ሶሎሞን በየነ
የአፈር ምርምር ለአገሪቱ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የአፈር ምርምር ሀገሪቱ ለምታራምደው ግብርና ሥራ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበትም ብሔራዊ የአፈር ምርመራ ማዕከል በአዋጅና ደንብ የተቋቋመ ሲሆን ተጠሪነቱም ለግብርና ሚኒስቴር ነው።
ተቋሙም አፈር ምርመራና ምርምር ላይ የሚሰራ አንድ ለእናቱ የሆነ ብቸኛ የፌዴራል መንግሥት መስሪያቤት ሲሆን የሚገኘውም በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአዲሱ ወረዳ 01 በተለምዶ ፍላሚንጎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ጀርባ ነው።
ማዕከሉ የአፈር፣ የእፅዋትና የውሃ ነክ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በአሲዳማ አፈር ልማት ላይ ምርምር የሚያካሂድና ትንተና የሚሰጥ አገራዊ ተቋም ከመሆኑም ባሻገር የጥራጥሬ ሰብሎችን ምርታማነትን የሚጨመር ህያው (Bi0fertilizer) ማዳበሪያ በማምረት በመላው አገሪቱ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እንዲሁም የምርቱ ተጠቃሚ ለሆኑ ሌሎች አካላት በተመጣጣኝ ዋጋ በማሰራጨት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ እየደገፈ የሚገኝ ተቋም ነው።
እንዲሁም ተቋሙ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ትኩረት የሰጠውን የመስኖ እርሻ ማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት የመጠቀምና አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ቴክኖሎጂ ላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመስጠትና ግብዓቶችን በማቅረብ አገሪቱ ከውጭ አገር የምታስገባውን የስንዴና መሰል የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተከናወነ ያለውን ሥራ በእጅጉ እያገዘ ይገኛል።
ብሔራዊ የአፈር ምርመራ ማዕከል በአገሪቱ ያለ ብቸኛ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በሁሉም ክልል የሚገኙ 17 የአፈር ምርመራ ላብራቶሪዎችን (ቤተሙከራዎችን) አቅም በስልጠና፣ በማቴሪያል፣ በመሳሪያ ተከላናና ገጠማ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍና እገዛ የሚያደርግ ነው።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲዎችን የአፈር ምርመራ ማዕከላትን አቅም ለማጠናከር የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ከመሆኑ ባለፈ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የተግባር ትምህርት ድጋፍ የሚሰጥ እንዲሁም ለዘርፉ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ማዕከሉ የአገሪቱን የአፈር ለምነት መረጃ የሚያመለክት አገር አቀፍ የአፈር መረጃ ካርታ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን የአገራችን አርሶ አደሮችና ሌሎች የመረጃው ተጠቃሚ አካላት በአፈር መረጃ ካርታው በመታገዝ የተሻለና ሳይንሳዊ የሆነ የማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። እያደረገም ይገኛል።
በዚህም የአገሪቱን የአፈር ሀብት መረጃ በማስተዳደር የአፈር ሀብት መረጃውን ወቅታዊና ዘለቄታዊ ማድረግ እንዲቻል የማዕከሉን አቅምና ደረጃ ከፍ በማድረግ ማዕከሉን ወደ ኢንስቲትዩት ከፍ ለማድረግ ማለትም <<የኢትዮጵያ የአፈር ሀብት ኢንስቲትዩት>> ሆኖ እንዲቋቋም በማስፈለጉ የሚኒስትሮች ምክር ቤር ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባው በደንብ ቁጥር 418/2010 በወሰነው መሠረት የኢትዮጵያ የአፈር ሀብት መረጃ ኢንስቲትዩት ሆኖ እንዲቋቋም ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ውሳኔው እየተጠበቀ ይገኛል።
በጥቅሉ ማዕከሉ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ / FAO)ና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ድጋፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተሰራና በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ብሎም በአፍሪካ ከሚገኙ ጥቂት ደረጃቸውን ከጠበቁ ላብራቶሪዎች ግንባር ቀደም ሲሆን፤ ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝና አያሌ ሙህራኖችን ያፈራ ተቋም ነው።
እጅግ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ፈሶበት በአፍሪካ ካሉት ከፍተኛ የአፈር ምርምር ማዕከሎች አንዱና ግንባር ቀደም የሆነው ይህ ማዕከል በቅርብ ጊዜም ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በተገኘ የ1.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት በከፊል እድሳት ተደርጎለታል።
ቀሪ እድሳቱን ለማስጨረስ ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር (GIZ) በተገኘ 1.2 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማደስ ዝግጅቱ ተጠናቆ በሚገኝበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ማዕከሉ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ማስፋፊያነት እንዲውል የተወሰነ መሆኑን በመግለጽ፤ የካሳና የምትክ ቦታን ለመወሰን ያመች ዘንድ የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ማዕከሉ እንዲያቀርብ ሲል ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ቂ/ክ/ከ/መ/ል/ከ/ማ/ጽ/ቤት/197/11 በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቋል።
የተቋሙ ሠራተኞችም ተቋሙ በመልሶ ማልማት ግንባታ እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ ይህን ማዕከል መልሶ በሌላ ቦታ ለመሥራት ቢታሰብ ላብራቶሪውን ለመሥራትና መሣሪያዎቹን ለመግጠም ቢያንስ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት የሚፈጅ ሲሆን፤ በማዕከሉ የሚገኙ ከህንጻው ጋር ተያይዘው የተዘረጉ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መሣሪያዎች ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ የሚል ስጋት ያነሳሉ።
በመሆኑም እንደዚህ አይነት ከአገርም አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ ላብራቶሪ ለመገንባት ቢታሰብ አገሪቱን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣት ከመሆኑም ባሻገር ከሚወስደው ጊዜ አንፃርም በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በመኖሩ አገሪቱን ከፍተኛ ኪሳራ ላይ የሚጥል ይሆናል ይላሉ።
ሠራተኞቹም ይህንን የአገር ሀብት የሆነ ብቸኛ ማዕከል በውጭ እንደማንኛውም ቤት አይቶ በልማት ተነሺ ቤቶች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ተገቢ ባለመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን እንዲያጤኑት ግፊት ቢያደርጉም ሰሚማጣታቸውን ገልፀው፤ ማዕከሉ ቢፈርስ በአገሪቱ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርትና መርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ እንዲሁም አገራዊ ኪሳራው ላይ በቂ ጥናት ሳይደረግበት ከይዞታው ላይ ለማንሳት የተወሰነውን ውሳኔ መንግሥት ቆም ብሎ እንዲያስብበትና ህብረተሰቡም ስለተቋሙ ግንዛቤ ኑሮት በኔነት ስሜት እንዲጠይቅ በማድረግ ከታሪክ ተወቃሽነት እራሳቸውን ነፃ ለማድረግ እንደሚከተለው ቅሬታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።
የሠራተተኞቹ ዝርዝር አቤቱታ
ሠራተኞቹ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ ብሔራዊ የአፈር ምርመራ ማዕከል ቀደም ሲል በግብርና ምርምር ኢንስቲትትዩት ማቋቋሚያ በወጣው አዋጅ ሥር የአፈር ጥናት ላብራቶሪ በሚል በኢንስቲትዩቱ ተካቶ የነበረ ሲሆን፤ ማዕከሉ ከአፈር ባሻገር በውሃና እጽዋት ላይ ምርመራና ምርምር የሚያደርግ ብቸኛ አገራዊ ተቋም ከመመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሚፈለገው አካል ሁሉ ስለአፈር፣ ውሃና እፅዋት መረጃ እንዲያቀርብ በሚል በ1982 ዓ.ም በዓዋጅና ደንብ እራሱን ችሎ ተቋቁሟል።
ማዕከሉም በተባበሩት መንግሥታት የምግብ ዕርዳታ ድርጅት (ፋኦ) ዕርዳታ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተሠራ ማዕከል ሲሆን፤ አሁን ማዕከሉ ያለበት ቦታ ለቤተሙከራ ሥራው ተስማሚ መሆኑ በባለሙያ ተፈትሾና ተጠንቶ የተመረጠ ቦታ ነው። የቤተሙከራ ሥራ ሲሰራ ኬሚካሎችና አሲዶች በአካባቢው ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ህንፃው፤ ወለሉም፤ ግድግዳውም፤ ዙሪያውን ሙሉ ለሙሉ በኮንክሪት የተሰራ ነው። የህንፃው ወለል ላይ የተነጠፈው ሴራሚክ አሲድና ቤዞችን መቋቋም የሚችል ንጣፍ ከውጭ አገር መጥቶ የተገጠመለት ነው።
የማዕከሉ ቤተሙከራ ወይም ላብራቶሪው የተገነባው ማንኛውም አይነት ኬሚካላዊ ለውጦች በቤተሙከራ ውስጥ በሚካሄዱበት ወቅት በሰውና በአካባቢው ላይ ተጽኖ እንዳያሳድር ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፤ ለእያንዳንዱ የኬሚካል ፍሳሾች በየራሳቸው መፋሰሻ መስመር አልፈው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ታንከር ውስጥ ከተቋተ በኋላ የማጣራት ሥራ ተሠርቶ በፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦ የሚወገድ ይሆናል። በመሆኑም ለዚህ ተብሎ በእያንዳንዱ ክፍል የተገጠሙ ቱቦዎችና የኤሌክትሪክ መስመሮች የተገጠሙለት መሆኑን ሠራተኞቹ ይናገራሉ።
በጥቅሉ ማዕከሉ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ፈሶበት በአፍሪካ ካሉት ከፍተኛ የአፈር ምርምር ማዕከሎች አንዱና ግንባር ቀደም በሚባል ደረጃ የተገነባ ሲሆን፤ ማዕከሉም የአፈር፣ የዕጽዋትና የውሃ ናሙናዎችን ከመመርመር ባሻገር የጥራጥሬ ሰብሎች ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ የሚጨምር ህያው ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ በመላ አገሪቱ የማሰራጨት ሥራ ይሠራል። ይሄን ማዳበሪያ በግል የሚያመርቱ ድርጅቶችን በመቆጣጠርና ስልጠና በመስጠት ጭምር እገዛ እንደሚያደርግ ይናገራሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ብሔራዊ የአፈር ምርመራ ማዕከል በአገሪቱ ያለ ብቸኛ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በሁሉም ክልል የሚገኙ 17 የአፈር ምርመራ ላብራቶሪዎችን (ቤተሙከራዎችን) አቅም በስልጠና፣ በማቴሪያል፣ በመሣሪያ ተከላናና ገጠማ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍና እገዛ የሚያደርግ ነው።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲዎችን የአፈር ምርመራ ማዕከላትን አቅም ለማጠናከር የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ከመሆኑ ባለፈ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የተግባር ትምህርት ድጋፍ የሚሰጥ እንዲሁም ለዘርፉ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ማዕከሉ የአገሪቱን የአፈር ለምነት መረጃ የሚያመለክት አገር አቀፍ የአፈር መረጃ ካርታ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን የአገራችን አርሶ አደሮችና ሌሎች የመረጃው ተጠቃሚ አካላት በአፈር መረጃ ካርታው በመታገዝ የተሻለና ሳይንሳዊ የሆነ የማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። እያደረገም ይገኛል ይላሉ።
ማዕከሉም በ2007 ዓ.ም ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በተገኘ 1.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት በከፊል እድሳት እንደተደረገለት የተቋሙ ሠራተኞች ጠቁመው፤ ነገር ግን እድሳቱን ለማካሄድ ጨረታ ሳይወጣ በሕገወጥ መንገድ ለአንድ ኮንትራክተር በመሰጠቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ጨርሶ እንዲያስረክብ የተባለውን ሥራ አራት ዓመት ውስጥ ጨርሶ እንዳላስረከበ እንዲሁም መሥራት ያለበትን አፍርሶ መሰራት የሌለበትን ሠርቶ በማዕከሉ ላይ ትልቅ ኪሳራ አድርሷል።
በጥቅሉ ኮንትራክተሩ መሥራት ያለበትን አጠቃሎ ሠርቶ ሳያስረክብ ገንዘቡን ወስዶ መቅረቱንና እስካሁን እርክክብ ሳይደረግባቸው አዲስ የተገነቡ ሁለት ክፍሎች ተዘግተው አገልግሎት ሳይሰጡ እያረጁ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ የጀርመን ተራድኦ ድርጅ (ጂአይዜድ) የማዕከሉ እድሳት ሙሉ ለሙሉ አለ መጠናቀቁን ሲሰማ የማዕከሉን ቀሪ እድሳት ለማስጨረስ 1.2 ሚሊዮን ዩሮ በጀት መድቦ ለመሐንዲስ ከፍተኛ ወጭ አውጥቶ አስጠንቶ ማዕከሉን ለማደስ ዝግጅቱን አጠናቆ በሚገኝበት ወቅት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ማዕከሉ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ማስፋፊያነት እንዲውል የተወሰነ መሆኑን በመግለጽ፤ የካሳና የምትክ ቦታን ለመወሰን ያመች ዘንድ የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ማዕከሉ እንዲያቀርብ ሲል ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ቂ/ክ/ከ/መ/ል/ከ/ማ/ጽ/ቤት/197/11 በተጻፈ ደብዳቤ መጠየቁን ተናግረዋል።
የተቋሙ ሠራተኞችም መንግሥት እንደሚከተለው ፖሊሲ ለልማት ያስፈልገኛል ያለውን የማፍረስም የመገንባትም መብት ያለው ቢሆንም ቅሉ፤ ተቋሙ በመልሶ ማልማት ግንባታ እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ ይህን ማዕከል መልሶ በሌላ ቦታ ለመሥራት ቢታሰብ ላብራቶሪውን ለመሥራትና መሣሪያዎቹን ለመግጠም ቢያንስ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት እንደሚፈጅ በባለሙያ መጠናቱን ገልፀው፤ እንደዚህ አይነት ከአገርም አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ ላብራቶሪ ለመገንባት ቢታሰብ አገሪቱን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣት ከመሆኑም ባሻገር ከሚወስደው ጊዜ አንፃርም በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በመኖሩ አገሪቱን ከፍተኛ ኪሳራ ላይ የሚጥል ይሆናል ይላሉ።
አገሪቷ ከያዘችው የግብርና መር ኢኮኖሚ አንፃር የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ተቋማትን ማፍረስ መንግሥት ከቆመለት ፖሊሲ አንፃር የሚፃረር ተግባር ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ላብራቶሪው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ መልሶ ለመገንባት ቢታሰብ አገሪቱን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ከመሆኑ ባለፈ አብዛኛዎቹ የላብራቶሪ መሣሪያዎች በፋኦ ዕርዳታ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የገቡ ከመሆናቸው በተጨማሪ መንግሥት አሁን ላይ በዓለም ገበያ የማይገኙ በጣም ጥራት ያላቸው እቃዎችን ከውጭ ገዝቶ አምጥቶ በማዕከሉ እንዲገጠሙ አደርጓል።
ስለዚህ ማዕከሉ ሲፈርስ እነዚህ እቃዎች ከጥቅም ውጭ ስለሚሆኑ እቃዎቹን ለመግዛት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቅ ከመሆኑ ባለፈ በገያ ላይ የማይገኙ እቃዎችም እንደሚኖሩ ሠራተኞቹ ያሳስባሉ።
በመሆኑም ይህንን የአገር ሀብት የሆነ የአገሪቱ ብቸኛ ማዕከል በውጭ እንደማንኛውም ቤት አይቶ በልማት ተነሺ ቤቶች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ተገቢ ባለመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን እንዲያጤኑት ግፊት ቢያደርጉም ሰሚማጣታቸውን የተቋሙ ሠራተኞች ገልፀው፤ ማዕከሉ ቢፈርስ በአገሪቱ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርትና መርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ እንዲሁም አገራዊ ኪሳራው ላይ በቂ ጥናት ሳይደረግበት ከይዞታው ላይ ለማንሳት የተወሰነውን ውሳኔ መንግሥት ቆም ብሎ እንዲያስብበት አሳስበዋል።
ክፍለ ከተማው ይዞታውን ለልማት መሰጠቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ለማዕከሉ ሲጽፍ ማዕከሉ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ስለሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መልስ ይስጥበት የሚል ደብዳቤ ሲጻፍለት በሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኢታ የነበሩት ዶክተር ካባ ኦርጌሳ፤ ትብብር ይደረግላቸው ከሚል መልስ ውጭ የትኛውም አካል ተቋሙ ሲፈርስ በምን መልኩ አገራዊ ኃላፊነቱን ማስቀጠል እንዳለበት እንዲሁም የሠራተኛው ዕጣ ፈንታ ምን ይሁን ምን በግልጽ የተሰጠ መረጃ አለመኖሩን ይናገራሉ።
በተጨማሪም ማዕከሉ በመልሶ ማልማት ሲፈርስ ለአገር የሚያስከትለው ኪሳራ ታሳቢ ተደርጓል ወይ የሚል ጥያቄ ሲነሳ ቁርጥ ያለ መተማመኛ መልስ የሚሰጥ አካል የለም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለልማት ያስፈልጋል ስለተባለ ሊፈርስ ነው ከሚል ወሬ ውጭ ምንም ተጨባጭ ምላሽ ለሠራተኛው እንዳልተሰጠ ተናግረዋል።
በጥቅሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ማዕከሉ ቀደም ሲል ተጠሪነቱ ለግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በነበረበት ወቅት በሙያው የበቁ ተመራማሪዎች ተቋሙን ይመሩት ስለነበር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአፈር፣ የውሃና እፅዋት ምርመራ በማድረግ ከአገር ውስጥ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ኩራት የሆነ ተቋም የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በአንድ ቁራጭ ደብዳቤ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር እንዲደረግ ከተወሰነ ወዲህ ተቋሙን የኔነው ብሎ የሚመራው ባለቤት ማጣቱንም ተናግረዋል።
የማዕከሉ በልማት መነሳት እንደአገር የሚያስከትለው ቀውስ
ባንድ ወቅት የግብርና ሚኒስቴር ማዕከሉን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር አስቦ በባለሙያ ባስጠናው ጥናት መሰረት ላብራቶሪውን መልሶ ለመገንባት ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት ከመፍጀቱ ባሻገር የሚያስወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ባለበት እንዲሆን መወሰኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው፤ ስለዚህ ይሄንን ማዕከል መልሶ ለመገንባት እስከ ሰባት ዓመት የሚፈጅ ከሆነ ከ2011 ዓ.ም ማዕከሉ በልማት ይፈርሳል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የተደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ባለመኖሩ በቀጣይ ማዕከሉ የሚፈርስ ከሆነ የተቋሙን አገራዊ ተልዕኮ የሚያስተጓጎል ነው የሚሆነው፡፡
እንዲሁም ይህ ማዕከል ሲነሳ የውሃ፣ የዕፀዋትና የአፈር ምርመራ ከማድረግ ባሻገር የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተግባር ትምህርት የሚያገኙበትና ከፍተኛ ተመራማሪዎች የምርምር ሥራ የሚሰሩበት ተቋም በመሆኑ ነገ ላይ ይህ ተቋም ቢፈርስ በዘርፉ የሚፈሩ አያሌ ተተኪ ተመራማሪዎችን እንደሚያሳጣ ተናግረዋል።
በአበባ ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ በጥቅሉ በግብርናው ዘርፍ በአገሪቱ ኢንቨስት የሚያደርጉ ኢንቨስተሮች ወደ ማዕከሉ መጥተው የአፈር ንጥረ ነገር እንዲሁም የውሃና የዕፅዋት ምርምራ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ኢንቨስትመንቱ እንደሚገቡ ጠቁመው፤ ስለዚህ የላብራቶሪው መፍረስ በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉና ለማድረግ የሚያስቡ ባለሀብቶች ላይ ጫና የሚፈጥር ከመሆኑ ባለፈ በአገሪቱ ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽኖ እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በመላ አገሪቱ ላሉ 17 የክልል የአፈር ምርመራ ላብራቶሪዎች የስልጠና የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የተለያዩ ማሽኖችን የመግጠምና የመጠገን አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ለእናቱ የሆነ ብቸኛ ተቋም መሆኑን የሚናገሩትቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ደርጅቶች ለማህበረሰቡ ዕርዳታ የሚሰጡት የአፈር ለምነቱን መርምረው ነው። በመሆኑም ድርጅቶቹ የአፈር ለምነት ምርመራ የሚያስደርጉት ከዚሁ ማዕከል ነው። ስለዚህ እነዚህ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ነገ ላይ ለህብረተሰቡ ዕርዳታ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በሁሉም ክልሎች ላሉ ወረዳዎች የአፈር ካርታ አሰርቶ መስጠቱን ጠቁመው፤ ማዕከሉ የኢትዮጵያ የአፈር ሳይንስ ማህበር ጽህፈት ቤት መገኛ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፕሮፌሰር ደረጃ የደረሱ አያሌ የአፈር ሳይንስ ሙሁራን መገኛቸው በማዕከሉ ስለሆነ እነዚህ ተመራማሪዎች ብዙ ጥናቶችን/ ጆርናሎችን በማሳተም ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግት ችለዋል፡፡ ስለዚህም ነገ ላይ ማዕከሉ ከፈረሰ ተመራማሪዎች በዘርፉ በሚያደርጉት ጥናት ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥርባቸው ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ማዕከሉ በኢትዮጵያ ብቸኛው የአፈር ሙዚየም መገኛ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ያሉ አፈሮችን ወደ ማዕከሉ በማምጣት እንደ ባህሪያቸው የተቀመጡበት ማዕከል መሆኑን ነው የሚናገሩት ። ስለዚህ ይህንን የመሰለ ሌላ ላብራቶሪ ቅድሚያ ሳይገነባ ነባሩን ላብራቶሪ ማፍረስ እነዚህን ሁሉ የአገር መረጃዎች እንደ ማጥፋት እንደሚቆጠር ተናግረዋል።
እንዲሁም ማዕከሉ ከመፍረሱ በፊት ደረጃውን የጠበቀ ሌላ ተለዋጭ ላብራቶሪ ሳይሰራ ነገ ልቀቁ ቢባል ተቋሙ ውስጥ ያሉ እጅግ አደገኛ ኬሚካሎችና አሲዶች የት እንደሚቀመጡ ጥያቄ የፈጠረባቸው መሆኑንም የማዕከሉ ሠራተኞች ያላቸውን ሥጋት ገልፀዋል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ደረጃውን የጠበቀ ላብራቶሪ ተገንብቶ በተገቢው መንገድ ካልተቀመጡ በስተቀር በዘፈቀደ የሚጣሉ ከሆነ በሰውና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉም ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በአገሪቱ 50 በመቶ የእርሻ መሬት በአሲዳማ አፈር ተጠቅቷል ብሎ መንግሥት እንደሚያምን ገልፀው፤ ማዕከሉ የአፈር ምርመራ በማድረግ ይሄንን መረጃ መጀመሪያ ለመንግሥት ተደራሽ ከማድረጉ ባሻገር አሲዳማ አፈርን ለማከም ኖራ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን የሚያመርቱትን ኖራ ጥራቱን የሚመረምረውና የሚያረጋግጠው ይሄ ተቋም ነው። ስለዚህ ነገ ላይ ይሄ ተቋም ሲፈርስ አሲዳማ አፈርን ለመመርመርና ለማከም በሚደረገው ሥራ ላይ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል።
ማዕከሉ የተለያዩ ምርምሮቸን በማድረግ ሳይንሳዊ የሆኑ ውጤቶችን ለአግሮ ኢኮኖሚስትና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መረጃ የሚሰጥ ተቋም መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ተቋሙ መንግሥት ከያዘው ግብርና መር ፖሊሲ አንፃር እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ ተቋም ነው።
በተለይ የመስኖ እርሻ ከማስፋፋት አንፃር መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ይሄንን የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት ደግሞ ዘመናዊ የሆነ የዕፅዋት፣ የአፈርና የውሃ ላብራቶሪ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ከመስክ የአፈር፣ የውሃና የዕጽዋት ናሙና በመውሰድ አካላዊና ኬሚካላዊ ይዘቱን መርምሮ ተስማሚውን ሰብል ለመዝራት እንዲቻል ማዕከሉ ትልቅ ሚና የሚጫወት ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም ይሄነን ተቋም በመልሶ ማልማት ማፍረስ ማለት ከላይ የተዘረዘሩትን አገልግሎቶቸን አገሪቱ እንድታጣ ከማድረጉ ባለፈ አገሪቱን ለከፍትኛ ኪሳራ የሚዳርግ ነው። ስለዚህ መንግሥት ቆም ብሎ ተቋሙን ለአገሪቱ እያበረከተ ያለውን ፋይዳ አጥንቶ ቢቻል ተቋሙ ባለበት ቦታ አገልግሎቱን እንዲሰጥ የሚያደርግበትን ሁኔታ ቢያመቻች ካልሆነም ደግሞ ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት እንዳይቋረጥ ከቦታው ከመነሳቱና ላብራቶሪው ከመፍረሱ በፊት ሌላ ተለዋጭ ላብራቶሪ ተሰርቶ ሠራተኛው ወደ አዲሱ ላብራቶሪ ገብቶ የተቋሙን አገራዊ ተልኮ ማስቀጠል እንዳለበት ቅሬታ አቅራቢዎቹ አሳስበዋል።
ማዕከሉ በልማት ይፈርሳል የሚለው ውዝግብ በሠራተኞቹ ላይ ያሳደረው ጫና
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የተቋሙ ሠራተኛ በሚገባ ሥራውን አክብሮ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ነገር ግን ተቋሙ በአዋጅና ደንብ የተቋቋመ መስሪያ ቤት እንደመሆኑ መጠን ተቋሙን በልማት ለማንሳት ሲታሰብ ሠራተኛው ለመልሶ ማልማቱ ተባባሪና ቀናኢ እንዲሆን በደብዳቤ ከመገለጹ በፊት ሠራተኛውን ሰብስቦ ስለታሰበው ልማት የሚመለከተው አካል ማወያየት ሲጠበቅበት እስካሁን በወሬ ደረጃ እንጂ ማንም አካል ኃላፊነቱን ወስዶ ሠራተኛውን ያወያየ አካል የለም።
ስለዚህ አንድ በአዋጅ የተቋቋመ መስሪያ ቤት መንግሥት አያስፈልገኝም ብሎ በአዋጅ እስካላፈረሰው ድርስ የተቋሙ ሥራ መቀጠል እንዳለበት የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በወሬ ደረጃ አንዴ ወደ ገብርና ሚኒስቴር ሌላ ጊዜ ወደ ገብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም ወደ ክልል የአፈር ምርመራ ላብራቶሪዎች ሥር ሠራተኛው ተካቶ ሥራውን ያከናውናል ከሚል ማረጋገጫ ከሌለው ወሬ በስተቀር የተቋሙን ሠራተኞች ሰብስቦ ተጨባጭ መረጃ የሰጠ አካል ባለመኖሩ፤ ተቋሙ ፈርሶ ሠራተኛው ወዴት እንደሚሄድ እንዲሁም የተቋሙን አገራዊ ተልኮ እንዴት እንደሚያስቀጥሉ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።
እንዲሁም የመረጣችሁት ቦታ ምትክ ይሰጣችሁና እስኪሰራላችሁ ድረስ ለጊዜው የሆነ ህንፃ ተከራይታችሁ ሥራችሁን ትቀጥላላችሁ የሚባል ወሬም መኖሩን ጠቁመው፤ ማዕከሉ ላይ ቢሮ ላይ ቁጭ ተብሎ የሚሰጥ የቢሮ አገልግሎት ስለሌለ ሁነኛ መፍትሄ ከወዲሁ መፈለግ እንዳለበት ጠቁመ ዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች የሚሰሩት ሥራ አይቆምም። ተቋሙ ሥራውን ይቀጥላል ከተባለ ለሠራተኛው ህንፃ ተከራይቶ መስጠት ሳይሆን ማዕከሉ ከመፍረሱ በፊት የራሱ ላብራቶሪ ተገንብቶለት የላብራቶሪ እቃዎቹ ተገጥመው ወደ ራሱ ህንፃ ነው መግባት ያለበት። ነገር ግን ተለዋጭ ላብራቶሪ ቀድሞ ሳይገነባ ማዕከሉን ከወዲሁ ፈርሶ ሥራው ቢቆም ማነው ኃላፊነቱን የሚወስደው የሚል ጥያቄ ሲነሳ በማዕከሉ ዳይሬክተርም ሆነ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ከወሬ በዘለለ ኃላፊነቱን ወስዶ መልስ የሚሰጥ አካል እንደሌለ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር እንደመሆኑ መጠን ሚኒስቴሩ የማዕከሉ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ማድረግ ያለበትን ጥረት እያደረገ አለመሆኑን ሠራተኞቹ ጠቁመው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅድሚያ በሥሩ የሚመራውን ተቋም ደህንነት መጠበቅ ይገባው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሠራተኛው አሁንም ሥራውን ሳያቆም በተገቢው እየሰራ ቢሆንም ተቋሙ ፈርሶ ወዴት እንደሚሄድ ግልጽ ነገር ባለመቀመጡ ሠራተኛው ቀደሞ እንደሚሰራው ሥራውን በሞራል እየሰራ አለመሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው፤ ከዚህ ቀደም ማዕከሉ ሊታደስ ነው ተብሎ የማዕከሉ ሠራተኞች ወደ ግብርና ሚኒስቴር እንዲሄዱ ተደርገው በነበረበት ወቅት ከሌላ ተቋም የመጣቹህ ናቹህ እየተባሉ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችና የደረጃ ዕድገት እንዳያገኙ ተደርገው ከፍተኛ እንግልት ሲደርስባቸው እንደነበር አውስተዋል።
በመሆኑም በቀጣይ ተቋሙ ፈርሶ ሠራተኛው ወደ ሌሎች ተቋመት የሚበተን ከሆነ መሰል ችግሮች ይደርስብናል የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው፤ በማዕከሉ ዳይሬክተርም ሆነ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ስለተቋሙ የወደፊት ዕጣፈንታ ለሠራተኛው አስፈላጊውን መረጃ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ሠራተኛው ከፍተኛ መወዛገብ ላይ ነው። እንዲሁም ተቋሙ ነገ ላይ ቢፈርስ እንደ አገር የሚሰራውን ተግባር ሊያስቀጥል የሚችልበት ምንም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እስካሁን አልተሰራም። ስለዚህ የሚመለከተው አካል መጥቶ ሠራተኛውን እዲያወያያቸውና መፍትሄ እንዲሰጣቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠይቀዋል።
የትምህርት ዕድል አግኝተው እራሳቸውን በትምህርት አሻሽለው ከከፍተኛ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተው ቢመጡም የተቋሙ ዕጣ ፈንታ ባለመታወቁ ዕቅድና አላማ ኑሯቸው በሞራል በተማሩት ትምህርት ተቋሙን እንዳያገለግሉ እንቅፋት ሆኖብናል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ሠራተኞቹ ከዚህ በፊት የነበሩ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒትር ዴኢታዎችን ስለተቋሙ ዕጣ ፈንታ ሰበስበው እንዲያወያየቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ፤ ዴኢታዎቹ መጥተን ሠራተኛውን እናወያያለን እያሉ በተደጋጋሚ ቃል ቢገቡም እስካሁን ድረስ አንዳቸውም እንኳን መጥተው ሠራተኛውን ሳያወያዩ ሁለት ሚኒስትር ዴኢታዎች ከቦታቸው ተነስተው ሦስተኛ ሰው በቦታው መተካቱን ገልፀዋል።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ምላሽ
የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሬ መኩሪያ በሠራተኞቹ የተነሱ አብዛኞቹ ቅሬታዎች ተገቢ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን ከእውነት የራቁና ተራ ኩነና መሆኑን ገልፀው፤ እንደአመራር እስካሁን ሠራተኛውን ሰብስበው ስለተቋሙ በግልጽ ማወያየት ያልቻሉት ስለተቋሙ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከበላይ አካል በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በእርሳቸው በኩል ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤትም ሆነ ለሚመለከተው አካል ተቋሙ ለአገር እያበረከተ ያለውን ፋይዳ እንዲገነዘቡ የማድረግ ሥራ መሥራታቸውንና ነገ ላይ ተቋሙ ቢፈርስ በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እንዲሁም የሚያስከትለው አገራዊ ኪሳራ ምን እንደሚመስል በደብዳቤ ጭምር ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ከክፍለ ከተማው ጋርም የካሳና የግምት ሥራውን ኮሚቴ አዋቅረው በጋራ በመሥራት የህንፃው ግምት ተጠናቆ የማቴሪያል ግመታ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ክፍለ ከተማው የተለያዩ የምትክ ቦታዎችን ለማዕከሉ አቅርቦ የማማረጥ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ከበላይ አካል ጋር በመነጋገር የተረጋገጠ መረጃ በመያዝ ስለተቋሙ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለሠራተኛው ግልጽ የማድረግ ሥራ በቀርቡ እንደሚሠሩና ማዕከሉ በልማት ሲነሳ የተቋሙ ተልዕኮ እንዳይቋረጥ ሠራተኛው በግብርና ምረምር ኢንስቲትዩት ሥር ሆኖ በኢንስቲትዩቱ ባሉ የምርምር ማዕከላት የምርምር ሥራውን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አበራ ለማ በሰጡን መረጃ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአስር ዓመት ዕቅድ ሲዘጋጅ በሚኒስቴር መስሪያቤቱም በተጠሪ ተቋማቱም ላይ የሪፎርም ሥራ ሠርቷል። በመሪ ዕቅዱም ሥራዎች መመራትና መደራጀት ባለባቸው ቦታ እንዲመሩና እንዲሰሩ ተወስኗል፡፡
በዚሁ መሰረት ከስድስት ዓመት በፊት ተጠሪነቱ ለግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የነበረውን የብሔራዊ የአፈር ምርመራ ማዕከል ወደ ቀድሞው ቦታው የመመለስ ሥራ ይሠራል፡፡ ማዕከሉ የምርምር ሥራ ስለሚሰራ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር መሆን አልነበረበትም። የማዕከሉ ሥራ ከግብርና ምርምር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩ ጋር እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ስለዚህ ማዕከሉ በግብርና ሚኒስቴር ሥር የነበረውን አወቃቀሩን ቀድሞ ወደ ነበረበት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመመለስ ሥራ ነው የተሰራው። ምክንያቱም ማዕከሉ የሚሰራው የምርምር ሥራ ሆኖ እያለ ከልማቱ ጋር መቀላቀል ስለሌለበት ተጠሪነቱ ወደ ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲመለስ ተደርጓል።
በመሆኑም ማዕከሉ ሠራተኞቹን ይዞ ወደ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ይገባል ማለት ነው። ስለዚህ በኢንስቲትዩቱ ሥር ደረጃውን የጠበቀ ላብራቶሪ ስላለ የማዕከሉ ሠራተኞች ወደዛ ገብተው ይሠራሉ። ማዕከሉ ወደ ግብርና ኢንስቲትዩት በመግባቱም የሚጠፋ ንብረትም፤ የሚበላሽ ማሽንም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ሥር የነበረውን አወቃቀሩን ወደ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር እንዲሆን ማድረግ ለተቋሙ ትኩረት አልተሰጠውም ማለት እንዳልሆነ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልፀው፤ ማዕከሉ በልማት መፍረሱ እንደአገር የሚያስከትለው ኪሳራ ታስቦበታል ወይ? ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ከመልሶ ማልማቱ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ተቋማትም ሆነ የግል ኢንቨስትመንት ሲገነባ የግል መኖሪያም ሆነ የመንግሥት ተቋማት በመልሶ ማልማት ይነሳሉ። ምንም ችግር የለውም። የተለየ ነገር የተፈፀመ ነገር የለም።
ማዕከሉ በግበብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር መጠቃለሉ የበለጠ ይጠናከራል እንጂ የሚዳከምበበት ሁኔታ አይኖርም። ለማዕከሉም ምትክ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል፤ ማሽኖቹም ሆነ አጠቃላይ ንብረቱ የሀገር ሀብት ስለሆነ በጥንቃቄ ሥራው ይከናወናል›› ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ውድ አንባቢዎቻችን በቀጣይ ክፍል የማዕከሉ ዳይሬክተርን ዝርዝር መልስ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ስለጉዳዩ የሚሰጡን ምላሽ ካለ ዝርዝር ጉዳዩን ይዘንላችሁ የምንቀርብ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013