ታምራት ተስፋዬ
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው መስቀል አደባባይ ላይ በአንድም ሆነ በሌላ ትዝታ የሌለው የለም። አደባባዩ ለክብረ በዓል፣ ለአምልኮት፣ለፖለቲካ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ፣ ለስፖርታዊ ውድድር ለሩጫ፣ለእግር ኳስ፣ ለማረፊያ፣ ለኪነጥበብ በተለይ ለሙዚቃ ትእይንት፣ ለፓርኪንግ፣ ለማስታወቂያ፣ ወዘተ የሚውል የአዲስ አበባ ሕዝባዊ አደባባይ ነው።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ግልጋሎት ይሰጥ እንደነበር የሚነገርለት የመስቀል አደባባይ ይህ ነው የሚባል እድሳትም ሆነ ማሻሻያ ሳይደረግለት ረጅም አመታትን ለማስቆጠር ተገዶ ቆይቷል። ባሳለፍነው አመት በአንፃሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪነት አደባባዩን ለሕዝባዊ አደባባይነት (ፐብሊክ ስፔስ) በሚመጥንና በዘመናዊ ሁኔታ ለመገንባት እና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የህዝብ አደባባይ ለማድረግ ተወስኖ ወደ ስራ ተገብቷል።
መስቀል አደባባይ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የህዝብ አደባባይ ለማድረግ እና ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ የሚዘልቀውን መንገድ ዳርቻ ለማስዋብ እንዲሁም ተጨማሪ መናፈሻዎችን የመንገዱ አካል አድርጎ የተጀመረው የዚህ ፕሮጀክት ግንባታም ከተጀመረ ዘጠነኛ ወሩን አስቆጥሯል።
ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚሆንበት ይህ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ሺ አራት መቶ ተሽከርካሪዎች ለማቆም የሚያስችል የመሬት ውስጥ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ፋውንቴን (የውሃ ፏፏቴ) አረንጓዴ አፀድ፣ የካፌና የሬስቶራንት አገልግሎት፣ መዝናኛ ማዕከላት እንዲሁም መቶ የሚሆኑ የመፀዳጃ ቤት ይኖሩታል። 24 ሰአት ዘመናዊ የደህንነት ጥበቃ የሚሠጡ በርካታ ካሜራዎች ይገጠሙለታል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ የአፈፃፀም ደረጃ እና በግንባታ ምእራፍ ስላጋጣሙ ፈተናዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ በሰጡት ምላሽ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማን ነባራዊ ሁኔታ ዘመናዊ በሆነ መልኩ የሚቀይሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ ከሚገነባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱም የመስቀል አደባባይ ተሽከርካሪ ማቆሚያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ሺ አራት መቶ ተሽከርካሪዎች ለማቆም የሚያስችል የመሬት ውስጥ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)ን፣የደረጃ ንጣፍ እና ማስዋብን ጨምሮ ከመስቀል አደባባይ ማዘጋጃ ቤት የሚዘልቅ መንገድ ማስዋብን ያጠቃልላል።
ፕሮጀክቱም የከተማ ዲዛይን ደረጃ የጠበቀ፣ሕዝባዊ አደባባይነት (ፐብሊክ ስፔስ) በሚመጥን ዘመናዊ ሁኔታ ለመገንባት እና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የህዝብ አደባባይ በማድረግ ከቀድሞው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የሚገነባ ነው።
የፕሮጀክቱ አፈፃፀም በአሁኑ ወቅት በውጤታማ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኢንጂነር ሽመልስ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት የሲቪል ስራ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ ተጠናቋል፣ከአንድ ወር በኋላም ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል›› ብለዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የሚቀሩት የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ሺ አራት መቶ ተሽከርካሪዎች ለማቆም የሚያስችል የመሬት ውስጥ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ግንባታም ሱቅ እና መፀዳጃ ቤትን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የኤሌክትሮ መካኒካል እና የቬንትሌሽን መግጠም ስራ ብቻ እንደሚቀረው ተናግረዋል።
ከላይ የሚታየውን አብዛኞች የሚያውቁት የሚመለከቱት የደረጃ ንጣፍ እና የስቴጅ መድረክ ስራ መጠናቀቁን ያስታወቁት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ አሁን ላይ የሚቀሩ ስራዎች አደባባዩ ቀደም ሲል የነበረውን ያረጀ መልክ በውበት ለመለወጥ እና ዘመናዊ የሆነ መብራቶችን መትከል ጨምሮ የተለያዩ የማስዋብ ስራዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ሶስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚረዝመው እና የፕሮጀክቱ አንድ አካል የሆነው የመስቀል አደባባይ ማዘጋጃ ቤት መንገድ ማስዋብ ፕሮጀክት ግንባታ 75 በመቶ መድረሱ የገለፁ ሲሆን፣አብዛኛው የአፈር ቁፋሮ፣የሙሌት እና ሰብ ቤዝ ስራዎች መጠናቀቃቸው ተገልጿል። በአሁኑ ወቅትም የአረንጓዴ ስፍራ ቦታዎችን የማልበስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የሚገነባበት አካባቢ የተለያዩ ቅርሶች የሚገኙበት እንደመሆኑ ፕሮጀክቱ የቅርሶች ጥበቃን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙ ቅርሶችን አይደለም፣ወደ መንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ወሰን ሶስት እና አራት ሜትር የገቡ ዳር ትራኮንን ጨምሮ ታላላቅ ህንፃዎች ከማፍረስ ይልቅ ከዲዛይኑ ጋር አጣጥመን አልፈናል››ብለዋል።
‹‹እኛ የያዝነው እቅድ ሁለቱንም በአንድ ጊዜ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው››ያሉት ኢንጂነሩ፣ ይህን አቅጣጫ በማስቀመጥም ፕሮጀክቶቹ በታቀደው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከመግባባት ላይ ተደርሶ ግንባታቸው እየተፋጠነ መሆኑንም አስታውቀዋል።‹‹ፕሮጀክቶቹን በተቃደው ጊዜ ለማጠናቀቅም ሌት ተቀን 24 ሰአት እየተሰራ ነው››ብለዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣መስቀል አደባባይ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ስያሜው ከማግኘቱ በፊት በእስጢፋኖስ አደባባይነት እንደሚታወቅ፣ ከ1967 ዓ.ም መገባደጃ ጀምሮ በዘመነ ደርግ ‹‹አብዮት አደባባይ›› ይባል ነበር። ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ቀድሞው መጠሪያ መስቀል አደባባይ መመለሱ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013