ራስወርቅ ሙሉጌታ
ቤተሰብ በጋብቻ እንደሚመሰረት ሁሉ በፍቺ ይፈርሳል። በተለምዶ በቤተሰብ ህጋችን ከተቀመጡት ጋብቻ ከሚፈርስባቸው መንገዶች በተጨማሪ ተጋቢዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ሲሉ ህጋዊ ፍቺ ሳይፈጽሙ የሚያደርጉት መለያየት አንዱ ሲሆን ሳይፋቱ ፍቺ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህ ሳይፋቱ ፍቺ ምንም እንኳን በህግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ ባይሆንም እንኳን ውርስ ላይ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አለው።
ለመሆኑ ሳይፋቱ ፍቺ በኢትዮጵያ ህግ እንዴት ይታያል የሚለውን የህግ ባለሙያና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑትን አቶ አቤል ልዑል ሰገድን አናግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
1. ጋብቻና ውጤቶቹ
በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ መሰረት ጋብቻ በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ሊፈፀም ይችላል። እነሱም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሐይማኖት እና በባህል መሰረት የሚፈፀሙ የጋብቻ አይነቶች ናቸው ሲል አንቀፅ አንድ ያስቀምጣል። በተጨማሪም ጋብቻ ከላይ በተጠቀሱት በአንዳቸው ሥነ-ሥርዓቶች ቢፈጸም እንኳን ውጤቱም አንድ መሆኑን የዚሁ ህግ አንቀፅ 40 ያትታል። ጋብቻ በተጋቢዎቹ ላይ ሁለት ዓይነት ውጤት ይኖረዋል።
የመጀመሪያው በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት ሲሆን፤ በስሩም የመከባበር፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ፣ ቤተሰብን በጋራ የማስተዳደር እና በጋራ አንድ ላይ የመኖር ግዴታዎችን ያቅፋል። ሁለተኛው ውጤት ደግሞ ጋብቻ በተጋቢዎች ንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት ነው። ይህም ተጋቢዎች ጋብቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ በግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ እና በስጦታ በየግላቸው ያገኙዋቸው ንብረቶች የግል ንብረታቸው ሆነው ሲቀሩ ከዚህ ውጪ ያሉ ንብረቶች በሙሉ የጋራ ንብረት ይሆናሉ።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ባህላዊ፣ ሰዋዊ እና ፖለቲካዊ መብቶችን ያፀደቀች ሲሆን፣ በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 34 ስር ቤተሰብ ዓለምአቀፋዊ መብቶችን ባማከለ ሁኔታ ተገልጿል። በዚህም መሰረት አንቀጹ ቤተሰብ ለአንድ ማህበረሰብ ሁነኛ ምንጭ ነው በማለት ያስቀምጠዋል።
በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አነቀፅ 5 ስር ህገ መንግስቱ ለሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ፍ/ቤቶች የቤተሰብ ጉዳይን እንዲያስተናግዱ ቢፈቅድም የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 322 እና የክልል የቤተሰብ ህጎች ቤተሰባዊ ጉዳዮች ሊታዩ የሚችሉት በፍ/ቤት ስልጣን ስር ነው በማለት አትተዋል። ስለ ጋብቻ እና ውጤቶቹ ይህን ያህል ካልን በመቀጠል ደግሞ ጋብቻ የሚፈርስባቸውን መንገዶች እንመልከት።
2. ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶች
ጋብቻን ለመፈፀም መከተል የሚገቡ ሥርዓቶች እንዳሉ ሁሉ ለማፍረስም ሥርዓቶች አሉት። የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ አንድ ስር እንደሚያመለክተው ጋብቻ የተፈፀመበት ሥርዓት ማናቸውም አይነት ቢሆን የጋብቻው መፍረስና የሚያስከትለው ውጤት አንድ አይነት ነው።
ምንም እንኳን የጋብቻ ፅንሰ ሃሳብ አንድ ወንድና ሴትን በትዳር እስከ ህልፈተ ህይወታቸው በፍቅርና በምርጫ ማስተሳሰር ቢሆንም በተግባር ግን ሁል ጊዜ ተፈፃሚ አይሆንም፤ ምክንያቱም ጋብቻ በብዙ ምክንያቶች ሊፈርስ ስለሚችል። እነዚህም ምክንያቶች በሁለት ሲከፈሉ የመጀመሪያው በህጉ አሰራር መሰረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተጋቢዎች ድርጊት ነው። (ይህ ሁለተኛው መንገድ ፍቺ ይባላል) በህጉ አሰራር ጋብቻ የሚፈርሰው የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 75 (1 እና 2) መሰረት በሚከተሉት መንገዶች ነው።
• ከተጋቢዎች አንዱ ሲሞት
• ከተጋቢዎች አንዱ ላይ በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ
• ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች አንዱ በመጣሱ ምክንያት በህግ መሰረት ጋብቻው እንዲፈርስ ሲወሰን ናቸው። ለምሳሌ ነፃ እና ሙሉ ፍቃድ አለመኖር፣ ተጋቢዎቹ 18 ዓመት ካልሞላቸው እና የስጋ ዝምድና ካላቸው ወ.ዘ.ተ የሚሉ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ ከአንቀፅ 6 እስከ 16 ድረስ የተቀመጡ ናቸው።
በተጋቢዎች ድርጊት ጋብቻ የሚፈርሰው ደግሞ በፍቺ ነው። ይህም ሁለት አይነት መንገዶች አሉት፡-
1. በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 77 እስከ 80 መሰረት ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት የወሰኑ እንደሆነ የፍቺ ስምምነታቸውን እና ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤት በጽሁፍ ለፍ/ቤት በማቅረብ ፍቺው እንዲፀድቅላቸው ሲጠይቁ ይህ በስምምነት ለመፋታት የሚቀርብ ጥያቄ ይባላል። በተጨማሪም ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት በሚያቀርቡት ጥያቄ ላይ ለመፋታት የወሰኑበትን ምክንያት እንዲገልጹ አይገደዱም። ነገር ግን ተጋብተው ስድስት ወር ያልሞላቸው ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት አይፈቀድላቸውም።
ፍርድ ቤቱም የፍቺ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ይመክራል፤ ሃሳባቸውን ካልቀየሩ ግን ከሶስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ባልና ሚስት ሃሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ጀምሮ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን እንደገና ማንቀሳቀስ ይችላሉ። ፍርድ ቤቱ የፍቺ ውሳኔ በሚያስተላልፍበት ጊዜ የባልና ሚስት ነፃ ፈቃድና ፍላጎት መሆኑን፤ እንዲሁም ስምምነቱም ከሕግ እና ሞራል ጋር የማይቃረን መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ነው።
2. በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 81 እስከ 84 መሰረት ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት በመሆን ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ (ይህ ደግሞ የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ ይባላል)። በዚህ አይነት ፍቺ ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት በመሆን የፍቺ ጥያቄ ሲያቀርቡ ፍቺ ለመጠየቅ ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ መግለጽ ይችላሉ።
ፍርድ ቤቱም የፍቺ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ይመክራል፤ ጊዜያዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ስለሚተዳደሩበት እና ስለሚኖሩበት ሁኔታና ቦታ፣ ስለልጆቻቸው አጠባበቅ፣ እንዲሁም ስለንብረታቸው አስተዳደር ትዕዛዝ ይሰጣል፤ ሃሳባቸውን ካልቀየሩ ግን ባለትዳሮቹ በመረጧቸው ሽማግሌዎች አማካይነት ጉዳያቸውን በዕርቅ እንዲጨርሱ ሊጠይቅ ይችላል።
ነገር ግን አሁንም ሃሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ ከሶስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ባልና ሚስት ሃሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤቱ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል። በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ከፍቺ በኋላ ፍቺው ስለሚያስከትለው ውጤት እንዲስማሙ ባልና ሚስትን ይጠይቃቸዋል፤ መስማማት ካልቻሉ ግን ፍርድ ቤቱ ራሱ የፍቺ ውጤቱ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል። በመጨረሻም ከባልና ሚስት አንዱ ለፍቺው ምክንያት ከሆኑ በሌላኛው ተጋቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በዳዩ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፍል ሊወሰን ይችላል።
3. ሳይፋቱ ፍቺ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ
3.1 በህግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ
የዚህ አይነት ፍቺ የሚያትተው በሦስቱም የጋብቻ ሥርዓቶች የተፈፀመ ጋብቻ የሚያበቃው በፍርድ ቤት ሲቋጭ ነው። የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በምዕራፍ አራት አንቀፅ 78 እና 82 በህግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ አካሄዶቹንና ስልጣን ባለው ፍ/ቤት መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። ይህም ተጋቢዎቹ ከሁለቱ የፍቺ መንገዶች በመረጡት መንገድ መፋታት ሲወስኑ ፍቺውን የመወሰን ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት መሆኑን ያትታል። በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃርና ከሌሎች ሀገሮች ልምድ በመቅሰም በህጉ ከተቀመጡት የፍቺ አይነቶች በተጨማሪ ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶች ደሞ የሚከተሉት ናቸው።
3.2 ሳይፋቱ ፍቺ
ሳይፋቱ ፍቺ ማለት በህግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ ሳይሆን በተግባር የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይጠብቁ የሚደረግ መለያየት ነው። ይህም ማለት ሳይፋቱ ፍቺ ህጉ ያስቀመጠውን የፍቺ ሥነ-ሥርዓት ሳይከተል እንዲሁም የፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ሳይኖረው በተጋቢዎች ስምምነት ብቻ የሚደረግ የፍቺ አይነት ነው። የዚህ አይነት ፍቺ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ቦታ ያልተሰጠው ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ እስከሰጠበት ድረስ የተከለከለ የፍቺ አይነትም ነበር።
ሳይፋቱ ፍቺ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ወይም የተደረገው የጋብቻ ውጤቶች መቆም ነው። በአብዛኛው ጋብቻ ሲኖር ግላዊ እና ንብረታዊ ውጤቶች አብረው ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፤ እንዲሁም ጋብቻ ሲፈርስ እነኚህ ውጤቶች አብረው እንደሚቆሙ ይታወቃል። ስለዚህ በህጉ የሚታመነው ጋብቻ ከነውጤቶቹ የሚቋረጠው በህግ አግባብ በሚደረግ ፍቺ ነው።
የሳይፋቱ ፍቺ ፅንሰ ሃሳብ የሚያትተው የጋብቻ ምስክር ወረቀት መኖር በራሱ ብቻ ጋብቻ መኖሩን አያመለክትም ነገር ግን ለጋብቻ መኖር ግላዊ ውጤት በጣም አስፈለጊ ነው። ስለዚህ ጋብቻ በህግ አግባብ ሳይፈርስ ቢቀርም እንኳን ግላዊ ውጤቱን ካጣ በተግባር ፈርሷል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም የጋብቻ ግላዊ ውጤት ለንብረታዊ ውጤት መኖር መሰረታዊ ነው። ስለዚህ የጋብቻ ግላዊ ውጤት መቋረጥ ከጋብቻ በፍ/ቤት በፍቺ ከመቋረጥ ያልተናነሰ ውጤት አለው በማለት ያትታል። ይህንንም ምክንያት በመቀበል ቀጥሎ እንደምናየው የ.ፌ.ጠ.ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ አስተላልፎበታል።
3.3 የፌ.ጠ.ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መ/ቁ.20938
የዚህ ክርክር ጭብጥ ሃሳብ አመልካች (ሁለተኛ ሚስት) እና መልስ ሰጪ (የመጀመሪያ ሚስት) አንድ ሰውን በተለያየ ጊዜ አግብተው የነበረ ሲሆን ባለቤታቸው በሞተ ጊዜ የወራሽነት መብት ላይ እኔ ነኝ ሚስት በሚል አለመስማማታቸው ነው። የመጀመሪያ ሚስት ከሟች ጋር በ1966 ጀምሮ በትዳር ሲኖሩ ቆይተው 1985 ዓ.ም ህጋዊ ፍቺ ሳይፈፅሙ ተለይተው የነበረ ሲሆን፤ ሁለተኛ ሚስት ደግሞ 1987 ላይ ሟችን አግብተው እየኖሩ ሟች ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ጊዜ 1989 ዓ.ም ድረስ አንድ ላይ ቆይተው እንደነበር አስረድተዋል።
በዚህም ሁኔታ በማድረግ የፌ.መ.ደ.ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ሚስት ከሟች ጋር ህጋዊ ፍቺ ስላልፈፀሙ ሟች እስከሞቱበት ድረስ ህጋዊ ሚስት እንደሆኑ አትቷል። ሁለተኛዋ ሚስት ይግባኝ ቢሉም የፌ.ከ.ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን አጽንቷል።
ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከሁለቱ ሚስት ነን ባዮች መካከል ውርሱ የሚገባትን ለመለየት ጋብቻ መኖሩን፣ የጋብቻ ውጤቶች መኖራቸውንና ከሟች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ከግምት አስገብቷል። በዚህም መሰረት የአሁኗ መልስ ሰጪ በ1966 የተጋቡትን የጋብቻ ውል ስታቀርብ አመልካች ደግሞ 1987 ከሟች ጋር ጋብቻ መፈፀሟን የሚያሳይ የጋብቻ ምስክር ወረቀት አቅርባለች በዚህም ምክንያት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ እንደሚያትተው ጋብቻ ግላዊና ንብረታዊ ውጤቶች አሉት በሚለው መሰረት ሟች ከመልስ ሰጪ ጋር 1985 ዓ.ም ተጣልተው መልስ ሰጪ ወደ አዲስ አበባ ሟች ደግሞ አመልካችን አግብተው ወደ አጋሮ መሄዳቸውን ተመልክቶ በማስረጃም ተረጋግጧል። ስለዚህም ችሎቱ ከዚህ መዝገብ የተረዳውን እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-
“የአሁኗ መልስ ሰጪ ምንም እንኳን ከሟች ጋር ቀደም ብሎ የተፈፀመ ጋብቻ የነበራቸው ቢሆንም በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በነበረው ጋብቻ መቀጠል አለመቻላቸውንና ሁለቱ በየፊናቸው የየራሳቸውን ህይወት መጀመራቸውን ነው”።
በተጨማሪም ሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዳተተው ምንም እንኳን የመልስ ሰጪ እና የሟች ጋብቻ በፍቺ ባይፈርስም ጋብቻው የሚያስከትለው ግላዊና ንብረታዊ ውጤቶች ግን ተቋርጠዋል፤ ይህንንም ሁለቱም ተለያይተው የየራሳቸውን ህይወት መጀመራቸውን ያሳያል። ስለዚህም ምንም እንኳን ጋብቻው በፍርድ ቤት ፍቺ ባይቋረጥም የጋብቻው ግላዊ ውጤት መቋረጥ በግልጽ ስለሚታይ ጋብቻው በፍቺ ተቋርጧል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
3.3.1.የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ፤
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 20938 ሰጥቶት በነበረው አስገዳጅ ውሳኔ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2012 ዓም ‹‹የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን ነው›› በማለት ሽሮታል።
ለውሳኔው መሻር ምክንያት የሆነው፤ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ወደ ጎን በመተው፣ ከሕግ አውጪ ዓላማ ውጪ በሆነ መልኩ ባልና ሚስት ፍቻቸውን በፍርድ ቤት መፈጸማቸው ሳይረጋገጥ፣ የሁለቱን ተጋቢዎች የንብረት ክፍፍልና የሕፃናት ጉዳይ ዓይቶ ተገቢውን ውሳኔ ሳይሰጥበት፣ ተጋቢዎች ተለያይተው በመኖራቸውና የየራሳቸውን ሌላ ሕይወት በመጀመራቸው ‹‹ጋብቻቸው ፈርሷል›› ብሎ ትርጉም መስጠቱ የሕጉን ዓላማ የሳተ መሆኑን፤ በሌላ መልኩ እንደዚህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ፣ ተጋቢዎች በቸልተኝነት ጋብቻቸውን ከፍርድ ቤት ዕውቅና ውጪ በፍች መልክ እንዲያቋርጡ መንገድ የሚከፍትና ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ መሆኑን እንዲሁም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 እና 82 ከተቀመጡት ድንጋጌዎችን በማለፍ አራተኛ የፍቺ ምክንያት ማስቀመጡ መሆኑንም ገልጿል።
በመሆኑም የሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ ውሳኔ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር፣ በአንቀጽ 51 ለፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር፣ በአንቀጽ 79(3) ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ ከሚሉት ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ ሆኖ ስላገኘው፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጉባዔው በሙሉ ድምፅ በመወሰን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84(1) እና በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3(1) ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን ቀርቦ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበልና ይሁንታ በመስጠት አስገዳጁ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን ሰርዞ ጋብቻ ሊፈርስባቸው ከሚችሉ ሦስት ምክያቶች ውጪ ዝም ብሎ መለያየትና መቆየት ጋብቻን ሊያፈርስ እንደማይችል ውሳኔ ሰጥቷል።
5.መደምደሚያ
ጋብቻ ከሚቋረጥባቸው መንገዶች መካከል ፍቺ እንዱ እና ዋነኛው መሆኑን የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ያትታል። ከፍቺና ህጉ ከሚያስቀምጠቸው ሌሎች ምክንያቶች በቀር ጋብቻ አይፈርስም።
የፌ.ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ አዋጅ ቁ.454/2005 እንደሚያትተው በፌ.ጠ.ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚተላለፉ ውሳኔዎች አስፈላጊውን ቴክኒካዊና አካሄዳዊ ሥነ-ሥርዓቶችና ግዴታዎች ካሟላ እንደ ህግ ይቆጠራል። በዚህም መሰረት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመ/ቁ.20938 በቀን 11/08/99 ዓ.ም ባሳተላለፈው ውሳኔ ምንም እንኳን ጋብቻ በፍርድ ቤት በሚደረግ ፍቺ ባይቋረጥም ግላዊ ውጤትን ካጣ እንተቋረጠ ይቆጠራል ሲል አትቷል።
ስለዚህ ምንም እንኳን በሀገራችን የቤተሰብ ህግ ስለ ሳይፋቱ ፍቺ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ባይኖርም በፌ.ጠ.ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረት የአንድ ጋብቻ ግላዊ ውጤት ከተቋረጠ ጋብቻው እንደተቋረጠ ይወሰዳል፤ ይህም ማለት ሳይፋቱ ፍቺ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ ስር እንደ እንደ የፍቺ አይነት ይቆጠራል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 20938 ሰጥቶት በነበረው አስገዳጅ ውሳኔ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2012 ዓ.ም ‹‹የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን ነው›› በማለት ሽሮታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013