ኢትዮጵያውያን ከዋክብት በቫሌንሲያ ማራቶን ይፋለማሉ

በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ ከተሰጣቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቫሌንሲያ ማራቶን ከቀናት በኋላ ይካሄዳል። በማራቶን ስመጥር መሆን የቻሉ ታላላቅ አትሌቶችን የሚያሳትፈው ይህ የማራቶን ውድድር ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያስተናግድ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድም አጓጊ ሆኗል። በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደግሞ በርቀቱ ካላቸው ፈጣን ሰዓትና ብቃት አኳያ የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝተዋል።

በመም እንዲሁም በጎዳና ላይ ሩጫዎች በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ በርካታ ገድሎችን ያስመዘገበው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እንዲሁም በቫሌንሲያ ማራቶን ያለፈው ዓመት አሸናፊው የነበረው አትሌት ሲሳይ ለማ የወንዶቹን ፉክክር ይመራሉ። በተመሳሳይ በሴቶች በኩል የቦታው ክብረወሰን ባለቤቷ አማኔ በሪሶ እንዲሁም መገርቱ ዓለሙን የመሳሰሉ ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ይሮጣሉ። ይህም ከአሸናፊነት ግምቱ ባለፈ በውድድሩ ፈጣን ሰዓት ይመዘገባል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጎታል።

ከረጅም ዓመታት በኋላ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሃገሩን መወከል የቻለው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በማራቶን የዓለም ሦስተኛው ፈጣን አትሌት መሆኑ ይታወቃል። በኦሊምፒኩ እንደታሰበው ውጤታማ ባይሆንም ከሚገኝበት ዕድሜ አኳያ ውድድሩን በመፈጸሙ በስፖርት ቤተሰቡ ሲደነቅ ቆይቷል። ከጥቂት ወራት በኋላም ቀነኒሳ ብርቱ ፉክክር ወደ ሚደረግበት የቫሌንሲያ ማራቶን መመለሱን አረጋግጧል። ቀነኒሳ ባለፈው ዓመት የቫሌንሲያ ማራቶን ተሳትፎ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የገባበት ሰዓትም ከ40 ዓመት በላይ ያሉ አትሌቶች ክብረወሰን በመባል ተመዝግቦለት ነበር። በዓመቱ ሌላኛውን ተሳትፎውን በለንደን ማራቶን በማድረግም ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በተደጋጋሚ ከሚገጥመው ጉዳት መልስ በጠንካራ አቋም ወደ ውድድር በመመለስ የሚታወቀው ቀነኒሳ አሁን ደግሞ ከኦሊምፒክ መልስ ቫሌንሲያ ላይ ለሌላኛው ድል ከሃገሩ ልጆች ጋር የሚፎካከር ይሆናል። 2ሰዓት ከ1ደቂቃ ከ41ሰከንድ የሆነ ፈጣን ሰዓት ያለው የረጅም ርቀት ንጉሡ ቀነኒሳ በውድድሩ ከሚካፈሉ አትሌቶች ሁሉ ቀዳሚ የሚያደርገው ሲሆን፤ ካለው ልምድና አቋም አንጻር የ2024 የውድድር ዓመትን በውጤታማነት ያጠናቅቃል በሚልም ይጠበቃል።

በፓሪስ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን አባል የነበረውና በጉዳት ምክንያት ያልተሳተፈው አትሌት ሲሳይ ለማ ደግሞ በቫሌንሲያ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የውድድሩ ተካፋይ ይሆናል። ባለፈው ዓመት በዚሁ ቫሌንሲያ ማራቶን አሸናፊ የነበረው ሲሳይ ያስመዘገበው 2ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ የግሉ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦለታል። ይህም ከታላቁ አትሌት ቀነኒሳ የጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ያለው ነው። አትሌቱ በዚህ ዓመት የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ቢሆንም የገባበት ሰዓት ግን በደቂቃዎች የዘገየ ነበር። አትሌቱ በስፍራው ካለው ተሳትፎ አንጻርም በቫሌንሲያ በድጋሚ አሸናፊ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ይሁንና በዚህ ውድድር የሚካፈሉት የርቀቱ እጅግ ጠንካራ አትሌቶች ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑ ግልጽ ነው።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና የፈጣን ሰዓት ባለቤቱ አትሌት ብርሃኑ ለገሠ ነው። የሁለት ጊዜ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ባለፈው ዓመት በአምስተርዳም ማራቶን 4ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው። አትሌቱ እአአ 2019 በርሊን ላይ ያስመዘገበው 2ሰዓት ከ2ደቂቃ ከ48 ሰከንድ የሆነ ሰዓትም በዘንድሮው የቫሌንሲያ ማራቶን ሦስተኛው ፈጣን አትሌት ያደርገዋል። አትሌት ደረሰ ገለታ እና ጉዬ አዶላም ባላቸው ፈጣን ሰዓት የውድድሩ አሸናፊ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ኮከቦች መካከል ይገኛሉ።

በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ የበላይነቱን የያዙት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲሆኑ፤ የቫሌንሲያ ማራቶን የክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት አማኔ በሪሶ ከሁለት ዓመት በኋላ በዚህ ውድድር ተመልሳለች። በወቅቱ ያስመዘገበችው ሰዓትም (2ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ58) የርቀቱ ሦስተኛው ፈጣን በሚል የተመዘገበም ነበር። ከዚያ በኋላ በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮን በመሆን ብቃቷን ስታስመሰክር በቶኪዮ ማራቶን ሦስተኛ እንዲሁም በፓሪስ ኦሊምፒክ አምስተኛ በመሆን ያጠናቀቀች ጠንካራ አትሌትም ናት። ይህም ከቀናት በኋላ በመጪው እሁድ ቫሌንሲያ ላይ በድጋሚ ታሪክ ልትጽፍ ትችላለች በሚል እንድትጠበቅ አድርጓታል።

ይሁን እንጂ እንደ መገርቱ ዓለሙ ካሉ የሃገሯ ልጆች ከፍተኛ ፉክክር ሊገጥማት ይችላል። እአአ በ2022 እና 2023 የለንደን ማራቶን ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው መገርቱ ከአማኔ በሁለት ደቂቃዎች የዘገየ ሰዓት አላት። ሌላኛዋ ተፎካካሪ አትሌትቶች ሕይወት ገብረኪዳን እንዲሁም ጥሩዬ መስፍንም በደቂቃዎች የዘገየ ሰዓት ያላቸው ቢሆንም ለአሸናፊነት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ።

ብርሃን ፈይሳ

 አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You