‹‹በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መጀመሩ በኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት የሚፈጥር ነው›› – ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) የቀድሞው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

/ይህ ቃለ መጠይቅ ከሁለት ሳምንት በፊት የተደረገ ሲሆን ፤ ዶክተር ብሩክ ታዬ በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው /

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት በተለያዩ ተቋማት ላይ የማሻሻያ ሥራ ከመሥራት ባሻገር ወቅቱን የሚመጥኑ አዳዲስ ተቋማትን በአዲስ መልኩ አቋቁሟል:: ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አንዱ ነው:: ባለስልጣኑ ለምን ተቋቋመ፣ ስልጣን እና ኃላፊነቱ ምንድነው ፣ ባለስልጣን ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ምን ምን ሥራዎችን አከናወነ? በዘርፉ ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎች ምንድን ናቸው? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከባለስልጣኑ የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በሕግ የተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት ምንድነው?

ዶክተር ብሩክ፡- ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1248 በ2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በሀገራችን ውስጥ ያለውን የሼርና የብድር ሰነዶች ሽያጭን በተመለከተ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ፤ የካፒታል ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ተደርጎ መከናወን እንዳለበት የማገዝ፤ የሀገራችንን የገበያ ሥነ ምህዳር የማሳደግ፤ ገበያ ላይ ተዋናይ የሚሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ ባንኮችን፣ ደላሎችን እና ‹‹የክሬዲት›› ካርድ ኤጀንሲዎች ፈቃድ መስጠት እና መቆጣጠር ነው::

በአጠቃላይ የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የካፒታል ገበያ የሚኖረውን ጉልህ ጠቀሜታ ለማስፈጸም የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ነው:: የአክሲዮን ድርሻ ሸጠው ወደ ገበያ መምጣት የሚፈልጉ አካላት ወደ ገበያ ከመምጣታቸው በፊት ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የደንበኛ እሳቤ መግለጫ ያቀርባሉ:: ያቀረቡት የደንበኛ እሳቤ መግለጫ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ መርምሮ ማጽደቅ አለበት:: የደንበኛ እሳቤ መግለጫ ከጸደቀ ወደ በገበያ መምጣት ይችላሉ::

አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ሚዲያዎች ስቶክ ማርኬት፤ ካፒታል ማርኬት፤ ሚኒ ማርኬት፤ ፋይናንሽያል ማርኬት እየተባለ ሲነገር ይሰማል:: አንዱ ቃል ሌላውን ተክቶ የመጠቀምም ሁኔታም አለ:: ቃላቶቹ የተውሶ ቃላት እንደመሆናቸው ትክክለኛ ትርጉማቸው ምንድን ነው?

ዶክተር ብሩክ፡- ቃላቶቹ ተወራራሽ ቃላት ናቸው:: አንዳንዶቹ አጠር ተደርገው ስቶክ ማርኬት፤ የሼር ገበያ እየተባሉ የሚገለጹ ናቸው:: ነገር ግን የካፒታል ገበያ የሚለው ገዥ ቃል ሲሆን ፤ ትርጉሙም እንደማንኛውም ገበያ አንድ ሰው ከማህበረሰቡ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚችልበት የገበያ ሥርዓት ነው:: በዚህ ዓይነቱ ገበያ ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆኑ፣ ለሚገዛው ሰው ትርፍ የሚሰጡ የብድር ሰነድ ከሸጡ ብድሩ የተቀመጠለትን ወለድ ከፍለው ሰዎች በገዙት ልክ ትርፍን የሚያካፍሉበትን የሕግ ማዕቀፍ የያዘ ነው::

‹‹ስቶክ ኤክስቼንጅ›› ወይም ‹‹የስቶክ ማርኬት›› ሲባል የድርሻ ገበያውን የሚገልጽ ነው:: በእኛ አጠራር ደግሞ ድርሻ የሚሸጥበት አሰራር ‹‹የሰነድ መዋለ ንዋይ›› ይባላል:: የሰነድ መዋለ ንዋይ ማለት አንድ ሰው አንድን ድርጅት በሼር ሲገዛ የዚያን ድርጅት ድርሻ የባለቤትነት ድርሻ እንዳለው የሚገልጽ ሰነድ ነው:: በሌላ በኩል አንድ ሰው አንድ ኢንቨስትመንት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሱን የሚገልጽበት ሰነድ ነው::

እነዚህ የድርሻ ‹‹ሰርተፍኬቶች›› የሚገዙበትና የሚሸጡበት ገበያ ደግሞ ‹‹ስቶክ ማርኬት›› ተብሎ ይገለጻል:: አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሰነድ መዋለ ንዋይ ገበያ ተብሎ በተቋቋመው አሰራር የብድር ሰነድ ይሸጣል፤ ይገዛል:: የብድር ሰነድ ማለት ደግሞ መንግሥት ብድር ከተበደረ በኋላ ብድር መበደሩን የሚያረጋግጥ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጠዋል:: ይህም እራሱን የቻለ የብድር ሰነድ ይባላል::

በአጠቃላይ ገበያው ሲገለጽ የካፒታል ገበያ ተብሎ የሚጠራ ነው:: በውስጡ የብድር ሰነድ የሚሸጥበት፤ የድርሻ ሰርተፍኬት የሚሰጥበት እና የሚሸጥበት እንዲሁም የሰነድ መዋዕለ ንዋይ የሚሸጥበት ነው:: ‹‹መኒ ማርኬት›› የሚባለው ደግሞ የገንዘብ ግብይት የሚደረግበት ነው:: ይህ ከእኛ ኃላፊነት ውጭ የሆነና ብዙ ጊዜ በብሔራዊ ባንክ በኩል የሚከናወን ነው:: ይህም ባንኮችን እርስ በርሳቸው መገበያየት ያስችላቸዋል:: በካዛናው ትንሽ ጥሬ ገንዘብ ያለው አንድ ባንክ ብዙ ገንዘብ ‹‹ሊኩዲቲ›› ካለው ሌላኛው ባንክ የሚያደርጉት ግብይት ነው::

ገበያው ወደ ውስጥ ሲገባ የተለያዩ የፋይናንሻል ፕሮዳክት (ውጤቶች) እየተፈጠሩ የሚሰሩበት ነው:: በአጠቃላይ በተለይ እኛ የተሰጠን ኃላፊነት ከመኒ ማርኬት ውጭ ያሉ ሁሉንም ግብይቶች መቆጣጠር እና ፈቃድ መስጠት ነው::

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ እንደ ተቋም በ2016 በጀት ዓመት ምን አቅዶ ምን አከናወነ? በ2017 በጀት ዓመት ምን አቅዷል?

ዶክተር ብሩክ፡– የተቋሙ የፕሮጀክት ቢሮ በብሔራዊ ባንክ ስር የተደራጀ ነበር:: እዚያ የነበሩ የሥራ ባልደረቦቼ የተለያዩ አዋጆችን የማርቀቅ እና የማጸደቅ ሥራዎችን ሲከናውኑ ቆይተዋል:: እኔ እዚህ ከመጣሁ በኋላ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ ሆኖኛል:: በዚህም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን እንደ አዲስ የማደራጀትና የማዋቀር ሥራ ሲሰራ ነበር::

በ2016 ዓ.ም በተለይም አዋጅ ጋር የተያያዙ በርካታ ሥራዎችን ስንሰራ ነበር:: በአዋጁ አስፈላጊ የሆኑ ሕግ ማዕቀፎችን ከማካተት በተጨማሪ የተለያዩ ፍቃዶችን መስጠት የሚያስችሉ መመሪያዎችን በማርቀቅ ፍቃድ የመስጠት ሥራዎችን ጀምረናል:: በ2016 ዓ.ም ዋነኛ እቅድ አድርገን የያዝነውና ያስፈጸምነው ይህንን ነበር::

በተጨማሪም በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሶስት የተለያዩ መመሪያዎችን ወደ ሥራ አስገብተናል:: እነዚህም የካፒታል ገበያ ፍቃድ የሚሰጥበት፣ በገበያው ላይ የሚሳተፉ ተዋንያን ደግሞ መሥራት የሚችሉበትን ፈቃድ የሚሰጥበትን እና ፈቃዱን ያገኙ ተዋንያን ምን ያህል ክፍያ ይከፍላሉ? የሚለውን የክፍያ መመሪያ ወደ ሥራ አስገብተናል::

በአሁኑ ወቅት በቅርቡ ይፋ ያደረግነው እና ያስተዋወቅነው የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች 9፡18 ገበያ ‹‹ስቶክ ኤክስቼንጅ›› ወደሥራ ለመግባት ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፍቃድ ሊሰጠው ያስፈልጋል:: ያንን ፍቃድ የምንሰጥበትን መመሪያ በማርቀቅ ውይይት በማድረግ በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ ወደሥራ ተገብቷል::

ከሕግ ማዕቀፍ አኳያ ትልቁን ሥራችን እሱ ነበር:: መሥሪያ ቤታችን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ራሳችንን በሠራተኛ እና በባለሙያ ማደራጀት ነበረብን:: ለዚህም በዓመቱ እንቀጥራለን ብለን ያቀድነውን ወጣት ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አማካሪዎች እንዲሁም በሌሎች ሀገራትም ጭምር በካፒታል ገበያ ላይ የሰሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አምጥተን ሥራችንን በሙሉ አቅም እየሰራን ነው::

ሌላው በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን ሥራ የሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ ግዢዎችን መፈጸም ነበር:: ምክንያቱም የካፒታል ገበያ ብዙ ሽያጭ እና ግዢ የሚደረገው በቴክኖሎጂ ነው:: ያንን ግዢ እና ሽያጭ የመቆጣጠር ኃላፊነት ስላለብን እሱን ለመቆጣጠር የሚያስችለን የቴክኖሎጂ ግዢዎችን እያጠናቀቅን ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በ2016 ዓ.ም ጨረታውን አውጥተን ያሸነፈውን አካል መርጠን አሁን የመጨረሻው ድርድር እና ንግግር ላይ እንገኛለን::

በ2016 በጀት ዓመት ሌላው ትልቁ ሥራችን የነበረው ስለ ካፒታል ገበያ ለማህበረሰባችን ማሳወቅ ነበር:: ለዚህ ይረዳ ዘንድ የተለያዩ መድረኮችን አዘጋጅተናል:: ክልሎች ድረስ በመሄድ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ አመራሮችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እና የቢዝነስ ማህበረሰቡን አወያይተናል::

የ2017 በጀት ዓመት ዋናው እቅዳችን ደግሞ ገበያ ማስጀመር ነው:: ገበያውንም ለማስጀመር በጣም በፍጥነት እና በጥንቃቄ እየሰራን ነው:: ይህን ለማከናወን የሚያስችሉ መመሪያዎች በሙሉ ተዘጋጅተዋል:: የቀረውን የቴክኖሎጂ ግዢ ደግሞ የኢትዮጵያ ‹‹ሴልስ ኤክስጄንጅ›› በራሱ እንደ ድርጅት ሆኖ ፍቃድ ወስዶ ሊጀምር ስለሆነ እነሱን ማገዝ እና የ2016 ከመጠናቀቁ በፊት በእኛ በኩል መሥራት ያለብንን ሥራዎች አጠናቀናል:: በእነሱ በኩል ደግሞ በ2017 መሥራት ያለባቸውን እያጠናቀቁ ነው:: የፈረንጆቹ 2024 ከመጠናቀቁ በፊት ሥራ ለማስጀመር እቅድ ይዘን እየሰራን ነው::

አዲስ ዘመን ፡- እነማን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለሽያጭ ተመረጡ? ለመምረጥስ መስፈርቱ ምን ነበር? መቼስ ለገበያ ይቀርባሉ?

ዶክተር ብሩክ ፡- ከኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በመነጋገር አምስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ካፒታል ገበያ ገብተው ከፍተኛ የሆነ ካፒታል እንዲያገኙ ለማድረግ እና ራሳቸውን ሊያጠናክሩ የሚችሉበትን መንገድ ለማየት ስንሰራ ቆይተናል:: በእኛ በኩል ድጋፍ ነው ምንሰጠው:: ዋናው ባለቤቱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ነው:: መጨረሻ ውሳኔውን ወስኖ ሊስት ይደረጉ ወይንም ወደ ካፒታል ገበያ ይምጡ አይምጡ የሚለውን የሚወስነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ነው:: በእኛ በኩል የሞያ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ነው::

በአማካሪዎች ቦርድ በኩል ምን ያህል ብቁ ናቸው? ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? የሚጎላቸውስ ምንድነው? የሚለውን አጥንተን ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አቅርበናል:: በእነሱ በኩል ቅድሚያ የሚሰጠውን አይተው እና ገምግመው ውሳኔ ያሳርፋሉ:: በውሳኔው መሠረት ወደ ካፒታል ገበያ የሚመጡበት ማዕቀፍ ይኖራል ማለት ነው::

ከዚያ ባለፈ ግን ከዚህ በፊትም በመንግሥት እንደተላለፈው የኢትዮ ቴሌኮም አስር በመቶ ወደ ገበያ እንደሚወጣ፤ ይህም በካፒታል ገበያ ማዕቀፍ እንደሚሆን በተነገረው መሠረት ከኢትዮ ቴሌኮምና ከአማካሪዎቻቸው ጋር ብዙዎቹን ነገሮች እያጠናቀቅን ነው:: የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለመሸጥ በቴሌቭዥን ማስታወቂያ እየተነገረ ነው:: ድርሻ ለመግዛት የቴሌ ብር “አፕሊኬሽን ዳውንሎድ” አድርጉ፤ ተዘጋጁ የሚል ማስታወቂያ እየተነገረ ነው::

በባለስልጣኑ በኩል ባለን ማዕቀፍ መሠረት 10 በመቶውን ወደ ገበያ የማውጣት ሥራውን በከፍተኛ ደረጃ እየሰራንበት ነው:: ሲጠናቀቅ ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን:: በአጠቃላይ ግን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም::

በሀገራችን ውስጥ ያሉ የግል ባንኮች ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ናቸው:: ከግማሽ ያላነሱ በማኔጅመንት እና በቦርድ ደረጃ ለእያንዳንዳቸው ከካፒታል ገበያ ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም ምን እንደሆነ፤ ለኢንሹራንስ ካምፓኒዎች እና ለሌሎች የግል ድርጅቶች በካፒታል ገበያ ውስጥ በመምጣት የሚፈልጉትን ማግኘት እንደሚችሉ መግለጫ ሰጥተናል::

የእኛ ኃላፊነት የካፒታል ገበያ ጽንሰ ሃሳቡ ምን እንደሆነ፣ በካፒታል ገበያ ምን ዓይነት ጠቀሜታ እንደሚያገኙ፣ በምን ዓይነት መንገድ እኛ እንደምንደግፋቸው፣ የእኛ የሕግ ማዕቀፎች ምን እንደሚመስሉ ማስረዳትና ማብቃት ነው:: ወደ ካፒታል ገበያ እመጣለሁ ወይንም አልመጣም የሚለው የራሱ የድርጅቱ ውሳኔ ነው::

በተጨማሪ የብድር ሰነድ ገበያውን በተለይ የኮርፖሬት የብድር ሰነድ ገበያውን ለማጠናከር ከአይ ኤፍ ሲ ጋር በመተባበር ራሱን የቻለ ትልቅ ፕሮግራም ቀርጸን ድርጅቶችን ለይተን እየሰራን ነው:: ድርጅቶቹ ምን ያህል ብር ያስፈልጋቸዋል? ከብድር ገበያው ላይ ሲመጡ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሕግ ማዕቀፍ ምን ይላል? በምን ዓይነት መንገድ እሱን ማሟላት ይችላሉ? የሚሉትን አብረን እየሰራን ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የግል ድርጅቶችን እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችንም እየደገፍን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮ ቴሌኮም ውጭ ይሸጣል ተብሎ የተመዘገበ ድርጅት አለ?

ዶክተር ብሩክ፡- ከሽያጭ ጋር ተያይዞ ባለቤቱ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስለሆነ ማን ይሸጣል ማን አይሸጥም የሚለውን መናገር የሚችለው እሱ ተቋም ነው:: በእኛ በኩል ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን እነዚህ ናቸው ተብሎ ሲነገረን እነሱን የመደገፍ ሥራ እንሰራለን::

አዲስ ዘመን፡- የስቶክ ማርኬት ጽንሰ ሃሳብ ለብዙሃኑ ግልጽ አይደለም:: ከዚህ አንጻር ወደ ትግበራ በሚገባበት ወቅትም የታቸኛው የማህበረሰብ ክፍል በምን ዓይነት መንገድ ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል?

ዶክተር ብሩክ፡- እስካሁን ባለን ግምገማ ብዙ ሰው ስለ ካፒታል ገበያ ቀጥተኛ እውቀት ባይኖረውም ስለኢንቨስትመት፣ ቁጠባ፤ ከባንክና ከኢንሹራንስ የአክሲዮን በሼር የሚገኝን ጥቅም በተለይም በአዲስ አበባ ያለው ማህበረሰባችን እና ለኢንቨስትመንት ቅርበት ያላቸው ሰዎች ትልቅ ግንዛቤው አላቸው:: ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አሁን በምናያቸው 18 ኢንሹራንስ ካምፓኒዎች እና የግል ባንኮች ወደ 400 ሺህ የሚሆኑ ኢንቨስተሮች አሉ::

እነዚህ ኢንቨስተሮች አሁን ላይ በጉልህ የሚታወቁና ባንኮችን እዚህ ደረጃ ላይ ማድረስ የቻሉ ናቸው:: ስለዚህ የስቶክ ማርኬትን ጽንሰ ሃሳብ ለብዙሃኑ ግልጽ ለማድረግ ከባድ ሥራ አይጠብቀንም:: ግልጸኝነት በሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ላይ ተጨማሪ መረጃ መስጠትና ባለሀብቶች ኢንቨስት በሚያደርጉበት ጊዜ መበርታት በሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ላይ በደንብ ማበረታትና ቅቡልነት እንዲኖረው ማስረዳት ስለሚጠበቅብን በእሱ ላይ እየሰራን ነው::

በክልል ደረጃ ክልል ላይ ያሉ ተቋማትን በተለይ ዩኒቨርስቲዎችን በመጠቀም የካፒታል ገበያ ጽንሰ ሃሳብ ምንድን ነው? የሚለውን በደንብ አድርጎ አጉልቶ ማህበረሰቡ እንዲገነዘበው ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ለመሥራት በ2017 በጀት ዓመት ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅብናል:: ይህም እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ ነው:: ነገር ግን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የቁጠባ ሃሳብ የምታስተምረው አይደለም:: ስለዚህ አንዱ ምቹ አጋጣሚ የመቆጠብና እንደ እቁብና እድር የመሳሰሉ ጉዳዮች መኖራቸው ነው::

እቁብ፤ እድር፤ በባሕላችን ያለና የነበረ ነው:: ይህንን የነበረንን ባሕል እና ግንዛቤ በተሻለ መልኩ ወደ ካፒታል ገበያ የማቀራረብ ጉዳይ እንጂ ከዜሮ ተነስተን እቁብ ወይም እድር ማለት ይህ ነው በማለት አናስተምርም::

በባንኮች ላይ ብዙ ሰው ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተረድተናል:: ያን ያማከለ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚደረግበት ሁኔታ እንዴት አድርገን እናሰራለን? የሚለው ላይ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰራን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ተቋማት ከተመዘገቡ በኋላ የካፒታል ገበያ ኃላፊነት ምንድን ነው? የኢንቨስተሮችን መብትና ደህንነትስ ከማስጠበቅ አኳያ ተቋሙ ሚናው ምንድን ነው?

ዶክተር ብሩክ፡– ማንኛውም ድርጅት ወደ ካፒታል ገበያ መጥቶ ገበያው ላይ ገንዘብ እና ሀብት ከማሰባሰቡ በፊት ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ:: እነዚህን መስፈርቶች ካሟላ በኋላ ወደ ገበያው ይገባል:: መስፈርቶችን አሟልቶ ፈቃድ ተሰጥቶት ያን ከጨረሰ በኋላ በየጊዜው የሚጠበቅበት እና የሚያሳውቃቸው መስፈርቶች አሉ::

ለምሳሌ በየስድስት ወሩ ፋይናንሻል ሪፖርት ለማህበረሰቡ ማቅረብ አለበት:: ይህን ካላቀረበ ቅጣትና ከፍተኛ የሆነ የዲስፕሊን ርምጃ ሊወሰድበት ይችላል:: ወደ ገበያው የሚገባው እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን ለመፈጸም ቁርጠኝነት ተላብሶ ነው::

ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ደግሞ (exposer plat form) በሚል የሚያዘጋጀው አለ:: ድርጅቱ ስድስት ወሩ እንዳለቀ በሚሰጠው ጊዜ ይህን ፋይናሽያል ሪፖርቱን አክሲዮኑን ለገዛው ሰው ማሳወቅ አለበት:: በዚህም የፋይናንስ ጤንነቱን ማሳየት አለበት:: እንደ መሥሪያ ቤት ይህንን ቁጥጥር እናደርጋለን:: ድርጅቱ ላይ ስድስት ወር ከመድረሱ በፊት የተለያዩ ለውጦች ቢኖሩ ለምሳሌ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢነሳ፤ ቦርድ ላይ ሰው ቢነሳ፤ ኮንትራት ያለው ከሆነ ለድርጅቱ የወደፊት ትርፋማነት አመላካች ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳወቅ አለበት::

በምን ያህል ጊዜ የሚለው ሁሉ በመመሪያችን በግልጽ ተመላክቷል:: ስለሆነም ባለስልጣኑ የገበያ “ሰርቪላንስ” ዲፓርትመንት ስላለው ጊዜውን ጠብቆ እያንዳንዱን ድርጅት ለማህበረሰቡ ማሳወቅና አለማሳወቁን ቁጥጥር ያደርጋል:: በቁጥጥር ሂደቱ ላይ በመመስረት ያልፈጸመ ድርጅት ካለ አስፈላጊው የሆነ አስተዳደራዊ ርምጃዎችን እንወስዳለን:: የካፒታል ገበያ እስካለ ድረስ ቁጥጥር የምናደርግበት ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ማጭበርበሮችና አሻጥሮች እንዳይኖሩ ባለስልጣኑ ትክክለኛ የሆነ መረጃ ከማግኘት አኳያ ምን ዓይነት ስልቶችን ይጠቀማል?

ዶክተር ብሩክ፡- ለእኛ ትልቁ ሥራ የሚሆነው አሻጥር እንዳይፈጠር ማድረግ ነው:: ከተፈጠረም በአዋጅ በተሰጠን ሥልጣን መሠረት አስፈላጊውን የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ እናደርጋለን:: በካፒታል ገበያ ውስጥ የሚያጭበረብሩ አካላት ምን ዓይነት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በግልጽ ተመላክቷል::

የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ የእስር ቅጣት እንደሚወሰድባቸው አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል:: ስለዚህ ወደ ካፒታል ማርኬት የሚመጡት ድርጅቶች ይህን በግልጽ ተረድተው ነው:: ነገር ግን ችግሮች አይመጡም ማለት አይቻልም፤ ይመጣሉ:: ለምሳሌ የውስጥ አዋቂ መረጃ ያለው ሰው መረጃውን ተጠቅሞ ገበያው ላይ ትክክኛ ያልሆነ ትርፍ ቢያገኝ የምንቆጣጠርበት የራሱ የሆነ አሰራር ስላለ በዚያ መሠረት ቁጥጥር እናደርጋለን::

ከዚያ ባለፈ ግን የእኛ ትልቁ አጋር የምናደርገው የምርመራ ጋዜጠኞችን ነው:: ችግር ሲኖር የምርመራ ጋዜጠኞች ምርመራ አድርገው መንስኤውን ለይተው ችግሩን ለማህበረሰቡ ያሳውቃሉ:: እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች በምናገኝበት ጊዜ ፈጣን ርምጃ እንወስዳለን:: ለዚህም ከብሉምበርግ ጋር በመተባባር 50 ጋዜጠኞችን በመምረጥ የፋይናንሻል ጋዜጠኝነት ላይ ከመስከረም ወር ጀምሮ ስልጠና ለመስጠት እየሰራን ነው::

ይህም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ወጥቶበት የሚከናወን ነው:: ይህን የተደረገበት ዋና ምክንያት ሁሉንም መከታተልና ስለሁሉም መረጃ ተቋሙ ብቻውን ሊደረስበት ስለማይችል የፋይናንሽል ጋዜጠኝነት ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞች ችግሩን ነቅሰው እንዲያወጡ በር የሚከፍት በመሆኑ ነው::

ከዚያ ባለፈ የውጭ ኦዲተሮችን በአጋርነት እንጠቀማለን:: የውጭ ኦዲተሮች የድርጅቶችን ሂሳብ በርብረው፣ አይተው እና ፈርመው የሚያስቀምጡት ሰነድ ስላለ እሱ ሰነድ አንዱ የቁጥጥር መንገድ ነው:: ኦዲተሮች ትክክለኛ የድርጅቱን አሁናዊ ሁኔታ የሚያስቀምጥ መሆኑን ስለሚገልጹ መረጃውን ለካፒቲል ገበያ ማሳወቅ አለባቸው:: ስለዚህ ድርጅቶችን የምንቆጣጠርባቸው የተለያዩ ማዕቀፎች አሉ:: በባለስልጣኑ ጭምር ምርመራ ላይ የተቋቋመ ቡድን አለ::

በተጨማሪም በአዋጅ ያልተሰጠን መብት ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ድርሻ የያዙ አሉ:: ስለዚህ በተናበበ መንገድ ለማድረግ ከፍትህ ሚኒስቴር፤ ከፌዴራል ፖሊስ፤ ከፋይናንስ ደህንነት፤ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ታስክ ፎርስ (ግበረ ኃይል) አቋቁመን ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ ገብተናል::

ስለዚህ ገበያው ላይ ያሉ የማጭበርበር ሁኔታዎች ሲኖሩ አንደኛው ያለውን መረጃ ለሌላኛው እንዲያጋራ እርስ በርስ በመተባበርና በመተጋገዝ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ የምንቀያየርበት አሰራር ተፈጥሯል:: የፍትህ ሚኒስቴርም ክስ የመመስረት መብት ስላለው እነሱን እየረዳን ኢንፎርሜሽን እያቀበለን በዚያ ላይ ተመስርተን አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚጣልባቸው መንገዶች ተዘርግቷል::

አዲስ ዘመን፡- ሀገራችን የስቶክ ማርኬት ወይም የካፒታል ገበያ ውስጥ መግባቷ ምን ታተርፋለች? እስሁን ባለመግባቷስ ምን አጣች?

ዶክተር ብሩክ፡- የወደፊቱን ማየትና በዚያ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መነጋገር የተሻለ ነው:: ምክንያቱም አሁንም ቢሆን ብዙ ዕድሎች ስላሉ ስለእሱ መነጋር የተሻለ ነው:: የካፒታል ገበያ ትልቁ ጠቀሜታ ዕጥረት ያለበት የፋይናሻል ሀብትን በተቻለ መጠን ከተጠቀምን ትልቅ ጥቅም የሚያመጣ እና የተሻለ ቦታ ላይ የሚያደርስ ነው ::

የፋይናንሽያል ሀብት ሁልጊዜ በጣም ስለሚያንስ አቅርቦትና ፍላጎት አይጣጣምም:: ስለዚህ ባለው አቅርቦት ለኢኮኖሚው ትልቅ ቦታ እንዲኖረው ኢንቨስት ማድረግ ላይ የሚመከር ስለሆነ የካፒታል ገበያ ትልቁ ሚናው ይህ ነው:: ከማህበረሰቡ ገንዘብ ተሰብሰቦ የኢቨስትመንት እቅዱ ታይቶ ወደ ኢኮኖሚው በሚሄድበት ጊዜ የትኛውም ዘርፍ የኢኮኖሚ ትርፍ ሊያስገኝ ወደሚችል ዘርፍ መሄድ እንዲችል ማስቻል ነው::

አትራፊ የሆኑ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከባንክ ብድር ውጭ ሌላ አማራጭ እንዲያገኙ ያስችላል:: ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሥራ እድል አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው:: ስለሆነም በኢትዮጵያ የካፒቲል ገበያ መጀመሩ በኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት የሚፈጥር እና ለእድገቱም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው ::

አዲስ ዘመን፡- የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋት በተለይም ብዙ ቦታ የሚጀመረው የማኑፋክቸሪንግ ዘረፍ እንዲያድግ ባለስልጣኑ ምን ዓይነት ድጋፍ አለው?

ዶክተር ብሩክ፡- አንድ ሰው በቀጥታ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሲሰማራ የቢዝነስ እቅድ በተገቢው ሁኔታ በማዘጋጀት፤ የፋይናሽያል ፕሮጀክቱንና ፊዚቭል ጥናቱን ሰርቶ ተደራጅቶ ገበያው ላይ መጥቶ ያለ ምንም ኮላተራል ለማህበረሰቡ ሃሳቡን ሽጦ ገንዘብ ማግኘት ይችላል:: የካፒታል ገበያ ያመጣው ለውጥ ይህን ነው:: አንድ ማኑፋክቸሪንግ ሥራ ላይ መሰማራት የሚችል አካል ባንክ ቢሄድ የመጀመሪያ የሚጠየቀው ኮላተራል ነው::

በካፒታል ገበያ ማቀፍ ግን እኛ ያስቀመጥናቸው መስፈርቶች እስካሟላ ድረስ ማሳመን የሚጠበቅበት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን አይደለም፤ ባንኩን አይደለም:: ኢንቨስት የሚያደርገውን ማህበረሰብ ነው:: ኢንቨስት የሚያደርገውን ማህበረሰብ ኪሳራ እወስዳለሁ ሃሳቡ ጥሩ ነው፤ የመሳካትና ያለመሳካት ዕድሉ 50 በ50 ነው፤ ግን ግድ የለም ዕድሉን ልይ በማለት 10 ሺህ ብር ኢንቨስት ሊያደርግበት ይችላል::

በፊት እንደዚህ ዓይነት ሥነ ምህዳር አልነበረም:: አሁን ግን ትላልቅ ራዕይ ላላቸው ሰዎች 120 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ላይ ተማምነው የሚፈልጓቸውን ሃሳቦች ሕግና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ መመሪያው ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እስካሟላ ድረስ ገበያው ላይ መጥቶ ማሳመን የሚጠቀምበት ማህበረሰቡን ነው::

ማህበረሰቡ ካመነበት ኢንቨስት ያደርግበታል:: የተመሰረቱ ድርጅቶች ማለትም ማኑፋክቸሪንግ ካምፓኒዎች በ10 ዓመት የሚከፈል ረጅም የብድር ሰነድ መሸጥ ይችላሉ:: በሌላ በኩልም 30 እና 40 በመቶ የራሳቸውን ድርጅት ሼር ሸጠው ተጨማሪ ፋይናንስ አምጥተው ማስፋት ይችላሉ:: ይህን ሁሉ ከዚህ በፊት ያልነበረ ነው::

ይህንን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ብቻ ሳይሆን የግብርና ዘርፉ ጭምር ቱሪዝም፤ ማዕድን፤ ሁሉ ይጠቀሙበታል:: የውጭ ሀገር መንግሥታት የብድር ሰነድ ሽጠው መሠረተ ልማታቸውን ይገነባሉ:: የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲገነባ ሁላችንም ቦንድ ገዝተናል:: ቦንዱ የብድር ሰነድ ነው:: ስለዚህ በግድቡ ላይ ሰነድ በመግዛት የብድር ዐሻራችን አስቀምጠናል:: ስለዚህ መስፈርቱን የሚያሟሉ ድርጅቶች መስፈርቱን እስካሟሉ ድረስ ሰነድ ሽጠው ገንዘብ የሚሰበስቡበት መንገድ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ዜጎች ሃሳባቸውን የሚሸጡበት እንደመሆኑ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ላይ ምን ታስቧል? የሕግ ጥበቃስ አለው?

ዶክተር ብሩክ፡– የአዕምሮ ንብረት ጥበቃን በተመለከተ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ አለ:: ይህን የሚያስፈጽመው ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው:: ከእኛ ጋር በተያያዘ በቀጥታ አንድ ድርጅት ወደ ገበያ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሃሳብና ሀብት የእኔ ብቻ ነው የሚል አካል ካለ ያንን ሀብት ቁጥጥር ከሚያደርግ ተቋም የሚያስፈልገውን መረጃ ይዞ መምጣት አለበት:: እኛ ግን ስለአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ፈቃድ መስጠት ወይም የመቆጣጠር ኃላፊነቱ የለንም::

ነገር ግን የሚጠቅመው ሃሳብ የሚፈጥሩ ስታርትአፕ ላይ የሚጠቅመው አድገው ጥሩ ቦታ በሚደርሱበት ጊዜ የካፒታል ገበያ ኢንቨስተሮቹ ራሳቸው ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበት ማቀፍ ይፈጥራላቸዋል:: ኢንቨስተሮች ሼር ሽጠው ለመውጣት ቢፈልጉ እያንዳንዱን ነገር የካፒታል ገበያን የሕግ ማዕቀፎች መሠረት አድርገው ስለሚፈጽሙ ከፍተኛ ዋስትና ያለው ነው::

“ዩኑኮርን” የሚባሉት ድርጅቶች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ማስገኘት ከቻሉ ስታርት አፖች ይፈጠራሉ:: ይህም መጀመሪያ ኢንቨስት ያደረገው ሰው የሚመጣው በካፒታል ገበያ ማዕቀፍ እንደሆነ ስለሚያውቀው ደፍሮ ኢንቨስት ያደርጋል:: ውጤታማ ከሆነ በካፒታል ገበያ ሊወጣ ይችላል::

አዲስ ዘመን፡- በስቶክ ማርኬት ላይ የመንግሥትን ሳይሆን የሀገርን ሉዓላዊነት ያስጠብቃሉ ተብለው የሚጠበቁ ትልልቅ ድርጅቶች በእጅ አዙር ለሌሎች እንዲዞሩ ይደረጋል ይባላልና ከዚያ አንጻር የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

ዶክተር ብሩክ፡- ይህ የኢኮኖሚ ርእዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ እይታ ነው:: ከዚህ በፊት የነበሩ በተለይም በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ከኒዮሊበራሊዝም ጋር በተገናኘ በርካታ ሀገራት ላይ የነበሩ ችግሮች አሉ:: በተለይ የፕራይቬታዜሽን ሥራዎች ላይ ማህበረሰብን በሚጎዳ መንገድ ፕርይቬታይዝድ ተደርገዋል የሚል ትችቶች አሉ::

ጥያቄው ያንን ሃሳብ የያዘ ይመስላል:: በእኛ በኩል ግን የምናየው ገበያው ጤናማ ውድድር ላይ በመመስረት ገበያውን የሚያበለጽግ እና የሚያሳድግ መሆኑን ነው:: የኢትየጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ የሆነው:: ቀዳሚ የሆነውም ተወዳዳሪ ስለሆነ ነው::

ኢትዮ ቴሌኮም ከሳፋሪኮም ጋር ስለሚወዳደር እያደገ መጥቷል:: ስለዚህ ውድድር መጥፎ አይደለም:: ነገር ግን ጥያቄው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በተመለከተ ስለሆነ ፤ የመንግሥት ወደ ግል ይዙሩ አይዙሩ የሚለውን በርካታ የፖሊሲ ሃሳቦችን አይቶ መወሰን ያስፈልጋል። እኔ እስከማውቀው ድረስ በዚህ ስድስት ዓመት ውስጥ አንድም የመንግሥት የልማት ድርጅት ወደ ግል አልዞረም::

ከዚያ በፊት 256 የሚሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ዙረዋል:: ስለዚህ ተነጻጻሪ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል:: የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞራሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ይዞራል ወይም ደግሞ ካፒታል ገበያ ላይ ሼራቸው ይሸጣል ሲባል በአጠቃላይ ካለው የኢኮኖሚክ ፖሊሲ ጋር አንድ ላይ ተቻችሎ የሚሄድ መሆን አለበት::

በተለይ ወሳኝ (ክርቲካል) ያልሆኑት የሆኑት ላይ በከፊል ወሳኝ ያልሆኑት ላይ በሙሉ መንግሥት መግባት የለበትም:: የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተወዳዳሪ ለመሆን ካፒታል ይፈልጋሉ:: ስለሆነም ወደ ግል ዘርፉ ለማዛወር መጀመሪያ የሚታየው እና የሚለየው ሀገራችንን ይጠቅማል ወይም አይጠቅምም የሚለው ነው::

ለዚህም የኢኮኖሚ “ፕራግማቲዝም” የሚለው ፍልስፍና በኢኮኖሚ አስተዳደሩ ላይ ትልቅ እይታ ያለው ነው:: ሀገር የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ ፕራግማቲክነቱ ታይቶ፤ እውነታው ተረጋግጦ ድርጅቶቹ ወደ ግል ይዙሩ አይዙሩ የሚለው ውሳኔ በዚያ መልክ ቢታይ::

አሁን ላይ እንደ ሀገር ክልከላ የሚደረግባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ሁሉ እየተቀነሱ ነው:: በኢንቨስትመንት አዋጁ ላይ ከተፈቀዱት ውስጥ የተከለከሉት በጣም ጥቂት እና በጣት የሚቆጠሩ ናቸው:: ማንም ተነስቶ የፈለገውን ሥራ መሥራት ይችላል:: ባንክ ማቋቋም፤ ኢንሹራስ፤ አየር መንገድ ማቋቋም ይችላል:: ተከለከለ የሚባል ነገር የለም:: በእጅ አዙር ለሌላ የሚሰጥበት አካሄድ ስለሌለ ዋናው ጥንቃቄ ማድረግ እና የፖሊሲውን ሃሳብ ጠብቆ ማስኬድ ላይ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ካፒታላቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቢሮክራሲዎችን በመቀነስ ሂደቱን ጤናማ ከማድረግ አንጻር ተቋማችሁ ምን ያደርጋሉ?

ዶክተር ብሩክ፡- ባንኮች አሁን ባሉበት ሁኔታ ሼር ወይም ባለድርሻ ካምፓኒ ናቸው:: እነዚህ ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን መሸጥ በሚፈልጉበት ጊዜ የሚገዛ ሰው በዋትስ አፕ ወይም በፌስ ቡክ አፈላለግው ይገዛሉ:: ይህን ሁሉ አሰራር የሚያስቆም እና በተማካለ ሥርዓት እንዲገባ የሚያስችል መመሪያ እያወጣን ነው:: ባንኮች የብድር ሰነድ ወይም አዳዲስ የብድር ሰነድ መሸጥ ቢፈልጉ እንዲሁም ተጨማሪ ድርሻ መሸጥ ቢፈልጉ ካፒታል ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ይጠቅማቸዋል::

ምክንያቱም ይህ ቁጥጥር የሚደረገው ኤሌክትሮኒክስ ስለሆነ ‹‹ትራንዛክሽን›› ዋጋው በጣም ባጣም ያነሰ ያደርገዋል:: ስለሆነም ብዙ ሰው እዚህ ላይ እንዲሳተፍ እና ለእነሱ የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል በቶሎ በፍጥነት እንዲያገኙ የሚረዳቸው ይሆናል:: በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ሲሰራበት የነበረው አካሄድ ብዙ ግድፈቶች አሉት:: እነሱን በደንብ አይተን የእርምት ርምጃ መወሰድ ያለበትን በአዋጁ መሠረት እያየን ነው::

ሌሎችን ደግሞ አስቻይ እና “ፕሮሲጀራል” ነገሮች በመመሪያው መሠረት አዘጋጅተናል:: ስለዚህ ለባንኮቹ የእረጅም ጊዜ ብድር ሳይሸጡ በ20 እና በ30 ዓመት የሚከፈል የብድር ሰነድ ሸጠው በገበያ ላይ ገንዘብ አግኝተው ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ማበደር እንዲችሉ የሚፈቀድላቸው ይሆናል:: ከዚያም ባለፈ ለሼር ሆልደሮቹ/ ዋነኞቹ ባለቤቶቹ ደግሞ ሼራቸውን መሸጥ በሚፈልጉበት ጊዜ መንገላታት አያስፈልግም ገበያው ላይ ያሉ ደላሎች አሉ:: እነዚያ ደላሎች ባነሰ የገበያ ዋጋ የንግድ ልውውጡ በታወቀ አግባብ ይረዳቸዋል::

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን::

ዶክተር ብሩክ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

በመልካም አስተዳደር እና ምርምራ ቡድን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You