በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
ዛሬ በትህነግ ጭፍራዎች የተናበበ፣ የተቀነባበረና የተቀናጀ ዘመቻ በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ በጊዜያዊነት የጠለሸውን የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ገጽታችንን እንዲሁም እውነትንና ፍትሕን በፈጠራ ትርክት ለማዳፈን እየተሸረበ ያለውን ሴራ ባሰብሁ ቁጥር ምን አልባት የለውጥ ኃይሉ የሚሰጡ አንዳንድ አስተያየቶችንና ጥቆማዎችን ጆሮ ሰጥቶ ቢያዳምጥ ኖሮ ጉዳቱን መቀነስ ይችል ነበር ይሆን !? በሚል ቀናነት ጀግናው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት መቐሌን በተቆጣጠረ ሰሞን በዚሁ ጋዜጣ ቀጣዩ አውደ ውጊያ የፕሮፓጋንዳው ግንባር መሆን አለበት በሚል ለመጠቆም የሞከርሁበትን መጣጥፍ ሳልጨምር ሳልቀንስ እንዲህ አቅርቤዋለሁ።
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከስግብግቡ የትህነግ ጁንታ ጋር ተገደን የገባንበት ጦርነት በአውደ ግንባር ብቻ የተወሰነ አይደለም ። በእፉኝቱ ትህነግ ስፖንሰር ከሚደረገው ተልዕኮና ስምሪት ከሚሰጠው ዲጂታል ወያኔ ህልቁ መሳፍርት ከሌለው የሀሰት መረጃና ሆን ተብሎ ከተዛባ መረጃ ጭምር እና የሴራ ኀልዮት ጋር እንጂ። ይህ የከሀዲና የሌባ ስብስብ ከ27 ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኋላ በህዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሉ ከመንበሩ ከተፈነገለ በኋላ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጎ 24 ሰዓት የውሸት፣ ሆን ተብሎ የተዛባና የሴራ ኀልዮትን ፍላጻ ሲያንበለብል ባጅቷል። በዚህም በሀገሪቱ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል።
ንጹሐን ተገድለዋል። ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ በስግብግቡ የትህነግ ከሀዲ ቡድን ግፍ መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲንቀሳቀስ እና ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባ የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ወናፍ በተናበበና በተቀናጀ አግባብ በማህበራዊና መደበኛ ሚዲያ የሀሰትና የተዛባ መረጃውን እያራገበ ይገኛል። ጦርነቱን እራሱ ለኩሶ እያለ የተወረርሁ ድቤውን ይደልቃል። ያልታጠቀውን መሳሪያ ታጥቄያለሁ፤ በሰማዩ እንዳሻው ፈንጭቶ ወታደራዊ ኢላማውን መትቶ የተመለሰን ተዋጊ ጀት መትቼ ጣልሁ፤ ወዘተረፈ አይነት ነጭ ውሸቶችን በፎቶ ሾፕና በቪዲዮ እያቀናበረ በመላው ዓለም በተበተኑ ጭፍራዎቹ አማካኝነት እየነዛና እያራገበ ይገኛል።
በማህበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያው ሀሰተኛው፣ የተዛባው ሆነ አሳሳቹ መረጃ የትየለሌ በመሆኑ ሕዝብ በአሰስ ገሰስ የመረጃ አረንቋ መዋጡን ለማረጋገጥ የትህነግ ምንደኛ የፕሮፓጋንዳ ጭፍራ ማህበራዊ ሚዲያውንና ዘርፎ ያቋቋመቸውን መደበኛ ሚዲያውን እንዴት በውሸት እንዳጥለቀለቀው መመልከትና መረዳት ይችላል። ከጦርነቱ ይልቅ የመረጃ አውደ ውጊያው አየሩን፣ ምድሩንና መልካው ብቻ ሳይሆን ቨርቹዋል የሆነውን ዲጂታል ዓለምንም አዳርሶታል ።
ይህ አልበቃው ብሎ በሴራ ኀልዮት እያወናበደ ይገኛል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሴረኛውን የትህነግ ወታደራዊ ቡደን ውሸትና ቅጥፈት ጠንቅቆ የሚያውቀው ቢሆንም ጥቂት የዋሆችን ማቄሉና ማሞኘቱ አልቀረም ። በአለማቀፉ ማህበረሰብና ሚዲያም መጀመሪያ አካባቢ መደናገር ፈጥሮ እንደነበር ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን የወጡ ዜናዎችንና መግለጫዎችን መለስ ብሎ መቃኘት ይበቃል ።
የውሸት፣ የተበረዘና የተዛባ መረጃ እና የሴራ ፖለቲካ አይደለም ፖለቲካዊ ግንዛቤያችን ዝቅተኛ ለሆነው እና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላላቆምነው ይቅርና ለአሜሪካና ለምዕራብ አውሮፓም ፈተና ሆኗል። የ2016ቱን የአሜሪካ ምርጫ ፣ የእንግሊዝ ከሕብረቱ የመነጠል ሕዝበ ውሳኔን፤ የአሜሪካ 2020 ምርጫ፤ ወዘተረፈ ያስታውሳል። በዚህ ምርጫ ጮህ ብለው ከተሰሙ የሴራ ኀልዮት /conspiracy theory /” ዲሞክራቶች ግራ አክራሪ ሶሻሊስት እና የባዕድ አምልኮ ተከታይ ናቸው። “ የሚሉት ይገኙበታል።
የኩባን ሶሻሊዝም ሸሽተው በፍሎሪዳ በብዛት ነዋሪ የሆኑ ኩባ አሜሪካውያን ትራምፕን የመረጡት ከፍ ብዬ የገለጽሁትን የሴራ ወሬ አምነው እንደሆነ ሲኤንኤን በምርጫው ሰሞን አውርቶናል። ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ሽንፈቴን አልቀበልም የሚሉት ራሳቸው አበክረው ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል ሲሉ ያሟረቱትን ሟርት ሴራ ሰበብ አድርገው ነው። እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ትራምፕ ከ20ሺህ በላይ ውሸቶችን በመዋሸት የነጩን ቤተ መንግስት ጥላሸት ቀብተውታል። እሳቸው መች በዚህ ያበቁና እለት በእለት በቲዊተር ገጻቸው በሚያዥጎደጉዱት የሴራ ኀልዮት የተነሳ በአሜሪካውያን መካከል መከፋፈልን ፈጥረዋል። የምርጫው ሒደትና ውጤት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። በአሜሪካ የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ ከአንድ ጊዜ በላይ ምርጫ ያስፈልጋል ያሉት 44ኛው የአሜሪክ ፕሬዝዳንት ፤ በገደምዳሜ የሚቀጥለውን የ2024 ምርጫም ዲሞክራቶች ማሸነፍ አለባቸው ማለታቸው ነው ።
ባራክ ሁሴን ኦባማ “ዘ ፕሮሚስ ላንድ “ የተሰኘውን አዲሱን መጻፋቸውን በሚያስተዋውቁበት በዚህ ሰሞን በቢቢሲ አርት የታሪክ ሊቅ ከሆነው ዴቪድ ኡሉሶጋ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በአንድ የምርጫ ጊዜ” የእውነትን መበስበስ “ ማስቀረት አይቻልም ። እንግዲህ የዴሞክራሲ ዋስና ጠበቃ በሆነችው እና የዴሞክራሲ ተቋማት በአስተማማኝ መሰረት የገነባችው አሜሪካ “እውነት” እንዲህ ፈተና ውስጥ ከገባች ዲጂታል ወያኔ 24 ሰዓት የሚረባረብባት የእኛ “እውነት“ በምን ጎኗ ትችለዋለች። አሜሪካ በዜጎቿ መካከል ልዩነትን በመጎንቆል ላይ የሚገኘውን የሴራ ኀልዮት የመቀልበስ ትልቅ ኃላፊነት ከፊት እንደሚጠብቃትም ፕሬዝዳንት ኦባማ ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት ተንቦርቅቋል።
በእንቅርት ላይ እንዲሉ በማንነት ላይ ለምትንጠራወዘው ሀገራችን የሴራ ኀልዮት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በተግባር እያየነው ነው። በተለያዩ ምክንያቶች በዜጎች መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚደረገው ጥረት ለአንድ ወገን ብቻ ማለትም ለፖለቲከኞች ወይም ለመንግስት የሚተው ሳይሆን የመላ ዜጋውን ተሳትፎ፤ መዋቅራዊ ለውጥ እና በዜጎች መካከል የመደማመጥ ባህልን ማጎልበት እንደሚጠይቅ ፕሬዝዳንት ኦባማ ይመክራሉ ።
የሴራ ኀልዮት፣ ሚስ ኢንፎርሜሽን እና ዲስኢንፎርሜሽን እርስ በእርስ የሚመጋገቡና የሚናበቡ ሁነቶች ናቸው። ሚስ_ና_ዲስ ኢንፎርሜሽን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ስለሚመስል እየተተካኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል። ብያኔአቸው ግን ለየቅል ነው። ሚስኢንፎርሜሽን የተሳሳተ ወይም አሳሳች መረጃ ሲሆን ዲስኢንፎርሜሽን ደግሞ እውነትን ለመሸፋፈን ወይም የሕዝብ አስተያየት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሆን ተብሎ የሚነዛ የሀሰት መረጃ ነው።
እፉኝቱ ትህነግ በፕሮፓጋንዳ ጭፍራው አማካኝነት ስልጣን ላይ እያለም ሆነ ከተፈነገለ በኋላ አሳሳች፣ እውነት የሚያጠየም እና የሴራ ኀልዮትን እያዛነቀ ሌት ተቀን እየባዘነ ይገኛል። በተለይ በሰሜን ዕዝን አረመኔያዊ ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከወሰነበት ደቂቃ አንስቶ ምን አልባት በየዕለቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀሰተኛ፣ እውነትን የሚበርዙና የደባ መረጃዎችን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያ እያንበለበለ ይገኛል። በጀግናው የመከላከያና የሚሊሻ ኃይሎች በቀናት አውደ ውጊያ ድባቅ ሲመታ ያለ የሌለ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና የዘረፈውን ሀብት ለፕሮፓጋንዳ ማሽነሪው እያዋለው ይገኛል።
ለመሆኑ የሴራ ኀልዮትስ ምንድን ነው !? ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ባለስልጣናት አልያም የተወሰኑ የፖለቲካ፣ የአይዶሎጂና የኢኮኖሚ ቡድኖች ሚስጥራዊ ዕቅድ ውጤት የሆነ ሁነት ወይም ክስተት የሴራ ኀልዮት Conspiracy Theory ሲል ይበይነዋል የእንግሊዘኛው መዝገበ ቃላት ሜሪያም ዌቢስተር። ( A theory that explains an event or situation as the result of a secret plan by usually powerful people or groups .) የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሰናዳው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ፤ አድማን ፦ ሴራ ዱለታ ፤ ሲል በአጭሩ ይተረጉመዋል ።
ሆኖም በባለስልጣናት፣ በመንግስት ሆን ብሎ ጉዳት ለማድረስ በሚስጥር የሚፈፀም ደባም የሴራ ኀልዮት ነው ሲሉ ድርሳናት ትርጉሙን ሰፋ ያደርጉታል። ታዋቂው የፖለቲካ ሊቅ ማይክል ባርኩን በበኩሉ ኀልዮቱ አፅናፈ አለም universe በአፈተት በአቦሰጥ ሳይሆን በንድፍ design ትመራለች በሚለው ተረክ ላይ የተዋቀረ ነው ሲል ይሞግታል።
እንደ ባርኩን ትንተና የሴራ ኀልዮት 3 መገለጫዎች አሉት። የመጀመሪያው ምንም ነገር በአጋጣሚ አይሆንም። ሁለተኛው ደግሞ ምንም ነገር ላይ ላዩን እንደምናየው ፣ እንደመስለን አይደልም ። ሶስተኛው ደግሞ ሁሉም ነገር እርስ በርሱ የተያያዘ ነው ብሎ ያምናል። ሌላው የኀልዮቱ ባህሪ ይላል ባርኩን ውሸት መሆኑን በመረጃ ለማስተባበል ፈታኝ መሆኑ ነው።
የኀልዮቱ መነሻ የመሪዎች ግድያ ሲሆን ዘመኑም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ መሆኑ ድርሳናት ያትታሉ። ከእያንዳንዱ ክስተት ጀርባ ሴራ ደባ አለ በማለት በዜጎች በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን የሚቀፈቅፍ ኀልዮት ነው። በታላቁ መፅሐፍ ፦
“ በእግዜአብሔር እናምናለን ። “እና “ አይኖቹ በምድር ሁሉ ያያሉ።” ከሚለው ቅዱስ ቃል ላይ ተመስርቶ በአሜሪካ የአንድ ዶላር ላይ ፈጣሪ ሁሉን እንደሚያይ ፤ አሜሪካ በቅጥሩ በጥበቃው ስር እንደሆነች የሚወክለውን ምስል ( the all seeing eye ) ሳይቀር በአሜሪካ መስራች አባቶች የተሸረበ ሴራ ተደርጎ መቆጠሩ ኀልዮቱ ምን ያህል ጥርጣሬን ለመዝራት ምን ያህል ምቹ እንደሆነ ያሳያል። አንዳንድ የስነ ልቦና ሊቃውንት ኀልዮቱ በማኪያቬሊያዊ ፅንሰ ሀሳብ በዜጋውና በሕዝብ መካከል ፍርሀትን በመንዛት ላይ ያተኮረ መሆኑን ይተነትናሉ።
በአለማችን በሴራ ኀልዮት አብነትነት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል የአሜሪካዊ 35ኛ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ላይ የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ ) እጁ አለበት። እ.አ.አ. በ1971 አፓሎ የተሰኘች የአሜሪካ መንኮራኮር ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ማረፏን የሚክደው እንዲሁም በተለምዶ በ9/11 አልቃይዳ በዓለም የንግድ ድርጅት ህንፃዎች ፣ በፔንታጎንና በመንገደኞች አውሮፕላን ከ3ሺህ በላይ አሜሪካውያንና የውጭ ዜጎች ባለቁበት የሽብር ጥቃት አሁንም ሲ አይ ኤ ተሳትፎበታል።
ኤች አይ ቪ/ኤድስን አሜሪካ ነች ጥቁሮችንና ሌሎች ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የፈጠረችው እና የእንግሊዟን ልዕልት ዲያና ፈረንሳይ ፓሪስ በመኪና አደጋ የሞተችው በሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ኤም አይ 6 እና በንጉሳዊ ቤተሰቡ ሴራ ነው የሚሉ ይገኙበታል።
እንደ መቋጫ
እውነተኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የተጋነኑና በማህበረሰቡ ዘንድ ሽብር የሚለቁ መረጃዎችን መከላከል ይቻላል ። መንግስትም ሆና ባለድርሻ አካላት ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎችን ከስር ከስር የማድረስ ኃላፊነት አለባቸው ። እግረ መንገድ ሕዝብን ካልተገባ ፍርሀትና ውዥንብር መከላከል ይቻላል። ዳሩ ግን ትክክለኛ መረጃን የማድረስ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑ ሊጤን ይገባል። አንድ መረጃ ከማጋራት ወይም ከመለጠፍ በፊት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይሁን ለሌላ ተግባር በምንጭነት ከመጠቀም በፊት ከሌሎች ምንጮች ጋር ማመሳከር የተቀናጀ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀም ሰዎች ስለምናጋራው ጹሑፍ ፣ ምስልና ድምፅ ቆም ብለን ማሰብ፣ ለዋቢነት፣ ለአጋዥነት ስለምንከፍተው ድህረ ገፅ፣ ጦማር ታማኝ ምንጭ መሆን አለመሆን ማጣራት በማስከተል አስተያየት ( ኮሜንት ) ከመስጠታችን በፊት ማውጣት፣ ማውረድና ማመዛዘን ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን ሀሰተኛ ፣ የተዛባና የጥላቻ መረጃ ዘርጋፊዎችን ፣ ነዥዎችንና ለፋፊዎችን በሒደት ማስቆም እንችላለን።
መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከወሰነ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት ከጎኑ ከመቆሞ ባሻገር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እና ግምቱ ቀላል ያልሆነ የአይነት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን እንዳረጋገጠው ሁሉ በውጭም በአገር ቤት ያሉ ዜጎች በተወሰነ ደረጃ የዲጂታል ወያኔን ፕሮፓጋንዳ እየመከቱ ቢሆንም ፤ እውነትን ይዞና ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ ሀገርና ሕዝብ ለዛውም ከትህነግ ጋር ለሚደረግ የጸረ ፕሮፓጋንዳ ትግል ሁሉም ዜጋ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ሊንቀሳቀስና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሚሊሻ በጦር ግንባር ያስመዘገበውን አንጸባራቂ ድል እኛ በእሱ መስዋዕትነት በሰላም እየኖርን በእጅ ስልካችንና በኮምፒዩተር ቁልፎች የምንደኛውንና የቅጥረኛውን የዲጂታል ወያኔ ጭፍራ ፕሮፓጋንዳ መክተን የፕሮፓጋንዳ አውደ ውጊያውን ማሸነፍና የጀግናው ሰራዊታችንን አኩሪ ድል መደገምና ማህበራዊም ሆነ መደበኛ ሚዲያውን በሀገር ፍቅር ሱናሚና በአርበኝነት ማጥለቅለቅ ይጠበቅብናል ።
ለሀገራችን ሁላችንም አምባሳደር ፣ ጋዜጠኛና ሕዝብ ግንኙነት ነንና። ይህ ዘርፈ ብዙ ጦርነት በድል እስኪደመደም ሁላችንም የእውነት፣ የፍትህና የሉዓላዊነት ሰራዊት መሆን አለብን። ለዚህ ክቡር ዓላማ የህይወት መስዋዕትነት ብንጠየቅ እንኳ ወደኋላ የማንል ጊዜያችንን፣ እውቀታችንንና ገንዘባችን ሰውተን የድሉ ተቋዳሽ መሆን ይጠበቅብናል።
እዚህ ላይ ሳላነሳ የማላልፈው መንግስት ጊዜ ሳያጠፋ የተጣራ መረጃ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሚዲያዎች የሚያደርስ፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ፤ “ማቋቋሙና ሰው መመደቡ የዲጂታል ወያኔን ፕሮፓጋንዳ በተወሰነ ደረጃ መመከትና በዓለማቀፍ ማህበረሰቡና በምዕራባውያን ዘንድ የነበረውን ብዥታ ማጥራት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሆኖም መረጃ የማጣራቱ ተግባር ለዚህ አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉም የመንግስት ሚዲያ መረጃ የማረጋገጫ / ፋክት ቼክ / ክፍል ሊያደራጅ ይገባል። በዘመነ ማህበራዊ ሚዲያ ሚሰና ዲስ ኢንፎርሜሽንና እና የሀሰት ዘገባን ተከታትሎ ማምከን የሚቻለው እውነትን የማጣሪያና የማረጋገጫ ራሱን የቻለ ክፍል ሲኖር ነውና። ዜጋውም የዚህ አካል ሊሆን ይገባል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና እውነተኛ ዜጎች ታፍራና ተከብራ ለዘላለሞ ትኑር !
አሜን።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013