አዲሱ ገረመው
ጉዞ ወደ “የበረሃዋ ገነት”
ክፍል ሁለት
በአዲስ አበባ ጎሮ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ላይ የተመለከትነው ያን የመሰለ ሲኖ ትራኮች ግጭት እየዘገነነን የአደማ ፈጣን መንገድ የክፍያ ሥፍራ ደረስን። ይህ ፈጣን መንገድ ከ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት በዘመናዊነቱ በአገሪቱ የመጀመሪያው ነው።80 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዲስ አዳማ የፈጣን መንገድ 31 ሜትር ስፋት ሲኖረው፥ በአንድ ጊዜም በግራና በቀኝ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ያስተናግዳል።
መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ አዳማ ለመጓዝ የሚወስደውን ከአንድ ሰዓት የበለጠ ጊዜ ወደ 40 ደቂቃ ያሳጠረ ነው፤ይህም ጉዞውን እንደሚያፈጥን እሙን ነው። በዚህ መንገድ መጓዝ ፍጥነት ብቻ ሳይሆን ምቾትም ይሰማል። በተለይ ወደ ሌላ ቦታ ሲጓዙ ሰቀቀን የሚሆነው የትራፊክ አደጋ ሀሳብ ውስጥ ላይገቡ ይችላሉ። ምክንያቱም ተሽከርካሪዎች በምን አይነት ፍጥነትና በየትኛው መስመር መጓዝ እንዳለባቸው አመላካች ጽሁፎች በየኪሎ ሜትሮች ተለጥፈዋልና።
ከአዳማ የሚመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተሰልፈው አጋጠመን፡፡ምክንያቱ ታዲያ መንገድ ጠቦ አሊያም ተዘጋግቶ እንዳይመስላችሁ። ከፈጣን መንገድ መውጫው ላይ ጠበቅ ያለ ፍተሻና ቁጥጥር ስላለ ነው። ሁሉም ተሽከርካሪ ይፈተሻል። የተሽከርካሪዎቹ ቁጥር ብዙ ቢሆንም ፈታሾች በንጽጽር ጥቂት ናቸው። ለዚህም ይመስላል መኪኖች ረጅም ጊዜ ለመቆም የተገደዱት።
በዚህ የፍተሻ ሥፍራ ከታዘብኩት ነገር አንዱ አራት ቁጥር የሆኑና በጥቁር የቀለም መደብ የተጻፉት የመንግስት ተሽከርካሪዎች ከየትና ወዴት ነው ከሚል ቃል ውጭ እምብዛም አለመፈተሻቸውን ነው። በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ወንጀል ይሰራባቸዋል ተብሎ ስለማይታሰብ ይሆን? ይህ ሆኖ ከሆነ ጎበዝ እንኳን ታርጋ የሰውን ነፍስ መቀየር የሚቀራቸው ዘራፊዎች ባሉባት አገር እንዲህ በቀላሉ ማለፉ ጥሩ አይመስለኝም።
ሾፌራችን የክፍያ ደረሰኙን ከተቀበለ በኋላ መኪኖች እንደ ውሃ በሚፈሱበት መንገድ የኛም ኮስትር ወግ ደርሶት ይፈስበት ጀመር። ይገርማችኋል ይሄንን መንገድ ብዙ ጊዜ ብመላለስበትም ዛሬ ግን በትዝብት ለመመልከት ነው ፍላጎቴ። የጉዞ ማስታወሻ ትረካዬን ሳስብ የጨነቀኝ መታመን ያቅተኛል ብዬ አይደለም፤ ያየሁትን በትክክል መግለጽ ይቸግረኛል ብዬ ነው።
የአዳማ ፈጣን መንገድ ያስጎመዣል፤ ስምንት ትልልቅ ድልድዮችን፣ ከ77 በላይ አነስተኛ ድልድዮችን፣ 43 የሚደርሱ የእግረኛና የተሽከርካሪ መተላለፊያዎች የተገነቡለት ፈጣኑ መንገድ የመዘመናችን አንዱ ማሳያ እንደሆነ ገባኝ። ሆኖም በየ መሀሉ የሚገጥሙን አንዳንድ ነገሮች ዝመናው በቀረብኝ ያስብላሉ፡፡
ፈጣኑን መንገድ በደንብ ተያይዘናል። አንዳንዱ አዲስ የሆነበትና ሊያየው የቋመጠለትን ፈጣኑን መንገድ መሳጭ በሆነ ድባብ “ማየት ማመን ነው” እንደተባለ ሰው ግራ ቀኙን ያማትራል። የቻይናውያንን የመንገድ ግንባታ ጥበብ አየን። ባየነው ችሎታና የኮንስትራክሽን አቅም ተደነቅን። እውነትም ማየት ማመን ነው። የአገር ውስጥ የመንገድ ስራ ተቋራጮችም ከዚህ መማር ይኖርባቸዋል።
አንዳንድ ቦታ ላይ መንገዱ ተበላሽቶ እየተጠገነ ነው። ፈጣኑ መንገድ የዕድሜውን ያህል አይደለም። መጎሳቆል ይታይባታል፤አልፎ አልፎ የተጎዱት አካላቱም ይህንኑ ይጠቁማሉ። መቼም ይሄ ዕዳው ተከፍሎ ያላለቀ መንገድ ለወጭ መዳረጉ ሁሉንም ያስቆጫል። ከሁሉም የሚያናድደው ፍጥነት መቀነሻ ተብለው የተካሄዱት ግንባታዎች በአሽከርካሪዎች ተለምደዋል፤በዝግታ ሊታለፉ ሲገባ በፍጥነት ይነዳባቸዋል። አይ የኛ ነገር በቃ ተቃርኖ የሚባል ነገር እኮ አይተወንም። ይሄንን ሳይ በከተማችን “መሽናት ክልክል ነው” ተብሎ በተጻፈባቸው ሥፍራዎች ላይ የሚሸኑ ሰዎች ትዝ አለኝ።
ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን አለፍ እንዳልን ከመካከላችን አንደኛው ውሃ ሽንት መጥቶበት ሲያቁነጠንጠው አስተባባሪው ለሹፌሩ ነገረው። ችግር ቢያጋጥም ከዋናው መንገድ ወደ ዳር ወጣ ብሎ ለመቆም ምቹ የሆነበት አካባቢ ላይ ሹፌሩ መኪናውን አቆመ። ለመሽናት የጠየቀው አንድ ሰው ቢሆንም ብዙዎች ተከትለውት ወረዱ። ይሄ ሽንት የሚሉት ነገር ስለሽንት ሲወራ ወይም ሰው ሲሸና ሲታይ መጣሁ መጣሁ ይል አይደል፡፡
ይሄንን በመሰለ መንገድ እየተጓዙ የጽዳት ችግር ሲያጋጥም ምንኛ ያናድዳል መሰላችሁ። ለሽንት መሽኛ ተብሎ መጸዳጃ ቤት ባለመዘጋጀቱ በመንገዱ ዳር ነው ሰዎች የሚጸዳዱት። በውጭው ዓለም እንዲህ አይነት መንገድ ሲሰራ ለተጓዡ ተዝናኖትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ማረፊያዎች ጭምር አብረው ይዘጋጃሉ።ይሄ በቀጣይ ሊሰሩ በታሰቡ ፈጣን መንገዶች ላይ ሊታሰብ የሚገባ አብይ ጉዳይ ነው።
ለሽንት የወረዱት ተመልሰው አለፍ ስንል ደግሞ ሌላ አዲስ ክስተት አየን።መኪና ይሁን መጋኛ የመታው ምንነቱ የማይታወቅ አንድ እንስሳ ተገድሎ መንገዱ ላይ ይታያል። የኛ ተሽከርካሪ በፍጥነት ይጓዝ ስለነበር ብዙም ለማየት አልተቻለኝም። ክስተቱ ግን አንድ ነገር እንድገምት አድርጎኛል።
እንስሳትም ሆኑ ሰዎች ወደ መንገዱ እንዳይገቡ የሚከላከል የሽቦ አጥር በመንገዱ ዳር አለ። ነገር ግን በማን አለብኝነት አጥሩን በገነጠሉ ሰዎች አማካኝነት እንስሳት ወደ መንገዱ እየገቡ የመኪና እራት ሆነው ይቀራሉ። ፎቷቸውን ማንሳት ባልችልም፤ አጥሩን ጥሰው ገብተው በነጻነት ዘና ብለው በመንገዱ ዳር እያወጉ የሚጓዙ ሁለት ሰዎችንም ተመልክቻቸዋለሁ። ምን ይታወቃል እኔን አልገጠመኝ ይሆናል እንጂ ህጻናትም ዘለው ወደ መንገዱ ይገቡ ይሆናል። ፈጣኑ መንገድ ፈጣን እርምት ይሻል።አጥሩ በቀላሉ ሊገነጠል የሚችል በመሆኑ እንዲህ አይነት ችግሮች ሳይከሰቱ መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል።
ጉዞአችን ቀጥሏል። ጸሐይዋ ሙቀቷን እየጨመረች ነው።ፈጣኑን መንገድ አገባድደን ክፍያውም ተፈጽሞ የስምጥ ሸለቆዋን አዳማ በጀርባዋ (በምዕራብ) በኩል አርገን አለፍናት። የወለንጭቲንና መተሀራን አቅጣጫ ይዘን ነጎድን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013