ኢትዮጵያ በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ምርት ከፍተኛ እምቅ አቅም እንዳላት ይታወቃል። በበርካታ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም እህሎቿ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎች በመያዝ እየመራች ትገኛለች። የሀገሪቱን የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም እህሎች ይበልጥ ውጤታማና ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ይገኛል። ምርታማነትን በማሳደግ፣ ጥራትን በማረጋገጥና እሴት በመጨመር የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ለዓለም ገበያ የማቅረብ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
በቅርቡ ደግሞ ላኪውን የሚያበረታታ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ተደርጓል፤ ማሻሻያው ንግዳቸውን እያሻሻለላቸው ስለመሆኑም ላኪዎች ሲገልፁ ይሰማል። ላኪውንና ገዢውን ለማገናኘት የሚያግዙ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች በየጊዜው እየተዘጋጁ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ገዢዎችንና ላኪዎችን ያገናኘ እና የተለያዩ ሀገራት የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶች የተዋወቁበትና ላኪዎች የገበያ ትስስር የፈጠሩበት ጉባኤ ተካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ጋር ያዘጋጀው 13ኛው የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከአንድ መቶ በላይ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል። መድረኩ የውጭ ንግድ ብዝሀነትና ተወዳዳሪነት እንዲጎለብት፣ በገበያ መዳረሻ፣ በምርት ተደራሽነት እና ሰፊ የትስስር ሥራ ለመሥራት ያስቻለ ነው። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ምርቶች ከ800 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ዓመታዊ ገቢ ታገኛለች።
ሚኒስትሩ የተወሰኑ የጥራጥሬ ዓይነቶችን በአብነት ጠቅሰው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ በባቄላ ምርት ከዓለም ሁለተኛ፣ በምስር ምርት ከዓለም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ነች። በአብዛኛዎቹ የቦለቄ ምርቶችም በዓለም ከአንደኛ እስከ 10ኛ ደረጃ አምራች ተብላ ትታወቃለች። ባለልዩ ጣዕም ምርቶችም የሚመረቱ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ገበያ ተመራጭ አድርጓታል።
ከቅባት እህሎች አኳያ በተለይ በሰሊጥ ምርት ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛዋ አምራች ሀገር መሆኗንም ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ቀይና ነጭ ወይም የወለጋና የሁመራ የሚባሉ ሁለት ዓይነት የሰሊጥ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በስፋት እንደምታቀርብም አስታውቀዋል።
እነዚህን ምርቶች በሀገር ውስጥ እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ የማቅረብ ጅምር ሥራዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በጥሬው ከሚላከው አኩሪ አተር ዘይትና መኖ እየተመረተ መሆኑን አመልክተዋል።
መሰል መድረኮች መዘጋጀታቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ለማሳየት እንደሚያስችላት አስታውቀዋል። በዓለም የሚታወቁ ትልልቅ ገዢዎች በመድረኩ መሳተፋቸውን አመልክተው፣ ይህም ስለኢትዮጵያ እምቅ አቅምና ስላሏት ምርቶች በዝርዝር መረጃ ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑን አስታውቀዋል። መሰል መድረኮች ላኪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ ገበያ መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሃሳብ የሚያቀርቡበት ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ሃሳቡም ለመንግሥት በተደራጀ መልኩ ቀርቦ የእርምት ርምጃዎች የሚወሰዱበትን እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ዘንድሮ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በጣም እያንሰራራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በቀሪ ጊዜያት የመንግሥትን ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። አንዱ ጥረትም የዚህን ዓይነት የገበያ ትስስር የሚያሳድጉ መድረኮችን ማዘጋጀት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሁለት ወራት በኋላም ዱባይ ላይ ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚካሄዱ ጠቅሰው፣ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በተመሳሳይ አፍሪካ አቀፍ የኢግዚቢሽን መድረኮች እንደሚዘጋጁም አመልክተዋል። የኢትዮጵያን ምርቶች ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለሚሰሩ አካላት በዚህ መልኩ የሚዘጋጁ መድረኮች ገዢና ሻጭን በማገናኘት እገዛ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
ባለፈው በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ 120 ሚሊየን ዶላር ኮንትራት መፈረሙን ጠቅሰው፣ በዚህኛው መድረከም 150 ሚሊየን ዶላር ኮንትራት እንደሚፈረም ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ የምርት ጥራትን አስመልክተው ሲያብራሩም፤ ኢትዮጵያ የምርት ጥራትን ለማረጋገጥም በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የጥራት መንደር መገንባቷን ተናግረዋል። ሀገሪቱ በሁሉም ወጪና ገቢ ቅርንጫፎች አካባቢ የተደራጀ የጥራት ቁጥጥር መሳሪያና የሰው ኃይል እንዳላትም ጠቅሰው፣ በብዙ ሀገሮች ዘንድ በጥራት የማትታማ ሆና መቆየቷንም ገልጸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሀገርን በማይወክል ነጋዴ አንደኛ ደረጃ ምርት ተብሎ ሁለተኛ ደረጃ ምርት የመላክ ጉዳይ እንደሚስተዋልም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት የመላክ እድል አነስተኛ መሆኑን አመልክተዋል። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ድርጅት በሁሉም ቦታዎች እንዳለ ጠቅሰው፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ17 ቅርንጫፎች ወጪና ገቢ ንግድ ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ጥራት ይቆጣጠራል ብለዋል።
በኮንትራቱ መሠረት ያለመላኩ ጉዳዮች አሉ እንጂ የኢትዮጵያ ምርት ጥራት የለውም የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ አልፎ አልፎ አንደኛ ደረጃ ተብሎ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ምርቶችን የመላክ ድርጊቶች የሚያጋጥሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህም ቢሆኑ በተገባባቸው ውለታ እና ኮንትራት መሠረት እንደሚታረሙ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከአቻ አዳጊ ሀገራት ጋር ስትነጻጸር የተሻለ የጥራት አቅርቦትና ሥርዓት ያላት ሀገር ናት። ለእዚህ ሥራም በንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ስር ብቻ አራት ተቋማት አሉ። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የቦለቄና የሰሊጥ ደረጃ ያዘጋጃል። በወጣው ደረጃ መሠረትም የጥራት ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ድርጅት ደግሞ የቁጥጥር ሥራ ይሠራል። በሶስተኛነትም የኢትዮጵያ የተስማሚነት አገልግሎት ድርጅት የተቆጣጠረባቸው መሳሪያዎች ትክክል ስለመሆናቸው የሚያረጋግጥ የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት አለ። እነዚህ ተቋማት ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር ስለመሆናቸው የኢትዮጵያ አክሬዲቴሸን አገልግሎት ተቋም ይሠራል። በዚህ ሁሉ ሥራም በተባለው የጥራት ደረጃ መሠረት ምርቶችን ለገዢዎች ማቅረብ ላይ ያለው ችግር እየቀነሰ መጥቷል።
የንግድ ሥራን አመቺና ቀላል ከማድረግ ጋር ተያይዞ ግምገማ እየተደረገ መሆኑን ዶክተር ካሳሁን ጠቅሰው፣ ላኪነትን አዲስ የሚቀላቀሉት ላኪዎችም በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው በኦንላይን የንግድ ፍቃድ አውጥተው ሥራ መጀመር የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ላኪዎችን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የንግድ ሥራውን ክፍት አድርጓል ሲሉም ጠቅሰው፣ ለእዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በአብነት ጠቅሰዋል፤ በማሻሻያው መሠረት የወጪ ንግዱ አትራፊ እንዲሆን እገዛ ማድረግ መጀመሩን ገልጸው፣ ከዚህ በፊት የወጪ ንግድ አትራፊ አልነበረም፤ ዶላር ለማግኘት እና በተገኘው ዶላር ለማትረፍ የሚደረግ ገበያ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ ከውጭ ምንዛሬ ግብይት አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው በኋላ የወጪ ንግዱ አትራፊና ውጤታማ መሆን ጀምሯል፤ ከ20 እስከ 30 በመቶ ትርፍ የሚገኝበት ዘርፍ ነው። በርካታ ነጋዴዎች ፍቃድ እያወጡ የወጪ ንግዱን ዘርፍ እየተቀላቀሉ ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የክህሎት ችግር ያለባቸውንና ድጋፍ የሚፈልጉትን በመደገፍ ብቁ ነጋዴ ለማፍራት በትኩረት እየሠራ ነው። ዘርፉ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አኳያ ገና ቢሆንም፣ ከነበረችበት እንቅልፍ ግን እየነቃች ወደፊት እየተስፈነጠረች ናት ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ወሳኝ አውታር በመሆን በወጪ ንግድ በኩል የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ነው። ለእዚህ አላማ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች የኢኮኖሚው ዋልታ ናቸው። 75 በመቶ የኢትዮጵያ የውጭ ምርት የሚገኘውም ከግብርና እና ከግብርና ጋር ከተያያዙ ምርቶች ሲሆን፣ 80 በመቶ ያህል የሰው ኃይል የያዘ ዘርፍ ነው።
መድረኩ ዓለም ወደ ሀገራችን መጥቶ በዘርፉ ያለውን አቅም እንዲያይ ማህበሩ፣ አምራቾች፣ ህብረት ሥራ ማህበራት እና ላኪዎች ከውጭ ሀገር ገዢዎች ጋር እንዲገናኙ እድል የፈጠረ ነው። እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ ሰጪና ለወደፊትም ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ ከዓለም ጋር መገናኘት የሚያስችል ድልድይ ነው።
መድረኩን ለመታደም ከ23 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ120 በላይ የውጭ ሀገር ደንበኞች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ከተሰማሩ የማሽነሪ እቃዎች አቅራቢ ህብረት ሥራ ማህበራት እና ላኪዎች ጋር ያገናኘ መሆኑንም አመልክተዋል።
ዘርፉ የዓለም አቀፍ ንግድ አካል እንደመሆኑ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ የማይወስነው ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች አሉበት ይላሉ። ለአብነት የዓለም አቀፍ የካርጎ፣ የሎጂስቲክስና የኮንቴይነር እጥረት በዘርፉ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። የቀይ ባሕር አካባቢ የሰላም እጦት ሌላው በሀገሪቱ የወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳደረ ችግር ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ በዚህ መካከል ሆናም ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ዋና ዋና ገዢዎች፣ ቱርክ፣ ህንድ፣ እስራኤል፣ ቻይና፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮችን የመሳሰሉት በመድረኩ መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል። ከአቅራቢዎች መካከልም የኢትዮጵያ አቅራቢዎች፣ ከምስራቅ አፍሪካ ታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ከምዕራብ አፍሪካ ናይጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ በኮንፍረንሱ ተሳትፈዋል። ይህም ዓለም አቀፍ አቅርቦት እና ፍላጎት ምን እንደሚመስል፣ የኢትዮጵያ አምራቾች እና ነጋዴዎች በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ እንዲያሳልፉ እንደሚያግዛቸውም አመላክተዋል።
አቶ ኃይሉ ሰርቤሳ በላኪነት የሚሰራው የብሪጅ ቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ኩባንያቸው በዘርፉ ለ20 ዓመታት መሥራቱን ጠቅሰው፣ የሰሊጥ፣ ነጭ ቦለቄና ቡና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ላኪው ገበያው ላይ ብዙ ዘመን ለመቆየት እንደሚያስብ ድርጀት መንቀሳቀስና የተፈጠሩትን ምቹ ሁኔታዎች ለመጠቀም ብልህ ሆኖ መገኘት አለበት ሲሉም አስገንዝበው፣ ጥራት ያለው ምርት በማዘጋጀት ለውጭ ገበያ መላክ እንደሚገባው ጠቁመዋል። ይህን ማድረጉ ቀጣይነት ያለው ገበያ መፍጠር ያስችለዋል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ እንደ ሀገርም ሀገሪቷ ቀጣይነት ያለው ገበያ የምታገኘውና ከተለያዩ ሀገራት ገዢዎች ሊመጡ የሚችሉት ላኪው ዝግጁ ሆኖ በመገኘት ገዢው የከፈለበትን ጥራት ያለው ምርት ማግኘት የሚያስችለው አሠራር መዘርጋት ሲቻል ነው። በተለያየ ደረጃ ያሉ ጥራት የሚያስጠብቁ አካላትም እንዲሁ በሀገራዊ ኃላፊነት መሥራት አለባቸው። የምርቱን ጥራት ለማስጠበቅ መንግሥትም ወደ ትግበራ ያስገባውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አጠናከሮ መቀጠል አለበት።
አቶ ኃይሉ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ኮንፍረንስ ላይ ተሳትፈዋል፤ ሁነቱ መዘጋጀት ከጀመረ ወዲህ ላኪነትን የሚያበረታታ ሥራ እየተሠራበት የመጣና መሻሻል የታየበትም ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምርት ወደ ውጭ ሀገር በሚልኩበት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ አግኝተው ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንጂ የኤክስፖርት ዘርፉ ራሱን ችሎ አትርፎ ቢዝነስ ሆኖ የሚሰራበት ሁኔታ አልነበረም ብለዋል። መንግሥት በቅርቡ ወደ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት አስተዳደር ሥርዓት የወጪ ንግዱ ራሱን ችሎና አትራፊ ቢዝነስ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ አስታውቀዋል።
አሁንም ቀሪ ሥራዎች ይኖራሉ ብለን እናስባለን ያሉት አቶ ኃይሉ፣ በንግድ ሚኒስቴር እንዲሁም በቡናና ሻይ ባለሥልጣን አካባቢ የሚደረጉ የመሸጫ ዋጋዎችን የማስቀመጥ ነገሮች በጊዜ ሂደት ይነሳሉ ብለን እናስባለን ሲሉም ጠቁመዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ባለመሆናችንና ገበያውም ሊብራላይዝ መሆን ስለሚገባው በቀጣይ ነፃ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል ሲሉም አመልክተው፣ አሁን መንግሥት የሚወስዳቸውን ርምጃዎች ተከትሎ በድርጅታቸውም ሆነ በኤክስፖርት ዘርፉ ላይ ለውጥ እየታየ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀድሞው አሠራር የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ መጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረግ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን 50 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥ፣ እንዲሁም 50 በመቶውን ደግሞ ወዲያው መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። ይህም በተለይ ላኪውን በጣም እንደሚጠቅም ጠቅሰው፣ የውጭ ምንዛሬው ላኪው ያስፈልጋል በሚለው ጊዜ የሚጠቀመውና ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥ የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል። ማሻሻያው በተለይ ኤክስፖርት ዘርፍ ላይ ለሚገኘው ላኪ በጣም እንደሚጠቅም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም