ትራምፕ በቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ  አዲስ ታሪፍ ተግባራዊ ሊያደርጉ ነው

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በጨበጡ በመጀመሪያ ቀናቸው በቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ አዲስ ታሪፍ ተግባራዊ ሊያደርጉ ነው፡፡ ትራምፕ ይህን የሚያደርጉት በሕገ-ወጥ መልኩ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎችን ለመግታት እና የአደገኛ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከል እንደሆነ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥር 20 ቀን 2025 ሥራቸውን የሚጀምሩት ትራምፕ በመጀመሪያው ቀናቸው ከካናዳ እና ሜክሲኮ የሚገቡ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ የሚጭን ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ አስታውቋል። የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ፌንታኒል የተባለውን ዕፅ ለመሥራት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እንድታቆም ቻይናን መማፀኑ ይታወሳል።

ዋሺንግተን እንደምትለው ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ በፌንታኒል ምክንያት 75 ሺህ አሜሪካውያን ሞተዋል። ካናዳ እና ሜክሲኮ በሕገ-ወጥ መልኩ ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞችን እስኪያስቆሙ እንዲሁም ፌንታኒል የተባለው ዕፅ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ እስኪያግዱ ድረስ ታሪፍ ተጥሎባቸው ይቆያል።

ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ነው ይህን ያስታወቁት። “ሜክሲኮ እና ካናዳ ይህን ሥር የሰደደ ችግር የመቅረፍ ኃይል አላቸው” ብለዋል። ትራምፕ የቤይጂንግ ባለሥልጣናትንም ወርፈዋል። እሳቸው እንደሚሉት የቻይና ባለሥልጣናት ፌንታኒል የተባለውን ዕፅ የሚያመርቱ ሰዎች በሞት ለመቅጣት ቃል ገብተው ነበር።

በዋሺንግተን የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ “ቻይና ሆን ብላ ፌንታኒል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲገባ እያስደረገች ነው የሚለው ሐሳብ በፍፁም ውሃ የሚያነሳ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። “ቻይና የምታምነው የቻይና-አሜሪካ ምጣኔ ሀብታዊ እና የንግድ ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ ነው። በንግድ ጦርነት አሊያም በታሪፍ ጦርነት ማንም አያተርፍም” ብለዋል።

ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ሜክሲኮ እና ቻይና ላይ እስከ 100 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ እጥላለሁ በማለት ሲያስፈራሩ ተሰምተዋል። ቻይና ከእንግዲህ በኋላ በንግዱ ዘርፍ ከአሜሪካ ልዩ ስፍራ የሚሰጣት ሀገር አትሆንም ሲሉ ለቻይና የሚሰጠው ቦታ እንደሚቀንስ ጠቆም አድርገው ነበር።

የቻይና ምጣኔ ሀብት በተለያዩ ምክንያቶች እየተንገዳገደ ባለበት ወቅት ነው አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ታሪፍ ለመጫን ቃል የገባው። የንብረት ገበያ መዳከም፣ የሀገር ውስጥ የመግዛት አቅም መቀነስ እና መንግሥት ከሀገር ውስጥ የወሰደው ብድር መጨመር የቻይናን ምጣኔ ሀብት እየተፈታተኑት ይገኛሉ። አዲሱ የትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ዩኤስ-ሜክሲኮ-ካናዳ የገቡትን ዩኤስኤምሲኤ የተባለ ስምምነት የሚሽር ነው።

ይህ ትራምፕ የፈረሙት ስምምነት ወደ ተግባር የገባው በአውሮፓውያኑ 2020 ሲሆን ሦስቱ ሀገራት በመካከላቸው ነፃ የሆነ ንግድ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው። ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ቃል ከገቡ በኋላ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር በንግድ እና የድንበር ጉዳዮች በስልክ ማውራታቸውን ተዘግቧል። ትራምፕ ሦስቱ ሀገራት ላይ ታሪፍ ጨመሩ ማለት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል ማለት ነው ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው ።

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You