በቅድሚያ የዛሬዋን፣ ባለ1.4 ቢሊዮን ህዝቧን ቻይና (中) ትናንት እንመልክት። ይህን ስናደርግ በቀጥታ የምንሄደው ወደ ጥንታዊው ፍልስፍናዋ ነውና መዛግብትን ፈትሸን፤ ስለሷ የተደረጉ ጥናቶችን አገላብጠን ያገኘናቸውን በይዘታቸው ጠብሰቅ ያሉ ሶስት አንቀፆችን እንዳሉ እናስቀምጥ።
የቻይና ፍልስፍና የምንለው የቻይና ምሁራን ለረጅም ዘመናት ሲያዳብሯቸውና ሲያስፏፏቸው የኖሩትን የተለያዩ የፍልስፍናና የአስተሳሰብ ዘርፎችን በአንድነት ነው። የቻይና ፍልስፍና በሦስት የተወሰኑ ታሪካዊ ደረጃዎች አልፏል። የመጀመሪያውና ከቹ ስርወ መንግሥት የመጨረሻዎቹ ዓመታት ጋር ግጥም የሆነው የጥንታዊው ደረጃ (ክላሲካል ስቴጅ) የተባለው ነው። ይህ ወቅት በቻይና ፍልስፍና እድገት የታየበት ዘመን ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ6ኛው እስከ 2ኛው ምዕት ዓመት ያለውን ዘመን ያጠቃልላል።
ሁለተኛው ዘመን የመካከለኛው ዘመን የሚባለው ሲሆን ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2ኛው እስከ 11ኛው ምዕት ዓመት ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ይህ ወቅት በተለይ የሚታወቀው የቻይና ፍልስፍና የተለያዩ የውጪ አስተሳሰቦችን ማዋሃድና መቅሰም የቻለበት ዘመን በመሆኑ ነው።
ዘመናዊው ጊዜ (ዘ ሞደርን ኤጅ) የሚባለው ደግሞ ከ11ኛው ምዕት ዓመት እስካሁን ያለው ዘመን ነው። ይህ ወቅት ከዚህ በፊት የነበሩት የቻይና ፍልስፍናዎች የዳበሩበትና ለትምህርት ወደ ተለያዩ አገራት በሄዱና በተመለሱ ቻይናዊያን (እንዲሁም በትርጉም ስራዎች) አማካኝነት አዳዲስ በተለይም ምዕራባዊው አስተሳሰብ በስፋት የገባበት ወቅት ነው። በዚህ ዘመን ውስጥ የቻይና ፍልስፍና ያዘነብል የነበረው ወደ ሰብዓዊነት እንጂ ወደ መንፈሳዊነት አልነበረም። ከሃይማኖታዊነት (ሚስቲሲዝም) ይልቅ ወደ ምክንያታዊነት (ራሽናሊዝም) የሚያደላ ነበር ማለት ነው። (እድሜ ለሙሉጌታ ጉደታ በዚህ ጉዳይ ይህን ያህል ካልን ስራዎቹን ማንበብ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመን እንለፈው።)
ከላይ የቻይናን አጠቃላይ ፍልስፍናዊ ይዞታ ጨምቀን (ሰፋና ገፋ አድርጎ መሄዱን ለአንባቢያን በመተው) ካስቀመጥነው በተጨማሪ ቻይና በ(ኒኦ) ኮንፊሺየስ፤ የኮንፊሽየስ ዘመነኛና የ‹‹ክላሲካል›› ታኦይዝም፤ እንዲሁም የ‹‹Tao Te Ching›› ነው ደራሲ ላኦ ትዙ፤ ካርል ማርክስ፣ በማኦ ዜዱንግ እና የመሳሰሉት ፍልስፍናዎች አማካኝነት አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ መድረሷን ማስታወስ ይገባል።
ሌላውና ለቻይና (በተለይም ኢኮኖሚያዊ) እድገት መስፈንጠር ከምዕራቡ ዓለም ፍልስፍናዎች ይመቸኛል፣ ያዋጣኛል … ያለችውን ወስዳ አኝካ፣ አላምጣና ውጣ ከራሷ እንዲስማማ አድርጋ ስራ ላይ ያዋለቻቸው ሁለት ሲሆኑ እነሱም ተግባራዊነት (ፕራግማቲዝም) እና ቁስአካላዊነት (ማቴሪያሊዝም) ናቸው። ሌሎችንም እንደሁኔታው እየወሰደች ሲሆን የሄግል ስራዎችንም (ቅፆቹን) በደ ቻይንኛ በመተርጎም ለዜጎቿ እያቀረበች መሆኑን ከ”ቻይና ዳይሊ” መንግሥታዊ ጋዜጣ መረዳት ችለናልና ፍልስፍና በቻይና የገቢው ቦታ አለው ብቻ ሳይሆን የብልፅግና መሳሪያ ነው ማለት ነው። (‹‹ኢ ችንግ›› (I Ching)ንና የመሳሰሉትን መጻሕፍትም ከዚሁ ጋር አያይዞ ማሰቡ ጠቃሚ ነው።)
“5 ቱ የተፈጥሮ አካላት ዋናዎቹ (ምድር፣ እንጨት፣ እሳት፣ ውሃ እና ብረት) ምደባ (በአምስት ከፍሎ የማየቱ) መነሻው ከባህላዊ የቻይና ፍልስፍና ነው፡፡” የሚለውና በብዙዎች የሚጠቀሰውም ጉዳይ የቻይናና ህዝቧ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
የላይኛው መንደርደሪያም ሆነ ቀጥለን እንደ አዋዜ እያዋዛን የምናሰፍረው ጽሑፍ ዋና አላማ ከትላንትናው የችግርና ችጋር አረንቋ ለመውጣት፣ የዛሬው አስደማሚና ላንዳንዶቹም አስደንጋጭ እድገት ላይ ለመድረስ፣ እንዲሁም በዛሬው ላይ ቆሞ ነገው ላይ ተስፈንጥሮ ጉብ ለማለት ትልቁ መሳሪያዋ የአባቶች፤ የጥንታዊያን ፈላስፎች እውቀትና ምክረ ሀሳብ መሆኑን ማመልከት ነው።
ለመነሻ ያህል ይህንን ያህል ካልን ወደ ተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ እንመለስና አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ ።
ዛሬ እንደምናያት እሲያዊቷ ቻይና ማደግ ብቻ አይደለም፤ የፖለቲካ ጡንቻዋም ፈርጥሟል። ከዓለም 2ኛም አድርጓታል። መፈርጠሟም ለአሜሪካ ከማበደር (ማበደር አዲስ ነገር ባይሆንና የዲፕሎማሲው አካል ቢሆንም) ጀምሮ እስከ ማእቀብ መጣል ድረስ ሄዳለች። ማዕቀብ ከጣለችባቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት መካከል የቀድሞው የንግድ ዘርፍ ጸሐፊ ዊልበር ሮስ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከዛ በፊትም ቻይና የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ማይክ ፖምፕዮን ጨምሮ 27 የትራምፕ ዘመን አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወቅ ነው። በጦር መሳሪያ የመገዳደሩም ነገር በዛው ልክ ጠንካራ ሆኖ “እስኪ … እስኪ …” መባባል ደረጃ ላይ ደርሳለች ብቻ ሳይሆን አልፋ እንዳትሄድ ሁሉ ከፍተኛ ስጋት አለ። (እዚህ ላይ የወደፊቷ ዓለማችን በቻይና ቁጥጥር ስር እንደምትሆን የብዙዎች እምነት ሲሆን፣ ጥያቄው ከዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ጋር የማትተዋወቀው ቻይና እንዴት አድርጋ ዓለምን አንድ አድርጋ ልትመራ ትችላለች? የሚለው መሆኑን አስታውሰን ብናልፍ ችግር የለውምና አድርገነዋል።)
ሕዝባዊ ሬፑብሊክ ቻይና የራሷን ባህልና እሴት ጠንቅቃ ከማወቅም አልፋ የሌላውንም ለማወቅ እየሄደችበት ያለው ሩቅ መንገድ የሚያስቀና ሲሆን፤ አንዱም እኛኑ ይመለከታል። (ብዙ ነገሮቿ እኛን ከእኛ በላይ (በተለይም የተፈጥሮ ሀብታችንን) ስለማወቋ አመላካች ናቸው።)
በቤይጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ መምህርት የሆነችው ጃንግ ቹንጋይ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገረችው በቻይና የአማርኛ ትምህርት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ቋንቋው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሊሰጥ ችሏል። (ግዕዛችንን እነማ እነማ አገራትና ዩኒቨርሲቲዎቻቸው በከፍተኛ ዲግሪ ደረጃ እንደሚያስተምሩት እያሰብን።)
እዚህ ላይ ዛሬ በቻይና ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሚከታተሉ ቻይናዊያን የነገዎቹ “በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደሮች” ስለመሆናቸው መከራከር ከንቱ ነውና የቻይናን ስትራተጂካሊ የማሰቧን ነገር አድንቀንላት ወደ ወዳጅነታችን እንለፍ።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ ቢዝነስ ጉዳዮች አማካሪ ሚስስ ሊዩ ዩ እንደሚሉት የቻይናና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1930 በተደረገ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ነው። “ከ2017 ጀምሮ ደግሞ ወዳጅነታችን የዕድገቱ የመጨረሻ ማማ ላይ ደርሷል”። የሚሉት አማካሪዋ “በዚህም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በልዩ ቁርኝት ላይ የተመሰረተ ወዳጅነትን የፈጠሩት ቻይናና ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን ተባብረው የማይሰሩበት መስክ እስኪጠፋ ድረስ እንደ ብረት የጠነከረ ወዳጅነትን መስርተዋል፡” ይህ ብቻም አይደለም “ታሪካዊው የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሁለቱ አገራት አልፎ ለአፍሪካ ቻይና ትብብርም በአርዓያነት መወሰድ ያለበት ነው” ሲሉም ነው ሚስስ ሊዩ ዩ የተናገሩት።
አሁን፤ በሁለቱ አገራት መካከል የትብብር መስኩ በእጅጉ እየሰፋ በመምጣቱ ኢትዮጵያ በቤጅንግ ከሚገኘው ኤምባሲዋ በተጨማሪ በዋን ዡ፣ ሻን ሃይና ቹን ቹን ግዛቶች ተጨማሪ ሦስት አቢይ ቆንስላዎችን ከፍታ እየሰራች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፤ በልማቱ ዘርፍም ከሚጠበቀው በላይ ስለመሄዳቸው (የእነአሜሪካ መንጨርጨርን ጨምሮ) በቂ ማሳያ ነው።
ከቻይና በተገኘ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ሃያ ስድስት ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ፤ ከነዚህ መካከልም የኢትዮ ጅቡቲ አገር አቋራጭ ዘመናዊ የባቡር መስመር፣ ቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሞጆ ሐዋሳ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ፣ አዲስ አዳማ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቁጥር ሁለት ተርሚናል ማስፋፊያ መኖሩ ወዘተርፈ የዚሁ የሁለቱ አገራት የልማት ትብብራቸው ማሳያ ነው።
ስለኢትዮ-ቻይና ባጠቃላይም ሲኖ-አፍሪካ ግንኙነትና ትብብር ይህ ማሳያ በመሆኑ ወደ ቻይና “Xiaokang society” እቅድና አላማው አንዳንድ ሀሳቦችን እንለዋወጥ። ከዛ በፊት ግን . . . ከዛ በፊት ግን ስለ “ ጥቅስ” እናውራ።
ቻይናዎች፣ እዚህ እኛው ጋ፣ ከአ.አ ወደ ደብረ ዘይት ሲሄዱ ከሃይዌይ ከወጡ በኋላ በስተቀኝ በኩል በገነቡት ሰፊ (ፋብሪካ?) ዋና በር ላይ አስደማሚና ዘላለማዊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል፤ የሀብትን (የተፈጥሮም ይሁን ሌላ) አላቂ መሆኑንና ፈጠራ ግን ገደብ የለሽ መሆኑን፤ በመሆኑም ሀብትን በአግባቡና በጥበብ መጠቀም ተገቢ እንደሆነ የሚያሰርፅ ጥቅስ በትልቁ አስቀምጠዋል፤ “Resources are limited; Creativity is unlimited” የሚል። ይህ ለእኛ አይነቶቹ ቁጥር አንድ ሀብት አባካኞች ከትምህርትም በላይ ተግሳፅ ነውና ጽሑፉን በ”ተጠቃሽ ጥቅሶች” ማስታወሻ ውስጥ ቢሰፍር ተገቢ ቦታው ይሆናል።
ባለፈው ሰሞን በ1921 በ50 አባላት የተመሠረተውና ዛሬ 95 ሚሊዮን አባላት ያሉትን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን (ሲሲፒ) 100ኛ ዓመት (Founding Anniversary) ባከበሩበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ ለህዝባቸው ቻይናን ማዘመንና ድህነትን ጨርሶ ማጥፋትን ታርጌቱ ያደረገውን የአምስት ዓመት (2021-2025) እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ስያሜውንም “Xiaokang society” ሲሉ ገልፀውታል፤ ሲያሰፉትም “building a Xiaokang society in all respects.” ከእቅዱ መሳካት በኋላ የሚኖረውንም ማህበረሰብ በሚያስጎመዥ መልኩ ዘመናዊነትን በተጎናፀፈ መልኩ የበለፀገ ማህበረሰብ […] a moderately prosperous society in all aspects.” ሲሉ አስቀምጠውታል። (የዚህ ጸሐፊ ጥልቅ ምኞት ቻይና ከአምስት ዓመት በኋላ ይህ በሁሉም ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ላይ የሚገኝን ማህበረሰብ ፈጥራ ስትመለከት እኛ እዛው “በ1997 ለኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤት የተመዘገባችሁ …” እምንልበት ቦታ ላይ እንዳንገኝ ነው።)
እዚህ ላይ የብዙዎች ጥያቄ ጥያቄ ሆኖ የመጣው “እንዴት?” የሚለው ሲሆን፤ መልሱም “በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የአሁኑን የቻይና አጠቃላይ እድገት በእጥፍ በማሳደግ” የሚለው ነው።
ቀጥለን የእስካሁኑን የቻይና አጠቃላይ እድገት እንመልከትና የ2025ቱን ከእቅዱ ተነስተን “እንተንብይ”።
የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2000 ከነበረበት በ10 እጥፍ በመጨመር ቻይናን በዓለም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ቀዳሚዋ ለማድረግ ተችሏል። በታቀደው መሠረት በ2010 የነበረውን አጠቃላይ እድገቱን በ2020 በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል። በዚህም መሰረት የአገሪቱ ጂዲፒ 100 ትሪሊዮን ዩዋን (14.7 ዶላር) በመድረስ ከዓለም ኢኮኖሚ 17 በመቶን ሊይዝ ችሏል። የአገሪቱ የከፍተኛ ሼር ድርሻ (A-Share) 10.8 ትሪሊዮን ዩዋን (1.67 ትሪሊዮን ዶላር) የደረሰ ሲሆን 12.5 በመቶ ድርሻንም (የቶታል ማርኬቱን) ይዟል። በ2020 አድርገዋለሁ ብላ ባቀደችው መሰረት የከፋ ድህነትን አጥፍታለች፤ 100 ሚሊዮን ህዝብን ከድህነት አውጥታለች። የንፁህ ሀይል (ክሊር ኢነርጂ) ፍጆታን 24.3 በመቶ አድርሳለች። ባጠቃላይ የጋራ ብልፅግናን እውን የማድረጉ (ሰነዱ moderately prosperous society, basically well-off society መፍጠር ነው የሚለው) ጉዳይ እየተሳካላት ሲሆን ይህ ሁሉ ለአሁኑ (“Xiaokang society”) እቅድ በመደላድልነት አገልግሏል።
ይህ ብቻም አይደለም፣ በ200 አጠቃላይ የህዝቧ የነፍስ ወከፍ ገቢ 32ሺህ 189 ዩዋን ($4.665) የደረሰ ሲሆን ልክ እንደላይኛዎቹ ሁሉ ይህም በ2025 በእጥፍ ያድጋል። በዚሁ ዓመት ከ1.3 ቢሊዮን ህዝቧ ውስጥ 95 በመቶው የጤና ዋስትና፤ 90 በመቶው የማህበራዊ ዋስትናው ተረጋግጦለታል። እንደ አዲሱ እቅድ ከሆነ በ2025 ሁሉም ሙሉ ይሆናል።
የአገሪቱ የባህል ኢንዱስትሪ በ2010 ከነበረበት 17 በመቶ በመምዘግዘግ በ2019 ለአጠቃላይ ጂዲፒው 4.5 ድርሻን ማበርከት የቻለ ሲሆን፤ ይህም ከአምስት ዓመት በኋላ እጥፍ ይሆናል። በ100 ፐርሰንት ያድጋል። ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ በእነዚሁ ማሳያዎች እናቁመው።
“ቻይናን ለዚህ ያበቃት መደላድል ምንድን ነው?” የሚለው የብዙዎች መነጋገሪያና የሰሞኑ የመገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተ ሲሆን፤ ከወደ ቻይና በኩል የሚሰጠው የእቅዱ ማብራሪያ በአጠቃላይ ቻይና በሯን ዘግታ መስራት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ያስመዘገበችው ፈጣን ሁለንተናዊ እድገቷና እሱን ተከትለው የተገኙት ውጤቶች መሆናቸው፤ እቅዱን ወደ ተግባር ሊለውጥ የሚችል ከፓርቲ አመራር ጀምሮ እስከመጨረሻው ባለሙያ ድረስ፤ እንዲሁም በአጠቃላይ የ7ቻይና ህዝብ ዘንድ ፍላጎቱ፣ አቅሙና ብቃቱ ያለ መሆኑ ነው።
ከዚህ አኳያ “ቻይና ይህንን አታሳካውም” ያለ አካል እስካሁን ባይኖርም ከሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አኳያ አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሱ የሚያብጠለጥሉ ወገኖች ግን አልጠፉም፤ በተለይ ከእሷ በተቃራኒ አይዲዮሎጂ ከቆመው ካፒታሊስቱ ጎራ። (በነገራችን ላይ “Xiaokang” የሚለውን ቃል ወደ አሁኑ ዘመን በማሻገር ስራ ላይ ያዋለችው ከ200 ዓመት በፊት የነበሩት የቻይና አሰላሳዮች፣ ፈላስፎች ለተመሳሳይ ዓላማና ተግባር ይጠቀሙበት የነበረውን ቃል (ጽንሰ ሀሳብ) መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም እንደዚህ አይነት ወደ ብልፅግና የሚያመሩ ጽንሰ ሀሳቦችን ብትጠቀም የት በደረሰች፤ አሰባሳቢ ሀይል/አቅምም በሆናት ነበር።)
ስር ነቀል የተባለለትንና በታሪክ የተመዘገበውን የባህል አብዮት (1966-1976) ያካሄደችው ቻይና እንቅስቃሴው፤ እንዲሁም ከአባቶች የወረሰችውና አሁንም ድረስ የምታራምዳቸው “ሕጋዊነት” (ሌጋሊዝም)ን የመሳሰሉ ጥብቅ ፍልስፍናዎች ከነበረችበት የድህነት አረንቋ ትወጣ፤ ስርአት ያለውና ሰራተኛ ህዝብ ይኖራት ዘንድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ይነገራል። ተቃዋሚዎች (በተለይ ፓርቲው) ቢኖሩትም እስካሁን ጎልቶ የሚሰማው ድምፅ እየተናገረ ያለው የአብዮቱን አዋጭነት (የቻይናን ማደግ) በመሆኑ ቻይና ስትኮራበት ነው የሚታየው።
ፈጣሪ የዛ ሰው ይበለንና የዛሬ አምስት ዓመት ደግሞ ስለእቅዱ አፈፃፀምና ስለ”Xiaokang society” እንፅፋለን። ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013