ፍቅሬ አለምነው
ዓድዋ አባቶቻችን በወራሪው የጣሊያን ሠራዊት ላይ የተቀዳጁት ዓለም ከዓለም ያስተጋባ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ታላቅ ድል ነው። የዓድዋ ድል በሥልጣኔ ገፍተናል በጦር ኃይል የመጠቅን ነን ያሻንን እናደርጋለን ለሚሉት እብሪተኛና አምባገነናዊ ኃይሎች ሁሉ አንንበረከክም የሚል ብርቱ መልዕክት አስተላልፏል።
አዎን የአባቶቻችን ልጆች ነን። ትናንትም አልተንበረከክንም። ዛሬም ወደፊትም አንንበረከክም። ኢትዮጵያን በኃይል፣ በተጽእኖ፣ በማስፈራራት ጫና በማድረግ ማንበርከክ መቼም አይቻልም።
የብራስልስ ውል ፈራሚዎቹ እንግሊዝ ጣሊያንና ፈረንሳይ አፍሪካን ለመቀራመት ወስነው በተንቀሳቀሱበት ወቅት ጣሊያንም በበኩሏ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ ከንቱ ሕልም አልማ ነበር። በእሳተ ገሞራ የመጫወት ከንቱ ሕልም። ኢትዮጵያ ቀደምትና ጥንታዊ ከሆኑት የዓለማችን ሀገራት አንዷ ናት። የሰው ልጅ መገኛ ምድር የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች ውብ ሀገር።
ይህችን ሀገር ለመዝረፍ ለመመዝበር በጦርነት ለመውጋት ቱርኮች፣ ድርቡሾች፣ ግብጾች፣ ሱዳኖች በአቅሟ ሶማሊያ በግብጽ እየተረዳች ጣሊያኖችም ሞክረዋል። ኢትዮጵያ መቀበሪያቸው ሆነች እንጂ አንዳቸውም ሕልማቸውን አላሳኩም። ዛሬም በተለያየ መልኩ ለሚፈታተኑን የዓድዋ መልዕክት ነው ያለን። እናንተ ትጠፋላችሁ እንጂ ኢትዮጵያ አትጠፋም። አንንበረከክም!!
ኢትዮጵያውያን ለነፃነታችን ቀናኢ ለክብራችን ሟች የራሳችንን አሳልፈን የማንሰጥ የሰውም የማንፈልግ ነን። ጣሊያን የገዘፈ ሠራዊት ዘመናዊ መሣሪያ ቦምብ መትረየስና መድፍ አስታጥቃ ባሕርና ውቅያኖስ አቋርጣ በመምጣት በኤርትራ በኩል በመግባት ትግራይን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ ነበር። ወደ መሀል ሀገር ለመስፋፋት የነበራት አላማ የመከነው በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች ታላቅ ተጋድሎ ነው። ዓድዋ ላይ ተደምስሳ ተቀብራለች።
አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ይመሩት የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወረኢሉ ከቶ፤ እግረኛና ፈረሰኛ ሆኖ በመዝመት በራሱ ስንቅና ትጥቅ የነጭ ወራሪ ሠራዊትን ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁር ሕዝብ ኃያል ክንድ ደቁሶ ሰባብሮ በጥቁር መሬት ላይ ቀብሮታል።
ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ አርአያ፣ ኩራት፣ ተምሳሌት፣ ፋና የሆነ ድል ነው የዓድዋው ድል። የአንንበረከክም ለወራሪዎች አንገዛም እምቢ አሻፈረን፤ ለሀገሬ ለነፃነቴ እሞታለሁ እሰዋለሁ ያሉ ትንታግ ጀግኖች ተአምራዊ በሆነ የውጊያ ስልት ጠላትን ድል የመቱበት ድል ነው የዓድዋ ድል።
ድል አድራጊዎቹ ለጠላት እሳት ረመጦቹ በመድፍና በመትረየስ ፊት ግንባራቸው የማይታጠፈው ጭርሱንም ሞትን ንቀው እየሸለሉ እየፎከሩ ተንደርድረው የሰላቶን አንገት በጎራዴ እየቀነጠሱ ደረቱን በጦር እየወጉ ያስመዘገቡት ድንቅ ድል ነው የዓድዋ ድል። ዛሬ በየቦታው ከጀርባ ለሚልከሰከሱት በኢትዮጵያ ላይ እየዘመቱ ላሉት ባእዳንና ቅጥረኞቻቸው ሁሉ ዘመን የማይሽረው የአንንበረከክም መልዕክት ያስተላለፈ ነው የዓድዋ ድል።
የአላጌው የመቀሌውና በመጨረሻም የዓድዋው ተከታታይ ድል ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ የተከወነ ነው። የጥቁር ሕዝብን ዘር ለማጥፋት ያሴሩትን ነጮች ቅስም በመስበር አንድ አፍታ ቆመው እንዲያስቡ አድርጓል። በኢትዮጵያ ምድር ዓድዋ ላይ ጥቁር ሕዝብ በነጭ ወራሪ ጣሊያኖች ላይ ያስመዘገበው አብሪ ኮከብና አንጸባራቂ የሆነው ድል መላው አውሮፓን አሸብሯል። አንቀርቅቦ ንጦታል። እንዴት በጥቁር እንሸነፋለን በሚል።
ከዓድዋ ድልና የጠላት ሽንፈት በኋላ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ የዓድዋን ድል የሚሽር አንድ፤ አንድ ብቻ ጦርነት አድርጉና ድል አድርጉልኝ ሌላውን እኔ በእርቅ እፈታዋለሁ ሲል ጀነራሎቹን ተማጽኖ ነበር። ያንን እሳተ ገሞራ ክንድ የቀመሰ በጎራዴ የተቀላ ለአሞራ ሲሳይ የሆነውን የጣሊያን ወታደሮችና መኮንኖች ሬሳ ያየ ያስታወሰ የጣሊያን ጀነራል ሁሉ ለመዋጋት ወኔ አጣ። ወኔው ከዳው።
እሳቱ —— —- የእሳቱ ማገር
የአባ ጉረድ ልጅ—- ወንዝ የሚያሻግር !!
በለው ያለ እለት— ማቆሚያ የለው
የጠላት ነዶ——- የሚከምረው !!
በደም አበላ—- ሲታጠብ መሬት
ጠምዶ ማይፈታው—በለው ያለ ለት !!
መትረየስ ሲስቅ—መድፉ ሲያጓራ
ገዳይ ሰላቶ– ገዳይ–በመውዜር–እያንጠራራ
የኢትዮጵያ ልጅ—— ሞት የማይፈራ !!
እያሉ በታላቅ ጀግንነት ጠላትን አፍረክርከው አብረክርከው የደመሰሱት የእነዛ የእሳት ጉማጅ የሚባሉት ጀግኖች ልጆች ኢትዮጵያውያን ነን። ዓድዋን ማክበር ማለት አደራቸውን መጠበቅ ማለት ነው። ለሀገር ክብር ነፃነት ጸንቶ መቆም ጠላትን መመከት መታገል ማሸነፍ ነው።
በባዶ እግራቸው በቁምጣ ሱሪ እሾህና ገደሉን አልፈው በቂ ስንቅ ድርጅትና ዘመናዊ መሣሪያ ሳይኖራቸው ጋሻ ጦር ጎራዴ፣ ወጨፎ፣ ውጅግራ ለበን፣ ምኒሽር፣ አልቤን ጥንታዊ መሣሪያዎችን ይዘው በታላቅ ወኔ ኩራትና ክብር ዓድዋ ድረስ ተጉዘው ተዋግተው ድል ያደረጉት አባቶችህ አጽም እንዳይወቅስህ አንተ ትውልድ ሀገርህን ከውጭ ጠላትና በሀገር ውስጥ ከተፈለፈሉ ባንዳዎችና የባንዳ ውላጆች ነቅተህ ጠብቅ። ዛሬም ዓድዋን በሌላ መልኩ መድገም የሚያስፈልግበት ወሳኝ የታሪክ ወቅት ላይ ነን።
ዓድዋ ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል መቀጣጠል አርማ ሆኗል። የዓድዋው ድል ለፓን አፍሪካኒዘም መመስረትና ማደግ ለበርካታ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ ሀገሮች ነፃ መውጣት ታላቅ አርአያ ሆነ። ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት በጉልበት በኃይል በባርነት አስደግድገው ቀጥቅጠው ለመግዛትና ሀብቷን ለመዝረፍና ለመክበር ሲሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ገድለዋል። እንደ አውሬ በሰንሰለት አስረው በባርነት ወደ አውሮፓ አግዘዋል። የሰውን ልጅ እንደ ሸቀጥ ሸጠዋል። ለውጠዋል። በደልና ግፍ አይረሳም። አንረሳምም። የዓድዋው የአባቶቻችን ድል ይሄን ሁሉ የሰበረና ያንበረከከ ነው። መልዕክቱ ግልጽ ነው። በነፃነት የተወለድን፤ በነፃነት የኖርን ኩሩና ጀግኖች ነን። ለየትኛውም ኃይል አንንበረከክም። ለሀገራችን ለክብራችን ለነፃነታችን ታግለን ተዋግተን ሞተን ድል ማድረግ እንችላለን ነው የዓድዋው መልዕክት።
ጣሊያኖች የሰለጠኑ ሕዝቦች ስለሆኑ ዘመናዊ የጦር መሣሪያና የተማሩ የጦር መሪ ጀነራሎች ስላላቸው በየትኛውም ጦር ሜዳ አይሸነፉም የሚለውን የነጮች ቅዠት ያመከነ፤ ጥቁሮች በጦር ሜዳ ተዋግተው በወታደራዊ ስልትና ስትራቴጂ ልቀው ማሸነፍ እንደሚችሉ ለዓለም ያረጋገጠ ድል ነው ዓድዋ።
ዓድዋን የታደጋት ከወራሪው የጣሊያን ሠራዊት መንጋጋ ፈልቅቆ ነፃነት ያቀዳጃት ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥቶ ሀገሬ ብሎ የዘመተው ሕዝብ ነው። ሌላ ማንም አይደለም።
በአጼ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ የሚመራው በርካታ ራሶችና ደጃዝማቾች በጦር መሪነት የተሰለፉበት የኦሮሞው ፈረሰኛና እግረኛ፤ የአማራው፤ የሶማሌው፤ የወለጋው፤ የሐረሩ፤ የባሌው፤ የጋምቤላው፤ የቤኒሻንጉሉ ወዘተ ሠራዊት ተሰባስቦ ሀገሬ ተወረረች ብሎ ተዋግቶ ነው ትግራይ መሬት ላይ ጣሊያንን አፈር አስግጦ የደመሰሰው።
አባቶች ቢያልፉም ታሪካቸው ገዝፎ ይኖራል። የዓድዋ ታሪክ የተመዘገበው በአጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መሪነት የተሰለፈው ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣ ሠራዊት በፈጸመው ታላቅና ድንቅ ተጋድሎ ነው።
የዓድዋ ድል መላውን የዓለም የጥቁር ሕዝብ ከዘር መጥፋት የታደገ ታላቅ አንጸባራቂ ዓለም አቀፋዊ ድል ነው። የቅኝ ግዛት ዘመን እሳቤያቸው ድል የተመታው ምዕራባውያን አፍሪካን በእጅ አዙር ለማስገበር ብዙ ደክመዋል። ዛሬም አልተኙም። ዛሬም ሉአላዊና ነፃ በሆኑ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ገብተን እንፈትፍት እናቡካ እንጋግር እያሉ ነው። በአንድ ሀገር ሉአላዊነትና የውስጥ ጉዳይ መግባት አይቻልም። ዓድዋ ዛሬም ነገም ወደፊትም ይደገማል። አንንበረከክም!!
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013