዚህ በፊት የተፈፀሙ ሕገወጥ ሰነዶች ካሉ ሲስተሙ በራሱ ያስወግዳቸዋል። ይህም ሕጋዊ ዶክመንቶችን መሠረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት እንድንችል አድርጎናል። በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎት፤ ከባንኮች እና ከ33 በላይ ከሚሆኑ የፋይናንስ ሴክተሮች ጋር ለማስተሳሰር ሞክረናል። ይህም ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ መሬት ቢያገኙ እንኳ አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ ማድረግ አስችሏል።
አሁን ከመሬት ጋር የተገናኙ ሰነዶች ልክ ናቸው? አይደሉም? ለማለት የጀርባ ማህተም የሚባል ነገር አናይም። ሰነዶቹ (መረጃዎቹ) ‹‹ባር ኮድ›› አላቸው። ከውል እና ማስረጃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ ከሲስተም ጋር አስተሳስረናል።
ለሽያጭ ወይም ለሌላ ጉዳይ የሚመጡ የመሬት ሰነዶች ከባንክ ብድር የተወሰደባቸው መሆን አለመሆናቸውን ባንኮችን መጠየቅ ሳያስፈልግ እዚሁ ማየት እንችላለን። ስለዚህ በአንድ ቦታ ላይ ብድር ወስዶ ሌላ ቦታ ላይ በተሳሳተ ካርታ ሌላ አገልግሎት ለማግኘት ጥረት የሚያደርግ ካለ አይሳካለትም። ሰዎች እጃቸው ላይ ፎርጂድ ካርታ ሊይዙ ይችሉ ይሆናል፤ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት በሕጋዊው ብቻ ነው።
አሁን ቢሮው ከሚሰጣቸቸው አገልግሎቶች 27 ለሚሆኑት በኦንላይን አገልግሎት እንሰጣለን። ቀሪ 40 የሚሆኑትን አገልገሎቶች ደግሞ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅታችንን አጠናቀናል። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ከአሁን በኋላ በመሬት ዙሪያ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆነ ሁኔታ በኦንላይን ለመስጠት አቅደናል።
ሌላው በቢሮው የተሰራው ሪፎርም ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ወረዳ በሚገኙ ተቋማት ለሚሰሩ ሠራተኞችም ሆነ ለተገልጋይ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥረው ነው። ከዚህ አኳያ በተለያዩ ደረጃዎች በሚገኙ የቢሮው ተቋማት ላይ በርካታ ማስተካከያዎች ተሰርተዋል።
ሌሎች በቢሮው ከተከናወኑ አብይ ተግባራት መካከል ከጨረታ ሰነድ ጋር የሚገናኙት ጉዳዮች ይጠቀሳሉ። ቀደም ሲል ጨረታዎችን የምናዘጋጀው እና የምንሸጠው ራሳችን ነበርን። የጨረታ ሰነዶችን እኛ እናትማለን፤ እኛ ደረሰኝ እንቆርጣለን፤ እኛ እንሸጣለን። በዚህም በቢሮው በራፍ ላይ ረጃጅም ሰልፎች እየተፈጠሩ ደንበኞቻችንም ለአንግልት ይዳረጉ ነበር። አሁን በሕግ ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ሥራውን በመስጠት የደንበኞችን እንግልት እና ቢሮው ያወጣቸው የነበሩ ወጪዎችን መቀነስ ተችሏል።
ከዚህ ቀደም አስራ አምስት ሚሊዮን ብር ያወጣንበት የመጀመሪያ ዙር ጨረታ በሁለተኛው ዙር በሕግ ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ሥራውን ስንሰጥ ሶስት ሚሊየን ብር ብቻ ነው ያወጣነው። ተጫራቾቹም በቀላሉ ፀሐይ እና ዝናብ ሳይመታቸው፤ ለደላላም ሳይጋለጡ የጨረታ ሰነዱን በቀላሉ ማግኘት አስችሏቸዋል። የሶስተኛ ዙር በተመሳሳይ መንገድ ጨረታ አከናውነናል።
በዚህም እኛን ብቸኛ የመሬት አገልግሎት ሰጪ እንድንሆንና መንግሥት መያዝ ያለበትን ስፍራ ይዞ ሌላ የግሉ ሴክተር ደግሞ አገልግሎት እስካቀላጠፈ ድረስ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ቢሳተፍበት ችግር ሊሆን እንደማይችል ማየት ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ከመሬት ጋር ተያይዞ የነበሩት በርካታ ደንቦች፤ መመሪያዎች እና ሰኩላሮች እንደነበሩ ነግረውናል። ከዚህ አንጸር የመመሪያዎች ብዛት በመሬት አገልግሎት ዘርፉ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ኻሊድ፡- በከተማ አስተዳደሩ ከመሬት አገልግሎት ጋር የተገናኙ አስራ ሁለት መመሪዎች ነበሩ። ሁሉም ተጻራሪ ናቸው ባንልም እርስ በእራሳቸው የሚቃረኑ መመሪያዎች ነበሩ። ሁሉም የየራሳቸው ድክመት ነበረባቸው። ያ ማለት ግን ሁሉ መመሪያዎች ችግር ይፈጥራሉ ማለት አይደለም። ከብዛታቸው እና ካለመናበባቸው አኳያ አገልግሎትን ሊያወሳስቡ ይችላሉ።
መመሪያዎች የሰዎቹ ፍላጎቶች መሆን የለባቸውም። አገልግሎቱን የሚያሳልጡ መሆን አለባቸው እንጂ የሚያወሳስቡ መሆንም የለባቸውም። ይሄ ለእንግልት እና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄ መነሻ ነበር። አንዳንድ መመሪያዎች ደግሞ ከላይ ሲታዩ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ የማይመስሉ ነገር ግን ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ ነበሩ።
ሕጎች ለሰውም ለአገልግሎትም ቀላል ሆነው አገልግሎትን የሚያቀላጥፉ መሆን አለባቸው። በመመሪያዎች ላይ የሚኖሩ የሕግ ክፍተቶች ለባለሙያ፣ ለደላላ፣ ለደንበኛም እንዲሁም ለየትኛውም አካል ቢሆን ለብልሹ አሰራር የሚጋልጡ መሆን የለባቸውም።
በሥራ ሂደት ያየናቸውን እና ለብልሹ አሰራር ሊያጋልጡ ይችላሉ ያልናቸውን መመሪያዎች፣ ደንቦች እና አጠቃላይ ሕጎችን አስተካለናል። ስለዚህ ተጻራሪ የነበሩ እና አገልግሎት አሰጣጥን ያወሳስባሉ፤ ለብልሹ አሰራርም በር የሚከፍቱ ናቸው ያልናቸውን ሕጎች የማስተካከል ሥራ ተሰርቷል። በእዚህ ሂደት ከአመለካከት ክፍተት የተፈጸሙ ጉድለቶች ይኖራሉ።
የሕግ ክፍተቶች ያመጧቸውን ተጽእኖዎች ለመናገር ግን ተጨማሪ ጥናቶችን ማድረግ ያስፈልጋል። ምን ያህል ችግር ፈጥሯል? የሚለውን ለማወቅም ባለፉት ሃያ፤ ሰላሳ ዓመታት ከተማ አስተዳደሩ ‹‹ሴንትራል ቤዝ ማፕ›› አልነበረውም፤ አሁን ነው ‹‹ሴንትራል ቤዝ ማፕ›› የተዘጋጀው።
‹‹ሴንትራል ቤዝ ማፕ›› የለውም ማለት አንድ ይዞታ ከትክክለኛ ቦታ ለመውጣቱ ማረጋገጫ ሰነድ የለውም እንደ ማለት ነው። በዚህም እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ቤዝ ማፕ ፈጥሮ ላልተገባ አላማ ሊጠቀም ይችላል። ይሄ ‹‹ሴንትራል ቤዝ ማፕ›› ባልነበረበት ያመጣው ጉዳት ምን ያህል ነው? ብሎ ለመገመት አይቻልም።
‹‹ሴንትራል ቤዝ ማፕ›› ሲኖር ግን አንድ ባለይዞታ ካርታ ሲወስድ ስሙ፤ የት አካባቢ እንደሆነ፤ የትኛው ፓርሰል ላይ ምን ያህል ቦታ እንደወሰደ መረጃው ለሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ይደርሳል። በዚህም የጠፋ መሬት ካለማወቅ አያስቸግርም። ‹‹ሴንትራል ቤዝ ማፕ›› ባልነበረበት ሁኔታ በሕጎች ክፍተት የደረሰውን ጉዳት መናገር አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- መሬት ወረራን ከመከታተል እና ከመቆጣጠር አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው? ምንስ ተጨባጭ ለውጥ አምጥታችኋል?
አቶ ኻሊድ፡- መሬት የጋራ ሀብታችን ነው። አንዱ ጠባቂ የሚሆንበት ሌላው ደግሞ አይቶ የሚያልፍበት ሁኔታ መኖር የለበትም። ከዚህ አንጻር የመሬት ወረራን መከላከል የሚቻለው ሕዝብን በማሳተፍ ነው።
በተጨማሪም የመሬት ወረራዎች እንዲቀለበሱ ለማድረግ እና ለመከላከል በወረዳ ደረጃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍተን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወን ነው። በዚህም በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉንን ክፍት መሬቶች ሁሉ ኦዲት በማድረግ ወደ መሬት ባንክ አስገብተናል። በተጨማሪም እስከ ወረዳ ድረስ ያለ የኛ ተቋም ከደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ጋር ለመሥራት ተስማምቶ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ በመሆኑም ዛሬ ላይ ወረራ የለም። ምክንያተም በወረራ ቢይዙም እንደፈለጉት ማድረግ አይቻሉም። ያሉንን ክፍት መሬቶች ወይም ደግሞ የመንግሥት ባለቤትነት ያላቸው መሬቶችን ቆጥረን ተረካክበናል።
አንድ መሬት ባንክ አድርገናል ማለት ለሕጋዊ ሥራ እንጠቀምበታለን ማለት ነው። ለተለያዩ ተግባራት ከባንክ ወጪ የሚደረጉ ቦታዎችንም ‹‹ቤዝ ማፕ›› ላይ እንጭናቸዋለን። ስለዚህ ገቢ ወጪውም ኦዲት ይደረጋል። ይሄን አደረግን ማለት ደግሞ የሚወረር መሬት አይኖርም። ሕጋዊ ሆኖ የሚተላለፍ መሬት ብቻ ነው የሚኖረው።
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋን መሬት ለኢንቨስትመንት የማዋል ሥልጣን የማነው?
አቶ ኻሊድ፡- ለኢንቨስትመንት ከሚሰጥ መሬት ጋር በተያያዘ የከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን አለ። ለምሳሌ የመንግሥት ተቋማት፤ ሆስፒታሎች የጤና ተቋማት የመሬት ጥያቄ ያቀርባሉ። በዚህ ጊዜ ከተማ አስተዳደሩ ሲወስን ነው የመሬት ልማት እና አስተዳደር መሬት ማስተላለፍ የሚችለው።
በምደባ ከሆነ ደግሞ መሬት የመስጠት ሥልጣኑ የካቢኔው ነው። ከዚያ ውጭ እንደ ከተማ አስተዳደር መሬት በጨረታ ይሸጣል። ጨረታም ሲወጣ ጨረታ እንደምናወጣ ለከተማ አስተዳደሩ እናሳውቃለን። ሲፈቀድ መሬቱን የማስተላለፍ እና ጨረታን የማውጣት ኃላፊነት የኛ ነው። መሬት ለኢንቨስትመንት የመስጠት ሥልጣኑ ግን የከተማ አስተዳደሩ ነው። የኛ ሚና መሬቱን ማዘጋጀት እና ማቅረብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለአልሚዎች ወይም ለኢንቨስተሮች በምን መመዘኛ ነው ቦታው የሚሰጣቸው?
አቶ ኻሊድ፡- በሊዝ አዋጅ 721/ 2004 መሬት የሚተላለፍባቸው አማራጮች በግልጽ ተቀምጠዋል። በዚህ መሠረት አልሚዎቹ ወደ ተቋሙ ሲመጡ በመጀመሪያ ያላቸውን የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ቀርጸው ለከተማ አስተዳደሩ ያቀርባሉ። ነገር ግን ፕሮፖዛል ስላቀረቡ ብቻ መሬት አይሰጣቸውም። ምክንያቱም ፕሮፖዛል ለሚያቀርቡት አካላት የከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አሉ። እነዚህ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጡ ጉዳዮች በአዋጁ በግልጽ ተቀምጠዋል። ያንን መሠረት በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የአልሚዎችን ፕሮፖዛል ከተቀበለ መሬት ይዘጋጅላቸዋል።
መሬት የሚዘጋጀው ለሚፈለገው አላማ እንጂ ለአየለ፤ ለከበደ ተብሎ አይደለም። መሬት ለሞል፤ ለኢንዱስትሪ፣ ወዘተ. ተብሎ በየዓይነቱ ይዘጋጃል። መሬቶቹ ከተዘጋጁ በኋላ እነዚህ መሬቶች ወደ ካቢኔ ይሄዳሉ። ከግለሰቦቹ ፕሮፖዛሎች ተነስተው የትኞቹ ተጨባጭ ፕሮፖዛል አላቸው? የትኞቹ የሊዝ አዋጅ 721/2004 ላይ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተዋል የሚለውን በመገምግም ከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ ይሰጣል።
ፈቃዱን ተከትሎ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ መሬት በማዘጋጀት የማስተላለፍ ሥራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ መሬት የሚሰጠው ለግለሰቦች ብቻ ነው ወይስ ለመንግሥት ተቋማትም ጭምር?
አቶ ኻሊድ፡- መሬት ለግለሰቦችም ሆነ ለመንግሥት ተቋማት እንዲሰጣቸውም እንዳያሰጣቸውም የሚያደርጋቸው ፕሮጀክታቸው ነው። የጠየቀው ሁሉ መሬት አይሰጠውም። የከተማ አስተዳደሩ ለከተማው መነቃቃት አቅም ይሆናሉ የሚላቸውን ፕሮጀክቶች ያያል። ለምሳሌ ሰዎች መሬት ያገኙና አጥረው የሚያስቀምጡ ከሆነ ወይ ደግሞ የፋይናስ አቅማቸው መሬቱ ቢሰጣቸው ለማልማታቸው ጥያቄ የሚሆን ነገር ካለ ጥያቄ ስላቀረቡ ብቻ አይሰጣቸውም። አሁን ላይ መሬት ሰጥተናቸው ማልማት ያልቻሉ ሰዎችን መሬት ነጥቀን ወደ ጨረታ እያወጣን ነው።
በሊዝ አዋጁ ላይ አልሚዎች የፋይናንስ አቅማቸውን እንዲያስቀምጡ ያዛል። ለምሳሌ አንድ ፕሮጀክቱ እስከ አምስት መቶ ሚሊየን ብር ይፈጃል ከተባለ እና አልሚው ያቀረበው የባንክ መረጃ ለሥራው ይመጥናል ተብሎ ከሚገመተው በታች ከሆነ ለዚህ ግለሰብ መሬት መስጠት ነገ ፕሮጀክቱን ለመሥራቱ ጥያቄ ያስነሳል። በደንቡ ላይ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ለሰዎች ሳይሆን የፕሮጀክታቸውን ተጨባጭነት መሠረት ተደርጎ ለአልሚዎቹ ቦታ እንዲያገኙ ይደረጋል።
ከአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ማለትም ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ተቋማት እና ለሌሎች የመንግሥት ተቋማት ማስፋፊያ ሲጠይቁ ከያዙት አላማ እና ግብ አንጻር መሬት ይተላለፋል። ለግል ሆስፒታሎችም በተመሳሳይ ይሄው ይፈጸማል። ነገር ግን ይሄንን ስናደርግ በትኩረት የሚታየው ተቋማቱ ይዘውት የሚመጡት ፕሮጀክት ነው። ይህ ማለት ይዘውት የመጡት ፕሮጀክት ለምን ያህል ዜጋ የሥራ እድል እንደሚፈጥር፤ የሚፈጥረው የቤት ሀብት ቁጥር ፤ ሰርተው ሊያጠናቅቁበት የሚችሉበት አቅማቸው እና ከዚህ ቀደም የነበራቸው ታሪክ ተጠንቶ ቦታውን እንዲያገኙ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ይሄ አካሄድ ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ አያደርግምን?
አቶ ኻሊድ፡- ጉዳዩን የሚወስነው በየቦታው ያለ ግለሰብ ወይም በየአካባቢው እና በየጥሻው ስር ያለ ደላላ አይደለም። ውሳኔው የሚመጣው ከከተማ አስተዳደሩ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ የሚሰጠው በሚገባ አጥንቶ እና ፕሮጀክቱን ተመልከቶ ነው። የመሬት ልማት እና አስተዳር ቢሮ ፣ ክፍለ ከተማ፤ ወረዳ መሬት አይሰጡም። ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ለሀገር እና ለከተማው ይጠቅማል፤ ማህበራዊ ችግሮችንም ያቃልላል ብሎ ላመነበት ነው መሬት እንዲሰጥ የሚያደርገው ።
ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የከተማ አስተዳደሩ ለከተማዋ መነቃቃት በሚል ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ነበሩ። አሁን ግን ሁኔታዎች ጥብቅ ናቸው። ለምሳሌ የጨረታ ጉዳይን ስንመለከት፤ በጨረታ ሁሉም ሰው ሊሳተፍ ይችላል። ይህ ከተሳትፎ አንጻር ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሰነዱን ከገዛ በኋላ ግን የሚራገፈው ሰው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። አንዳንዱ ደላላ በሌለው ‹‹ፐርፎርማ›› ተጫርቶ ለባለሀብት መልሶ ይሸጣል። አሁን ላይ ይህ እንዳይሆን ሕጋችንን የማስተካከል ሥራዎችን ሰርተናል። በዚህም ሕገ ወጥ ሰንሰለቱን መበጠስ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ላይ የመኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለ ይታወቃል። ያንን ችግር ለማቃለል ለአልሚዎች ቦታ ከመስጠት እና ከመቆጣጠር አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ኻሊድ፡- በቀድሞው አካሄድ የቤት ፈላጊዎችን የቤት ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነት በመንግሥት ላይ ወድቆ ቆይቷል። አሁን ይህ ዓይነት አካሄድ አዋጭ አይደለም። በመሆኑም በዚህ ዓመት እንደ ከተማ አስተዳደር በተለየ ሁኔታ በ70/30 ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህ ፕሮጀክት የከተማዋን የቤት ችግር ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ‹‹በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነር ሺፕ›› ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መንግሥት ቦታ አልሚዎች እያቀረበ ነው። በዚህም መንግሥት የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። መንግሥት ከሚያገኘው ድርሻ ለነዋሪው እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤት በማቅረብ የቤት ችግር የሚቃልልበትን አማራጭ እየፈጠረ ነው።
ለዚህ የሚሆኑ ቦታዎችን ወስነናል። ከዚህ በኋላም ቤት ሰርቶ የማስረከብ ኃላፊነት የቤቶች ልማት ኤጀንሲ ብቻ አይሆንም። የግል ዘርፉም የሚሳተፍበት ይሆናል። በዚህም ለ70/30 ፕሮጀከት በርካታ መሬቶችን አቅርበን ቤቶቹ እየተገነቡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከመንግሥት መሬት ወስደው በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ በማያለሙ ባለሀብቶች ላይ ምን ዓይነት ርምጃ ትወስዳላችሁ? ምን ያህል ሄክታርስ እስከ ዛሬ ተመላሽ አድርጋችኋል?
አቶ ኻሊድ፡- አንዱ ክፍተት የነበረው አልሚዎቹ መሬት ከወሰዱ በኋላ ፈጥኖ ወደ ልማት ያለመግባት ችግር ነበር። ለምሳሌ በ2015 ዓ.ም ፈጥነው ወደ ልማት ያልገቡ አልሚዎችን ውል አቋርጠናል። በዚህም ከ90 ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ለጨረታ አቅርበን ለሌላ አልሚ አስተላልፈናል።
በነገራችን ላይ ማልማት ጊዜ ይፈልጋል፤ ለባለሀብቶቹም እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችን መረዳት ያስፈልጋል። የገበያውን፤ የከተማውን ኮንስትራክሽን ሁኔታ እና የግብዓት እጥረቶች ሁሉ ታሳቢ አድርገን ረጅም ጊዜ የወሰዱ እና እነዚህ ጉዳዮች የማይመለከቷቸውን አልሚዎች መሬት ውል እንዲቆራጥ ተደርጓል፤ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናቸው ወደ ሥራ ያስገባናቸውም አሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ ያልገቡ እና ያላጠናቀቁ አንድ ሺህ 30 አልሚዎችን ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ በመምከር በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ነው። አልሚዎቹ አሁን ጥሩ ለውጥ እያመጡ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለባለሀብቶች በኢንቨስትመንት አዋጁ እና በሊዝ አዋጁ ላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ቦታን ከማስረከብ አኳያ ያለችሁ አፈጻጸም ምን ይመስላል?
አቶ ኻሊድ፡- ከተማ አስተዳደሩ ለወሰነላቸው ባለሀብቶች መሬት የማስተላለፍ ችግር የለብንም፤ ለእነሱ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ መስኮት አለን። ለምሳሌ ካቢኔው ወስኖለት እንደመጣ ከ15 እስከ 20 ቀን ባሉት ጊዜያው ውስጥ ቢሮክራሲውን አልፈው እንዲሄዱ እናደርጋለን።
ነገር ግን ለምሳሌ አንድ ሰው ለከተማ አስተዳደሩ የመሬት ጥያቄ ባቀረበ ጊዜ ፕሮጀክቱ አዋጭ ‹‹ፊዚብል›› የማይሆን ከሆነ በሁለት ወርም ቢሆን የመሬት ጥያቄው መልስ ላያገኝ ይችላል። ይሄ ሲነገራቸው ግን አዋጭ ‹‹ፊዚብል›› ያልሆነውን ፕሮጀክታቸውን ማስተካከል አለባቸው። በ2016ዓ.ም ታማኝ የሆነና መፈጸም የሚችል ፕሮጀክት ላላቸው አልሚዎች ሙሉ በሙሉ መሬት ሰጥተናል።
አዲስ አበባ ላይ የፀዳ መሬት የለም። የጸዳ መሬት ማስተላለፍ የሚቻለው በመልሶ ማልማት ነው። ይህም የሚሆነው በፊት የነበረውን አካሄድ እና አሰራር ተከትለን ነው ። በዚህም ተነሺዎቹ ካሳ እና ምትክ ይሰጣቸዋል። ካሳ ከተሰጣቸው ቦታው ክፍት ተደርጎ ለአልሚው ይተላለፋል።
አንድ ባለ ሀብት መሬት እንዲያገኝ ተወስኖለት የካሳ ክፍያውን ማስገባት ባለበት ጊዜ ካላስገባ ችግሩ የመንግሥት አይሆንም። የአልሚው ጉድለት ነው። አልፎ አልፎም እንዲሁ አልሚው የካሳ ክፍያውን ካስገባ በኋላ አንዳንዴ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ። በዚህ ጊዜ መንግሥት ጣልቃ እየገባ ተከራክሮ ሰዎቹን ያስነሳል።
አዲስ ዘመን፡- በባለሀብቶች የአርሶ አደሮች መሬት ሲነጠቅ እና ድንበር ሲገፋ ምን ዓይነት ርምጃ ትወስዳላችሁ? ከካሳ ጋር ለሚነሱባችሁ ጥያቄዎችስ ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጣላችሁ?
አቶ ኻሊድ፡- እነዚህ ጥቄዎች በቀድሞው አሰራር ሊነሱ የሚገባቸው ናቸው። አሁን ባለው አስራር ባለሀብቱ ራሱ ነው ካሳ ከፍሎ የሚያስነሳው። ለቦታውም የሚገባውን ካሳ ይከፍላል። ከዚህ በፊት በነበረው አካሄድ አርሶ አደሮች የሚገባቸውን ካሳ አግኝተዋል ብለን አናምንም።
እንደ መንግሥት ፤ እንደ ሰውም የምንወስደው አንድ አቋም ለተነሽዎች ተገቢው ካሳ መከፈል አለበት የሚል ነው። በዚህ አቋምም ካሳ ባልተከፈለባቸው ቦታዎች ላይ የልዩነት ካሳ እየተከፈለ መሬቶች እየተላለፉ ነው። በዚህ ጊዜ መተማመን ይፈልጋል። አልሚዎች መሬቱ ስለተሰጠ በሚል ጥያቄ ያለበትን ሰው ዝም ሊለው አይገባም።
መንግሥት የልዩነት ካሳ በወሰነባቸው ቦታዎች ላይ የልዩነት ካሳውን እየከፈልን እያስነሳን ነው። በዚህ ረገድ የካቢኔ ውሳኔን ገዥ እና ትልቁ ሕጋዊ ውሳኔ አድርገን እንወስዳለን። ከዚህ በፊት የነበረውን የልዩነት ካሳ ለመክፈል ፍቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች ካሉ መንግሥት የሚከፍለውን ካሳ ይከፍላል። ክርክርም ካለ የሚከሰሰው መንግሥት ስለሆነ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ምላሽ እንሰጣለን። አሁንም ግለሰቦችም የሚነሷቸው ጥያቄዎች ካሉ ቢሯችን ኃላፊነት ወስዶ ያስተካክላል።
አዲስ ዘመን፡- ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን በ2015 ሰኔ ወር ላይ አጠናቆ ባስገባው ጥናት መሠረት አዲስ አበባ ላይ የመሬት ዝርፊያ እንዳለ አመላክቷል። በዚህም አንድ ሺ 963 ጥቆማዎች ደርሰውታል። ከዚህ ውስጥ 418ቱ ውሳኔ አግኝተዋል። ከዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ በላዩ ደግሞ በእግድ ላይ እንዳሉ ጥናቱ ያሳያል። ተቋማችሁ እንደዚህ ዓይነቱን የመሬት ዝርፊያዎች ለማስቀረት ምን እየሰራ ነው?
አቶ ኻሊድ፡- መረጃው ምን ያህል ከዚህ ተቋም ጋር ይገናኛል ስለሚለው መረጃው የለኝም። በዚህ ዙሪያ በቂ መረጃ ስለሌለኝ ምላሽ የለኝም። ነገር ግን ለእኛ መነሻ የሚሆነን የከተማ አስተዳደሩ በ2015 በውስጥ አቅም ያደረገው የመሬት ኦዲት ሥራ አለ። ይህ የኦዲት ሥራ የእዚህ አካል ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ከዚህ ውጭ የሆነ በከተማው ያለ ነገር አይኖርም።
ከተማ አስተዳደሩ በኦዲት ግኝቱ ያገኘውን መሬት ሁሉ ባንክ አድርገናል። በዚህ ውስጥ የግለሰቦች ቤት የለበትም ማለት አንችልም። መንግሥት ግን እየተከራከረበት ነው። ተሳስተን ባንክ ያደረግነው መሬት ካለም ይስተካከላል።
አንዳንዴ መረጃዎች ሳይገኙ ባንክ የተደረገ መሬት ላይ ሕጋዊ ሰዎች ይመጡና የጎደለ ነገር ካለ ይስተካከላል። በትክክለኛው መንገድ መሬት ያልያዙ ሰዎች ካሉ ግን ለመንግሥት ገቢ እየተደረገ ለሚፈለገው አላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።
ከምንም በላይ የመሬት ተቋም ኮሚቴ አያስፈልገውም። ራሱን ችሎ በራሱ መመራት አለበት። በራሱ አቅም ሌብነትን እና ብልሹ አሰራርን መጋፈጥ አለበት ብለን የሪፎርሙ አንድ አካል አድርገነዋል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ሕገ ወጥ የሆኑ የግለሰብ ፋይሎች አምክነን ግለሰቦቹ በሕግ እንዲጠየቁ ያደረግንባቸው ፋይሎች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ላይ በኮሚቴ ‹‹በአርሶ አደር ነው›› እየተባለ የተዘረፈ መሬት አለ ይባላል። ለዚህስ ተጠያቂው ማነው?
አቶ ኻሊድ፡- የከተማ አስተዳደሩን የኦዲት ግኝት ተመርኩዞ ቢሯችን ርምጃ ወስዷል። የዓለም ባንክም ይሁኑ ሌሎች ግለሰቦች ከከተማ አስተዳደሩ የተለየ ግኝት ይኖራቸዋል ብለን አንገምትም፤ ካለም አምጥተን ማየት እንችላለን። በኮሚቴ መወሰን አያስፈልግም፤ አይጠቅምም ሳይሆን ተቋማትን ግን አያበቃም።
ይህ ጉዳይ ተቋሙ ሪፎርም ሲያደርግ በከፍተኛ ደረጃ የታገለበት ጉዳይ ነው። ሕገ ወጥ ማህደሮችን አጥርተንም ርምጃ ወስደንበታል። ይሄንን የፈጸሙ ከ620 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ጉዳይን ጸረ ሙስና እንዲያየው እና በፍርድ ቤት እንዲታይ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ የመሬት ዘረፋ ላይ የመንግሥት ባሥልጣናት እጃቸው እንዳለበት ይነገራል። እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ ኻሊድ፡- በየትኛውም ጥናት ከተሞች ላይ የሚደረጉ የሙስና ወንጀሎች ትልቁን ቦታ የሚይዙት ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ሙስናዎች ‹‹ፖለቲካል ኮራብሽኖች›› ናቸው። በዚህ ውሰጥ አመራር ፤ የፖሊሲ አውጭ፤ ደላሎች፤ ባለሀብቶች እና ባለሙያዎች ይኖሩበታል። 20 በመቶው የሚሆነው ደግሞ የባለሙያ ነው።
የውጭም የውስጥም ተሳታፊዎች ባሉበት ሁኔታ ችግሩን የአንዱ አካል ብቻ ማድረግ አይገባም። ችግርም የለም ብሎ መካድ አያስፈልግም። መንግሥት ችግሩን እንደ ችግር ወስዶ በስሩ ያሉ አመራሮችን እና ባለሙያዎችን ማጥራት አለበት። ለዚህም ነው ተቋማዊ ሪፎርሙ ያስፈለገው። ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሚሆኑ የሕግ ክፍተቶች፤ አደረጃጀቶችን /ስትራክቸሮችን/ የማስተካከል ሥራ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ሥርዓት እንዲኖር እያረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ምን ያህል አመራሮች እና ባለሙያዎች ላይ ርምጃ ወስዳችኋል?
አቶ ኻሊድ፡- በ2016 ዓ.ም 181 በሚሆኑ አመራሮች እና ሠራተኞች ላይ ርምጃ ወስደናል። ይሄ ማለት ግን መሬት የሰረቀ ብቻ አይደለም። ኃላፊነቱን ባልተወጣና በተገቢ መልኩ ሥራውን ባልመራ የሥራ ኃላፊ ላይ ጭምር የተወሰደ ርምጃ ነው።
አሁን ተቋሙ ላይ ያረግነው ሪፎርም ስርቆትን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና አለው። ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ለውጥ ለማምጣት ያደረግነው ጥረት ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው። ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ችግር አሁን የተፈጠረ አይደለም። ከቀደሙት ዓመታት እየተንከባለለ የመጣ ችግር ነው። የመመሪያዎች እና የሰርኩላሮች መብዛት ለመሬት ዝርፊያ ይጋብዙ ስለነበር ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችገሮች ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተፈጠሩ ናቸው።
በከተማዋ ከመሬት ጋር የተያያዙ 12 መመሪያዎችን የማስተካከል ኃላፊነት የወደቀው በቢሮው ወይም በለውጡ መንግሥት ላይ ነው። አሁን እየተደረገ ያለው ሪፎርም ይሄንን ችግር ይዘጋል። ችግሮች እንዳሉ ሁሉ በተቋሙ ጥሩ የሚባሉ አመራሮች እና ባለሙያዎችም ነበሩ።
አዲስ ዘመን፡- ፀረ ሙስና ባካሄደው ጥናት ከ296 ሺ በላይ መሬት ተወሮ 240 ሺ ካሬ ተመልሷል። ይሄ ሁሉ መሬት ሲወረር ቢሮው ምን እየሰራ ነበር?
አቶ ኻሊድ፡- መንግሥት እንደ መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት እንጂ የወረራው መነሻ አሁን አይደለም። በተለያየ ጊዜ የመንግሥት ትኩረት ሌላ ጉዳይ ላይ በሆነ ጊዜ የተደረጉ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ምርጫ 1997ዓ.ም ተከትሎ የተደረጉ ወረራዎች ነበሩ። የመንግሥትን ሁኔታ እያዩ የውስጥም የውጭ አካላት መሬት ይቀራመታሉ። ከተማ አስተዳደሩ ኦዲት አድርጎ በግኝቱ መሠረት ርምጃ እየተወሰደ ነው። በወረራው ላይ ብዙ ሚና የሚጫወቱ አካላት ግን አሉ።
ነገም ወረራ ሊኖር ይችላል። ሰው መንግሥት ያለበትን ሁኔታ እና ጨለማን ተገን አድርጎ መሬት ይወራል። እኛ እንደ ተቋም ግኝቱ ሲደርሰን ጊዜ ርምጃ እንወስዳለን።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር እናመሰግናለን።
አቶ ኻሊድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም