ፍቅሬ አለምነው
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለረዥም ዘመን ሲኩራሩበት ከነበረው ተአማኒነት፤ ተጠያቂነት፤ ግልጽነት፤ ሚዛናዊነት የሚለው የይስሙላ ጭንብላቸው ማታለያና መነገጃ መሆኑ ይፋ እየወጣ መጥቷል። ድሮም በተልእኮ የሚሰሩ የወደዱትን የሚክቡ የጠሉትን እስከ መቃብር የሚያሳድዱ ናቸው።
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የአንድ ወገን ድምጽ ልሳን ፖለቲካና ኢኮኖሚ አላማ ማራመጃ ጥቅማቸውን ማስፈጸሚያ ማስከበሪያ መሣሪያዎች ናቸው። ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ምንም ይሁን ምን እውነትን ይያዝ አይያዝ ፤ግፍ ይሰራ አይሰራ፤ በደል ይፈጸም አይፈጸም፤ ረብጣ ዶላር እስከተከፈላቸው ድረስ በሀገራትና በመንግሥታት ላይ ከእውነቱ ውጪ ይዘምታሉ። ጦር ይሰብቃሉ። ይወጋሉ። ያዋጋሉ።
የእነሱን ፍላጎት የማይጠብቅ መንግሥትና ሀገር ከሆነ ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው በስም ማጥፋትና ማጠልሸት አልፎም ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲያጣ ይዘምቱበታል። በዚህም አያባሩም። በበርካታ ሀገራት እንደታየው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ጦር አዝማች ሆነው በመቀስቀስ ዜና ዘገባዎችን በመስራት የዘመቻ መኮንን በመሆን አገርና ሕዝብ ያስደበድባሉ።ሕዝብን ለስደት አገርን ለውደመት የዳረጉ ፤የኃያላን መንግሥታትን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆሙ መሣሪያዎች ናቸው። ስለሚዲያና ፕሬስ ነጻነት ሚዛናዊነት የሚያወሩት ሁሉ የገዘፈ ቅጥፈትና ውሸት ነው።
በእብሪት አብጦ የነበረው ራሱ ጦር ሰብቆ በኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጦርነት ከፍቶ ወታደሮቻችንን በግፍ በአረመኔነት የጨፈጨፈው የትህነግ ጁንታ በተወሰደበት የአጸፋ እርምጃ ድባቅ ተመቷል። ዛሬ በትግራይ መሬት ለተከሰተው ምስቅልቅል ሁሉ ከጁንታው በላይ ተጠያቂ የለም። ሕዝብን የከፋ ችግርና የጦርነት እሳት ውስጥ የማገደው እብሪተኛውና ደንቆሮው ጁንታ ነው።ለብዙ ሺህ ሕዝብ መፈናቀል መሰደድ ምክንያት የሆነው፤ በሰላሙም ቀን ሴቶችን ሲደፍር ወንዶችን ሲያኮላሽ የተመዘገበ ታሪክ ያለው ሰው በላው ጁንታው ትሕነግ ነው።
በአማራውና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ስውርና ግልጽ የዘር ማጥፋት አውጆ ሲገድል ሲረሽን ፤ሲገርፍ፤ ሲያሰቃይ የኖረው በጨካኝነቱ አቻ የሌለው ይኸው የአረመኔ ቡድን ነው። ከመቀሌ ጀምሮ በትግራይ የተለያዩ ቦታዎች ሀገሬ ብሎ እነሱኑ ሲጠብቁ የኖሩትን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ድንገተኛ ወረራ ፈጽሞ መሣሪያ ዘርፎ የገደላቸው ልብሳቸውን አስወልቆ በባዶ እግራቸው እንዲሄዱ ያደረገው፤ በሴት ወታደሮች ላይ በጭካኔ የተሞላ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈጸመው ጁንታው ነው።
በትህነግ ጁንታ የተጨፈጨፉት የተረሸኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች ነው። ጁንታው በታሪክ ይቅር የማይባል ወንጀል ግፍ በደል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ፈጽሟል።
የሀገር ሕልውናን የሚፈታተን ወንጀል በፈጸመው ወንበዴና ሽፍታ ቡድን በሆነው ጁንታ ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ግዴታውን ተወጥቷል። በአጭር ግዜ በተካሄደው ውጊያ የትህነግን ወታደራዊ እብሪት አስተንፍሶ አከርካሪውን ሰብሮ ሕግና ስርዓት እንዲከበር አድርጓል።
እንዲህ አይነቱን ድርጊት የትኛውም መንግሥት አይታገስም። ጁንታው በሥልጣን ላይ በነበረበት ሰዓት በዘረፈው የኢትዮጵያ ገንዘብ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን አክቲቪስት ቅጥረኛ ነጮችን በብዙ ሺህ ዶላር እየከፈለና እየገዛ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ እንደበደለ፤ ግፍ እየተሰራ እንዳለ፤ የዘር ማጥፋት እንደተካሄደ አድርጎ የሚነዛው የሐሰት ፕሮፓጋንዳና የሚያስተጋቡት ውሸት ተቀባይነት የለውም። ጁንታው ራሱን ንጹህና ተበዳይ አድርጎ ለዓለም ሕብረተሰብ ለማሳወቅ የሀሰት ዶክመንተሪ እስከ ማሰራትና ማሰራጨት ደርሷል። አጥብቀን ልንታገለው ይገባል።
ከበቂ በላይ የሰነድና የሰው ማስረጃዎች ፤ግፍ የተፈጸመባቸው ወታደሮችም ሆኑ ሲቪሎች ሞልተው የተረፉ ቢሆንም በመንግሥት በኩል ይሄንን የማጋለጥ ስራ በተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች በስፋት አልተሰራም። ዶክመንተሪ አልተዘጋጀም። በሀገር ውስጥ ያሉትም ዋነኛ ሚዲያዎች እነ ሸብ ረብ እለታዊ ዜና ዘገባ ክዋኔዎችን ከመሸፈን የዘለለ በተጠናከረ ማስረጃ የጁንታውን ሴራና ወንጀለኛነት የሚያጋልጥ ሥራ ሲሰሩ አይታዩም። የጁንታው ደጋፊዎች ጭምብል አጥልቀው የበግ ለምድ ለብሰው ያደቡ ተኩላዎች በመንግሥታዊ መዋቅሩ በቢሮክራሲው ውስጥ ዛሬም ተሰግስገው ይገኛሉ።
አዲስ አበባ በመንግሥት ቤት እየኖሩ በመንግሥት በጀት እየተንቀሳቀሱ የተለመደውን የስለላ ስራቸውን እየሰሩ ለውጭ ሚዲያዎችና ለኤምባሲዎች ጁንታውን ደግፈው መረጃ ሲያቀብሉ ሲያስተላልፉ ከውጭ መጡ ለተባሉት 9 ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የተሳሳተ መረጃ ምንጭ በመስጠት ሲሰሩ ውለው ያድራሉ።
ከትግራይ ውጪ ዋነኛው የጁንታው የኢኮኖሚ ጉልበትና ምንጭ፤ የፖለቲካና የስለላ ኃይሉ አባላቱ በስፋት ያሉት አዲስ አበባ ነው። ይሄ የተረሳ የተዘነጋ ጉዳይ ይመስላል። ውሎ አድሮ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም። ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቃለመጠይቅ የሚደረጉ የራሳቸውን ሰዎች ምን ምን መናገር እንዳለባቸው ጭምር አስቀድመው በማዘጋጀት ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ የተዛቡ እኩይ መልእክቶችን እንዲያስተላልፉ የሚያደርገው ይኸው አዲስ አበባ ያለው ኃይል ነው።
በዚህም ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም መንግሥትና ሕዝብን የማጠልሸቱን ሥራ በስፋት ተያይዘውታል።
እነቢቢሲ፤ ሲኤንኤን፤ አልጀዚራ፤ ዶቼቬሌ፤ አጃንስ ፍራንስ፤ አሶሽየትድ ፕሬስ በሀገር ውስጥ እንደ ልብ እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው እውነቱን እንዲረዱ ነበር። እነሱ ግን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ እየዘመቱ የፈጠራ ወሬ እያሰራጩ ይገኛሉ። በገንዘብ የተገዙ ቅጥረኛ ሚዲያዎች ናቸው። ሀገራችንን ለቀው ሊወጡም ይገባል።
እነዚሁ ሚዲያዎች ናቸው ለበርካታ ሀገራት መፈራረስ መበታተን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መግባት በዚህም የየመንግሥታቸውን ድብቅ ብሔራዊ የፖለቲካ አጀንዳ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ የኖሩት።
የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ መፋጠን ሊያልቅ በመቃረቡም ደስተኞች አይደሉም። የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አይፈልጉም። ጁንታው በነዚህ የሚዲያ ተቋማት ሁሉ ስልጣን ላይ በነበረበት ሰዓት የራሱን ሰዎች አስቀጥሮ ቦታ አስይዟል። ዛሬ ለጁንታው ወግነው ኢትዮጵያንና ልጆቿን የሚወጉትም እነሱው ናቸው።
በአጭሩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚባሉት በሌሎች ሀገራት እንደለመዱት ኢትዮጵያን ተረኛ ኢላማ አድርገው ለማፈራረስ ለመበታተን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህን ሥራ የሚሰሩት በከፍተኛ ደረጃ በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ገንዘብ በመደገፍ ሲሆን በእቅድ እየተሠራ ያለ ስራም ነው።
ሚዲያዎቹ የፈጠራቸውና የሚያስተዳድራቸውን ባለሀብት ፍላጎትና ጥቅም ማስጠበቂያ መሣሪያዎች ናቸው። የፕሬስ ነጻነት የሚለው የምእራባውያን ፌዝና መራራ ቀልድ የሚጠቅመው የእነሱን ብሔራዊ ጥቅም አላማና ፍላጎት እስካስከበረ ግዜ ድረስ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ አይታሰብም። እንዲኖርም አይፈቀድለትም።
ሚዲያዎች ያውም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ የሚባሉት ሁሉ የየመንግሥታቸው ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅም ማስከበሪያ መሣሪያዎች ናቸው። እያንዳንዳቸው በሀገራቸው መንግሥት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት መርህ ተቀርጸው ነው የሚንቀሳቀሱት።ተላላኪዎቻቸውን በየሀገሩ እያሰማሩ ዓለምን እያመሱ ኖረዋል። ዛሬ ደግሞ ፊታቸውን ወደ እኛ አዙረው እየወጉን እያደሙን ይገኛሉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ዘረኞችን ፋሽስቶችን ደግፎ ስለሰብዓዊ መብት ሊያወራ ሞክሯል። ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ሠራዊት በጁንታው ሲገደል ሲጨፈጨፍ፤ ሴቶች ሲደፈሩ፤ በግፍ ገደል ሲወረወሩ ጁንታው በአማራውና በኦሮሞው ላይ የዘር ማጥፋት ሲፈጽም አውደልዳዩ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ማፈሪያ ድርጅት የት ነበረ ?አንሰማችሁም። አምነስቲ ኢንትርናሽናልም ሆነ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተብዬዎቹ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አያገባቸውም። እየገቡ እንዲያቦኩ እንዲፈተፍቱም አንፈቅድም። ኢትዮጵያ በእነሱ የተለመደ ሴራ አትፈርስም። ድንቄም ዓለም አቀፍ ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች !
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013