ስለ ሙዚቃ አፈጣጠር እንዲሁም እኛ ስለ ሙዚቃ ያለንን ልምድም ሆነ አተያይ በሚመለከት የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን የሚመረምረው የሙዚቃ ፍልስፍና (Philosophy of music) እንደሚያመለክተው የሙዚቃ ፍልስፍናዊ ጥናት ከሌሎች የፍልስፍና ዘውጎች፣ በተለይ ከዲበ-አካል (ህላዌ)ና ሥነውበት (metaphysics እና aesthetics) ጋር ያለው ግንኙነት የቅርብ ነው። በመሆኑም ስለ ሙዚቀ ሲነሳ፤ ስለ ድምፃዊያንም ሆነ ስራዎቻቸው ሂስ ሲሰጥ እነዚህንና ሌሎችንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት ማለት ነው።
ሙዚቃን በተመለከተ፣ ከራሳችን ከቅዱስ ያሬድ (ድጓ፣ ጾመድጓ፣ ዝማሬ፣ ምሥዋዕትና፣ እና ምዕራፍ) ጀምሮ በርካታ ስመ ጥር ፈላስፎች አብዝተው የተፈላሰፉ፣ የተመራመሩ፣ የተወዛገቡና የተከራከሩ ሲሆን አንድ የሚያደርጋቸው አቢይ ጉዳይ ቢኖር ሙዚቃ አያስፈልግም አለማለታቸው ነው። እንደውም እንደ ፕሌቶ ከሆነ ሙዚቃ የሰውን ባህርይ ትቀርፃለች። የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮችን ከመወሰን አኳያም የራሷ የሆነ ከፍተኛ ድርሻ አላት። ይህ ብቻም አይደለም፣ ዴመንና ፕሌቶ እንደሚስማሙበት ከሆነ የሙዚቃ ዘይቤ ሲቀየር የመንግስት መሰረታዊ ህጎችም አብረው ይቀየራሉ።
ፕሌቶ ሌላ የሚያክለው የሙዚቃ ሰብአዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን እሱም ከጤና ጋር የሚገናኘውና “ሙዚቃ ዋጋ ያለው የስሜትና የባህሪ ጥራት ስለሚያስገኝ ብቻ አይደለም። ጤናንም ስለሚያስገኝ ጭምር ነው።” የሚለው ነው። ደራሲና ተርጓሚ ሙሉጌታ ጉደታ በ”የፍልስፍና ወግ” ትርጉም ስራው፣ ፕሮታጎራስ (ከ 480-410 ዓክልበ.) ገጽ 326 ጠቅሶ እንዳስነበበን ከሆነ የሰው ልጅ ከልጅነቱ ጀምሮ የሙዚቃ ስልጠና ያስፈልገዋል።
ፕሌቶ እንደሚለው በሙዚቃ አማካኝነት ነፍስ ስምምነትንና ቅላፄን ልትቀዳጅ፤ እንደውም ለፍትህ የተዘጋጀች ልትሆን ትችላለች። በተስተካከለ ሁኔታ የተፈጠረ ሰው ኢ-ፍትሀዊ ሊሆን ይቻለዋልን? ለዚህ ነው የሙዚቃ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ የሚሆነው። ቅላፄና ስምምነት ከነፍስ ስውር ቦታ ድረስ ዘልቆ የመግባት ችሎታ አላቸው። እንቅስቃሴያቸው ግርማ ሞገስ ያለው ስለሆነ ነፍስን ውብ ያደርጓታል።
ሙዚቃ ለትምህርት ጠቃሚ መሣሪያ ነው። ‘ምክንያቱም ከምንም ነገር በላይ የሙዚቃው ምት እና ዜማ ወደ ነፍስ ውስጥ ገብተው ጠንካራ ስሜት የመፍጠር ሃይል አላቸው።’ ሲልም ልክ እንደ አርስቶትል ሁሉ የሙዚቃን ሰብአዊ-ሁለንተናዊ ፋይዳ ያስረግጣል ሲልም ሃሳቡን ያጠናክራል – ፕሌቶ።
ስለ ሙዚቃ ሲነሳ አንድ የማይዘለል፤ በሙዚቃና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ አካላት በመሪ ቃልነት የሚጠቀሙበት የፕሌቶ ሙዚቃን በያኝ አረፍተ ነገር ቢኖር ከላይ (ከታችም) ያልነውን የሚያሰርፀው፤
“ሙዚቃ የስነምግባር ህግ ነው። ለሁለንታ ነፍስን ይሰጣል፣ ለአእምሮ ደግሞ ወደ ምናቡ ዓለም የሚያስፈነጥረውን ክንፍ፣ ለህይወትና ሌሎች የላቀ ደስታንና የመንፈስ ልእልናን፤ እንዲሁም፤ ሙዚቃ የመርህ ህልውና ሲሆን ይህም ለመልካም፣ ፍትሀዊ፣ እና ውብ ለሆኑት ሁሉ አጋዥ መሳሪያ።” በማለት የሙዚቃን ሰብአዊና ኪናዊ ፋይዳን ያሰምርበታል።
በተለይ “Music is a moral law. It gives soul to the universe, wings to the mind.” የሚለው በምእራቡ ዓለም ለሙዚቃ አድናቂችም ሆነ ድምፃዊያን፤ አጥኝዎችም ሆነ የዘርፉ ምሁራን ማስቲካቸው በቻ ሳይሆኘ ሎጓቸው ሁሉ ነው።
ፕሌቶ (ዘኒከማሁ) እንደሚለው “… በሁላችንም ውስጥ፣ ጥሩ ሰዎች ናቸው በሚባሉት ውስጥ ሳይቀር፣ ተኝቶ የሚገኝ ወይም አድፍጦ የሚጠባበቅ አውሬያዊ ባህርይ አለ።” በመሆኑም ይህን አውሬያዊ ባህርይ መግራት የግድ ነው። ይህን ለመግራት ደግሞ ተመራጩ “የጭካኔ ዘዴ በሆነው የፖሊስ ዱላ” ሳይሆን በ”ሙዚቃ ነው። ሙዚቃ ነው ይህንን የሰውን ልጅ አውሬያዊ ባህርይ የሚያለሰልሰው።” ለዚህ ተገባራዊነት ደግሞ በስነ ምግባር የታነፀ፣ የስነምግባር መሰረት ያለው መንግስት ያስፈልጋልና እሱንም መፍጠር ይገባል። ይህን አይነቱን መንግስት ለማምጣት ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ ነው መሰራት ያለበት። ለአካል ጥንካሬ ስፖርትን፣ ለመንፈስ እርካታና ለባህርይ ልስላሴ ሙዚቃን የተማረ።
ፈላስፋው እንደሚለው ከሆነ ሁለቱም ከመጥን እንዳያልፉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈጋል። ስፖርቱም ከመጠን ካለፈ በጉልበት ማሰብንና መተማመንን፤ ሙዚቃውም ጥሩ ከሚባለው በላይ ከሆነ መቅለጥን ያመጣሉና ሁለቱም በአግባቡ መሆናቸው ላይ መጠንቀቅ ይገባል።
(ከዚህ ሙዚቃንና ሙዚቃን ከስርዓተ ትምህርት አኳያ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ለመረዳት የእጓለ ዮሀንስን “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”ን መመልከት ጠቃሚ ነው። የከበደ ሚካኤል ብያኔም በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በቀዳሚ ረድፍ ላይ ሊሰፍር የሚገባው ፈር ቀዳጅ (በአገራችን) ሃሳብ ነው።)
የላይኛው መንደርደሪያችን ሙዚቃን ስንሞዝቅ፣ ስናዳምጥ፣ ስንወድም ሆነ ስንጠላ፤ ስናየውም ሆነ ስናሳየው፤ ስንጠቀምበትም ሆነ ሳንጠቀምበት ስንቀር በምክንያት መሆን እንደሚገባ ከስሩ ለማስመር ሲሆን፤ የሙዚቃንም ሰብአዊ ፋይዳ ጥግ ለማሳየትና ልዩ ትኩረትንም የሚሻ እንጂ በወኔና ስሜት የሚገባበት ቸበር ቻቻ እንዳልሆነ ለማሳየት ያህል ነው። በእግረ መንገዳችንም ዓለማየሁን ስናደንቅ አስተዋፅኦውን (ወደፊት በአጥኚዎች የሚረጋገጥ ሆኖ) ከዚሁ አኳያ መረዳት አስፈላጊነቱን ለማወጅ ነው። ስለ ሙዚቃ አጠቃላይ ምንነት፣ ፋይዳና ኪናዊነት የአንድሪው ካንያን “The Philosophy of Music” (2017) ጥልቅ ጥናት ማንበብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በትህትና ስንጠቁም፤ እሱን ሳያነቡ ሙዚቃን ወደ ማሄስ (“አስተያየት መስጠት” አላልኩም) ተግባር መሄድ ስህተት መሆኑንም በመግለጽ ነው።)
ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ባጋጠመው ድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም ተለይቷል፤ ተለይቶናል። የዛሬ ሳምንት በዛሬዋ ቀንም ሥርዓተ ቀብሩ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል። በመሆኑም ዓለማየሁን ከማስታወስ፣ ከዛም ባለፈ ኪነጥበባዊ ውለታውን ላለመብላት በማሰብ በዚህ ገፅ ላይም ልናስበው ማንነቱና አገራዊ፣ ኪነጥበባዊና ድምፃዊ አስተዋፅኦው ግድ አለን።
ዓለማየሁ እሸቴ ድሮም ድሮ ነው እንደሚባው ሁሌም በጥሩ ከሚነሱት ምርጥና አንጋፋ ድምፃውያን መካከል አንዱ ሲሆን፤ በተለይ ኢትዮያዊነት ከጥፍር እስከ ፀጉራቸው ከወረራቸው መካከል ከፊተኞቹ ተርታ የሚገኝ ነው። በመሆኑም በዘፈነበት፣ ባዜመበት፣ ከሚዲያዎች ጋር ባወራበት፣ ስራዎቹን በመደረከበት ሁሉ ኢትዮጵያ አለች። በቅርቡ ከአንድ መጽሔት ጋር ካደረገው ቃለመጠይቅ መረዳት እንደተቻለው ዓለማየሁ ኢትዮጵያዊነትን እስከ መጨረሻው ይዞት ዘልቋል። (እንደ ጥላሁን ሁሉ ምናልባትም ከሞተ በኋላም ስለ አገሩ የሚለን ይኖር ይሆናል።)
የዛሬው ጽሑፋችን ዓለማየሁን ከማስታወስ አኳያ እንዲታይልን እያሳሰብን፤ “ለመሆኑ ዓለማየሁ ማ’ነው? ስለ እሱስ ማን ምን አለ?” የሚለውን ይዘን አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተን እንወያይ።
ዓለማየሁ በአብዛኛው እውቅና ካገኘባቸውና በህይወት እያለም እራሱ ከሚያውቃቸው ስንጀምር፤ “የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ፈርጥ ድምጻዊ”፤ “የአሜሪካውያኑን ድምጻዊያን ፓት ቦን፣ ቢል ሃሊይ እና ኤልቪስ ፕሪስሊን የእንግሊዝኛ ዘፈኖች አብዝቶ ይጫወት የነበረ”፤ “በተለይ የሮክ የሙዚቃ ስልት ነፍሱ የነበረ ድምፃዊ”፤ “የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሲነሳ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ፤ የሙዚቃ ሥራቸውን በሸክላ ቀድመው ካሳተሙ የመጀመሪያዎቹ ድምጻዊያን መካከል አንዱ”፤ “የተለያዩ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ በሙዚቃ ወዳጆች ልብ ውስጥ ከፍ ያለ ክብር ያስገኙለት ድምፃዊ”፤ “በቄንጠኛ አለባበሱና የፀጉር ስታይሉ [አበጣጠሩ] በዘመኑ ወጣቶች ልብ ውስጥ የገባ”፤ መንፈሳዊ መዝሙሮችን በመዘመር፤ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው በሚገባ የሚታወቅ” እና የመሳሰሉትን እናገኛለን።
ዓለማየሁ ለአማርኛ ዘፈን ብዙም ግድ ያልነበረው ሰው እንደ ነበርና፤ ለጥላሁን ገሰሰ ልዩ ክብርና ፍቅር ያለው ከመሆኑ የተነሳም አማርኛ “ከዘፈንኩም የጥላሁን ገሠሠን ‘እንክርዳድ እንክርድድ የተንከረደደ’ የሚለውን” ነው በማለት በአንድ ወቅት ተናግሮ እንደነበር፤ አርቲስቱ በወጣትነቱ ልቡ በሆሊውድ የፊልምና የሙዚቃ ሥራዎች የሸፈተ እንደነበርና ወደዚያው ለመሄድም በመርከብ ጉዞ ጀምሮ ቀይ ባህር ድረስ መሄዱን፤ ይሁን እንጂ ሳይሳካለት ቀርቶ መመለሱን በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉለት ቃለ መጠይቆች ተናግሯል። ምፅዋ በቆየባቸው ጥቂት ቀናትም ያሰማቸው በነበሩት ምዕራባዊ ዘፈኖች የምፅዋ መርከበኞችን በፍቅሩ ጥሏቸው እንደነበርም ይነገርለታል። (ይህ በፈረንጅኛው መለኪያ born musician ያሰኘዋል።)
የፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ (ከ1955 እስከ 1961 ዓ.ም) በመሆን ስራውን የጀመረው አለማየሁ በብዙ መልኩ በአድናቂዎቹ ዘንድ የሚታወቅ ሲሆን ከላይ ከዘረዘርናቸው በላይ የሚከተሉት የምስክርነት ቃላትም ተሰጥተውት እናገኛለን።
“በተለየው ድምጽህ፣ ልዩ በሆነው መድረክ አያያዝህ፣ ፍፁም የራስህ ቀለም በሆኑት ዜማዎችህ ዓለማየሁ እሸቴ የተባለ ታላቅ ስም አኑረሃል። ስለዚህ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በተለየ አሻራ ህያው ሆነህ ለትውልድ እንደምትተላለፍ ጥርጥር የለውም” (ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ)፤ “ጋሽ ዓለማየሁ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ እጅግ በጣም ከልቤ አዝኛለሁ። ታላቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው ነበር። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ መቼም የማይረሳ ሥራን ለሀገራችን ያበረከተ ታላቅ ሰው ነበር” (ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ)፤ “ድምጻዊ ዓለማየሁ በኢትዯጵያ ሙዚቃ የሬኮርዲንግ ታሪክ ውስጥ የተሳኩ እና ጥራታቸው ከፍ ያሉ ከ400 በላይ ሥራዎችን አበርክቷል፤ አለማየሁ ‘ወርቃማው’ ተብሎ ለሚጠራው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን የመጀመሪያው ተጠቃሽ ድምጻዊ ነበር፤ ‘ጌሪ ኮፐር’፣ ‘ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ’፣ ‘አለማየሁ ቴክሱ / ነጭ ነው ፈረሱ’ እየተባለም በአድማጮቹ የአድናቆት ቅፅሎች ይወደስ ነበር” (የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት)፤
ዓለማየሁ እስካሁን ድረስ ከ62 በላይ ዜማዎቹ በሸክላ ተቀርጸው 15ሺህ ያህሉ እንደተሸጡለት (ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 30-31፣ የሚለው ተጠቅሶ ተፅፎ እንዳገኘነው) የሚነገርለት፤ እንዲሁም “ተማር ልጄ [ዋው!!!] (ይህ ሥራው ከ35 ዓመታት በላይ እድሜን አስቆጥሯል። በዚሁ ዘፈኑም እአአ በ2015 በጀርመን አገር ሽልማት ተበርክቶለታል። ከእስካሁኑ የበለጠም ወደፊት እንደሚወደድ መከራከር አይቻልም።)፣ እዬዬ፣ ማሪኝ ብዬሻለሁ፣ ስቀሽ አታስቂኝ፣ ማን ይሆን ትልቅ ሰው፣ እንደ አሞራ ክንፍ / አውጥቼ ልብረራ፤ ውዷ ባለቤቴ እና በመሳሰሉት ድንቅ ዘፈኖቹ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው አርቲስት “[ዓ]ለማየሁ እሸቴ ለሚወዳት ኢትዮጵያ በጥበብ ሥራዎቹ ብዙ ያደረገ ሃገር ወዳድ ባለሙያ ነበር” በማለት የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም የተሰማቸውን ኀዘን በከተማው ህዝብ ሥም ገልፀውለታል።
አዲስ አበባ ቤቴ፣ የወይን ሐረጊቱ፣ እንዲህ ነው ወይ መውደድ፣ ምሽቱ ደመቀ፣ ችግርሽ በእኔ አልፏል፣ የሰው ቤት የሰው ነው፣ ታሪክሽ ተፅፏል፣ ደንየው ደነባ፣ ወልደሽ ተኪ እናቴ፣ ለሰሚው ይገርማል፣ የአባይ ዳር እንኮይ፣ ኮቱማ ፍቅርዬ፣ እንግዳዬ ነሽ እና ሌሎችም በከስሙ እኩል የሚየታወቁለት ዓለማየሁ ከተለያዩ ባንዶች ጋር ተጣጥሞ መስራቱም ይነገርለታል።
“ፖሊስ ኦርኬስትራም ካፈራቸውና ለሀገር ካበረከታቸው በርካታ ሙያተኞች መካከልም አንዱ ዓለማየሁ እሸቴ ነው። አርቲስት ዓለማየሁ እሸቴ ከፖሊስ ሰራዊት አልፎ ለሀገርና ልህዝብ በርካታ አስተማሪና አዝናኝ እንዲሁም ሀገራዊ ዜማዎችን በጥሩ ተሰጥኦ ተጫውቶ አልፉዋል። ከሀገርም አልፎ በበርካታ ሀገራት ተዘዋውሮ ስራዎቹን ተደራሽ ያደረገ ድንቅ ባለሙያ ነበር። የፌዴራል ፖሊስ የኪነጥበባት ምክትል ዳይሬክቶሬትም ለአርቲስቱ ቤተሰቦች ለሙያ ባልደረቦቹና ለመላው ኢትዮጵያዊ አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።” ሲል ፌዴራል ፖሊስ ኀዘኑን የገለፀለት ዓለማየሁ ከፖሊስ ኦኬስትራ በተጨማሪ በሮሃ ባንድ፣ በሸበሌ ባንድ፣ በአይቤክስ ባንድ፣ በዓለም ግርማ ባንድ፣ የራሱ በሆነው ሶሊኮስ ባንድ እና በሙላቱ አስታጥቄ ባንድ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎቹን ማበርከቱ ተነግሮለታል።
በኢትዮጵያ በሚዘጋጀው የ5ኛው ለዛ ሽልማት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴን ከሁሉም ለየት የሚያደርገውና (ሰሞኑን ሲነገርለት ያልተሰማው) ይህ ጸሐፊ የታዘበው ጉዳይ ቢኖር ድምፃዊው የህግ ሰው፣ በህግ እና በህግ የበላይነት የሚተማመን፤ በፍትህና ርትእ የሚመካ፤ ለጥበብ እድገት የሚቆረቆር፤ መብትና ግዴታውን ለይቶ የሚያውቅ ሰው መሆኑን ሲሆን፤ ለዚህም ዋቢ የሚያደርገው፤ በተለይም “ሳንሱር ተነሳ” ከተባለ ወዲህ “ምንተፋ” እንደ ሰደድ እሳት ከዳር እዳር በተቀጣጠለው የፈጠራ ስራዎች የአደባባይ ምንተፋ ምክንያት በእነ ላፎንቴን ላፍ የተደረገበትን “ያ ጥቁር ግስላ” ዜማውን አስመልክቶ መንታፊዎቹን ፍርድ ቤት ገትሯቸው የነበረ መሆኑ ነው፤ (ዝርዝሩን በወቅቱ ለንባብ ሲበቁ የነበሩ የህትመት ሚዲያዎች በሚገባ ስለዘገቡት እነሱን መመልከቱ ጠቃሚ ነው።) በተለይ ይህንን የኪነጥበብን ማንነትና አጠቃላይ ህግን የማስከበር ስራ ከዛ በፊትም ሆነ ከዛ በኋላ ማንም አድርጎት የማያውቅ (ሰልፍ መውጣትን ካልቆጠርልናቸው በስተቀር፤ አፍሬምና ይልማ ገብረአብም እንደ መካሰስ አድርጓቸው ነበር) ከመሆኑ አኳያ ዓለማየሁን በተለይ እንዲቆም ያደርገዋል።
ይህ ጸሐፊም “ምንተፋ – #1 የጥበብ ገዳይ” በሚል ርእስ “ዓለማየሁ እሸቴ “ያ ጥቁር ግስላ” የሚለው ከመታወቂያ በላይ መታወቂያው የሆነው ዜማው በላፌንቴኖች ተልፎበት ሸንጎ ቆሟል፤ አቁሟቸዋልም። በአቋሯጭ ‘ድምፃዊያን’ የፈጠራ ስራቸውንና ምርጥ ዜማቸውን ከተመነተፉትና አንጀታቸው እርር፤ ቆሽቴያቸው ቅጥል ካለባቸው ድምፃውያን መካከል መቸም ሙሉቀን መለሰን የሚያክል ያለ አይመስለኝም።” በማለት መፃፉን ያስታውሳል። (በዕውቀቱ ሥዩም “ያ ጥቁር ግስላ” ግጥም ደራሲ ጸጋዬ ወይን ገ/መድህን ነው ብሏል።)
ሶስቱንም (ceremonial purposes, recreational purposes, እና artistic expression የሚባሉትን) ዋና ዋና የሙዚቃ ሚናዎች/ተግባራት “ጥንቅቅ” አድርጎ የተካነው ዓለማየሁ ለወደፊት ምቹ የጥናትና መርምር መነሻ የሆኑ ስራዎችን አበርክቶ ያለፈ ሲሆን ለምሳሌ ያህልም የሮክ ሙዚቃ አድናቂና ተጫዋች መሆኑ በራሱ ዓለማየሁንና ስራዎቹን ከ”philosophy of the rock music” አኳያ አጥንቶ አንዳች እውነታ ላይ መድረስ ይቻላል ማለት ነው። ሌሎች ስራዎቹንም እንደዛው።
በመጨረሻም የዓለማየሁን “አንጋፋው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ በልብ ህመም ምክንያት ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም በ79 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።” የሚለውን ዜና ህልፈተ ህይወት መስማታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት የኀዘን መግለጫ ጽሑፋችንን እናጠናቅቅ።
ሀገሩን አጥብቆ በመውደድና ለሀገሩ ከልብ በመሥራት ለብዙ ከያንያን አርአያ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴ ማረፉን ሰምቼ እጅግ አዝኛለሁ። ሰሞኑን ወጣትና አንጋፋ ከያንያን ስለ ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጀ ሙዚቃ እንዲያወጡ ሲያስተባብር እንደነበር አውቃለሁ። ሥራዎቹ ኢትዮጵያን ከፍ እንዳደረጉ ይኖራሉ። ለኢትዮጵያ የሠራ ያርፋል እንጂ አይሞትም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014