ጌትነት ተስፋማርያም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ በተሻሻለው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1049/2009 እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 63/2007 በዘርፉ ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ የኩነቶች መረጃ ማለትም የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የጉዲፈቻ፣ ልጅነትን መቀበልና አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅ የመሳሰሉ ምዝገባዎች የማከናወን ኃላፊነትም አለበት። ምዝገባዎቹ ወጥና ቀጣይነት ባለው የአሰራር ስርዓት ላይ እንዲመሰረቱ በከተማ አስተዳደሩ በበላይነት የማስተባበር፣ ከኩነቶች ምዝገባ የተገኘውን መረጃ በማዕከል አደራጅቶ በመያዝ በወቅቱ ለፌደራል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ቅጂዎች የማስተላለፍ ግዴታ ተጥሎበታል።
መረጃዎቹ ለማህበራዊ፣ ለአስተዳደራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ለተለያዩ ፕሮግራሞች እቅድ ብቁና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ የማቅረብ እና የከተማ አሰተዳደሩ የነዋሪዎች አገልግሎት ለመስጠት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም ነው። በኤጀንሲው እስከ ወረዳ በተዘረጋው የአገልግሎት ጽህፈት ቤቶቹ አማካኝነት ከበርካታ ተገልጋዮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያደርጋል።
ተቋሙ ለሚያከናውናቸው ስራዎች እንዲሁም ስለሚያጋጥሙት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን:- ባለፉት ጊዜያት ኤጀንሲው በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ምን ያህል ሰዎችን አስተናገደ፤ አንዳንድ ስራዎች ከእቅድ አንጻር አፈጻጸማቸው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዶክተር ታከለ :- ስራዎቻችን ሰፊ ናቸው። በቀጥታ ከህብረተሰቡ ጋር የሚያገናኙ አገልግሎቶችን እንሰጣለን። በ2013 በጀት በሁለተኛው ሩብ ዓመት 41 ሺህ 634 የልደት ምዝገባ እና ማስረጃ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ለ51 ሺህ 321 አገልግሎት ተሰጥቷል፤ ይህም ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ 123 ነጥብ 26 በመቶ ነው።
የጋብቻ ምዝገባ እና ማስረጃ አገልግሎትን በተመለከተ 14 ሺህ 108 ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ለ12ሺህ 966ቱ አገልግሎት ተሰጥቷል። አፈፃፀሙ 91 ነጥብ 90 በመቶ ነው። በሌላ በኩል ለ1ሺ888 የፍቺ ምዝገባ እና ማስረጃ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ታቅዶ ለ 884 የተሰጠ ሲሆን አፈፃፀሙ 46 ነጥብ 82 በመቶ ሆኗል። የሞት ምዝገባ 4ሺህ 371 ነው፤ ይህ ከታሰበው ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ 15.45 በመቶ ይጠጋል።
ለ ለ6ሺህ 795 ተገልጋዮች የልደት ፤ የጋብቻ ፤ የሞት ፤ፍች እና ጉዲፈቻ እርማት ፤ እድሳትና ግልባጭ ተሰጥቷል። የማንዋል የነዋሪነት መታወቂያ ለ100 ሺህ ሰዎች ለመስጠት ታቅዶ ክንውኑ ግን ለ418ሺህ 718 ሰዎች እንደተሰጠ ያሳያል፤ ይህም አፈፃፀሙ 418 ነጥብ 72 በመቶ መድረሱን ያሳያል።
ሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች በተቋሙ ስር ተሰጥተዋል፡፡ አንዳንዶች ከእቅድ በላይ ሌሎቹ ደግሞ ከተቋሙ አሰራር ክፍተትም ሆነ ከተፈጥሯዊው የሞት፤ ልደት እና ሌሎችም ሁነቶች ጋር በተያያዘ ከእቅዱ ያነሰ አፈጻጸም ያሳዩ አገልግሎቶች አሉ።
አዲስ ዘመን:- በአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራዎችን ከማከናወን አንጻር በኤጀንሲው እና በወረዳዎች ማዕከላት ላይ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆኑን ተገልጋዮች ይገልጻሉ። ችግሩ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር ታከለ :- እንደተቋም የምትመራቸውን ክፍሎች አቀናጅቶ መምራት የሚጠበቅብህ ኃላፊነት ነው። ከዚህ አንፃር በወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ስር ዓመታዊ እቅድ ሲዘጋጅም ሆነ አፈፃፀም ሪፖርት ሲገመገም ቅንጅታዊ ችግሮችን በትኩረት ይታያሉ። ችግሩ ያለው ግን በወረዳዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያሉት የወሳኝ ኩነት ሰርተፍኬት መስጫ ቢሮዎች ለየወረዳቸው ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ነው ተጠሪነታቸው። እንደኤጀንሲ እነሱን በቀጥታ ለማዘዝ አሊያም ይህን አድርጉ ለማለት አንችልም።
ዞሮ ዞሮ እኛ የምናቅዳቸውን ጉዳዮች እየተገበሩ በጋራ እንሰራለን። በሌላ በኩል እስከታች ወረዳ ድረስ ያለውን የወሳኝ ኩነት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዝርጋታ እና የማስተዳደር ስራ የሚሰራው ኤጀንሲያችን ነው። ከስራ ክፍፍሉ ጋር ተያይዞ ወረዳዎች ጋር ሲደርስ የቅንጅት ችግር እና የመንጠባጠብ ችግር ያጋጥማል።
ወረዳዎች ላይ ደግሞ ስራዎችን በእውቀት ከመምራት አንጻር እንዲሁም ተገልጋዩን በተገቢው ሁኔታ ከማስተናገድ አንጻር ክፍተቶች እና የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት ይታያል። ይህን ለማስተካከል አመራሮችም ሆነ የባለሙያዎች ቡድን ተመድቦ ክትትል ያደርጋል። በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች በወሳኝ ኩነት ጽህፈት ቤቱ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን አይተው ማስተካከል ቢኖርባቸውም እኛ ሰራተኛ መድበን እያንዳንዱ ወረዳ ላይ ያለውን ክፍተት ለማስተካከል ጥረት እያደረግን ነው።
በማዕከል እና በክፍለ ከተማ ደረጃ ስድስት አይነት የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች ይሰጣሉ፤ በወረዳ ደረጃ ደግሞ 16 አይነት አገልግሎቶች ናቸው ያሉት። አገልግሎቶቹን ደግሞ በወጣላቸው ስታንዳርድ መሰረት ያለመተግበር ችግር ይስተዋላል። ለአብነት በኤጀንሲው መዋቅር የሚሰጡ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የሚታገዝ በመሆኑ መብራት በሚጠፋበት ወቅት በማንዋል አገልግሎት ሲሰጥ በምን ያህል ስታንዳርድ እንደሚሰጥ ክትትል ተደርጎ ውጤቱ አይያዝም። ይህንን ክፍተት ለመሸፈን በየወቅቱ ማስተካከያዎች እየተደረጉ ይገኛል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራውን ለማስቀጠል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ስለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነትና ፋይዳ ከማዕከል፣ ክፍለ ከተማ ፤ ከወረዳ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ምክክር በተለያዩ ጊዜያት እየተደረገ ይገኛል።
እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የአዲሱ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት እንዲዘረጉና አደረጃጀታቸውን እንዲከልሱ ወቅቱን የጠበቀ የአቅም ግንባታ ስራዎች በመስራት እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ተችሏል። ይህም ለቅንጅታዊ አሰራር መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እናምናለን።
አዲስ ዘመን:- በርካታ ወረዳዎች ላይ ሄዶ ማየት ቢቻል የልደት፤ የሞት እና የጋብቻ ምዝገባ ሰርተፍኬቶችን ለመውሰድ የሚያቀኑ ተገልጋዮች ሲጉላሉ እና ረጅም ሰልፍ ሲይዙ ይስተዋላል፤ ችግሩን ለመቅረፍ ምን ታስቧል?
ዶክተር ታከለ :- እውነት ነው፤ አገልግሎቱን ለማግኘት መጉላላት ይኖራል። በተለይ መጉላላቱ አንዱ ችግር የሲስተም መቆራረጥ ችግር ነው። መብራት ሲጠፋ አሊያም የኔትወርክ መስተጓጎል ሲያጋጥም ስራዎች በአፋጣኝ አይከናወኑም። የሲስተም ችግሩን ለመቅረፍ ያለኢንተርኔት አማራጭ /በአፍላይን/ ፎርሞች መሙላት የሚቻልበትን አሰራር ዘርግተናል።
በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንዲለማ የተደረገው የኦፍላይን አሰራር (Offline Registration) በአዲስ አበባ በሚገኙ 96 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ተደርጓል። የሲስተም መቆራረጥ ችግር የኦፍላይን ምዝገባ አሰራሩ በተዘረጋባቸው ወረዳዎች ላይ እንደችግር ሊነሳ አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ተገልጋይ እንደየአመጣጡ በቴክኖሎጂው መሰረት ሳይጉላላ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ይደረጋል።
ሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮችም በመተግባር ላይ በመሆናቸው ችግሩ ተፈትቶ የተሟላ ግልጋሎት ይሰጣል። ከቴክኖሎጂ ማስፋፋትና አጠቃቀም ማሳደግ ጋር ተያይዞ የኦፍላይ ምዝገባ በከተማዋ ከሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ 81 በመቶዎቹ ላይ መተግበር መቻሉ የሚያበረታታ ቢሆንም በቀጣይ ግን በሁሉም ማዳረስ ይገባል የሚል እቅድ ነው ያለን። ከ121 ወረዳዎችን ባለፈ ተጨማሪ አራት ወረዳዎች ላይ አገልግሎቱን በማዳረስ በ125ቱ የአዲስ አበባ ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
በሌላ በኩል ግን ከሰራተኞች ክፍተት ጋር ተያይዞ የተገልጋዮች መጉላላት ሊያጋጥም ይችላል። በፍጥነት መረጃዎችን መዝግበው ወደማዕከል ከመላክ አንጻር ወረዳዎች ላይ ችግሮች አሉ። በእጅ ተጽፈው የሚሰጡ የወሳኝ ኩነት ሰርተፍኬቶችንም በፍጥነት መዝግቦ ያለማስረከብ ችግር አለ።
በሌላኛው ጎን ደግሞ ተገልጋዮችን አክብሮ በጊዜ መሸኘት አለብን የሚለውን ጉዳይ በአንዳንድ አካባቢ ሲተገበር አይታይም። መመሪያን መነሻ አድርጎ አገልግሎት አለመስጠት ፤ ባለጉዳይ ማመላለስ ፤ የመንግስት ስራ ሰዓት ጠብቀው አገልግሎት የማይሰጡ ፈጻሚዎች መኖራቸው እና አዳዲስ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት ውስንነት መኖሩ በየወቅቱ በተደረገው ግምገማ ማየት ተችሏል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከደንበኛ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ አንድ ሺህ ሰራተኞችን ለአምስት ቀናት ለማሰልጠን ዝግጅት ተደርጓል። ይህም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን የዘገየ አሰራር በመጠኑ ለማስተካከል ይረዳል።
አዲስ ዘመን:- በየጊዜው የሚደርሱ የተገልጋይ ቅሬታዎችን ከመፍታት እና መልካም ተሞክሮዎችን ከማስፋፋት አንጻር ምን ተሰርቷል?
ዶክተር ታከለ:- የማዕከልና የክፍለ ከተማ አመራር እንደ አስፈላጊነቱ በየ15 ቀኑ፤ በየወሩና በየሩብ ዓመቱ የኤጀንሲው ተግባራት አፈፃፀማቸው እየተገመገሙ እንዲሔዱ ይደረጋል። ከተገልጋዮች የሚደርሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ ስለመፈታታቸው እና ተጨማሪ ስራ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንዲለዩ ይደረጋል።
በ2013 በጀት ዓመት እስከ 2ኛው ሩብ ዓመት ብቻ የቀረቡ ቅሬታዎችን መመልከት ብቻ ከማዕከል ቢሮ በስድስት ወር የቀረቡ ቅሬታዎች አሊያም አቤቱታዎች ብዛት 26 ናቸው፤ ሁሉንም እንደየችግሮቻቸው ግዝፈት እና መጠን ለመፍታት ተሞክሯል።
በተመሳሳይ በክፍለ ከተማ ላይ በሚገኙ የወሳኝ ኩነት ዳይሬክቶሬቶች ስር የቀረቡ 42 ቅሬታዎች ነበሩ፤ ከዚህ ውስጥ በስድስት ወሩ ውስጥ 33ቱ ተፈተዋል። ቀሪዎቹም በአሁኑ ሰዓት ቅሬታቸው እየተፈታ እንደሚሆን ይገመታል።
ችግሮቹ በፈጻሚው አካል በኩል ደራሽ ስራዎችን ከመደበኛ ስራዎች ጋር አስተሳስሮ ባለመስራት፤ የወረዳ አመራሩ የሚያገጥመው የግብአት ችግሮች በራስ ዓቅም አለመፍታት እንዲሁም ታችኛው አመራር ሁሉም ችግሮች የማእከል አመራር እንዲፈታለት ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ይሆናሉ።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጡ በሲስተም እንዲከወን የተለያዩ ሰበቦች በመደርደር በቁርጠኝነት አለመያዝም ሊሆን ይችላል። ይህንን ችግር ግን አንዳንድ ጊዜ ታች ድረስ ወርደንም ቢሆን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው።
በሌላ በኩል ግን በአደረጃጀትና በአሰራር የተጠናከረ ሞዴል የኤጀሲው መዋቅር በመፍጠር ረገድ በቢሮ እና በግብአት ማሟላት እንዲሁም በአሰራር ስርአት የተሻሉ 20 ወረዳዎች ተለይተዋል። በቢሮዎቹ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ያሳዩትን መልካም ተሞክሮ በሌሎች ወረዳዎች ላይም ለማስፋፋት ጥረት ይደረጋል።
አዲስ ዘመን:- ከዲጂታል መታወቂያ ጋር በተያያዘ በመዲናዋ ጥቂት ሰዎች መታወቂያውን ሲያገኙ አብዛኛው ሰው ጋር አልደረሰም፤ አንዳንድ ወረዳዎች አገልግሎቱን ሲሰጡ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግን የቀድሞውን መታወቂያ እያደሉ ነው፤ ይህ ከምን የተፈጠረ ነው?
ዶክተር ታከለ :- በአሁኑ ወቅት በ96 ወረዳዎች ላይ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት እየተሰጠ ነው። በቀጣይ በ125ት ወረዳዎች ላይ አገልግሎቱም ለማዳረስ የሲስተም ዝርጋታ እና አስፈላጊው የመሰረተ ልማት እንዲሁም የሰው ኃይል ማሰልጠን ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
የዲጂታል መታወቂያውን አገልግሎት ሁሉም ጋር ማድረስ ካልተቻለበት ምክንያቶች መካከል አንዳንድ አገልገሎቱን የሚሰጡ ጽህፈት ቤቶች ቤት ተከራይተው እያገለገሉ በመሆናቸው የተፈጠረ ነው። የተከራዩትን ቤት በሚቀይሩበት ወቅት የተዘረጋላቸውም ሲስተም ስለሚበላሽ እንደገና መስተካከል ይጠይቃል። ይህ ደግሞ የዲጂታል መታወቂያውን አገልግሎት ሳይሆን በማንዋል ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ያልተዳረሰባቸው ቢሮዎች አሉ፤ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው ቢሮዎች የዲጂታል መታወቂያውን ሲስተም መዘርጋት አይቻልም።
በሌላ በኩል ወረዳዎች ላይ የመታወቂያ ፈላጊዎች በብዛት በሚመጡበት ወቅት ሁሉንም በዲጂታል አሰራር ብቻ ማስተናገድ ስለማይቻል በማንዋልም ጭምር በመስራት አገልግሎቱን ለመስጠት ይሞከራል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የወሳኝ ኩነት የመረጃ ማደራጃ እና መሰብሰቢያ ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
ለዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት ከ700ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበዋል። ባለፉት ስድስት ወራትም ከ70 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ አግኝተዋል። በአጠቃላይ የዲጂታል መታወቂያ ያገኘው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር ደግሞ ወደ 230 ሺህ ይደርሳል። በቀጣይነት ደግሞ ሁሉም ተገልጋይ የዲጂታል መታወቂያውን እንዲያገኝ በዘመቻ ለመስራት ታቅዷል።
አዲስ ዘመን:- ከዲጂታል መታወቂያው ጋር ተያይዞ ያለውን ወጪ ለመሸፈን ከለውጡ በፊት 200 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ነበር፤ ገንዘቡ ምን ላይ ዋለ?፤ አሁንስ ያለው የዲጂታል መታወቂያ ወጪ በማን ነው የሚሸፈነው?
ዶክተር ታከለ :- እኔ ወደ ኤጀንሲው የመጣሁት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ቀደም ብሎ ተመድቦ ነበር ስልተባለው ገንዘብ ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም። አንድ አመራር ደግሞ ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይሰራም። ወደኋላ ያከለውን ጉዳይ የኦዲት ጉዳይ ነው የሚሆነው።
በአሁኑ ወቅት ያለውን የዲጂታል መታወቂያ ወጪ እየሸፈነ የሚገኘው ኤጀንሲው ነው። ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር የሚገዙ ግብአቶች አሉ። በየወረዳው ያለው የሲስተም አሰራር ወደማዕከል መረጃው ይላካል። በማዕከል ደረጃ ስለሆነ ማተሚያው ያለው አገልግሎቱን በእራስ አቅም እየተከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን:- የመታወቂያ አሰጣጥ ላይ ብዙ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፤ በአንድ የቤት ቁጥር ለ20 እና 30 ሰው ይሰጣል፤ ህጋዊ ያልሆኑ መረጃዎች ይሰጣሉ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ዲጂታል መታወቂያ አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ምን ተሰርቷል?
ዶክተር ታከለ :- በዲጂታል መታወቂያው ላይም አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ወንጀሎች ይጠፋሉ ብለን አንጠብቅም። የወንጀል ድርጊቱን ሊያስወግድ የሚችለው ሙሉ በሙሉ የአዲስ አበባ መታወቂያ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን መዝግበን ስንጨርስ ነው።
ሁሉም መታወቂያ ፈላጊ የመዲናዋ ነዋሪ ሲመዘገብ እና በዲጂታል አሰራር መረጃው ሲገባ ከመታወቂያ አወጣጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ያስችላል። አሁን ላይ ግን የሚታዩ ችግሮች አሉ። ከመታወቂያዎች ሃሰተኛነት ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ወንጀል ወደፍርድ ቤት የሚቀርብ አለ።
ባንክ ቤት ደርሰው የሚያዙም አሉ። በተመሳሳይ ኢሚግሬሽን እና ዜግነት ጉዳዮች ቢሮዎች ላይ ለውጭ ሀገራት ጉዞ ሄደው የሚያዙ አሉ። በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ ከ30 በላይ ሃሰተኛ ማስረጃዎች ተይዘዋል።
በወረዳ ደረጃም ሆነ ኤጀንሲው ውስጥ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተገልጋይ ላይ እንግልት የሚፈጥሩ እና ሃሰተኛ መረጃ በማዘጋጀት የሚጠረጠሩ ሰዎች ይያያዛሉ። በዲሲፕሊን የሚቀጡ ሰራተኞች አሉ አንዳንዶቹ ከስራ ተነስተዋል፤ በአንጻሩ ፍርድ ቤት የቀረቡ ጉዳዮችም አሉ።
በ2013 በጀት ዓመት እስከ ሁለተኛው ሩብ ዓመት በወረዳ ደረጃ በከባድ ዲሲፕሊን የተቀጡ እና ተጠያቂ የሆኑ ሰባት ሰራተኞች አሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ በፍርድቤት የተያዘ አንድ ባለሙያ አለ። ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ድረስ በቀላል ዲሲፕሊን የተቀጡ 13 ሰራተኞች ይገኛሉ።
የቁጥጥር እና አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ስራ ችግር በተገኘበት ቦታ ላይ ይቀጥላል። በብልሹ አሰራር ተግባር ላይ የተገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች የተጠያቂነት አሰራር መተግበር አበረታች ለውጥ ታይቷል።
ከግንዛቤ እና እውቀት ማነስ የሚመጡ ችግሮችን ደግሞ በስልጠና እና በምክክር መድረኮች ለማረቅ ጥረት ይደረጋል። አዳዲስ ሰራተኞች ሲቀጠሩ ስለወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ ጋር የተያያዙ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን እንሰጣለን። ይሁንና በቂ ነው ማለት አይቻልም፤ በየጊዜው የማሻሻያ ስልጠናዎች በዘርፉ መሰጠት አለባቸው።
አዲስ ዘመን:- 60 እና 70 ዓመት ያስቆጠሩ የልደት፤ የሞት እና የጋብቻ ምዝገባ ፋይሎች በቢሯችሁ ተከማችተው ከመገኘታቸው አንጻር የረጅም ዓመት መረጃዎች በሚፈለጉበት ወቅት አይገኝም የሚል ቅሬታ ይነሳል፤ ከዚህ አንጻር
ዶክተር ታከለ :- በአዲስ አበባ ከተማ ከ1935 ዓ.ም መጀመሪያ ከተሰጠው የጋብቻ ሰርተፍኬት አንስቶ እስካሁን ድረስ የልደት፣ ጋብቻ እና ሌሎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎች ሲከናወን ቆይቷል። የረጅም ጊዜ ፋይሎችን ሲጠይቁ አይገኝም የሚለው ግን እኛ ጋር መጥቶ ጠይቆ ያጣ ሰው የለም፤ ምክንያቱም አጣሁ ብሎ ሪፖርት ያደረገ ሰው የለም።
ምክንያቱም በካይዘን መርህ የተደራጁ እና ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ የተከማቹ ፋይሎች በኤጀንሲው ስር አሉ። ተገልጋዩ የሚፈልገውን መረጃ ዓመተ ምህረት እና ትክክለኛ ቀን እንዲሁም ስሙን በትክክል ከሰጠ ተመዝግቦ የሚገኝ በመሆኑ አምስት ደቂቃም ሳይፈጅ ይገኝለታል። የ1950ም ይሁን የ1960 ዓ.ም በሚፈለግበት ወቅት ማግኘት ይቻላል።
ፋይሎቹ ከጊዜ ብዛት ሊቀደዱ እና ሊበላሹ ይችላሉ። ችግሩ ግን አንድ አደጋ ቢደርስ አሊያም በዝናብ ምክንያት የተከማቹት ፋይሎች ቢጠፉ መልሶ ማግኘት የሚቻልበት እድል አለመኖሩ ነው። የሚያሰጋንም ሊደርስ የሚችለው አደጋ ነው።
ለዚህም ሲባል ዶክመንቶቹን ወደዲጂታል ለመቀየር እና በሶፍትዌር መረጃ ቋት ለማስገባት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። ዘመናዊ የስካን ማሽኖች እየገዛን ነው የሚገኘው ዶክመንቶቹን ስካን አድርጎ ወደዲጂታል መቀየር ከተቻለ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ መቀነስ ይቻላል። ከዚህ ውጪ ግን በርካቶች የቆዩ ፋይሎችንም በማግኘት አገልግሎቱን ተቀብለው እየተስተናገዱ ይገኛል።
አዲስ ዘመን:- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተገኘ የፋይናንስ ምንጭ የረጅም ጊዜ ፋይሎችን በዘመናዊ መልክ ሰንዶ ለማቅረብ የሚረዳ ማዕከል ግንባታ በቅርቡ አስጀምራችኋል፤ የማዕከሉ ችግር ፈቺነት ምን ድረስ ነው?
ዶክተር ታከለ :- ማዕከሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ እና ስራን የሚያቀላጥፍ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ የተከማቹ የልደት፣ ጋብቻ እና ሞት እና ሌሎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሰነዶችን በዘመናዊ መልክ የሚያደራጅ የመረጃ ማከማቻ ማዕከል ሲሆን፤ ለግንባታው 50 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ተመድቧል።
የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን በዘመናዊ መልክ ለማደራጀት እና ለቀጣዮቹ ጊዜያትም ኮምፒውተራይዝ ስርዓት መከተል አስፈላጊ በመሆኑ የማዕከሉ ግንባታ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። ማዕከሉ በሶስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደአገልግሎት ይገባል። አሁን ላይ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ግዥ ሂደት ላይ ነው የሚገኘው።
ማዕከሉ የሰነድ ማደራጃና ማስተዳደር አገልግሎትን ከማንዋል አሰራር ወደ ተቀላጠፈና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወደሚደገፍ አሰራር የሚቀይር በመሆኑ በተለያዩ ተቋማት ስር መረጃዎችን ለመተንተን እና ሳይንሳዊ አሰራርን ለመከተል ያስችላል።
የዘመናዊ ማዕከሉ መገንባት ተገልጋዮች በወቅቱ እና ትክክለኛውም መረጃ እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ የውልደት፣ ሞት፣ የነዋሪነት መታወቂያ እና ሌሎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎችን በኮምፒውተር በተደገፈ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለመሰነድ የሚያስችል በመሆኑ ለተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ግብአት እና ለአጥኚዎችም አስተማማኝ መረጃ ለመስጠት ያስችላል።
የተለያዩ ተቋማትም የከተማዋን ህዝብ ወሳኝ ኩነት መረጃ በሚፈልጉበት ወቅት በአግባቡ አደራጅቶ ለማቅረብ የሚያስችል ማዕከል ነው። በመሆኑም የማዕከሉ ግንባታ እንዲፋጠን የበኩላችንን ጥረት እያደረግን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን:- ኤጀንሲው ለቢሮ የሚጠቀምበት ህንጻ አዲሱ ገበያ በሚገኘው የሸገር የህዝብ መናፈሻ ግቢ ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለማዕከሉ ግንባታ ቋሚ ቦታ ከመፈለግ አንጻር ምን አይነት ዝግጁነት ነበራችሁ?
ዶክተር ታከለ :- ኤጀንሲው ያለበት ህንጻ በእራሱ ይዞታ ስር ስለሆነ ችግር ይገጥመናል ተብሎ አይታሰብም። የማዕከሉ ግንባታ በግቢው ከተከናወነ በኋላ ቦታ ይቀየር ቢባል እንኳን ብዙ የሚያስቸግር ጉዳይ አይኖርም።
ማዕከሉ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የሚደራጅ ቢሆንም ባስፈለገ ጊዜ መሳሪያዎቹን ከቦታ ወደቦታ አንቀሳቅሶ መጠቀም ችግር አይፈጥርም። ስለዚህ የቢሮ መቀየር አሊያም የማዕከል መለዋወጥ ቢያጋጥም አስፈላጊውን የሲስተም ሽግግር በማድረግ አገልግሎት የማዘመን ስራውን ለማስቀጠል የሚያግደን ምንም ችግር አይኖርም።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ታከለ :- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013