ዳግም ከበደ
ወጣቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ትኖራለች። ለአባት እና እናቷ ብቸኛ ልጅ ነች። ቤተሰቦቿ ባለፀጎች ባይሆኑም በኑሯቸው ግን ደስተኞች ናቸው። በትላልቅ እና ውብ ዛፎች ተከቧል፤ አካባቢውን አልፎ የሚፈሰው ወንዝ የሚያሰማው ድምጽም አካባቢን ተጨማሪ ልዩ ውበት አጎናጽፎታል።
መኖሪያ ቤታቸው በእንጨት የተሰራና ባለ አንድ መኝታ ቤት ነው። ወጣቷ ግን ቤቱን አትወደውም። በጣም አንሶባታል፤ ውብ አልሆነላትም።
ከቤታቸው ፊት ለፊት ካለው ተራራ ላይ የሚገኘውን የቤተመንግስት /ካስትል/ ቅርፅ ያለውን ቤት ሁሌም በርቀት ትመለከተዋለች፤ በርቀት ስታየው ትደሰታለች። ከምንም በላይ የወርቅ ቀለም ያለውን የቤቱን መስኮት ወዳዋለች፤ ይህ ሁሉ ቤቷን እንድትጠላ አደረጋት።
የተራራው ላይ ቤትን ለመጎብኘት ብትፈልግም፣ ቤተሰቦቿ እንደ አይናቸው ብሌን የሚጠብቋት ልጃቸው ብቻዋን ርቃ እንድትሄድ ስለማይፈልጉ ጥያቄዋ ሊመለስላት አልቻለም። ቤቱን ግን ያደገችበትን ቤት እንድትጠላ እያደረጋት መጣ። በተለይ የሚያንፀባርቀው መስኮት የራሷ እንዲሆን ትመኝ ጀመር።
የቤተሰቦቿን ፍላጎት ለማሟላት ብላ ለብዙ ጊዜ አርፋ ተቀምጣለች። እድሜዋ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ግን ቤቱን የመጎብኘት ፍላጎትዋ እየጨመረ መጣ። አድሜዋ ወደ 18 እየተጠጋ ነው ፤ አስተሳሰቧም እየተቀየረ ነው። «አሁን እኔ አድጌያለሁ። በአሮጌ ቤት ውስጥ አልኖርም። መኖር ያለብኝ የወርቅ መስኮት ባለው ቤት ውስጥ ነው» ማለት ጀመረች።
እናቷ የልጇን እያደገች መምጣት መገንዘብ ብዙም ሳትርቅ አካባቢዋን እየተዘዋወረች እንድትጎበኝ ፈቀደችላት፤ ወጣቷ በእዚህ የእናቷ ውሳኔ በእጅጉ ተደሰተች። አካባቢዋን በብስክሌቷ እየዞረች መጎብኘት ጀመረች። አሁንም ቢሆን ግን አካባቢው አላስደሰታትም።
ፍላጎቷ ተራራው ላይ ያለውን «ካስትል» የሚመስል ቤት ሄዶ መጎብኘ ሆነ። እናቷ ርቀሽ እንዳትሄጂ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥታለችና ወደዚያ መሄድ ግን አልቻለችም። ልቧ አሁንም አላረፈም፤ «ልሂድ ወይስ አልሂድ» የሚለውን ስታውጠነጥን ቆይታ ፈራ ተባ እያለች ተራራው ላይ ለመውጣት ወሰነች። ብስክሌቷ ላይ ፊጥ ብላም ጉዞ ጀመረች። መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆንም ብዙ ጥረት አርጋ ተራራው ላይ ደረሰች። ከርቀት ትመለከተው ከኖረችው ቤት ደርሳም መጎብኘት ጀመረች።
ቤቱ ግን እንደጠበቀችው አልሆነላትም። ከርቀት ስትመለከተው እንደነበረው ውብ አልሆንልሽ አላት። በጣም አርጅቷል፤ ቆሽሿል። መስኮቱም ወርቃማ አይደለም፤ ጥቁር መስኮት ነበር፤ አይማርክም።
በተመለከተችው ሁሉ ተገረመች። ታስበው በነበረው አፈረች። ለካ መስኮቱ ወርቃማ መስሎ ይታያት የነበረው ከተራራው ስር ካለው ወንዝ ጋር በገጠመው የፀሀይ ነፀብራቅ ሳቢያ ነበር።
ሜዳው ላይ አረፍ ብላ ማሰብ ጀመረች። ተራራው ላይ ባለው ቤት ለመኖር የነበራት ፍላጎት ብን ብሎ ጠፋ። ቁልቁል ወደ መኖሪያ ቤቷ ተመለከተች። መስኮቱ እንደ ወርቅ ያንፀባርቃል። በአካባቢያቸው ያለው ወንዝ ላይ የወጣው ፀሀይ መስኮቱ እንደወርቅ እንዲያንፀባርቅ እንዳደረገው ተረዳች፤ ፈገግ አለች፤ በምትፈልገው አይነት ቤት ውስጥ እየኖረች መሆኗን ተገነዘበች። የምትጠላው መኖሪያ ቤቷ ውብ መሆኑን ገባት።
ለተሳሳተ ውሳኔ የተዳረገችው ተራራ ላይ ያለውን ቤት ከርቀት ብቻ አይታ ያምራል ብላ በመደምደሟ ነው። በመገረም ስሜትም በብስክሌቷ ሆና ቁልቁል ወደ ቤቷ ወረደች። ለካስ የሚያንጸባርቅ ነገር ሁሉ ወርቅ አይደለም» አለች።
ከታሪኩ መረዳት እንደሚቻለው አርቆ ማሰብ የሚገባ መሆኑን ነው። አዎን! አይታችን ስል ሊሆን ይገባል። የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም ነው የተባለው። እኛ ግን የማናውቀው ሀገር ይናፍቀናል። ለመሆኑ መናፈቅ እንዴት ይከሰታል? የወጡበት፣ የወረዱበት ፣ አብረው የበሉት፣ የጠጡት ፣ የተጫወቱት፣ የተሯሯጡት፣ የሳቁት የፈነደቁት ነው የሚናፍቅ። ያላዩት ፣ያልኖሩት እንዴት ሊናፍቅ ይችላል።
እኛ ግን ያላየነው ሀገር ይናፍቀናል። ባልረባ መረጃ ላይ ተመስርተን የቆምንበትን ንቀን የማናውቀውን እናመልካለን። የሚናፍቀው ምንም የማይታወቅ ሀገር፣ ሰው፣ወዘተ እየሆነ ነው ።
በቂ መረጃ በሌላቸውና ጥቅማቸውን ብቻ በሚያሳድዱ ተራ ደላሎች መረጃ ላይ ተመስርተው ሀገራቸውን ትተው ባእድ ሀገር ሄደው ሀብታም መሆን የሚፈልጉ በርካታ ናቸው። የሚገርመው ደግሞ ይህን ብለው ሄደው ሰዎች ተጎድተው መጥተው እያዩም ሰዎች የማያውቁትን ሀገር እየናፈቁ ናቸው።
መፈለግ ብቻም ሳይሆን ጉዞ ጀምረውም በበረሃው በባህሩ ለሞት ለስቃይ የተዳረጉት ስንቶች እንደሆኑ ማንም አይስተውም። የተባለው ሀገር ደርሰውም እንዲሁ ጭራሸ ባልጠበቁት ስራ ውስጥ ገብተው አመታትን የገፉ ፣ በላባቸው ያፈሩትን ሀብት መቀማታቸው አንሶ ለእስርና ስቃይ የተዳረጉ በርካታ ናቸው።
የሕልም እንጀራ እያሰቡ መኖር ተለምዷል፤ ደፋሮች በዝተዋል ፤ ኑሮ ማለት እግር የቆመበት ነው የሚለው የማይገባቸው በርክተዋል። ከደጁ ሞፈር እየተቆረጠ ሞፈር ግዥ ገንዘብ ይዞ ገበያ የሚወጣን ምን ይሉታል። የኛ እንጀራ ደጃፋችን ላይ እያለ ከሩቅ ለማግኘት እንፈልጋለን።
በውጭ ሀገር ያሉ ዘመዶቻቸው እስኪወስዷቸው ድረስ እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ስንቶች እንዳሉ ሲታሰብ ደግሞ የተስፋ እንጀራ ነገር ያሳስባል። በሀገር ቤት የተገኘውን እየሰሩ ለመስራት እየሞከሩ የውጭውን መጠበቅ የባት ነው፤ መስራት በሚችሉበት አቅም ላይ ሆነው ከውጭ ቀለብ እየተሰፈረላቸው የተቀመጡ ምን ያህል እንደሆኑ ከየአካባቢያችን እንገነዘባለን።
እዚህ አገር ቤት ሰርተው ለመለወጥ ያልሞከሩ ውጪ ሀገር ሰርተው ይሳካላቸዋል ብሎ ማሰብ ያዳግታል። እዚህ ያለው የስራ ሞራል እኮ ነው አብሮ የሚሄደውና እንጀራ ሊያበላ የሚችለው። እዚያም ቁጭ ብለው ዳረጎት ሊጠብቁ ነው።
ሌላው ክፋት ደግሞ አይቶ አለመማር ነው። ብዙ ፈተና ካዩበት ተገፍተው ከወጡበት ባእድ ሀገር ተመልሰው መሄድ የሚፈልጉ ጥቂት አይደሉም። አንዴ አይደለም ፤ሁለቴም አይደለም በተደጋጋሚ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርገው ጠፍተው ተመልሰው ወደ ገፋቸው ሀገር የሄዱ ጥቂት አይደሉም። እነዚህ ወገኖች አሁንም ወደሚያውቁት ሀገር የሚሄዱ ይመስላቸዋል እንጂ ወደ ማያውቁት ሀገር ነው የሚሄዱት። ሰው ወደ ገፋው ሀገር ከሄደ ያን ሀገር አያውቀውማ ማለት ነው ፤ በቃ። እባካችሁ የማታውቁት ሀገር አይናፍቃችሁ! አይታችን ስል ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013