በመሰረቱ በፖለቲካ ቋንቋ “ሂሳብ አወራርዳለሁ” ማለት በግልፅ ቋንቋ “ደም ጠምቶኛል” ማለት ሲሆን ለዚህ ጥማቴም ስል የንፁሀንን ደም እስከማፍሰስ እዘልቃለሁ ማለት ነው። ጽንሰ ሀሳቡን የሂሳብ አያያዝ ሙያ ከሆነው “ሂሳብ ማወራረድ” (auditing)፤ የባህላዊ እሴት ከሆነው “መወራረድ” ፍፁም የተለየና ፅንሰ ሀሳቡን ኢሰብአዊ የሚያደርገውም ይሄው የአውሬ ፍልስፍናው፣ ተግባሩና አላማው ነው። እረኞች “እንወራረድ አህያ እንረድ” እንዲሉ መወራረድ ጤናማና ሰዋዊ ነው።
የእነ ጌታቸው “ማወራረድ” ግን አረመኔያዊና ኢሰብአዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሲሆን በመጨረሻም እራሱን ይዞት እንደሚጠፋ (የሌለውን ሂሳብ ለማወራረድ ሲኬድ ሌላ አወራራጅ አይመጣም ብሎ ማሰብ አይቻልምና) አመላካች ነው። (ስለ አህያ ከዚህ ጽሑፍ ግርጌ ያለ ውን ማስታወሻ ይመልከቱ፤)
“ሂሳብ ማወራረድ” ማለት በታሪክ “ደም የጠማው ሰው” (a bloodthirsty man) በሚል የሚታወቁትን የእነ ሂትለር ቤተሰብ አባል (በተግባር ማለት ነው) መሆንን ማረጋገጫ ማህተም ነው። ይህን ደግሞ እራሱ (ስመ ህወሀቱ ጌታቸው ረዳ) ባለቤቱ የተናገረው፤ ከመናገርም ባለፈ እያደረገው ከመሆኑ አኳያ ስለ ትክክልኛነቱ መጠራጠር አይቻልም።
ስራው ሁሉ የባንዳነት (renegade)፣ ሽብርተኝነት ነው ተብሎ እየተነገረለት ያለው ጌታቸው ረዳ – እብሪት፣ ግብዝነትና ከንቱነትን አጣምሮ በአንድ የያዘ በመሆኑ “እብሪተኛው ሰው!” (A man of vanity) የሚሉት ብዙዎች ናቸው። ነጋ ጠባ ብድግ እያለ በኢትዮጵያ ላይ በመደንፋቱ የተነሳም “A man of braggart” በማለትም ይጠሩታል። “ግብዝና ሚዛናዊነት የጎደለው ቃል አቀባይ” (He is a hypocrite and ill-balanced PR) የሚለውንም ለጌች ቋሚ መለያው ይሆን ዘንድ ያበረከቱ ባለ መርምሮ ተመልካች አይናማዎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
ጽንሰ-ሀሳቡን ከመዝገብ/ሂሳብ አያያዝ ሙያ ቦጭቆ በመውሰድ “ሂሳብ እናወራርዳለን” ባዩ ጌታቸው ረዳ ከላይ መጥነልነት የጠቀስናቸውን ሰብእናዎች የተላበሰና አገር ለማፍረስ ወገቡን አጥብቆ የተነሳ ሰው ብቻ አይደለም። ጉዳያችን አገራዊ ጉዳይ ላይ ነው የሚለው ጌታቸው ከቢቢሲው ሀርድቶክ አዘጋጅ ጋር ሲነጋገር ያለ ሟቋረጥ ዐቢይ ዐቢይ ሲል ጋዜጠኛው “ዐቢይ ዐቢይ ለምን ትላለህ፤ ዐቢይ እኮ ህጋዊ (ሌጂትመንት) መሪ ነው ….” እና የመሳሰሉትን ውርጅብኞች ቢያወርድበትም የሚያራምደው የምቀኝነት ፖለቲካን የሚመስል የግለሰብ ጥላቻ፣ የንዴት፣ የአሳማ ፖለቲካ አይዲዮሎጂ መሆኑ እስኪያስታውቅበት ድረስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ራስ ላይ አልወርድ ብሎ የማይገናኘውን ለማገናኘት ሲጥር ቆይቷል።
አንድ የትግራይ ተወላጅ አረጋዊ (የሐማሲዬኖችን አባባል ጠቅሰው) ስለ ጌታቸው “አይን አውጣው ድመት ስሙ ገብረማሪያም ነው” እንዳሉት እልም ያለ ውሸታም ነው። ይህን ውሸታም ሰብእናውን ደግሞ እዚህ መዘርዘሩ ምንም ፋይዳ የለውም፤ መለስ ብሎ እሱ እራሱ በተላዩ ጊዜያት የተናገራቸውን ማየቱ በቂ ነውና። (አቶ ጌታቸውን በይበልጥ ከህዝብ ያጣላች “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንወርዳለን” የምትለዋ እንደሆነች ልብ ይሏል።)
ከዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትና የህወሓት በገዛ ፈቃድ ወደ ኋላ መመለስን ተከትሎ በርካታ ተቃራኒና አውዳሚ አስተሳሰቦች ከጁንታው የፖለቲካ ማህፀን ሲፈለፈሉ የቆዩ ሲሆን፤ በተቃራኒው ከአንድነት ሀይሎች በኩል አፀፋው ሲሰጥ ከርሟል። ከእነዚህም መካከል፡-
“ለትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ይልቅ የሱዳን ህዝብ ይሻላል።” (ዶ/ር ደብረፂዮን)፤ “ከሱዳን የበለጠ ሽህ እጥፍ ግዜ የትግራይ ህዝብ ይበልጥብናል።” አቶ ገዱ እንዳርጋቸው ለደብረፂኦን የሰጡት መልስ፤ “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እስከ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን።” (ጌታቸው ረዳ)፤ “ኢትዮጵያን ለማዳን እስከ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን።” (የአንድነት ሀይሎች ለጌታቸው ረዳ የሰጡት ምላሽ) ወዘተረፈ።
እነዚህን ለማሳያነትና ሁሉም ሰው ጆሮ ላይ ቁጭ ብለው አሁንም አሁንም የሚያቃጭሉ፤ ሁሉም ሰው እርር ድብን ያለባቸው የጁንታው አውዳሚ አገላለፆች ከመሆናቸው አኳያ እዚህ አነሳናቸው እንጂ ከዚህ የበለጡ በርካታ አስተሳሰቦቹ እንዳሉ መታወቅ አለበት። ወደ ወቅታዊው “…ሂሳብ እናወራርዳለን” የአውሬ ፍልስፍና እንመለስ።
በአገራችን “ሂሳብ አወራርዳለሁ” የሚለው ቃል በማን እንደተጀመረ ባይታወቅም ወደ ፖለቲካው የውዝግብ፣ ጭቅጭቅና ሰጣ አገባ መድረክ ብቅ ካለ ሰንብቷል። ሰንብቷል እንበል እንጂ እድሜው ከድህረ 1983 ዓ/ም ወዲህ እጅግ የተንሰራፋው የጥላቻ፣ መጠላለፍና የዘር ፖለቲካ የፈጠረው ሳይሆን ስላለመቅረቱ መከራከር አይቻልም። ለዚህ ደግሞ በወቅቱ ጎምቱና ብርቱ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ለአንድ የሀገር ውስጥ ሚዲያ የሰጡት አስተያየት ነው።
ፕሮፌሰር (በወቅቱ ዶክተር) መረራ ጉዲና “በኢትዮጵያ የሚፈለገውን ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት የታሪክ ሂሳብ ማወራረድ ውስጥ መግባት አያስፈልግም።” ነበር ያሉት።
ከዚህ ከፕሮፌሰሩ አስተያየት በርካታ መሰረታዊ አስተሳሰቦችን ማውጣት የሚቻል ሲሆን ዋናው ግን “ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት የታሪክ ሂሳብ ማወራረድ ውስጥ መግባት አለብን(ኝ)/ወይም አለብን።” የሚል ወገን ነበር ማለት ነውና ሂሳብ ማወራረድ ከእሳቸው ንግግር በፊትም ነበር ብቻ ሳይሆን፤ በከፍተኛ ደረጃ የመወያያ፣ መከራከሪያ አጀንዳ ሁሉ እንደነበር መረዳት ይቻላል።
እርግጥ ነው የዛሬ አቋማቸውን በይፋ አናውቅም እንጂ “በኢትዮጵያ የሚፈለገውን ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት የታሪክ ሂሳብ ማወራረድ ውስጥ መግባት አያስፈልግም።” ማለታቸው ትክክል ነው። በአንድ አገር ህዝብ፣ በነበረ የአንድ የፖለቲካ ስርአት፣ በነበረ አንድ መንግስት ውስጥ ማን ከማን ነው ሂሳቡን የሚያወራርደውና ነው ሂሳብ ካላወራረድን ተብሎ አካኪ ዘራፍ የሚባለው? ሊሆን የማይችል ጉዳይ ሲሆን፤ ፍልስፍናውም የአውሬ ነው።
ህወሓት በመንግስት በኩል “በደንብ አስብበት፤ መልካም የሱባኤና የጥሞና ጊዜ ይሁንልህ” የሚለውን ታሳቢ በማድረግ የተኩስ አቁም ሲወሰድ እሱ ረጋ ብሎና አስቦ ወደ ሰላም የሚያመጣውን ፖለቲካዊ (ሶስተኛ) መንገድ እንደመፈለግና ማፈላለግ (ከውክልናው ጦርነት ባለሟሎች) ጭራሽ የሌለውን ሂሳብ ሊያወራርድ (በጩኸቴን ቀሙኝ እሳቤ) ላለፉት 50 አመታት “ጠላቴ ነው” ሲለው ወደነበረው አማራና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ዥው ብሎ ገባና የንፁሀንን ደም ዋንጫ አነሳበት። ይህ እንግዲህ ሂሳብ እናወራርዳለን ሲል የፎከረለትን አላማ ወደ ተግባር ሲቀይረው መሆኑ ነው።
“ለአፍ ዳገት የለውም” እንዲሉ ጌታቸው ረዳ ልክ እንደ ስራ ባልደረባው ሴኩቱሬ ስራው መሸርከት ነው እየተባለ መታማት ከጀመረ ሰነቧብቷል። ከጧት እስከ ማታ ከፌስቡክ እስከ ሀርድቶክ ድረስ የጌች ተግባርና ሀላፊነት ከህዝብ ጋር መጣላት፣ ወዳጅን እየቀነሱ ጠላትን ማፍራትና አገርን መካድ ነው – ይህንንም ለማስፈፀም “እስከ ሲኦል ድረስ …” እንደሚዘልቅ እለት በእለት ማስተጋባት ነው ስራው ሁሉ። (አይ ጌች እንደው ያንተ ነገር ግርም ይላል፤ ሰው እንዴት በገዛ አገሩ ላይ እንደዚህ የወገብ ቅማል ይሆናል? ጫካ ገብቶ፣ ምሽግ ቆፍሮ … ለመዋጋትም እኮ አገር ያስፈልጋል ጌች?)
“እዚህ ላይ ሒሣብ እናወራርድ ቢባል እኮ ትግራይ አትችለውም። እውነቱን እንነጋገር ካልን በትግራይ ሕዝብ ደምና አጥንት ከ46 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ሕወሓት በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ላይ የሠራው ግፍና በደል አንዲት ትግራይ ብቻ ሣትሆን መቶ ትግራዮችም ከፍለው አይጨርሱትም – ስማኝ ወንድሜ …” በማለት የፃፉትንና በጌች ላይ የተቀየሙትን ሰው ጠቅሼ ጉዳዩን የበለጠ ልለጥጠው አልፈለኩም እንጂ ጌች የሰራው (እና በኩባንያው በኩል ሊያከናውነው ያሰበው) ስራ የሚያቀባብር አይደለምና የመጨረሻውን ሂሳብ ማን እንደሚያወራርድ ወደ ፊት የምናየው ስለሚሆን ይዘለል።
ከሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ “በአገርህ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስማ፣ ክፉ አትናገር ….” ፍልስፍና ጋር አምርሮ የተጋጨው የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ልዩ አማካሪ ጌታቸውና ኩባንያው ማወራረድ ቀልድ መስሏቸው እንደ ቀልድ ይወረውሩታል እንጂ አወራርዳለሁ ሲሉ መወራረድ እንዳለ እንኳን የሚያውቁ አይመስሉም። ጉዳዩ ፈረንጆች “ቡመራንግ” እንዲሉ ተመልሶ እራስን በራስ ማጥፋትም ሊሆን እንደሚችል አልተገነዘቡትምና እውነት እውነት እላችኋለሁ ጉዳዩ ቡመራንግ ከመሆን አያመልጥም።
ጌታቸውና ባልደረባው አማራው ህወሓት ሴኩቱሬ ጌታቸው “በ45 ደቂቃ ኦፕሬሽን ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ዐመድ አደረግነው፤ በመብረቅ ፍጥነት …” ባለ በስንተኛው ደቂቃ ይሁን ቀን አላስታውስም ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ሂሳብ ማወራረዱ ይታወቃል። ከላይ የሆነ ቦታ “boomerang” ያልነው አይነት መሆኑ ነውና ጌችና ኩባንያውም የቃላት ምርጫና አጠቃቀማቸውን ከዚሁ ፐርስፔክቲቭ ቢያዩት ጥሩ ነው። (በተለይ “ጌታቸው ረዳን ብናገኘው እንደ አንድ የሕግ ሰውነቱ ስለ “Law-maker Law-breaker” ጽንሰ ሀሳብ እንዲያብራራልን እንጠይቀው ነበር” የሚሉ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመሆኑ አኳያ ጌታቸው ጊዜ ወስዶ ሊቆዝምበት ይገባል የሚል የበርካቶች ስምምነት አለ።)
ከአዲስ አበባና ኦሮማያ ልዩ ዞኖች ጋር ተያይዞ የተዘጋጀው አዲስ የከተማዋ የተቀናጀ ማስተር ፕላን መነሻነት በኦሮሞ ወጣቶች ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ አስመልክቶ፤
የተጠሩ አጋንንት ከጠሯቸው ጠንቋዮች አቅም በላይ ስለሆኑ ይህንን በተደራጀ የህዝብና የመንግስት ንቅናቄ መመከት ያስፈልጋል። ለምዝገባ ሲባል ህጋዊ የሆኑ ነገር ግን በግርግር ቤተ-መንግስት ገብተው ማደር የሚፈልጉ ፓርቲዎች በዚህ ግርግር ውስጥ አሉ። ኹከቱ ወጣቶች እና ህፃናት ብቻ ያሉበት አይደለም። የተደራጁ አርምድ ጋንጎች የታጠቁ ወንበዴዎች በየመንገዱ በየመንደሩ እየዞሩ ሁከት የሚፈጥሩበት ሁኔታ ነው ያለው። መንገድ በመዝጋት አሠልፈው በመኪና እስከ 5ዐዐ ብር ይቀበላሉ። ጋኔን የጠራው ወገን ጋኔኑን ስለመቆጣጠሩ እርግጠኛ መሆን አይችልም።
ነበር ያሉት። ጌታቸው አይናገርም፤ ከተናገረ ጥግ ድረስ ነው። ለሥነ ምግባር ጣጣ የለውም፤ ለሀይማኖቱ እንኳን አይሳሳም ወዘተ የሚሉ ሀሜት መሳይ ተግሳፆች በጌች ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ ሲሆን፤ አቶ ጌታቸው ይህ አሁንም ጭር እንዲል የሚፈልጉ አይመስሉም። ባለመፈለጋቸውም የንግግራቸውን ደረጃ ከፍ አድርገው ባዲስ መልክ (ኢትዮጵያን ማፍረስና ከዜጎች ጋር ሂሳብ ማወራረድ) ብቅ ብለዋል።
እርግጥ ነው በወቅቱ “ጋኔን” ማነው፣ “ሴይጣኑ”ስ? የሚሉና (ንግግሩን “የጋኔን ፖለቲካ” በማለት) የመሳሰሉት ከፍ ብለው ሲሰሙና ከተናጋሪው ጌታቸው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ሲጠበቁ የነበር ሲሆን ጌች በምን አይነት ታክቲክና ቴክኒክ እንዳለፉት ባይታወቅም መልሱ ሳይመለስ የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሓት ጋር ሂሳቡን በፖለቲካዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ አወራርዶ ፍቺ ፈጽሟል። ምን ያደርጋል፤ ላም እሳት ወለደች . . .
**************
(ጌታቸው ወልዩ በፌስቡክ ገፁ “በበርካታ ጥናቶች እንደተረጋገጠው አህያ ሁለገብነት (versatility)፣ ቆራጥነት (determination)፣ ጉልበት ያለውና ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆነ (will power dedication towards work and devotion)፣ በጣም ጠንካራ ሠራተኛ (very hard working)፣ በጣም ታማኝ (very loyal)፣ ከፍተኛ ብልሃት የሚታይበት (highly intelligent)፣ ለማመን የሚከብድ ከፍተኛ የሆነና እስከ ዕድሜ ዘመኑ የማስታወስ ችሎታ ያለው (incredible/ excellent memory)፣ ለአየር ፀባይ እውቂያ ቅርበት ያለው (ቀዳማዊ ኀይለ-ሥላሴ ስለ እንጦጦ አህዮች ተናገሩት የተባለውን ያስታውሷል) እና በሁሉም መልክዓ-ምድር/የመሬት አቀማመጥ መጓጓዝ የሚችል (all terrain animal) ታማኝ አገልጋይ ነው።” በማለት ያሰፈረውን ልብ ማለት በመግቢያችን ስለ ተነገረው ተረትና ምሳሌ በሚገባ ለመገንዘብ ይረዳል።)
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013