ኢያሱ መሰለ
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንድ ሀገር ከመቆሟ በፊት በየአካባቢው በተፈጠሩ ገዢዎች እጅ ስር ነበረች። በ18ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የየአካባቢው ገዢዎች አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት ይህ ቀረው የማይባል የእርስ በእርስ ግብግብ አድርገዋል። በሀገር ምስረታው ሂደት የብዙዎች አስተዋጽኦ እንዳለ ባይዘነጋም በይበልጥ አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሃንስ እና አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የማስተዳደር ጥረት አድርገዋል።
ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ቅርጽ /ካርታ/፣ ከህዝቦቿ የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት ጀርባ የአጼ ምኒልክ የመሪነትና አስተዳደር ፍልስፍና መኖሩ ይታወቃል። አጼ ምኒልክ አንድ ሀገርን ከመመስረት ባለፈ ህዝባቸውን አንድ አድርገው አስተዳድረዋል፤ አገሪቷንም ከወራሪዎች ታድገዋል። የነጮችን የበላይነት በመቀልበስ ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት ሆነዋል።
የአጼ ምኒልክ የአስተዳደር ፍልስፍና በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ሊጫን የነበረውን የባርነት ቀንበር ሰባብሯል። አንገቱን ደፍቶ ለተቀመጠው መላው ጥቁር ህዝብ ስለ ነጻነቱ እንዲንቀሳቀስ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ከዊክፒዲያ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ የማስተዳደር ወይም የመምራት ጥበብ ማለት፤ የማቀድ፣ የማስተባበር፣ የማግባባት፣ የመተግበር፣ የመገምገም፣ አቅጣጫን የማመላከት እና የመወሰን ችሎታን ያካትታል። ከዚህ አኳያ ሲመዘኑ አጼ ምኒልክ የተዋጣላቸው ሲሆኑ፤ በሚያራምዱት የአመራር ፍልስፍናቸውም የነጮችን የበላይነት፤ የጥቁሮችን የበታችነት የሚቀበሉ ሆነው አይገኙም።
አንዳንድ ጊዜ ስለ አመራር የተሰጡም ሆኑ ከመሪ ሚና ጋር የተያያዙ በርካታ ፍልስፍናዊ አተያዮች አሉ። እነዚህ አተያዮችም በተለያዩ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶች ሊሰጡባቸው ይችላሉ፤ ሲሰጡባቸውም ይስተዋላል።
እንደሚታወቀው ዓለም ካፈራቻቸው ፈላስፎች አንዱ አርስቶትል ነው። ሰዎች ከአርስቶትል የፍልስፍና አስተሳሰቦች የቀሰሟቸው ወይም የእርሱን ሀሳብ መነሻ አድርገው የደረሱባቸው እውነታዎች በርካቶች ናቸው። ፍልስፍና የግል እይታ እንደመሆኑ የአርስቶትል የግል ሀሳብም ሁሉንም ሰው ያስማማል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ዋለልኝ እምሩ ‹‹በፍልስፍና መደመም›› በሚለው መጽሃፉ የአርስቶትልን የፍልስፍና ሀሳብ እንዲህ አስቀምጦታል። ‹‹አርስቶትል የባርነት ስርዓት መኖሩ ትክክል መሆኑን ሲናገር ባሪያ መሆን ያለባቸው ዝቅተኛ የሰው ዘሮች እንጂ ግሪካውያን አይደሉም ይላል።
ለአርስቶትል ግሪካውያን ከማንኛውም የሰው ዘር የተሻለ የማሰብ አቅም ያላቸው በመሆኑ መተግበር ከቻሉ ዓለምን ሊገዙ ይችላሉ እስከ ማለት ደርሷል።›› ኽርደርና ሄግል የተባሉ ፈላስፎችም የጀርመን ህዝብን የበላይነት የሚያሳዩ አመለካከቶችን በፍልስፍና ስራዎቻቸው ውስጥ ማንጸባረቃቸውን ዋለልኝ ይጠቅሳል።
አዶልፍ ሂትለር የአርያን ዘርን ትልቅነት አውጆ ‘ተቀናቀኞቼ ናቸው’ ያላቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያንን ጨፍጭፏል። ድፍን አውሮፓን በቁጥጥሩ ስር ለማዋል የጦር አቅሙን አደራጅቶ ወረራ ያደረገው የጀርመኖችን የበላይነት ለማስፈን ካለው እራስን ከፍ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ከማየት የመጣ አስተሳሰብ ነው። በ18ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን በቀኝ ግዛት ስር በማዋል የሀገሪቱን ጥሬ ሃብት ለማጋበስና ህዝቡን የባርነት ቀንበር ለማሸከም ውቅያኖስ ተሻግረው የመጡት አውሮፓውያን ይህንኑ ሃሳብ የሚያራምዱ ስለመሆናቸው ስራቸው ይመሰክራል።
እንዲህ አይነቱ አስተሳሳብ ዓለምን ከለወጡ ፈላስፎች ስለመነጨ ብቻ ጤናማ ሀሳብ ነው ብለን አንቀበለውም። ምክንያቱም የፍልስፍና እውቀት መገለጫ የሆነው ምክንያታዊነት ይጎድለዋልና ነው። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሳብ እንዲያውም ፈላስፎች ሁልጊዜ ትክክለኛ መልእክት አስተላላፊዎች አለመሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
ዋለልኝ እምሩ በጽሑፉ እንደሚጠቅሰው ‹‹አካባቢያዊነት ከዓለማቀፋዊነት መብለጥ የለበትም፤ ፍልስፍና አካባቢያዊ ከሆነ ፍልስፍና መሆኑ ይቀርና በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ ባህላዊ እሳቤዎች መገለጫ መሳሪያ ሆኖ ይቀራል።›› ፍልስፍና አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች አድርጎ አይነሳም፤ በቦታ አይወሰንም፤ በምክንያት እንጂ በስሜትና በጥቅም አይመራም። ነገሮችን በተናጠል ይመረምራል እንጂ በደምሳሳው አይፈርጅም፤ በአምባገነናዊ አስተሳሰብ ላይ አይንጠለጠልም።
አውሮፓውያን አፍሪካን በቀኝ ግዛት ለመያዝ ሲያስቡ ምክንያታቸው ነጮች የበላይ፣ ጥቁሮች የበታች ናቸው የሚለውን የእነ አርስቶትልን ፍልስፍና ከማራመድ የመነጨ ነው።
ዛሬም ድረስ የሰዎችን የቀለም ልዩነት በተመለከተ እይታቸው የተንሸዋረሩ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። የስልጣኔ ቁንጮ ነች፤ ዲሞክራሲና ፍትህን አስፍናለች፤ የዓለማችንም ምሳሌ ነች በምትባለው ሀገረ አሜሪካን ሳይቀር ዛሬም ድረስ ነጮች ጥቁሮችን ሲበድሉ ማየት የተለመደ ነው።
በቅርቡ እንኳን ጆርጅ ፍሎይድ በተባለው አፍሪካ አሜሪካዊ ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ስንመለከት ምኒልክ ለዜጎቻቸው ያጎናጸፉት ክብር ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ እንረዳለን። በአውሮፓ እግር ኳስ ሜዳዎች በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው መገለልና የዘረኝነት ጥቃት የዘወትር ክስተት ነው። ምኒልክ ይህን አስተሳሰብ የሰበሩት ከመቶ ዓመት በፊት መሆኑ ሲታሰብ የአስተሳሰባቸው ልዕልና የት ድረስ እንደነበር በግልፅ እናያለን።
አጼ ምኒልክ ወራሪውን የኢጣሊያ ፋሺስት ወደ መጣበት እንዲመለስና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብር በዲፕሎሚሲ ቋንቋ አግባብተው ለመመለስ ሞክረዋል። ኢትዮጵያ በሞግዚት የማትተዳደርና እራሷን የቻለች ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን በምክንያት አስረድተዋል። ጣሊያኖች እምቢተኛ ሲሆኑና ድንበር አልፈው ወደ መሃል ሀገር ሲገሰግሱ ህዝባቸውን አንድ አድርገው ወራሪውን ጠላት በመመከት ኢትዮጵያን አስከብረዋል። የመጣውን ጠላት ተዋግተው ድል ለመንሳት የህዝባቸው አንድነት ትልቅ ሃይል እንደሚኖረው የተረዱት አጼ ምኒልክ ዜጎች ለአንድ ዓላማ በጋራ እንዲቆሙ በማድረግ አቅም ማሰባሰቡ የመጀመሪያው ተግባራቸው ነበር። በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር የተኳረፉና ልባቸው የሸፈተ ኢትዮጵያውያንን ሳይቀር አንድ ለማድረግ ሞክረዋል።
ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ‹‹አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሃፋቸው የክተት አዋጁን አስመልክተው ካሰፈሩት መልእክት ቆንጥረን እንመልከት። ‹‹የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስከ አሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ከሆነ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማለጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ›› ይላል።
አጼ ምኒልክ ‹‹የሀገሬ ሰው ከዚህ በፊት አላስቀየምኩህም፤ አንተም አላስቀየምከኝም።›› ማለታቸው በህዝቡና በእራሳቸው መካከል የነበረውን መከባበርና መተማመን፤ መተዛዘንና መቀራረብ፤ የበለጠ እንዲጠናከር ለማድረግ የተጠቀሙበት ስልት ነው። ከዚህ በፊት አልተቀያየምንም ማለታቸው ደግሞ ወደፊትም አንቀያየምም፤ የነበረን መልካም ግንኙነት ይቀጥላል፤ አሁን የሀገርህን፣ የሚስትህን፣ የልጆችህን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ወራሪ ስለመጣብህ ተባብረን እንድናስወግደው፤ ከጎኔ ቁም በሚል ለማግባባት ሞክረዋል። በሌላ በኩል ትእዛዛቸውን ሳይፈፅም የሚቀር ሰው ካለ ግን ቅጣት እንደሚጥሉበት፤ ቅጣቱም ይግባኝ እንደማይኖረው አበክረው ማሳሳባቸው ጠላትን ለማንበርከክ ሁሉን አይነት አቀራረቦች መጠቀማቸውን ያሳያል።
‹‹የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል እንዲሉ›› አጼ ምኒልክ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተደራጅቶ የመጣውን የኢጣሊያ ወራሪ ሃይል ቶሎ ብለው ከመግጠም ይልቅ አቅማቸውን እስኪያጠናክሩ ድረስ ጦርነቱን አዘግይተውታል። ያዘግዩት እንጂ ውስጥ ውስጡን ግን ዝግጅት ያደርጉ ነበር። ይህም በጠላት ላይ ድል ለመቀዳጀት ይከተሉት የነበረ አንዱ ፍልስፋናቸው መሆኑን የታሪክ መጽሃፍት ያስረዳሉ።
የተቻላቸውን ሁሉ ዝግጅት ካደረጉ በኋላ የማይቀረውን ጦርነት መርተው ኢጣሊያንን የሚያህል ትልቅ የጦር አቅም ያለው ሀገር አዋርደዋል፤ ከንቱነቱንም ለዓለም ህዝብ አጋልጠዋል። የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያና ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት ያጎናጸፈው በአጼ ምኒልክ የአመራር ብቃትና የውጊያ ፍልስፍና ነው። አጼ ምኒልክ የጠላትን አቅም እያሰለሉ፤ እንደ ሃይል መጠኑና አሰላለፉ ሰራዊታቸውን በአራት አቅጣጫ በማሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለድል በቅተዋል።
አጼ ምኒልክ የተማረኩ የኢጣሊያ ወታደሮችን በተለየ መንገድ ይንከባከቧቸው እንደነበር ተጽፏል። ፈልገው ሳይሆን በአንድ ሰው የተሳሳተ ሀሳብና ፍላጎት ምክንያት መጥተው እሳት ውስጥ የተማገዱ መሆናቸውን በመረዳታቸውም እንደሹመታቸውና ማዕረጋቸው በመለያየት አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ሁሉ ያደርጉላቸው ነበር።
ልብስ የሌላቸውን ልብስ በማልበስ፣ የቆሰሉት የሀኪም እርዳታና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ፤ ምግብ፣ መጠለያ፣ የኪስ ገንዘብ እየሰጡ አስቀምጠዋቸዋል። አልፎ ተርፎ ምርኮኞች የሙዚቃ መሳሪዎችን በመጫወት እንዲያሳልፉ እድል ይሰጣቸው ነበር። እንደውም ጃንሆይ ምርኮኞችን ያቀማጥላሉ በሚል መኳንንቱ የምርኮኞችን አያያዝ ይተቹ እንደነበር በታሪክ ፀሀፍት ተመዝግቦ ይገኛል።
በዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም ናኝቷል፤ ክብሯም ገኗል። በድሉ ማግስት አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት ዲፕሎማሲን በመምረጥ መወዳጀትን መርጠዋል። እንደ ቤልጄየም፣ ጀርመን እና ፈረንሳይን የመሳሰሉ ሀገራት ኤምባሲያቸውን ለመክፈት የቀደማቸው አልነበረም። እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በምስራቅ አፍሪካ በቀኝ ግዛት ከያዟቸው ሀገራት ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር ከኢትዮጵያ ጋር ለማካለል ስምምነት አድርገዋል። ኢትዮጵያ ከቀኝ ገዢዎች ጋር ስምምነት ማድረጓ ልዩ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።
የዓድዋ ድል በአፍሪካም ሆነ በዓለም ዙሪያ በነጮች ቀኝ ግዛት ስር ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች አንጸባራቂ ድል ነበር። በዓለም ዙሪያ በባርነት ቀንበር ስር ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች ከፍተኛ መነቃቃትን በመፍጠሩ ለፓን-አፍሪካኒዝም ፍልስፍናና ተግባራዊነት መነሻ ሆኗል። የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንደ ነጻነት ተምሳሌት በመቁጠር የሀገራቸው መለያ በማድረግ የነጻነት ተጋሪ እስከመሆን ድረስ ዘልቀዋል። ሌሎችም የካሪቢንያን ሀገሮች አረንጓዴ፣ ቀይ እና ቢጫ ቀለሞችን ለማንነታቸው እና ለነጻነታቸው መገለጫ አድርገው መርጠዋቸዋል። ይህ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ኢትዮጵያን የነጻነታቸው አለኝታ አድርገው በማየታቸውና ታሪካቸውን ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ለማስተሳሰር በመፈለጋቸው ነው።
የፓን አፍሪካን ሀሳብ ያመነጩት የትሪንዳዶና ቶቤጎ ዜግነት ያላቸው በሙያቸው ጠበቃ የነበሩት ሄንሪ ሲልቬስተር ዊሊያምስ ቢሆኑም የዓድዋ ድል ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተካሄዱትን የፓን-አፍሪካ እንቅስቃሴዎች እንዲፋጠኑ እድል የፈጠረ ክስተት ሆኗል። በቀኝ አገዛዝና በዘረኝነት አስከፊ ስርዓቶች መካሄድ ያለባቸውን የትግል ስልቶች ለማቀናጀት ጥቁር ምሁራንን ያሰባሰበ ጉዳይ ቢኖር ፓን አፍሪካዊነት ነው። ጽንሰ ሀሳቡም አፍሪካዊያን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ የትምህርት ዕድል እንዲስፋፋ፣ ማንኛውም የነጮች ተጽእኖ እንዲቆም፤ ባርነት እንዲወገድና የመሬት ይዞታ መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቅ ነው።
ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም በወረረችበት ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪካዊያን ኢትዮጵያን በመደገፍ ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ለመዋጋት ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩት ከፓን-አፍሪካ መመስረት በኋላ ነው። ይህም የፓን-አፍሪካን እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶት ነበር። የዓድዋ ድል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና ጽህፈት ቤቱም አዲስ አበባ ውስጥ እንዲሆን አንድ እራሱን የቻለ ምክንያት ሲሆን በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ደግሞ የምኒልክና የአጠቃላይ አባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ፤ የአሸናፊነት ስነልቦና አጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ማንነት አብሮ ሲነሳ ኖሯል፤ ይኖራልም።
አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን ለማዘመን ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ በወቅቱ ዓለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የዘመናዊ አስተሳሰብ አራማጅነታቸውን አሳይተዋል። እንደ ስልክ፣ ባቡርና የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ መኳንንቱ ከሰይጣናዊ አሰራር ጋር እያስተሳሰሩ ቢተቿቸውም እያግባቡ ቀስ በቀስ ጥቅሙን እንዲረዱ በማድረግ እንዲቀበሏቸው አድርገዋቸዋል።
አጼ ምኒልክ በእኩልነት የሚያምኑ መሪ ከመሆናቸው የተነሳ ሴቶች የበታች ተደርገው በሚታዩበት በዚያ ዘመን እቴጌ ጣይቱ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ሳይቀር ሀሳብ የመስጠት፣ የመደመጥና የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው እድል የሰጡ መሪ ናቸው። በየቦታው አካባቢዎችን የሚያስተዳድሩ ገዢዎች ደሃን እንዳይበድሉ ፍርድ እንዳያጓድሉ አጥብቀው ይመክሯቸው እንደ ነበር በታሪክ ተመዝግቦላቸው ይገኛል።
ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመመስረት ካላቸው ፍላጎት የተነሳም በየአካባቢው የነበሩ ገዢዎችን ወደ አንድ በማምጣት ትልቋን ኢትዮጵያ ሰርተዋል። የሚገዳደሯቸውን የአካባቢ ገዥዎች በሃይል ወደ ራሳቸው ከማምጣታቸው በፊት በማግባባት፤ አልፎ አልፎም በመ(ማ)ጋባት አንድ ሀገረ መንግስት ለመመስረት የቻሉ ታላቅና ከጊዜአቸው የቀደሙ፤ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ከዓድዋ እስከ ፓን-አፍሪካ የዘለቀ መሪ ነበሩ።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013