የከተማ ግብርና በአዳማ

የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ ጠቃሚ ተደርገው በመንግሥት እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። እንደ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ እና ባህር ዳር ያሉ ከተሞች ብዙ ሰዎች በከተማ ግብርና የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። በየከተሞቹ የላሞች ርባታ፣ ከብት ማድለብ፣ ዓሳና ዓሳማ ርባታን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያካትት የግብርና ሥራ እየተከናወነ ነው። አንዳንዱ ሥራ በመኖሪያ በአትክልት ስፍራዎች፣ በጣሪያዎች፣ በባዶ መሬቶች ወይም በቤት ውስጥ በትንንሽ እቃዎች ውስጥ እንኳን ሊከናወን ይችላል። ይህንን መሠረት በማድረግ መንግሥት ነዋሪዎችን በተለያየ መልኩ በማደራጀትና በማሰልጠን በከተማ ግብርና እያሰማራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ ግብርና ወሳኝ መፍትሄ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይ በከተሞች በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች በቂ ምግብ እንዲያገኙ ወይም ጤናማ ምግብ በቀላሉ መሸመት እንዲችሉ በከተማ ውስጥ በቂ አቅርቦት ሊኖር ይገባል። በዝቅተኛ ገቢ ከመሸመት ባሻገር የከተማ ግብርና የራሳቸውን ምግብ እንዲያመርቱ እና እንዲጠቀሙ የሚያስችል፤ አለፍ ሲልም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጣቸውም ባሻገር ለሽያጭ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ያግዛል።

የከተማ ግብርና ሥራም ይፈጥራል። በከተሞች ውስጥ ያሉ ብዙ ወጣቶች እና ሴቶች ሥራ የላቸውም። በከብት ርባታ፣ በጓሮ አትክልት ወይም ዶሮን በማርባት ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ። ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥ ገበያዎች ወይም ለሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች መሸጥ ይችላሉ። ይህም ድህነትን ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ፍቱን መሆኑን የግብርና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በተለይ ወጣቶችን በማደራጀት ለከተማ ግብርና ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል። በከተሞች ውስጥ ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት፣ የብድር አገልግሎትን በማመቻቸት እና የቴክኖሎጂና የግብርና መሣሪያዎችን እንዲሁም ሼዶችን በመገንባተ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።

የዝግጅት ክፍላችን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ የማህበራት አባላትን በአዳማ ከተማ አግኝቶ አነጋግሯል። አስተዳደሩ የቤተሰብ ብልፅግና በሚል አደረጃጀት እና በልዩ ልዩ መልኩ ነዋሪውን በማቀናጀት በከተማ ግብርና ውጤት እያመጣ ይገኛል።

ወጣት ትዝታ ገዛኸኝ በአዳማ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወተት ላሞች ርባታ ተደራጅታ እየሠራች ነው። ሥራቸውን ከጀመሩ አንድ ወር ከ15 ቀናት ማስቆጠራቸውን ትገልፃለች። በተሰጣቸው ሼዶች ውስጥ ሰባት ላሞችን አስገብተው ሶስት ጥጆች መውለዳቸውን ተናግራለች። በቀን 30 ሊትር የወተት ምርት እያገኙ መሆኑንም ገልፃለች።

‹‹የከተማው አስተዳደር ከስንቄ ባንክ ጋር አስተሳስሮ ለላሞቹ ግዢ አስከ ሁለት ሚሊዮን ብር አመቻችቶልን ሥራችንን ጀምረናል›› በማለት የምትገልፀው ወጣት ትዝታ፤ የቤተሰብ ብልፅግና በሚል አደረጃጀት ውስጥ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ ተናግራለች። የውሃ እና የመብራት፣ የመኖ አቅርቦት ውድነት ችግር እንዳለ በመግለፅ፤ አስተዳደሩ ጊዜያዊ መፍትሄ እየሰጣቸው ቢሆንም በዘላቂነት ችግሩን እንዲፈታላቸው ጥያቄ አቅርባለች።

ወይዘሮ መዲ አያና በአዳማ ከተማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው እድል ቤተሰብ ብልፅግና በሚል አደረጃጀት በወተት ላሞች ርባታ ከባለቤታቸው እና ከልጆቻቸው ጋር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። መሬት ተመቻችቶላቸው የርባታ ሼዱን በመሥራት ከስንቄ ባንክ ብድር ከብቶችን ገዝተው በማመቻቸት ሥራውን የጀመሩት ከአምስት ወር በፊት ነው።

‹‹ለ17 ዓመት አስተማሪ ነበርኩ›› ያሉት ወይዘሮ መዲ፤ በከብት ርባታ በግል በመሥራት የተሻለ ገቢ ለመፍጠር እና ቤተሰባቸውን ለመደጎም መደራጀታቸውን ገልፀዋል። አስተዳደሩ በዘላቂነት የውሃ አቅርቦት ችግር እስኪፈታ በቦቲ እያዳረሰላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በከብቶች ርባታ በሚያገኙት የወተት ምርት የተሻለ ቤተሰባቸውን እየደጎሙ መሆኑን ገልፀዋል።

ወጣት ቴዎድሮስ አደፍርስ በከተማ መልካ አዳማ በሚባል አካባቢ የዓሳ ርባታ እያካሄደ የሚገኝ ወጣት ነው። የከተማ አስተዳደሩ እና የግብርና ፅህፈት ቤት ባመቻቸለት ቦታ ላይ ከ50 በላይ የዓሳ ማምረቻ ፖንዶች መገንባቱን ገልጿል። የዓሳ ርባታ ከማድረግ ባሻገር ሌሎች ወጣቶች ተደራጅተው ዓሳ ርባታ ላይ ሲገቡ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ይናገራል።

‹‹በከተማዋ ዓሳን በርካሽ እና በጥራት የማቅረብ እቅድ አለኝ›› ያለው ወጣቱ፣ ይህንን ዓላማ ለማሳካት የከተማ አስተዳደሩ ብድር፣ ቦታ እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ከጎኑ መሆኑን ተናግሯል። የዓሳ ርባታ ቦታው ለምግብነት ከሚውለው በተጨማሪ ለመዝናኛ እና ጉብኝት እያዋለው መሆኑን ተናግሯል። በቀጣይ ሰፋፊ እቅዶችን እንዳሉት እና ከግብርና ፅህፈት ቤቱ እና አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

አቶ አመንቴ አዱኛ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የቦሌ ክፍለ ከተማ የግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ክፍለ ከተማው በቤተሰብ ብልፅግና እና በማህበራት በአምስት የተለያዩ ሞዴሎች (በወተት ላሞች፣ በስጋ ከብቶች ማደለብ፣ በዶሮ፣ በዓሳማ እና በዓሳ ርባታ ዘርፍ) ህብረተሰቡን በማደራጀት ወደ ሥራ ተገብቷል። በአጠቃላይ በክፍለ ከተማው 713 ሼዶች ያሉ ሲሆን፤ በወተት ላሞች ርባታ 368 ሼዶች ተሠርተዋል። ለከብት ማደለቢያ መዋል የሚችሉ 147 ሼዶች፣ ለዶሮ 154 እና ለዓሳማ 30 ሼዶች ተገንብቷል። ለዓሳ ርባታ ስምንት ቦታዎች ተለይተዋል፡፡

የከተማ ግብርና ሼዶች በማህበራት እና በቤተሰብ ብልፅግና የተደራጁ ሰባ ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚሉት የጽህፈት ቤት ሃላፊው፤ ተደራጅተው ከሚሠሩት ዜጎች በተጨማሪ በከተማ ግብርና ሥራዎቹ ሶሰት ሺህ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ያስረዳሉ። በእያንዳንዱ ሼዶች ከአምስት እስከ አስር የሚሆኑ ሰዎች ተደራጅተዋል። በወተት ከብት፣ በስጋና በእንቁላል ልማት ዘርፍ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር መንግሥት የያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል መሠረታዊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ተደራጅተው በሚሠሩ የክፍለ ከተማዋ ነዋሪዎች የሚነሱ የውሃ፣ የመብራት እና የመኖ ችግር መኖሩን አንስተዋል። ውሃን በተመለከተ የከተማዋን ከንቲባ በማስፈቀድ በጊዜያዊነት ችግሩን ለመፍታት ለሼዶቹ በቦቴ ውሃ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ነው። ውሃ ማከፋፈሉ የከተማዋ አስተዳደር የማህበረሰቡን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት የጀመረው ፕሮጀክት እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚህ መልኩ ይቀጥላል ይላሉ።

በክፍለ ከተማዋ በአጠቃላይ ተግባራዊ ሊደረጉ ለሚታሰቡ ፕሮጀክቶች 12 የመብራት ማሰራጫ ትራንስፎርመር አስፈልጓል የሚሉት አቶ አመንቴ፤ ለጊዜው ሁለት ትራንስፎርመሮችን ማቅረብ የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀሪውን ቀስ በቀስ ለማመቻቸት እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ መንገድን በተመለከተ ግን በቂ መሠረተ ልማት የተገነባ መሆኑን አመልክተዋል።

የመኖ አቅርቦት ችግርን በተመለከተ እንደ ከተማ አስተዳደር በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት ግዙፍ ማቀነባበሪያ በአዳማ እየተሠራ ይገኛል። ማቀነባበሪያው ችግሩን በዘላቂነት ይፈታዋል። በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ ስድስት ሰዎችን በመኖ አቅርቦት ላይ ብቻ በማደራጀት ወደ ሥራ ተገብቷል ይላሉ።

እንደ ጽህፈት ቤት ሃላፊው ገለፃ፤ በጥቅሉ ክፍለ ከተማው በከተማ ግብርና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው። ከዚህ ቀደም በከተማዋ ወተት የሚገዛው ከ80 ብር በላይ ነበር። አሁን ከተማው ባደራጃቸው ሼዶች ውስጥ ተደራጅተው በሚሠሩ ማህበራት አማካኝነት በተዘጋጀ አደረጃጀት ከ55 እስከ 60 ብር ድረስ ለህብረተሰቡ እየቀረበ ነው።

በተዘጋጁ የወተት ምርት ላሞች ማርቢያ ሼዶች ውስጥ እስከ 20 ከብቶች ይገባሉ። የወተት ምርት በሙሉ አቅም መቅረብ ሲቻል የከተማዋን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር የወተት ማቀነባበሪያ ለሌሎች አጎራባች ከተሞች በስፋት ማቅረብ ይጀመራል። ለዚህም በከተማ ግብርና ተደራጅተው የወተት ላሞችን ለሚያረቡ ማህበራት ከስንቄ ባንክ ጋር በማስተሳሰር በዝቅተኛ ወለድ የብድር አገልግሎት እየቀረበ ይገኛል ብለዋል። በሌሎች የከተማ ግብርና ዘርፎችም እንዲሁ የፋይናንስ እና የባለሙያ ድጋፍ ይቀርባል ይላሉ።

እንደአጠቃላይ የከተማ ግብርና ምግብ በቀላሉ ለማቅረብ ያስችላል። ምግብ ከጓሮ ማግኘት ሲቻል፣ በከተማ ውስጥ ከተደራጁ ማህበራት በርካሽ መሸመት ሲቻል፤ ሰዎች ትኩስ አትክልቶችን፣ ጥራት ያለው የዓሳ ምርት ፍራፍሬዎችን እና እንቁላልን እንደልባቸው ማግኘት ሲችሉ፤ በከተሞች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች እያንዳንዱ ቤተሰብ የተሻለ ምግብ እንዲመገብ እና ጤናማ ሆኖ እንዲቆዩ ይረዳቸዋል። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዜጎች ሁሉንም ነገር ከገበያ መግዛት ስለማያስፈልጋቸው ገንዘብ እንዲቆጥቡም ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

በተጨማሪ የከተማ ግብርና ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ባለታሪኮች ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ ናቸው። በከተሞች ውስጥ ያሉ ወጣቶች ብዙዎቹ ሥራ የላቸውም። ሴቶች እና ወጣቶች በቤታቸው ወይም በአካባቢያቸው በከተማ ግብርና ቢሳተፉ፤ ይህንን የሥራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ያስችላል። ተደራጅተው የሚሠሩ ወጣቶች ካሉበት ደረጃም በተሻለ ከፍ እያሉ ይመጣሉ፤ በሚያገኙት ገንዘብ ህልማቸውን ከማሳካት ባለፈ ለኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት ሃይል መሆን ይችላሉ። ይህ ለቤተሰብ እና ለኢኮኖሚ ጥሩ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ይህንን መሠረት በማድረግ የከተማ ግብርና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ መሆኑ በመንግሥት ታምኖበታል። ከተሞች እያደጉ ሲሄዱ እና ብዙ ነዋሪዎች ወደ ከተማ ኑሮ ሲገቡ የማህበረሰቡ የምግብ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል። በከተሞች ውስጥ እንደ ስጋ፣ ወተት፣ ዶሮ እና ሌሎች የምግብ አይነቶችን ማምረት ዛሬ የሚያጋጥመውን ከምግብ ዋስትና ጋር የተቆራኙ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል። በከተማ ግብርና ረሃብ፣ የሥራ አጥነትን እና የጤና ችግርን መቅረፍ ይቻላል።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም፤ የከተማ ግብርና ለአካባቢ ተስማሚ ነው። ቆሻሻን ወደ ብስባሽነት ቀይሮ ለማዳበሪያነት እና ለመኖነት በማቅረብ የከተማዋን ጽዳት ለመጠበቅ ይረዳል። ምግብ ከሩቅ ቦታዎች ስለማይመጡ በጉዞ ወቅት ለሚፈጠር ብክለት አይጋለጥም። በከተማ ግብርና አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ የቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችም ይህንን ያሳያሉ። በአዳማ ከተማ በግብርና ላይ የተሰማሩ ባለታሪኮች ምሳሌም የዚሁ አካል ነው። አበቃን!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You