ዳግም ከበደ
ወንዱ አያቴ ከሴቷ አያቴ ጋር ፍቅር ቀመስ ንትርክ ውስጥ ሲገባ “እያየኋት የምታስቀኝ ሚስት አገባሁ” ይላል። ዛሬ እኔም አንዳንድ ነገሮች ግርም ቢሉኝ ነገሮቹ ድንገት አዕምሮዬ ውስጥ ስንቅር አሉብኝ።
እንዲያው ዝም ብለው እያየኋቸው የሚያስቁኝ ሰዎች በዝተዋል። እንደው ማን ይሙት አሁን በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ባርነትን ምርጫው ያደረገ ግለሰብም ይሁን ቡድን ይኖራል ብሎ ማን ያስባል?!
እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው። ባርነትን የሚናፍቁ፣ ነፃነትን የሚሸሹ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች መኖራቸውን ስነግራችሁ ሃዘን እየተሰማኝ ነው። ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ የነፃነት ቀንዲል፣ ድል የማድረግ ምሳሌ፣ ቀና ብሎ የመሄድ አድባር ባለባት ኢትዮጵያችን ላይ መሆኑ ነው።
ይህ ነገር በባርነት ለዘመናት ሲማቅቁ የቆዩ አገራት ላይ ቢሆን ኖሮ ብዙም ላይገርመን ይችል ነበር። ምክንያት አላቸዋ! አንዳንዴ እኮ መገዛትም ሱስ ነው። ነገሩ ግን ወዲህ ነው፤ በተገላቢጦሽ የነፃነት ተምሳሌትና ምልክት በሆነችው አገራችን ላይ አይተውት የማያቁት አገር ናፍቋቸው፤ ቅኝ የመገዛት ዛር ይዟቸው የሚማቅቁ ድኩማኖች መኖራቸውን እያሰብን ድንቅ እያለን እንገኛለን።
አንድ ጓደኛዬ “እነዚህን ነበር አንድ ኬጅ ውስጥ ከቶ እንዲጎበኙ ማድረግ ››በማለት ቀኑን ሙሉ ሲያስቀኝ ውሏል። ለነገሩ እውነቱን ነው ጎብኚዎች ብዙ ጊዜ ያልተለመደ ነገር ቀልባቸውን ይስባቸዋል። ለዚህ ነው እርሱም ብስጭት ብሎ “ማስጎብኘት ነበር” በማለት ንዴቱን ለማብረድ የሞከረው።
ሰሞኑን “የዓድዋ ድል” የሚከበርበት ጠላቶቻችን ዓይናቸው ደም የሚለብስበትም የየካቲት ወርም አይደል?! ታዲያ ይሄን ጊዜ ነው አገር የመክዳት፣ የባንዳነትና የአላዋቂነት ዛራቸው ተነስቶ የሚያጓሩ “ባርነት አምላኪዎች” ቅዥታቸው የሚነሳባቸው።
የነፃነትን ምንነትና ጥቅም የተረዱ ይሄን ወር ከምን ጊዜም በላይ በኩራት ደረታቸውን ነፍተው እያከበሩት ሲውሉ፤ ግርና ብዥዠዥዥ ያለባቸው ደግሞ ታላላቅ ሰዎችን ሲረግሙ “የለምን ነፃ ሆንን?” ቁጭታቸውን ሲያላዝኑ ይሰነብታሉ።
ታዲያ ስለነዚህ ሰዎች ከማዘን በተለየ በዚህ በተከበረ ወር ላይ ጥቂት ነጥቦችን አንስቶ ለማረም መሞከር ይገባል ብዬ ተነሳሁ። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው።
የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው በዓድዋ የታላቅ ሕዝቦች ድል ነው።
ታዲያ ይሄን ታላቅ የኩራት ምንጭ ለትውልድ ልናሻግረው እንጂ ልናራክሰው፣ ተስፋ ልንጥልበት እንጂ ልንቆርጥበት አይገባም እላለሁ። ይህን ሃሳቤን ይበልጥ እንዲያጠነክርልኝ ደግሞ “የባርነት ያለህ” እያሉ ለሚያላዝኑት ቡድኖች የተለያዩ የታሪክ መዛግብትን ሳገላብጥ ካገኘሁት ሁለት ቅንጥብ ታሪኮችን እነሆ ልላችሁ ወደድኩ።
አንደኛው
ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል (የዓድዋ ድል) በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቷል። የምዕራባዊያን ጋዜጦች ሳይቀሩ በዓድዋ ድል ማግስት “የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፤ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ” ብለው እስከ መጻፍ እና ድሉን ከጫፍ እስከጫፍ እስከ ማስተጋባት ደርሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ የተባሉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሌሉበት (እርሳቸው በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ) የአፍሪካና የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተብለው ተመርጠዋል። ይሄ ክብር ላለፉት አባቶቻችን፣ አሁን ለምንገኘውም ለዛሬው ትውልዶችም ሆነ ወደፊት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለሚፈጠሩት አዳዲስ ትውልዶች የአንድነታችን መሰረት የጀግንነታችን መለኪያ እንደሆነ እንዲታወቅ እንፈልጋለን።
ታዲያ ይሄ እውነት ሲነሳ የሚያቅበጠብጣቸው የባንዳ ቅጥያዎች በአገራችን ላይ እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ? ይሄ ጥያቄ ለብዙ ጊዜያት ግራ ሲያጋባኝ ቢቆይም አሁንም ድረስ ቅሪቱ እዛም እዚህም ተንጠባጥቦ የሚገኘው የህወሓት ጁንታ ሴራ መሆኑን ግን ሙሉ በሙሉ ለማመን እየተቃረብኩ ነው።
ከዚህ በተለየ የሚነሱ አንዳንድ መግፍኤ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋነኝነት የጥላቻ ጥንስሱን የሰራው የኢትዮጵያውያንን አንድነት ሸርሽሮ በፍርስራሹ ላይ የማፊያ ቡድን ለዘላለሙ ለመትከል የቋመጠው ይሄው ቡድን በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይሄን የጥላቻ ድሪቶ ከጀርባችሁ ላይ ለመጣል አሁንም መመርመር፣ መጠየቅ፣ ማንበብ እና ማስተዋል አይለያችሁ ለማለት እወዳለሁ።
ሁለተኛው
የዓድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በሰባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1903) ከአንድ መቶ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት አሁን ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያለበት ሥፍራ አፄ ምኒልክ አደባባይ ነው።
በወቅቱ የነበረውን ድባብ ለማወቅ እንዲረዳን ስለ ክብረበዓሉ የተጻፉ በርካታ ጽሁፎችን ለመቃኘት ሞክሬያለሁ። ከዚህ ውስጥ ትኩረቴን የሳበው የጳውሎስ ኞኞ “የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት” የተሰኘው መጽሐፍ ነው። በዚህ በውብ ቃላትና የአተራረክ ስልት በተቀነባበረ ጽሁፍ ላይ እንዲህ የሚል መልክት እናገኛለን። “ዲፕሎማቶችና የውጭ አገር መንግሥታት ተወካዮች ዓርበኞች የመንግሥት ባለሥልጣኖች ብዙ ሺህ ፈረሰኞችና እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተገኝተዋል። ከፈረሰኞቹ ብዛት የተነሳ ፀሐይ በአቧራ እስከመጋረድ ደርሳ ነበር”
ይሄን ትዕይንት መለስ ብሎ ላስተዋለውና በእዝነ ህሊናው ለሳለው “ምን አለ ያን ጊዜ ተፈጥሬ በነበር” የሚል ምኞት በውስጡ ሳይንቀለቀል እንደማይቀር እርግጠኛ ነኝ። ይሄ ሁለተኛው ልባችንን ሊያሞቀውና በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ላነሳው የወደድኩት ታላቅ ክስተት ነው።
ይሁን እንጂ በየማህበራዊ ድረገፁም ሆነ አታሟቸውን በሚጎስሙበት ማሰራጪያ ጣቢያዎች ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ዝቅ ብለው በባርነት ማድቤት ውስጥ ካልተወሸቅን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖችን እያስተዋልን ነው። ታዲያ ልክ እንደዛሬው ጥቂት ታሪክ ከማቅመስና ልቦና ይስጣችሁ ብሎ ከመፀለይ የተሻለ ምን ይኖር ይሆን? እውነትም ልቦና ይስጣችሁ። ክብር የነፃነት ብርሃን ላሳዩን አባቶቻችን። ዓመት ዓመት ያድርሰን። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013