ጌትነት ምህረቴ
በአሁኑ ጊዜ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የጥራት ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።ተገንብተው የሚናዱ ህንጻዎች፤ ተሰርተው ብዙ ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ የሚፈርሱ መንገዶች መኖራቸው ይስተዋላል።አንዳንድ የተገነቡ ቤቶች ጥራት መጓደልም ለነዋሪዎች ስጋት የሚፈጥሩ ሆነዋል፡፡
ይህ የግንባታ ጥራት ችግርም የፌዴራል የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መኖሩን በክትትል አረጋግጧል።ተገንብተው ሳይጠናቀቁ የተናዱ፣ ተሰርተው አገልግሎት ሳይሰጡ የፈረሱ መንገዶችና ህንጻዎች መኖራቸውንም ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
የኢፌዴሪ የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎ እንደገለጹት፤ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተገነቡ ከተማ የማስዋብ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀውና በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተገነቡ የሚገኙና የተገነቡ ቢሆንም በአንጻሩ ደግሞ በየክልሉና በየከተማው የሚሰሩ ግንባታዎች ሳይመረቁ ጥገና ይጠይቃሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባታቸው ሳይጠናቀቁ ይፈርሳሉ።የተወሰኑትም አገልግሎት ሳይሰጡ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፡፡
ይህም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የጥራት ደረጃ ፈታኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ ያሳያል፤ በተለይ የግንባታ የጥራት ችግርን በዘላቂነት መፍታት ካልተቻለ አገርን ለኪሳራ ህዝብን ለእንግልት፤ ሰዎችን ለሞት፤ ንብረትን ለውድመት ይዳርጋል።ስለዚህ ስራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶችና ግብዓት አቅራቢዎች የግንባታ ጥራት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሀላፊነት ይኖርባቸዋል ይላሉ አቶ መስፍን፡፡
ባለስልጣኑ የተጓተቱና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የጥራት ችግር ያለባቸው የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር ከፊሎቹ ህንጻዎቹ ፈርሰው እንደገና እንዲሰሩ፣ የተወሰኑት የኮንትራት ውሉ ተቋርጦ ሌሎች አቅም ያላቸው ስራ ተቋራጮች እንዲገነቧቸውና ቀሪዎቹ ደግሞ በአሰሪውና በተቋራጩ የነበሩ አለመግባባቶች መፍትሄ አግኝተው ግንባታቸው እንዲቀጥሉ ማድረጉን ነው የጠቀሱት፡፡
በተለይ ባለስልጣኑ በዩኒቨርሲቲዎች እየተካሄዱ የሚገኙና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እየተጓተቱ የነበሩ የግንባታ ህንጻዎች ችግሮች መፍትሄ አግኝተው ግንባታቸው እንዲቀጥል ማድረጉን አንስተዋል።ከእነዚህ መካከልም የሰላሌ፣ የሀሮማያና የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
የህግ ማዕቀፎች በአግባቡ ስራ ላይ አለማዋላቸው፤ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች አደረጃጀታቸው ደካማ መሆን፣ ስራ ተቋራጮች የአቅም ውስንነት፣ ብልሹ አሰራርና ሙስና ለጥራት መጓደሉ መንስኤ ከሆኑት መካከል ይገኙበታል።እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት የሚጠበቅባቸው መሆኑንም አቶ መስፍን በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል፡፡
ባለስልጣኑ ከተቋቋመ ወዲህ ባለፉት ሁለት ዓመታት የግንባታዎችን ጥራት በማስጠበቅ ረገድ መጠነኛ ለውጦች መጥተዋል፤ የግንባታ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አምስት የህግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።ለአብነትም ቀደም ሲልም ሆነ በአሁኑ ጊዜ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አዋጅ አልነበረም።አሁን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አዋጅ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊጸድቅ ችሏል።የግንባታ ጥራትን የሚያስጠብቁ የስራ መመሪያዎችና ደንቦች መውጣታቸው ለግንባታ ጥራት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፤ ከአሁን በኋላ በአዋጁ መሰረት ለስራ ተቋራጩ የስራ ሰርተፍኬት መስጠት ብቻ ሳይሆን መንገድም ሆነ ህንጻ በጥራት መገንባት ያልቻለ ስራ ተቋራጭ የስራ ፈቃዱ ይቀማል፤ እንዲሁም ስራ ተቋራጩ የገነባው መንገድም ሆነ ህንጻ አገልግሎት ሳይሰጥ ቢፈርስና ከፍተኛ የጥራት ጉድለት ቢያጋጥመው በህግ ተጠያቂ ይሆናል፤ ወደ ኢንዱስትሪው የሚገባውም ማሽነሪና ብር ያለው ብቻ ሳይሆን በሙያው ውስጥ ያሉትን ባለሙያዎች ይበልጥ ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ የሚያበረታታ ነው።
እንደ አገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የጥራት ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ያሉት በፌዴራል ኮንስትራክሽን ስራዎች ቁጥጥር ባለስልጣን የህንጻ ስራዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር መሀንዲስ በረከት ተዘራ ናቸው። ኢንዱስትሪው በየዓመቱ 60 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱ በጀት ካፒታል የሚያንቀሳቅስ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉ የቁጥጥር ስራዎች አብዛኛው የኮንስትራክሽን ስራዎች በጥቂት ስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች የተያዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም በ2013 በጀት ዓመት 45 የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ህንጻዎች ግንባታ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ቢመደብም ይህን በጀት ከስድስትና ሰባት በማይበልጡ ስራ ተቋራጮችና ተመሳሳይ አማካሪዎች ስራው በብቸኝነት (ሞኖፖላይዝ) የተያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።ይህም ለሙስናና ለጥራት ጉድለት ትልቅ በር መክፈቱንና ከሀብት ክፍፍልም አንጻር አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረውም አመላክተዋል፡፡
ባለስልጣኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት 69 የመንግስት ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ቁጥጥር ማድረጉን አውስተው ባለቤቶች በወቅቱ ተገቢውን ክትትል አለማድረጋቸው፣ ዲዛይንና በመሬት የሚሰራው ስራ የሚጣጣም ያለመሆኑ፤ የስራ ተቋራጮቹ አቅመ ደካማነትና የግንባታ ጨረታ ሂደቱ ብልሹ መሆኑ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ምክንያት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።ጊዜ በተራዘመ ቁጥርም ስራ ተቋራጩ ሆን ብሎ ግንባታው እንዲጓተት ከማድረጉ በተጨማሪ የዋጋ ይስተካከልልኝ የሚል ጥያቄ በማቅረብ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋል።ይህም ለሙስና ለጥራት መጓደል ትልቅ በር ከፍቷል ባይ ናቸው፡፡
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በጊዜ፣ በዋጋ የሚመጣ ለውጥ ተገቢ ባይሆንም ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል ያሉት መሀንዲስ በረከት፤ በጥራት ረገድ የሚስተዋል ጉድለት ግን ገንዘብን ለኪሳራ የሚዳርግ ብቻ ሳይሆን ህንጻው ቢደረመስና ድልድዩ ቢፈርስ የሰዎች ህይወትን ሊቀጥፍና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህን ታሳቢ በማድረግ በግንባታ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ 102 የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በመጓተታቸው ምክንያትም 42 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ መጠየቃቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡የፕሮጀክቶች መጓተት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ጉዳቶችን ያስከትላል።
አንደኛ ፕሮጀክቶቹ ከተመደበላቸው በጀት ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃሉ፤ በብድር የሚሰሩ ከሆነ ተጨማሪ ወለድ እንዲከፈል ያስገድዳሉ፤ ሌላ ብድር ለማግኘትም መሰናክል ይፈጥራሉ።ሁለተኛ ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ ተጠናቀው ይሰጡት የነበረውን ጥቅም እንዳይሰጡ ያደርጋሉ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በቂ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት የሌለባት አገር ናት።እንዲሁም ኢንዱስትሪውና ግብርናው ወደኋላ የቀረ ነው።አገሪቱ እነዚህ ሁሉ ፈርጀ ብዙ ችግሮች እያሉባት ውስን የአገር ሀብት ፕሮጀክቶች በማጓተት የሚባክን ከሆነ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በኢኮኖሚው ላይ ተጨማሪ ኪሳራ ያስከትላል፡፡
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚዘገዩት በስራ ተቋራጩ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር፤ በመንግስታዊ ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ አሰራር፣ ቀና ትብብር አለመኖርና በዕቅዶች የተፈጻሚነት ጉድለት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
“እየለመነ ሳይሆን እየወሰነ የሚሰራ የፕሮጀክት አመራር ያስፈልጋል” ያሉት አቶ መስፍን፤ በአመራርነት የሚመደበው ሰው ፕሮጀክቶችን በጊዜ ከጨረሰ ሽልማት፤ በጊዜው ካላጠናቀቀ ደግሞ ተጠያቂነት እንዲኖር ሙሉ ሀላፊነትና ተጠያቂነትም ጭምር አብሮ የሚሰጥ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁ በግንባታው ጥራት ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ዶክተር መስፍን ገለጻ፤ ፕሮጀክቶችን የሚገነቡ ስራ ተቋራጮች በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው መመረጥ አለባቸው።ከተመረጡ በኋላ ደግሞ በአሰሪው በኩል በውሉ መሰረት አስፈላጊው ሁሉ ሊሟላላቸው ያስፈልጋል።እንዲሁም ስራ ተቋራጮችም በአገራዊ ሀላፊነትና በንጹህ ህሊና ፕሮጀክቶችን ሊሰሩ ይገባል፡፡
ፕሮጀክቶች የመንግስትን ሆነ የግል ድርጅቶችን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ መሳሪያዎች ናቸው የሚሉት አቶ መስፍን ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ የማይጠናቀቁ ከሆነ ተጨማሪ በጀትና ጊዜ የሚፈልጉ በመሆናቸው በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያስከትላሉ ብለዋል፡፡
የታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ የማዳበሪያ፣ የስኳርና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች በመጓተታቸው ተጨማሪ በጀትና ጊዜ በመፍጀታቸው ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሳቸው ይታወሳል፡፡ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ በታቀደለት ጊዜ ቢጠናቀቅና ኤሌክትሪክ ማምረት ቢጀምር ኖሮ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማሻሻልና ለውጭ አገራት በመሸጥ ተጨማሪ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻል ነበር።ሆኖም ግድቡ በመዘግየቱ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ኪሳራ ማስከተሉን የገንዘብ ሚኒስትር መረጃ ያመለክታል፡፡
ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅና የጥራት ችግር ተጨማሪ ወጪ ከመጠየቃቸው ባሻገር በአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላሉ። ፕሮጀክቶች በመጓተታቸውና የጥራት ጉድለታቸው አገሪቱ በፍጥነት አለማደግና ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል እንዳይፈጠርና ለሙስና መስፋፋትም ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለፕሮጀክቶች ጥራት ጉድለትና መዘግየት ዋናው ምክንያት የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር መሆኑን ጠቁመው፤ ለፕሮጀክቶች አመራርነት የሚመደቡ ኋላፊዎች “ልጥቀምህ ጥቀመኝ” በሚል ሳይሆን የሙያውን ስነ ምግባር የሚያከብሩ፣ የፕሮጀክቶች የጥራት ችግርና መዘግየት አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ነው ብለው የሚያስቡ፣ ህሊናና ችሎታው ያላቸው ቢሆኑ ውጤታማ ስራ ይሰራሉ፤ እንዲሁም አቅምን፣ ነባራዊና ተጠባቂ ስጋቶችን ያገናዘበ ዕቅድ መቅረጽም ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የግንባታ ፕሮጀክቶች የጥራት ችግርና መዘግየት ከሚያስከትለው ኪሳራ ለመዳን አሰራርን የሚያቀላጥፍ፣ ፈጣን ውሳኔ መስጠት የሚያስችልና ሙስናን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚከላከል ከተለመደው አሰራር የወጣ አዲስ የፕሮጀክት አስተዳዳር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የሚዘገዩት በመንግስታዊ ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ አሰራር፣ ቀና ትብብር አለመኖር፣ በፕሮጀክት አስተዳደር ችግርና በዕቅዶች የተፈጻሚነት ጉድለት መሆናቸውን ጠቅሰው ፤የፕሮጀክቶች መዘግየት ከሚያስከትሉት ኪሳራ ለመዳን አሰራርን የሚያቀላጥፍ፣ ፈጣን ውሳኔ መስጠት የሚያስችልና ሙስናን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚከላከል ከተለመደው አሰራር በመውጣት አዲስ የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት ፡፡
የፕሮጀክት አስተዳደር ብቃትና ሙያዊ ስነ ምግባር የተላበሰ መሆን ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተገነቡት ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቃቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች በማስፋትም በፕሮጀክቶች መጓተትና የጥራት ጉድለት የሚያጋጥመውን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ማዳን ይቻላል ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
እንዲሁም የፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት በሪፖርት ብቻ ሳይሆን በቦታው በመገኘትም ጭምር ያሉባቸውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት ማበረታታትና ችግሮች ካሉ በወቅቱ መፍታት ያስፈልጋል።የፌዴራል ኮንስትራክሽን ስራዎች ቁጥጥር ባለስልጣንም ፕሮጀክቶች የሚገነቡበት ቦታ ድረስ በመሄድ ለጥራትና ለመዘግየቱ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በአሰሪውና በስራ ተቋራጩ ውይይት እንዲፈቱ ማድረግ ችሏል።በዚህም ሲጓተት የነበረው ግንባታ እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ የመጣባቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በአብነት አነስተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013