‹‹የወለድነውን ሰላም ልንንከባከበው ይገባል፡፡››የሰላም እናቶች
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች እና አመራሮች ጋር በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ ተወያይተዋል፡፡ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ባደረጉት ንግግር ‹‹ጣና ላይ ያለው ችግር የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ችግር ነው›› ብለዋል፡፡
አብመድ እንደዘገበው ‹‹በኢትዮጵያ የትኛውም ቦታ ያለ ችግር የኢትዮጵያውያን ችግር በመሆኑ ጣና ሐይቅ ላይ የተጋረጠውን አስከፊ የእምቦጭ አደጋ ለመታደግ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል›› ብለዋል ምክትል ከንቲባው፡፡
‹‹የስኬታችን ሚስጥር አንድነታችን ነው፡፡ የኦሮሞ ወጣቶች ‹ጣና ኬኛ› ብለው በውቢቷ ባሕር ዳር መምጣታቸውን አስታውሰው የጣና ሐይቅን ከችግር ለመታደግ አሁንም ጅምሩ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል›› ብለዋል ኢንጂነር ታከለ ኡማ፡፡
‹‹አንድነታችንን የሚጠላው ጠላታችን ነው ፤ አንድነታችን የቆጠቆጣቸው ኃይሎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መሽገዋል›› ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ለፖለቲካ ትርፍ በየድረ-ገፁ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚጥሩ አካላትን ወጣቱ ሊጋፈጣቸው እንደሚገባም ሲያሳስቡም ‹‹በአንድነታችን ላይ የተቃጣውን የትኛውንም ዓይነት እምቦጭ በተባበረ ክንዳችን ልንነቅለው ይገባል›› ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከዘጠኙም ክልሎች የተውጣጡ የሰላም እናቶች ተገኝተዋል፡፡ የሰላም እናቶች በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹የወለድነውን ሰላም ልንንከባከበው ይገባል፣ ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባዋል›› ብለዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች ሰላም ከሌለ ሀገር እንደሌለ በመረዳት ለሰላም ቀን ከሌሊት ሊታትሩ እንደሚገባ እናቶች አሳስበዋል፡፡
ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች እና አመራሮችም ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ እሳቸውም የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች እና አመራሮች ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል እና መስተንግዶ አመሥግነዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንቦጭን ለመከላከል 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡