ይበል ካሳ
ለመግቢያና ለመግባቢያ
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች ከ40 እስከ 80 ካሬ ሜትር ቦታ የሚያስፈልጋቸው ገጠሩን ሳይጨምር በከተማ ውስጥ ብቻ በሚኖሩ የመካከለኛና ዝቅተኛ ኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ 51 ሚሊዮን የሚጠጋ የመኖሪያ ቤት እጥረት መኖሩን በተለያየ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።በመሆኑም አህጉሪቱ ውስጥ 17 አገሮች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተመዘገበ የቤት እጥረት አለባቸው።ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ደግሞ የእኛዋ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።እናም መንግስታት ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩበት በስተቀር የመኖሪያ ቤት እጥረት ከጦርነትም በላይ ለአፍሪካ የብጥብጥ፣ የጥፋትና የውድቀት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል የጉዳዩ አጥኝዎች በጥናታቸው ውጤት በሚያቀርቡት ምክረ ሃሳብ ይጠቅሳሉ።በመሆኑም በዘርፉ ያለውን ችግር መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ነውና መሪዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው አበክረው ይገልጻሉ፡፡
የሰነባበቱ የመኖሪያ ቤት ችግሮች
በኢትዮጵያ በፍጥነት ዕያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ በተለይም በከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ ችግር እየሆነ መምጣቱን ሕዝብም መንግስትም በአንድነት ይመሰክራሉ።ችግሩ ለዘመናት የተከማቸ መሆኑንም በተለያዩ አካላት በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ጥናቶች ያለመክታሉ።ከዚህ አኳያ በብዛት በከተሞች አካባቢ የተንሰራፋውንና በአጠቃላይ በአገሪቱ የተከማቸውን ውዝፍ የቤት ፍላጎት ለማሟላት 1.2 ሚሊዮን ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ የጥናት ውጤቶች ያመላክታሉ።በተጨማሪም አዳዲስ የቤት ፍላጎቶችን ለማሟላት ከ100 ሺሕ ቤቶች በላይ በየዓመቱ መገንባት ግድ ይሆናል። ጉዳዩን በበላይነት የሚያስተዳድረው መንግስታዊ አካል የሆነው የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃም በጥናት ከተጠቀሰው ጋር ተመሳሳይ ነው።በከተሞች አካባቢ የሚታየው የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ዝቅተኛ መሆኑ፣ በመላው የኢትዮጵያ ከተሞች የ1.2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጉድለት መኖሩንም ሚንስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት የተኬደባቸው ነባር መንገዶች
ሁኔታውን በሚገባ በማጤን በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን መንግሥት ይገልጻል።በዚህ ረገድ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን በመቅረፅና ሥራ ላይ በማዋል ሠርቷል።ለቤት ግንባታ ምቹና አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ጀምሮ የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የተቀናጀ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታ በአገሪቱ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰባችን ክፍሎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ።ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል 1ሺህ673 ቤቶችን በቤቶች ኮርፖሬሽን በኩል ለመገንባት የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ ወደ ሥራ መገባቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ይሁን እንጅ የተለፋውን ያህል ውጤት አለማግኘቱን መንግሥት ራሱ ይመሰክራል።የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግሮችን ለመፍታት ይህን ያህል ጥረት ቢደረግም፣ ቤቶች እየተገነቡም ቢሆን የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎትና አቅርቦት አሁንም ሊጣጣም አለመቻሉን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ችግሩ ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እንዲህ ይገለጻል።“ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል።ይሁን እንጅ አሁንም ከሚሊዮን በላይ ውዝፍ የቤት ዕጥረት ያለ ሲሆን አሉ የሚባሉት ቤቶችም 74 በመቶ ለኑሮ የማይመቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ናቸው።ይህ በእንዲህ እንዳለ ከህዝብ ቁጥር መጨመርና የቤተሰብ ምስረታ ማደግ ጋር ተያይዞ በከተማ ብቻ በዓመት ከ 400ሺህ ቤት በላይ አዲስ ፍላጎት እንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ። ዓመታዊ አቅርቦቱ ከነበረበት የተለወጠ ፍጥነት ቢያሳይም በዓመት 100ሺህ እንኳን አልደረሰም።ስለሆነም ይህ የቤት ጉዳይ በዕቅዱ ዝግጅት መነሻነት በልዩ ትኩረት መታየት ያለበት ነው።በአለፉት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት በመንግስት አስተባባሪነት ተገንብተው ለተጠቃሚ ከተላለፉ 384ሺህ107 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ በመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት 151ሺህ997፣ እንዲሁም በሪል ስቴት አልሚዎች 21ሺህ314 ቤቶችን ማቅረብ ተችሏል። የግል ቤት ሰሪዎችን ሳይጨምር የቀረቡ ቤቶች ከ557ሺህ417 አይበልጥም።ይህም ከላይ ከተገለጸው የቤት ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር ያለው ልዩነት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።መረጃው የሚያሳየው ከመሬትና መሰረተ ልማት አቅራቢነት በተጨማሪ ትልቁን የቤት አቅርቦት ሃላፊነት የተሸከመው መንግስት መሆኑን ነው።በከተሞች ያለው የቤት አቅርቦትና ፍላጎት ያልተጣጣመ መሆኑ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተገቢ ላልሆነ ወጪና መንገላታት በመዳረግ ለተወሳሰበ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች እያጋለጠው ይገኛል፡፡”ይላል።
እውነት ነው፤ ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም በአገሪቱ ውስጥ በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሚታየው የመኖሪያ ቤት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።ችግሩን ለማቃለል ሲደረጉ የቆዩ ጥረቶችም የቤት ፈላጊዎችን ፍላጎት ሊያሟሉ ባለመቻላቸው የቤት ዕጦት ችግር ይብሱን እያየለ እንዲመጣ አድርጓል።ምክንያቱም እስካሁን የተሄደባቸው የመፍትሄ መንገዶች ወይም ችግሩን የመፍታት አቅም የሌላቸው ራሳቸው ያረጁ ያፈጁ ናቸው። አለያም “አሮጌ ወይንን በአዲስ አቁማዳ” እንደሚባለው የቆየውን ችግር በአዲስ መፍትሔ ሳይሆን በአዲስ መፈክር ተሸክመው ለማለፍ የሚፈልጉ ነበሩ ማለት ነው።
አሮጌውን ችግር በአዲስ መፍትሔ
በዚህ ረገድ “ይህ መረጃ የሚያሳየው ከመሬትና መሰረተልማት አቅራቢነት በተጨማሪ ትልቁን የቤት አቅርቦት ሃላፊነት የተሸከመው መንግስት መሆኑን ነው።ይህ አሰራር ከፍተኛ ድጎማ የታከለበት ስለሆነ ለመኖሪያ ቤት ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ጥናቶች ያሳያሉ” የሚለው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጠው አባባል ትልቅ ቁም ነገርን ያዘለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግርን ለመፍታት ቤቶች እየተገነቡም እስካሁን ድረስ ችግሩ ያልተፈታበት ዋነኛውና ትልቁ ምክንያት አሁን በግልጽ እንደሚታየው በመንግስት ላይ የወደቀ ዕዳ በመሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመፍታት የሌሎች ሃገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በተለይም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።ከዚህም በተጨማሪ መሪ የልማት ዕቅዱ የፋይናንስ እጥረትም ሌላኛው የችግሩ ምንጭ መሆኑን እውቅና ይሰጣል።የቤት አቅርቦቱ የባለቤትነትን አማራጭ ብቻ ማዕከል ያደረገ መሆኑና ለኪራይ አቅርቦት ትኩረት አለመሰጠቱ እንዲሁም የቤት ገበያው እየናረ መሄድ እንደ ተጨማሪ ትልቅ ችግር አስቀምጧል፡፡
“ተደራሽ የቤት ልማት” በሚለው የዕቅዱ ንኡስ ክፍልም በከተማና በገጠር ማዕከላት ተደራሽና ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ማሳደግ እንደ ዓላማ፤ በከተሞች የቤት አቅርቦት መጠን አሁን ካለበት 64 በመቶ ወደ 80 በመቶ እንዲያድግ 4 ሚሊየን410 ሺህ 400 ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግንም እንደ ግብ አድርጎ በማስቀመጥ ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ ያመላክታል።የሚገነቡት ቤቶችም በመንግስት አስተባባሪነት 20 በመቶ፣ በመኖሪያ ቤት ኀብረት ሥራ ማኀበራት 35 በመቶ፣ በግለሰቦች 15 በመቶ፣ በሪል ስቴት ገንቢ ባለሃብቶች 10 በመቶ፣ በመንግሥትና በግል ባለሃብት አጋርነት 15 በመቶ እና በሽርክና 5 በመቶ መሆናቸውንም በዝርዝር አቅዷል።
ከደረጃ በታች ከሆኑ 74 በመቶ ቤቶች 10 በመቶ ማለትም 476 ሺህ በመልሶ ማልማት እንዲሁም 34 በመቶ የማሻሻያ ልማት በመካሄድ በድምሩ ወደ 30 በመቶ እንዲቀንስ ማድረግን በሁለተኛ ደረጃነት ዓላማው አድርጓል።ለዚህም ለቤት ልማትና ተጠቃሚ የሚሆን የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት፣ የቤቶች ልማት ፈንድ ማቃቋም፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በቤት ልማት ፋይናንስንግ እንዲሳተፉ ማድረግ ፣ የመንግስት ቀጥታ የቤት ግንባታ ተሳትፎና ድርሻ እየቀነሰ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ድርሻ እየጨመረ እንዲሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት አማራጮችን በማስፋት ባለቤትነትን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ በኪራይ የሚቀርብበትን አካሄድ መደገፍ በማስፈጸሚያ ስልትነት ለመጠቀም በእቅዱ ከተቀመጡት መካከል የሚጠቀስ ነው ፡፡
በዚህ ረገድ በቤት ግንባታ ላይ የሚሳተፉ እንደ ባንክ የመሳሰሉ የግል የፋይናንስ ተቋማትን ወደ ገበያው ማስገባት የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግሮችን ለመፍታት የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ።ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአክስዮን ሽያጭ መጀመሩን ያስታወቀውና በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው በቤት ግንባታ ላይ ያተኮረው “ጎህ ቤቶች ባንክ” ጥሩ ጅምር ነው።ባንኩ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቤት ፍላጎት ማሟላትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም መስራቾች ገልጸዋል ።የጎህ ቤቶች ባንክ ዓላማም ይህንን አገራዊ ጥልቅና ሰፊ ችግር ለመፍታት በመንግሥት፣ በማኅበረሰቡና በግሉ ዘርፍ የሚደረገውን ጥረት ማገዝና የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ባንኩ ተመሥርቶ ሥራ ሲጀምር አዳዲስ የመኖሪያ ቤት ለሚገነቡ፣ ያላቸውን ቤት ለማደስ፣ ለማሻሻልና ለማስፋፋት ለሚፈልጉ፣ መኖሪያ ቤት ሠርተው ለሚያከራዩና ለሚሸጡ፣ እንዲሁም መኖሪያ ቤት ለሚገዙ እንደየፍላጎታቸው፣ የመክፈል አቅማቸውና አዋጪነታቸው ተመጣጣኝ የገንዘብ ብድር ይሰጣል።ይህንን በማድረግ የቤቶችን ልማት በመላ የአገሪቱ ከተሞች በፍጥነትና በጥራት ያስፋፋል የሚል እምነታቸውን አደራጆቹ ገልጸዋል።ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትም በአነስተኛ ወጪ ውጤታማ ሥራ ይሠራል ተብሎ ይታመናል።እንደዚሁ በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ የአክሲዮን ሽያጭ ስራ የጀመረውና በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኝ ‹‹ጃኖ ባንክ አክስዮን ማህበርም›› በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂና በቤቶች ልማት ዘርፍ ለመስራት አቅዶ የተነሳ መሆኑን ከመስራቾች የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የቤቶችና ሞርጌጅ የቁጠባ ባንኮችን ማበረታታትና በስፋት ወደ ገበያው ማሳተፍ ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኑሮ ደረጃ ያላቸው ዜጎች በማህበር ተደራጅተው፣ ከገቢያቸው በዝግ አካውንት በየወሩ ገንዘብ በመቆጠብ፣ በረዥም ጊዜ ሞርጌጅ ቤቶች እንዲገነቡ በማድረግ የመኖሪያ ቤቶችን እጥረት ለመፍታት ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑን የቤቶች ልማትና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚመክሩት ሳይንሳዊ መፍትሔ ነው።ምክንያቱም የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግርን በመፍታት ረገድ መንግስትም እንዳመነው አንደኛውና ትልቁ ችግር በዘርፉ የሚያጋጥመው የፋይናንስ እጥረት በመሆኑ እንዲህ ዓይነቶቹ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ለቤት አልሚዎች ብድር በማመቻቸት ለተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች እንደ ገቢያቸው መጠን የረዥም ጊዜ ብድር በማበደር የሚሰሩ በመሆናቸው ነው።ቤት ሰሪዎች ከተበደሩበት ዓመት እስከ ጡረታ ሊወጡ አንድ ዓመት እስኪቀራቸው ድረስ ማለትም በትንሹ ከ25 እስከ 30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ብድር ማመቻችና ዋነኛ ዓላማቸውም ህብረተሰቡ ካለው ገቢ ቆጥቦ ቤት እንዲሰራ ሁሉንም ነገር ማመቻቸት ነው።እናም ታላቁ ሰው ሊቁ አልበርት አንስታይን እንዳለው በቆየውና በነበረው መንገድ እያሰቡና ሥራዎችን እያከናወኑ የቆዩ ችግሮችን መፍታት አይቻልምና የተከማቹ ነባር የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግሮቻችን ለመፍታት አዳዲስ መንገዶችን ልንከተል ይገባል በማለት የዛሬውን ጎጇዊ ጥንክራችንን አጠቃለልን።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013