ሰላማዊት ውቤ
እንኳን የኢትዮጵያ ዋና መዲና አዲስ አበባ ላይ ይቅርና ክልል ከተሞችም የቤት ኪራይ ዋጋ አይቀመስም። በአንድ ሺህ ብር የሚገኝ ምንም ዓይነት ቤት የለም። አተኩረው ሲመለከቷቸው ይዘታቸው ‹‹በጫት እንጨት የቆሙ ላስቲክ የተከናነቡ›› የሚመስሉት ቤቶች ከሁለት ሺህ በታች አይጠራባቸውም። የዋጋውን ነገር በመወሰን ባለቤቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ደላሎች ትልቅ ሚና አላቸው። መቀነስ ላይ ሳይሆን መጨመሩ ላይ። የወሩን ክፈሉና ግቡ ሊሉ ሳይሆን የሶስት ሲላቸውም የስድስት ወር የቤት ኪራይ አስከፍለው የድርሻቸውን ሊያግበሰብሱ። በዚህ መልኩ ተከራይ የት ልግባ እሚልበት ደረጃ ደርሷል። የዛሬው አነሳሳችን ግን ስለ ተከራዮች ሳይሆን አከራዮች ነውና ከተከራዮች አንደበት የሰማነውን እንደሚከተለው ከትበነዋል።
ወጣት ሳራ ግርማቸው አዲስ አበባ ውስጥ መገናኛ አካባቢ ተከራይታ ነው የምትኖረው ። የተከራየችው ቤት ‹ውስጥ መገናኛ› እየተባለ ሰርክ በታክሲ ረዳቶች ሲጠራ የሚሰማው አካባቢ ነው የሚገኘው። እዚህ ቤት ከገባች ሦስተኛ ወሯን ይዛለች። ከመግባቷ በፊት የነበረችበት ቤት እዚሁ አሁን ያለችበት መንደር አካባቢ በግምት ከ300 ሜትር ርቀት ላይ ነበር። የአከራዩዋ ነገር ምርር እንዳላት ያጫወተችኝ ፊቷ ይሄ ቤቷ ለመገናኛ አካባቢ በስድስት ዓመት ውስጥ 10ኛዋ ነው። አንድ ቤት ውስጥ አንድ ዓመት መቀመጥ አልቻለችም። ቶሎ ቶሎ የምትለቅበት ምክንያት ደግሞ የአከራዮች ፀባይ ስለማይመቻት መሆኑን ትናገራለች።
በእርግጥ ከአከራይ ጋር ባደሙባት ተከራዮች ምክንያት ከ10ሩ ቤት ሁለቱን ቤት የለቀቀችበትም ሁኔታ አለ። እዚህ ቤት ከመግባቷ በፊት ለስድስት ወራት የተቀመጠችበትን በአካባቢው ያለ ቤት በተከራይ ምክንያት ነው የለቀቀችው።ሥራ ስለሌላት እቤት ውስጥ ነው የምትውለው። ኪራዩንም የሚከፍልላት ጓደኛዋ ነው። አንዷ እንደ እሷ የቤት እመቤት የሆነች ተከራይ ታድያ የአከራይዋን እግር መውጣት ደግሞም በር ዘግተው መተኛታቸውን ጠብቃ ዘወትር ወደ ቤቷ ትመጣለች። ተኝታም ቢሆን አንኳኩታ አስነስታት ትገባና የባጥ የቆጡን ስትቀባጥር ታመሻለች። ቀንም ቢሆን እንዲሁ ስታደርግ ነው የምትውለው። የዛሬ ሦስት ወር ግድም አከራይዋ ድንገት ከውጪ ሲገቡ ቤቷ ውስጥ ያገኝዋታል። በእርግጥ አከራይዋ ለሁሉም ተከራይ ገና ከመግባታቸው በፊት አንዱ ተከራይ ሌላው ተከራይ ቤት ውስጥ እንዳይገባና ቡና ከመጠጣጣት ጀምሮ ድንገት ሲገናኝ የእግዚአብሄር ሰላምታ ከመለዋወጥ ውጪ ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። ይሄን አፍርሰው በመገኘታቸው ወድያውኑ ሁለቱንም አባረሯቸው ።እንደ አጋጣሚ አሁን ያለችበት ቤት ሲለቀቅ አይታ እሷ እዚህ ገባች። እዚህ ደግሞ የገጠማት ችግር ድራማ ነው የሚመስለው።
አከራዮቹ የሚኖሩት ከግቢ ውጪ ነው። ታድያ ቀንና ሌሊት ግቢውን የሚቆጣጠረውና ከእሷ ጋር ክፍሉን ግድግዳ የሚለየው ተወካያቸው ክፍሉን በአካባቢው ላሉ አንዳንድ ወጣቶች ለአልባሌ ነገር አሳልፎ ሥራ ያከራየዋል። እሱም ራሱ አንዳንድ ኢ-ሥነምግባራዊ ሥራዎቹን ይከውንበታል። በዚህ ምክንያት ሰላሟ ስለሚደፈርስ ድርጊቱን ላለማየት ቀኑን ከቤት ውጪ የምታሳልፍበት ሁኔታ ገጥሟታል። በተለይ ሌሊት መተኛት ባለመቻሏ ቤቱን ለመቀየር የተገደደችበት ሁኔታ ላይ ደርሳለች። ቢሆንም የኪራይ ቤት በቀላሉ ማግኘት አልቻለችም። አሁን ሦስት ሺህ ብር የተከራየችውን የሚያክል አንድ ክፍል ቤት አከራዮች እስከ ስድስት ሺህ ብር እየጠየቁበት ነው።
አቶ መርዳሳ ወርዶፋ ኡራኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ከመብራቱ ወዲያና ወዲህ እየተከራየ መኖር ከጀመረ ሁለት አሥርት ዓመታቶችን አስቆጥሯል። እንዳጫወተን ወደ አካባቢው በሥራ ምክንያት የመጣው ገና በ17 ዓመቱ ስለሆነ ድሮ የቤት ዋጋ እንዲህ ሳያሻቅብ በአካባቢው ከ300 ብር ጀምሮ እስከ 700 ብር ተከራይቶ ኖሮበታል። አሁን ግን በተለይም በአካባቢው የነበሩት ቤቶች ፈርሰው ነዋሪዎቹ ወደ ቡልቡላ ከሄዱ በኋላ በዚህ ዋጋ ቤት መከራየትና መኖር ቀርቶ ምሳና እራት መብላት እየከበደወ መምጣቱን ይናገራል። በዚህ ላይ ቤት የሚያከራዩት በልማት ምክንያት ሳይነሱ የቀሩ ውሱን ሰዎች በመሆናቸው የቤት እጥረት አለ። የባኞ ቤት ዕቃዎች የሚያቀርብበት የሥራ ቦታው እዛው አካባቢ ስለሆነ ከዑራኤል ርቆ መሄድ አይፈልግም። ነገር ግን አሁን ላይ ዑራኤል አካባቢ የቤት ዋጋ ተወድዷል። በተለይ ከመንገድ ብዙም ያልራቀ አካባቢ ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር ይጠየቅበታል። የተወደደው በአካባቢው ያለ ቤት ለመጋዘን ስለሚፈለግ ነው። እሱ በየወሩ ለመጋዘን 10 ሺህ ለመኖሪያ ደግሞ እንዲሁ በድምሩ 20 ሺህ ብር ለግለሰብ አከራዮች ይከፍላል። ሆኖም ገበያ ባልነበረበትና ኮቪድ ገባ በተባለበት ሰሞን ለክፉ ቀን ብሎ ያስቀመጠውን ነበር ይከፍል የነበረው። አከራዮቹ ከወሩ አንድ ቀን እንኳን ማሳለፍ አይፈልጉም። ክፍያ ካዘገዩባቸውም ያስወጣሉ። በዚያ ላይ ኪራይ ቶሎ ቶሎ ነው የሚጨምሩት። ማስወጣትና ከፍ ባለ ዋጋ ማከራየት ሲፈልጉ 10 ሺህ የነበረውን መጋዘን ወይም መኖሪያ ቤት በአንድ ጀንበር ወደ 20 ሺህ ብር ከፍ አድርገውት ያርፋሉ።
ዕድሜው ወደ ጎልማስነት እየተሸጋገረ ያለው መርዳሳ ሊያፍነው ያልቻለው ሳቅ እየመጣበት እንዳጫወተን ከውድነቱ ይልቅ የአከራዮቹ ባህርይ ያስገርማል። ቤቱን ለመከራየት የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ ድራማ እንጂ በገሀዱ ዓለም ያለ አይመስልም። እንዲህም ተከፍሏቸው ነፃነት አይሰጡ።‹‹ እቤት ውስጥ ሴት ይዞ መምጣት እንደማይቻል፣ ድንገት እንግዳ ቢመጣ እንኳን መፀዳጃ መጠቀም እንደማይችል፣ ጮሆ ማውራት፣ ሙዚቃ ከፍ አድርጎ መክፈት እንዲሁም ከሦስት ሰዓት በላይ ማምሸት አይቻልም›› ተብሎ ተነግሮት ነበር። አሁን የሚኖርበት ቤት የተከራየ ሰሞን ታድያ ከጓደኛው ጋር ሻይ ቡና ሲል ሳያስበው ከምሽቱ ሦስት ተኩል ይሆንበታል። አብራው ያመሸች ጓደኛውን ይዞ ወደ ቤት ይመጣና ከግማሽ ሰዓት ማንኳኳት በኋላ ባልና ሚስቶቹ አከራዮቹ ብቅ ብለው በሩን ከፈት አድርገው ሊያስገቡት ሲሉ ልጅቱን ያያሉ። ወድያው በሩን በእግሩ ላይ ዘግተው ተመለሱ። ቦታው አጎዛ ገበያ እየተባለ የሚጠራው ወንዝ አካባቢ ስለነበር ልጅቱ ጅብ ሲጮህ ትሰማና እሪታዋን ታቀልጠዋለች። ምን መጣ ብሎ ጎረቤት ይሰበሰባል። አከራዮቹም ይወጣሉ። በጎረቤት ቢለመኑም ሊያስገቧቸው ፈቃደኛ አልሆኑም። ልጅቱን ይዞ ወደ ሌላ ቦታ ተመልሶ በመሄድ አደረ። በማግስቱ ያን ቤት ለመልቀቅ ቢፈልግም በአካባቢው ሌላ ቤት ባለማግኘቱ አሁንም እዚሁ ቤት እየኖረ ይገኛል።
ንግስት አብርሃና እህቷ ኤልሻዳይ አብርሀ በጋራ እንዳጫወቱን መገናኛ አካባቢ በአንድ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት። ግቢው ውስጥ ከ20 በላይ ተከራይ አለ። ውሃ፣ መፀጃና መብራት የግቢው ቁልፍ ችግር ነው። ጋቢያቸውን ለብሰውና የዳንቴል ኮፍያቸውን አድርገው ሰርክ ውሀ የሚያስቀዱት አከራዩ ናቸው። ተከራይ እንኳን ከፍቶ መቅዳት ቧንቧውን መንካት አይፈቀድለትም። ውሀው የሚወርደው ደግሞ በቀጭኑ ነው። ያለማጋነን አወራረዱ እንደ ክር ነው። እንደገቡ ሰሞን በዚህ ተያይተው በመሳቃቸው አከራያቸው ሊያባርሯቸው ሲሉ በተከራይ እግዚኦታ ነው የተረፉት። ውሃው ከተደቀነ ከሰዓታት በኋላ ነው የሚሞላው። በዚህ ሁኔታ እዚያ ቤት ሆኖ ልብስ ማጠብማ አይታሰብም። የኤሌክትሪክ ምድጃ መጠቀም አይፈቀድም። መኖሩና አለመኖሩን ለማጣራት ፍተሻ የሚካሄድበት ጊዜም አለ። መብራት ቢያንስ ማታ ሁለት፣ ቢበዛ ሦስት ሰዓት ከቆጣሪ ይጠፋል። እስከ ማታ 12 ሰዓትና አንድ ሰዓት ላይለቀቅ ይችላል። የመፀዳጃ ነገርማ አይነሳም፤ ሰርክ ሰልፍ ነው። መፀዳጃ ለመጠቀም ሲል ከሌሊቱ 10 ሰዓት የሚነሳ ሁሉ አለ። በዚያ ላይ የሆድ ድርቀትም ሆነ ሌላ እክል ቢገጥም ከገቡ በኋላ መዘግየት አይቻልም። ወረፋው ዕድል የሚሰጥ አይደለም እንጂ ገደብ ስላለው ተከራዩ በፈለገው ጊዜ እየተመላለሰ መጠቀምም አይችልም። አብዛኛው የዚያ ግቢ ተከራይ የሚበላውና የሚጠጣውም ይሄን ታሳቢ አድርጎ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
‹‹ዕውነት ለመናገር ውሃ የምንቀዳውም ሆነ ልብስ የምናጥበው ከውጪ ነው። ቤቱን የተከራየነው ለአዳር ብቻ ነው›› ብላናለች ንግስት ሥራ ይረፍድብኛል ያለ ተቀድቶ ይቆይሃል መባሉን አክላ። ታናሽ እህቷ ኤልሻዳይ አከራዮች ቤታቸውን ለሴቶች፣ ልጅና ቤተሰብ ላለው ማከራየት አይወዱም። በዚህ ምክንያት ለብዙ ጊዜ ቤት አጥተው ብዙ እንግልት ገጥሟቸዋል። ለሁለት ሰው አናከራይም ብለዋቸው አቧሬ አካባቢ ብቻዋን ተከራይታ በነበረ ጊዜም የገጠማትን አጫውታናለች። አከራዮቿና ልጆቻቸው እስከ ንጋቱ አንድ ሰዓት ከቤት ካልወጣች ወይም በሯን ዘግታ ከተቀመጠች አንዴ መስኮቱን ሌላ ጊዜ በሩን እያንኳኩ ዛሬ ሥራ አትሄጅም እንዴ ይሏታል። ቅዳሜና እሁድ ላይ ሥራ የለም ብላ ብትመልስላቸው ታድያ ቤተክርስቲያን አትሄጅም እንዴ ይሏታል። የሚገርማት አንድ ጊዜ እንደማትሄድ ብትመልስላቸውም አለያም አሟትም ቢሆን ሙሉ ቀን እቤት ከዋለች ሙሉ ቀኑንም በዚህ ሁኔታ ሲያሰለቿት መዋላቸው ነው። በዚህ ምክንያት ከቤቷ ይልቅ ሌሎች አማራጭ መዋያዎችን ለመጠቀም ሳትወድ ተገድዳ ነበር።
በካዛንችስ ቅኝታችን ከተከራዮች በተደጋጋሚ የሰማነው በተለይም የመናኽርያ አካባቢ ነዋሪው አቶ ነብዩ አበበ ያጫወቱን እንደሌሎች አካባቢ በአከራዮች የከፋ ተግባር የሚፈፀም አለመሆኑን ነው። ‹‹ሰው አበዛህ አላበዛህ የሚልና ሰዓት ገደብ የሚጥል የለም። ተከራይ እንደልቡ ይገባና ይወጣል ሆኖም አሁን ላይ ካለው ኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ አከራዮች የቤት ኪራይ በእጥፍ እየጨመሩ ነው። ኪራይ የሚጨምሩት ደግሞ እጥፉን ነው። በተለይ ባልደራስና ራስ መስፍን አካባቢ ያሉ የጋራ መኖርያ ቤት አከራዮች ይሄ መለያቸው ነው። በዚህ ወር ለባለ አንድ መኝታ 13 ሺህ ብር ይከፍል የነበረው ጓደኛዬ በአንዴ ሦስት ሺህ ብር ጨምረውበታል። ልጅ ይዞ የትም መሄድ ስላልቻለ ተበድሮም ቢሆን እየከፈለ ይገኛል። ሆኖም ጭማሪው ቀጣይ መሆኑ አስግቶታል። አከራዮች ይሄን ተገንዝበው ለተከራዮች አስተያየት ማድረግ አለባቸው ›› ይላል። ቢያንስ የመክፈል አቅም ያለውን እያዩ ቢጨምሩ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ።
አቶ አወቀ ካሴ እንደሚሉት አሁን ላይ ያለውን የቤት ኪራይ ውድነት ሊፈጥረው የቻለው ዕለት ከዕለት እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ነው። ውድነቱ አከራይ ኪራይ እንዲጨምር አስገዳጅ ሆኖበታል። ‹‹በመሆኑም በአከራይ አልፈርድም›› ብለውናል። ነገር ግን ደግሞ የተከራይ ችግር እንደሚብስም አልሸሸጉንም። አሁን ላይ ግለሰብ ተከራዮች በተጋነነው ቤት ኪራይ ዋጋ የሚከፍሉት አጥተው ነጠላ አንጥፈው ወደመለመን እየደረሱ ነው። ትንሽ ቆይተው ደግሞ ጎዳና መውጣታቸው አይቀርም።
ወጣት አስናቀች ደቀባ እንዳጫወተችን መሥሪያ ቤቷ መናህርያ አካባቢ ስለሆነ ሂልተን ጀርባ ነው ተከራይታ የምትኖረው። በዚህ አካባቢ መኖር ከጀመረች አምስት ዓመቷን ይዛለች። አሁን ያለችበት ቤት ስትገባ 700 ብር ነበር ። ኑሮ ቢወደድም አከራዮቿ አቅም እንደሌላት ስለሚያውቁ አልጨመሩባትም።ሁሉም አከራዮች ጨካኞች ሁሉም ደግሞ ጥሩ አይደሉም ። ነገር ግን ለሁሉም ነገር መተሳሰቡ ቢኖር መልካም ነው ብላናለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013