የኮንስትራክሽን ዘርፉን ምርትና አገልግሎት ያሳየው ኤግዚቢሽን

ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የ20 በመቶ ድርሻ ያለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፤ በየጊዜው አዳዲስ ምርቶች ወደ ገበያ የሚገቡበትና አዲስ ተቋሞች ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀሉበት ነው። እነዚህን የዘርፉን ለውጦች ለዘርፉ ተዋናዮች ለማስተዋወቅና የመገናኛ ድልድይ በመሆን የሚያገለግለው የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርኢት ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደውና ዛሬ የሚጠናቀቀው ዓለም አቀፍ ትርኢት ከ20 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተካፈሉበት ሲሆን፤ ከ160 በላይ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያውያን ተመስርቶ ወደ ምርት ከገባ ስድስት ወራትን ያስቆጠረው ራይኖ ኬብል ማኑፋክቸሪንግ ፒኤልሲ በኤግዚቢሽኑ ምርታቸውን ይዘው ከተገኙ ድርጅቶች መሃል አንዱ ነው።

ድርጅቱ የተለያዩ አይነት የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን የሚያመርት ሲሆን፤ ፓወር ኬብል፣ ፌሌክሴብል፣ ስታንዳርድ፣ ድሮፕ ዋየር ኬብል ከሚያመርቷቸው ምርቶች ጥቂቶቹ ናቸው። የድርጅቱ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ፤ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ናቸው የምትለው የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዮዲት ክብሩ፤ ከፋብሪካው ምስረታ አንስቶ በሙሉ ኢትዮጵያውያን የሚንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊ ድርጅት መሆኑን ጠቁማ፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ረዥም ጊዜ ለመገልገል ሲያስቡ እንዲመርጧቸው አስበው የሚያመርቱ መሆናቸውን ትናገራለች።

እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጇ ማብራሪያ፤ የሚመረቱት የኤሌክትሪክ ኬብሎች አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው መመረታቸው ይረጋገጣል። ይህንን ተከትሎ የድርጅቱ ሁሉም ምርቶች የጥራት ሰርተፍኬት አላቸው። ድርጅቱ ደህንነትና ተመጣጣኝ ዋጋን አማክሎ የሚሠራ ሲሆን፤ ድርጅቱ በምርት ሂደት የሚጠቀማቸው ግብአት ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ተስማሚ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ገብቷል።

‹‹ጥራት የሌለው ኬብል ጥቅም ላይ ሲውል ቮልቴጅ ድሮፕ ያጋጥማል።›› የምትለው ዮዲት፤ ትክክለኛው ሃይል ተገልጋዩ ጋር ስለማይደርስ የሚያገኘው ግልጋሎት ረዥም ጊዜ ከመውሰድ አንስቶ መስመሮችን እና መገልገያዎችን የሚያቃጥል፣ ለኤሌክትሪክ ከፍተኛ ክፍያ ለመክፈል የሚያስገድድ እና አለፍ ሲልም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እና አደጋ እስከማድረስ የሚዘልቅ ጉዳት እንደሚያጋጥም ጠቅሳለች። ድርጅታቸው መሰል አደጋዎችን ለማስቀረትና ለትውልድ የሚሻገር ምርቶችን ማምረት ዓላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁማለች።

ሌላኛው በኤግዚቢሽኑ ስንዘዋወር ያገኘነው ሀገር በቀል ድርጅንት ፊስኮም ኢንጂነሪንግ ይሰኛል። ከተመሠረተ 20 ዓመታትን የተሻገረው ድርጅት ለህንጻዎችና ለመኖሪያ ቤቶች የደህንነት መጠበቂያዎችን ማቅረብና መግጠም ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በድርጅቱ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነው ኢንጅነር ዮናታን መኮንን፤ ድርጅቱ የእሳት አላርም ሲስተሞችን ጨምሮ የእሳት አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ሽያጭና ገጠማ፣ ከእሳት አደጋ መጠበቂያ ሲስተሞች፣ የደህንነት ካሜራዎች ሽያጭና ገጠማ ላይ የተሰማራ ድርጅት መሆኑን ይናገራል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የህንጻዎች ደህንነትን ማስጠበቅ ትኩረት እየተሰጠው መሆኑን የሚናገረው ኢንጂነር ዮናታን፤ ሆኖም የእሳት አደጋ አላርም አጠቃቀም አንጻር ውስንነት አለ ይላል። ለዚህም አላርም ሲስተሞቹ ተገጥመው በእጣን ጭስና በመሰል ሁኔታዎች “በተደጋጋሚ ይጮሃሉ” በሚል የማጥፋት ሁኔታ መኖሩን ይናገራል። የሕብረተሰቡ የአጠቃቀም ሁኔታ ችግር ከመኖሩ በስተቀር አሁን በሚሠሩ ህንጻዎች ላይ መሰል የደህንነት ግብአቶችን በማሟላትና አላርም ሲስተም በመግጠም ረገድ መሻሻል መኖሩን ጠቁሟል።

በሌላ በኩል በተደረጉ መሰል የማበረታቻ ሥራዎች በተሳቡ የህንድ ባለሀብቶች ከሁለት ዓመት በፊት ባህር ዳር ላይ የተከፈተው ራቫል ስቲል ማኑፋክቸሪንግ ፒኤልሲ በሲምፖዚየሙ ከሚሳተፉ ድርጅቶች መሃል አንዱ ነው። የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ ጸሀዬ ተስፋዬ ፌሮና ቱቦላሬ እያመረቱ መሆኑን ይናገራል። ለመንግሥት ፕሮጀክትም ሆነ ለግል ገንቢዎች ምርታቸውን በቀጥታ የግንባታ ቦታ ድረስ እያቀረቡ ይገኛሉ። በኤግዚቢሽኑ ከዚህ በፊት ከሚያውቋቸው ተጨማሪ አዲስ ደንበኞችን ለማግኘት ተስፋ አድርገው መሳተፋቸውን ይገልጻል።

አልፋ ፖስት ቴንሽን የተሰኘ ድርጅት አገልግሎቱን ለጎብኚዎች የሚያሳይበትን ቦታ ስንጎበኝ የድርጅቱን ሥራ ለጎብኚዎች ስታስረዳ ያገኘናት ሰላማዊት ፍቃዱ የቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ባለሙያ ናት። አልፋ ፖስት ቴንሽን የሚሰኝ የዘመኑ የግንባታ ግብአትን ከውጪ የሚያስመጣና በግንባታዎች ላይ ፖስት ቴንሽን የሚባል ሲስተም በመጠቀም የሚሠሩ ሥራዎችን ብቻ በመውሰድ የሚሠራ ልዩ ኮንትራክተር ነው።

ከዚህ በፊት በተለመደው አሠራር የህንጻ መዋቅር የሚሠራው ከብረት ከኮንክሪትና ሲሚኒቶ ነበር የምትለው ባለሙያዋ፤ ድርጅቱ ሥራ ላይ ያዋለው ፖስት ቴንሽን የብረት ፍጆታን 75 በመቶና የኮንክሪት መጠንን 30 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ታስረዳለች። ቴክኖሎጂው በብዛት በህንጻ ግንባታ ላይ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን ጠቁማ፤ የዋጋ ቅናሽ ያመጣል? የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ከቴክኖሎጂው ጋር ተያይዞ የሚጠይቁት ጥያቄ መሆኑን ትጠቅሳለች። ከግንባታው ላይ የብረት ወጪን 75 በመቶና የኮንክሪት ወጪ 30 በመቶ ተቀንሶና የፖስት ቴንሽኑ ወጪ ተጨምሮ በህንጻ ላይ በአጠቃላይ ከ15 እስከ 30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ያመጣል የሚለው ለሚነሳው ጥያቄ መልስ ነው ትላለች።

ፖስት ቴንሽንን ለግንባታ መጠቀም ከዋጋ ቅናሽ በተጨማሪ ሌሎችም ጥቅሞች አለው የምትለው ሰላማዊት፤ ጥቅም ላይ የሚውለው ኮንክሪት መጠን እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ኮንክሪቱን ቀላል ያደርገዋል ትላለች። ቅለቱም ከመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ በሌሎች ወቅቶች ተፈላጊ ነው።

በቀደመው አሠራር ሲሠራ ህንጻው ላይ ኮንክሪቱ ስለሚበዛ የህንጻው ቁመት ይረዝም እንደነበር በማንሳት ይህም አብሮት ለፊኒሽንግና ለመሰል ወጪዎች ይዳርግ ነበር። በፖስት ቴንሽን ሲሠራ የህንጻው ቁመት ስለሚቀንስ የህንጻ ጫናና ወጪውም አብሮ ይቀንሳል። በበፊቱ አሠራር ፍሬም ወርኩ ለማፍረስ በትንሹ 21 ቀን ያስፈልጋል። በፖስት ቴንሽን ሲሠራ የፍሬም ወርክ ከሦስት እስከ አራት ቀን ውስጥ ፈረሳውን ማጠናቀቅ ይቻላል። ይህም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ፍጥነትን ለመጨመር አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ጠቅሳለች።

ድርጅቱ ከተመሠረተ አራት ዓመት ባይሞላውም ከመቶ በላይ ፕሮጀክቶችን ተዋውሎ በመሥራት ላይ ይገኛል። ድርጅቱ ሲጀመር ለፖስት ቴንሽን ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ ከውጭ ያስገባ እንደነበር የምትናገረው ባለሙያዋ፤ በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆኑትን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ወደ ማምረት መሻገራቸውን ታስረዳለች።

በቀጣይ ቀሪውን 80 በመቶ ግብአት በሀገር ውስጥ የማምረት እቅድ አላቸው። ከዚህ ቀደም “ፖስት ቴንሽን ሰው ቴክኖሎጂ ስለሚወድ ብቻ ይጠቀመዋል እንጂ፤ ዋጋ አይቀንስም፤ ጥቅም የለውም!” የሚል አስተያየት ከተወሰኑ የዘርፉ ተዋናዮች ይሰማ እንደነበር በማንሳት፤ ድርጅታቸው ለዘርፉ ባለሙያዎች ስለፖስት ቴንሽን ግንዛቤ ለመስጠት ተደጋጋሚ ስልጠና መስጠቱንና አሁን በዘርፉ ባለሙያዎች የተሻለ ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቅሳለች።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብአት ከውጭ በማምጣት ከ60 ዓመት በላይ ልምድ ያለው ሬስ ኢንጅነሪንግ የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊ ነው። በአሁኑ ወቅት ለግዙፍ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚሆኑ ማሽኖችንና ጀነሬተሮችን እንዲሁም መለዋወጫዎችን ከአምራቾች አምጥተው ሀገር ውስጥ የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ናቸው። የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ ብሩክ ገብረሚካኤል በዘርፉ ድርጅታቸው ጥሩ ስም መትከሉንና በቀጣይም የዘርፉን ችግሮች የሚፈቱ ማሽኖች ማስመጣታቸውን የሚቀጥሉ መሆኑን ይናገራል።

በኤግዚቢሽኑ ላይ እየተዘዋወረች ድርጅቷንና አገልግሎታቸውን እያስተዋወቀች ለቀጣይ ሥራዎች የሚሆኑ ትውውቆችን ስትፈጥር ያገኘናት ዮርዳኖስ ስለሺ ፌርፋክስ ሶልሽን የሚባል ኮንሰልታንት ድርጅት የሽያጭና የሰው ሃይል ዳይሬክተር ናት።

በመድረኩ ለድርጅቷ በተሰጣት ቦታ ተወስኖ ከመቀመጥ እየተዘዋወረች የሌሎች ድርጅቶችን ምርትና አገልግሎት መጎብኘትም ሆነ የእራሷን ድርጅት ማስተዋወቅ መርጣለች። ኤግዚቢሽኑ የእነሱን ምርት ከማስተዋወቅ ባሻገር ከሌሎች አካላት ጋር ለመተዋወቅ ጠቃሚ ሆኖ ማግኘቷን ትጠቅሳለች።

ዘላቂነትና የአካባቢ ተፅእኖን መቀነስን በኤግዚቢሽኑ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን፣ በርካታ ኤግዚቢሽን አቅራቢዎችም የአካባቢ ተፅእኖን ለመቀነስ እና የረጅም ጊዜ ቅልጥፍናን ለማሳደግ የተነደፉ መፍትሔዎችን በትርዒቱ ላይ አሳይተዋል። በትርኢቱ ከሀገራችን ድርጅቶች በተጨማሪ ከበርካታ ሀገራት የተውጣጡ ድርጅቶች ምርታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ለአብነት የኬንያው ሲግኒፋይ፣ በስማርት ብርሃን እና በኤልኢዲ ሲስተሞች የኃይል ፍጆታን ለመቀነስ ያለመ ፍላጎት እና ፈጠራን አሳይቷል።

ዩኤስጂ ሚድል ኢስት አረንጓዴ የግንባታ ልምዶችን የሚያበረታቱ እና የአካባቢ ሥነ-ምሕዳርን የሚጠብቁ ቀላል ክብደት ያላቸውንና እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች ፈጠራውን አጋርቷል። የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ድርጅት የሆነው ኢሚሬትስ ኢንዱስትሪያል ፓናል ኃይል ቆጣቢ የግድግዳ እና የጣሪያ ሥርዓቶችን አስተዋውቋል።

ተሳታፊዎቹ፤ ኤግዚቢሽኑ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ምርትና አገልግሎት ለማስተዋወቅ የሚያግዝ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል አውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየሙን መርቀው የከፈቱት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ መድረኩ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ውጤታማነት በሚያገለግሉ ግብዓቶች ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብና በመስኩ ያለውን ችግር ለመፍታት ብሎም ዓለም አቀፍ ተሞክሮና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማግኘት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለፈጠራ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ቢሆንም፤ ለሰፊው ገበያ ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑን በማንሳት በመድረኩ ቀጣይነት ያለው የባለሀብቶች ፍላጎት ሊጨምር ይችላል። ለዚህም መንግሥት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን በተሳካ መልኩ ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስቡ እና የሚያበረታቱ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ግብአቶችን እና ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችሉ የተለያዩ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያ ርምጃዎች እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በዘርፉ የውጭ ኢንቨስትመንት እያበረታታን በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ አምራቾችን እና አቅራቢዎችን በማገዝ፣ በመተባበር እና በመቀናጀት ሀገሪቱን ማበልፀግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሚሊኒየም አዳራሽ ሰኔ 19 ቀን ተከፍቶ ዛሬ የሚጠናቀቀው የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ስትራቴጂክ አጋር የሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ ኤክስፖው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታትና ትብብሮችን በማጠናከር በኢትዮጵያ የትራንስፎርሜሽን ውጥን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል። መድረኩ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያሉ አዲስ ፈጠራዎች፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች፣ ግብአቶች፣ ቴክኖሎጂዎች የቀረቡበት ነው።

ከ20 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ160 በላይ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ተገኝተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ በሚገኙ አልሚዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላት መካከል ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቅሰዋል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You