ክፍለዮሐንስ አንበርብር
‹‹የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው። የመላው ዓለም ተፈጥሯዊ ግብር እና ሰብዓዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትህ ሕልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው… በአድዋ የታላቅ ሕዝቦች ታላቅ ድል ነው። ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስንሄድ 1ሺ66 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታላቁ ጦርነት የተደረገበትና ታላቁ ድል የተገኘበት ሥፍራ ዓድዋ ከተማና የከተማው ግድም ገመገሞች ይገኛሉ›› ይላል ከዊኪፒዲያ የተገኘው መረጃ ።
በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም፤ ወይም በአውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር የካቲት መጨረሻ እና መጋቢት መጀመሪያ ላይ 1896 የተካሄደ ጦርነት ነበር።ለጦርነቱ መነሻ የሆነው ውል የተፈፀመው በዚሁ ዘመን ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከውጫሌ ከተማ ግርጌ ከአምባሰል ተራራ ሥር ወሎ ውስጥ ንጉሥ ይስማ እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ ነው።
ሸልዶ ተራራ ወይም (ሶሎዳ ተራራ)፤ ማርያም ሸዊቶ፤ አዲ ተቡን፤ ረቢ አርእየኒ (እግዚሃር አሳየኝ)… በመሠኘት የሚታወቁት እነዚህ ገመገሞችና ተራራማ ሥፍራዎች ዋነኞቹ የጦር ግንባሮች ናቸው። በ100 ሺህ የሚሠላ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ወራሪዎችን ድባቅ ከመታና ረግጦ ካስወጣ በኋላ ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም እንዳማርያም ላይ ተሰባስቦ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን (ድሉን) ለሰጠው አምላክ ምሥጋና አቅርቧል። አባት ሆይ፤ ንቀውን የመጡ የአገራችንን ድንበርና ልዕልና የደፈሩ የአውሮፓ ወራሪዎችን እንድናሸንፍ ስለረዳኸን እናመሰግንሃለን ስለማለታቸው ታሪክ ያወሳል።
29ሺ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከ100ሺ እስከ 120ሺ የሚገመተው ሠራዊት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል ፤የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ ።
የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ ባበደ መንፈስ (በተቆጣና በቆረጠ መንፈስ በጀግንነት ስለመዋጋቱም የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር አህመድ ሐሰን እንደሚሉት፤ ዓድዋ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢጣሊያንን የቅኝ አገዛዝ መከራንና ወረራን ለመከላከል ያደረጉት ትግልና ጥረት በሙሉ በነበራቸው የጋራ ታሪካዊ አንድነት ላይ በመመርኮዝ፣ ለወሳኙ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች፣ በተለይም ለአፍሪካውያንና ለኢትዮጵያውያን የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል እና ወሳኝ ድልን በታሪክ ዓምድ ላይ ስለማስመዝገባቸው ይጠቁማሉ።
ይህ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል የድል ብሥራት የተገኘው ከሰማይ በወረደ ዱብ ዕዳ አልነበረም። ኢትዮጵያውያኑ ያንን ግዙፍ አፍሪካዊ ድል ለማስመዝገብ፣ ከተደረገው ሀገራዊ ዝግጅት፣ ከተደረገው ወሳኝና ረዥሙ የዘመቻ ጉዞ፣ ጉዞውም ተከናውኖ ወደ ተለያዩ አውደ ውጊያዎችና ወደ ወሳኙ የአድዋ ጦርነት ለመግባት ካስቻላቸው የስንቅ አሠናነቅ ፣ውጊያዎቹን ለማከናወንና ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ የወቅቱ ሠራዊት መከተሙን ይናገራሉ።
አገራዊው ዝግጅትም ቢሆን እጅግ የተለየ ስለመሆኑ የታሪክ ምሁሩ ያወሳሉ ። በንጉሠ ነገሥቱ በአፄ ምኒሊክ የዘመቻና የጦርነት አዋጅ ይጀምራል ። የአዋጁ ጥቅል ይዘት የዘመቻ ጥሪን ለኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ለሹማምንቶች አገራችን ኢትዮጵያ በጠላት ጥርስ ውስጥ መግባቷንና የቅኝ ተገዥነት ዕጣ ፋንታዋ መቃረቡን፣ በሕዝቦች የተባበረ አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ክንድ ግን ጠላትን መመከት እና በቅኝ መገዛት እንደማይቻል የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ‹‹በእግዚኣብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ ለጠላት አልሰጠውም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ፣ ለኃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ›› በማለት ሀገርን ከጠላት ለመታደግ ጥሪ አደረጉ ይላሉ።
ከታሪክ መረጃ ምንጮች የምንረዳው የሩቁንም ሆነ የቅርቡን የዘማች ሠራዊት ኃይል በማደራጀት ከሸዋና ከአካባቢው የተነሣው ዘማች ኃይል ወሎ ወረ ኢሉ ላይ እንዲከት፣ ከጐጃም፣ ከደንቢያ፣ ከቋራ፣ ከበጌምድር እንዲሁም ከጨጨሆ በላይ ያለውን አገር ሁሉ አሸንጌ ላይ እንዲከት፣ የሰሜኑንና የወልቃይት የጠገዴንም ሰው መቀሌ ላይ እንዲከት፣ የሐረር ዘማች በአዲስ አበባ በኩል ገና የጥቅምቱ ዘመቻ ሣይጀመር አዲስ አበባ ገብቶ ወረ ኢሉ እንዲከት፣ የወለጋው ሠራዊት መግባት የቻለው ገብቶ ክረምቱ በመስከረም ስለሚበረታ በውሃ (ጐርፍ) ሙሌት እንዲቆዩ መደረጉን ይናገራሉ።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ አዋጁ አገራዊ ንቅናቄን መፍጠሩና መተግበሩ ስለነበር በትክክል ተተግብሯል። እነ ካዎ ጦና፣ እና አባጅፋር፣ ደጃች ጆቴ (ቄለም)፣ ደጃች ገብረእግዚአሔርን ቀሪውን የአገሪቷን ክፍል እንዲጠብቁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። ለራስ ተሰማና (ኢሉ አባቦራ)፣ ለራስ ወልደ ጊዮርጊስ (ከፋ) በአውሣ በኩል የኢጣሊያንን አካሄድ እንዲከላከሉ መታዘዛቸውን ያወሳሉ ። ታዲያ በዚህ በሁሉ የተቀናጀ እና ኢትዮጵያውያን ጥምረት ጦርነቱ መጀመሩን ይናገራሉ።
የጦርነቱ ስልትና ቅንጅት፣የታሪክ መጽሐፍትን ዋቢ አድርገው እንዳገኙ የሚናገሩት ምሁሩ፤ ዓድዋ ብዙ መሥዋዕትነት የተከፈለበት መሆኑን ያመለክታሉ። በጣሊያን በኩል ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ይናገራሉ። በጦርነቱ 7000 ሰዎች ሲሞቱ 1ሺ500 ተዋጊዎች ቆስለው ነበር። 3000 ምርኮኞችም ነበሩ። እግሬ አውጪኝ ብለው የበረገጉ እና ደብዛቸው የጠፋ ቁጥራቸው አይታወቅም።
በኢትዮጵያ በኩልም በጦርነቱ ብዙ መስዋዕትነት እንደተከፈለ ያስታውሳሉ ። ለእናት ሀገር ኢትዮጵያ ሲሉም ከ4000 እስከ 6000 ሰዎች ሞተው ነበር። 8000 የሚሆኑ ቁስለኞችም ነበሩ ። ግን አንዳችም ምርኮኛ አልነበረም። አንዳችም የጠፋ ሰውም በታሪክ አልተመዘገብም። ሞት ወይንም ነፃነት ብለው ከቤታቸው በፉከራ እና ሽለላ የወጡ አርበኞች በዚያው እስከ መጨረሻው መሥዕዋት መሆኑን መረጡ። ለጠላት እጃቸውን መስጠት የሞት ሞት አድርገው ወሰደውት ስለነበር መማረክ አልፈልጉም።
ጦርነቱ በድል መጠናቀቁና ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲል መሆኗ በታሪክ የሚዘከር መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አህመድ፤ የሠራዊቱ ተዋፅኦ፣ ከወታደራዊውና ከነበረው የመሣሪያ አቅም፣ ውጊያውንና ጦርነቱ ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ከነበረው የመረጃ ፍሰት ዘዴ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት፣ የአብሮነትና የተቻችሎ የመኖር ልዩ መገለጫ፣ ቁም ነገሮች እየተፈተሹ፣ እየተፈለፈሉና እየተቀመሩ መታወስ አለባቸው ።
የተቀመሩት ቁም ነገሮች ለሀገር የመልካም ገፅታና ሀገርን ሀገር ለማድረግ እንዴት ክብደት ያለው ፋይዳ ሊገኝ እንደሚችል፣ ይህ ፋይዳ በተራው የአሁኑ ትውልድ ድህነትን፣ ኋላቀርነትንና ወደፊትም ቢሆን ችግሮች ቢያንዣብቡ፣ ማንዣበቡ ብቻ ሣይሆን ቢከሰቱ ከአያቶቻችንና ከአባቶቻችን የኢትዮጵያዊነት የጋራ የትግልና የድል ልምድ ምን እንደሆነ በሚገባ ማጤን ይገባል የሚል እምነት አላቸው ።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት አቶ ገዛኸኝ በርሄ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና የበላይ ነን ብለው ግፍ ሲያደርሱ ለነበሩት ደግሞ አንገት ያስደፋ ትንግርታዊ ክስተት ነው።
ዓድዋ ከድልም በላይ ነው ። ለድሉም መብቃት በወቅቱ የነበረውን ተግባቦት ስልት ማሳየት ተገቢ መሆኑን በመጠቆም ስልቱን አሁንም ድረስ በታሪክ የሚዘከር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ስለመሆኑ ያብራራሉ።
በወቅቱ የሀገሪቱ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ የነበሩት አጼ ምኒሊክ መላውን የሀገሪቱን ሕዝብ ለመቀስቀስ የተጠቀሙት አካሄድ እጅጉን የሚደነቅ እንደሆነ ይናገራሉ። በሥርዓተ መንግሥቱ ያኮረፈ ወይንም ቅራኔ ያለበትም ሆነ የተደሰተ ሁሉ ለእናት ሀገሩ ተመሳሳይ አቋም እንዲይዝ ያስተላለፉት ጥሪ እና በኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘናት የተሰጣቸው መልስ እጅጉን አስገራሚ ነበር።
ሁሉም ምርቱን ሰብስቦ ወረኢሉ ላይ ተገናኝቶ ጠላትን ለማደባየት እንዲሰለፍ ጥሪ ሲያስተላልፉ አቤት! ብሎ ለሀገሩ ያልገበረ ለሀገሩ ያልተሳተፈ አልነበረም ። ይህም አንድነትና ብርታት ኢትዮጵያን ለድል እንዳበቃ ይናገራሉ ።
በወቅቱ ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች ሳይኖሩ በነጋሪት ጉሰማ ብቻ ያ ሁሉ አርበኛ ለእናት ሀገሩ መሰለፉ እጅግ የሚያስደንቅ ሲሆን ለእናት ሀገር ጥሩ መረጃው የተላለፈበት መንገድ በራሱ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር እንደሆነ ያብራራሉ።
በጠላት በኩል በነበረው ዝግጅትና የተግባቦት ስልት ብሎም በወቅቱ የነበረውን ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅም የላቀ ብቃት የነበረ ቢሆንም አጼ ምኒሊክ የተከተሉት ስልት ከጠላት በእጅጉ ልቆ የተገኘ እና ውጤታማ እንደነበር ያስረዳሉ።
በጦርነቱ በምግብ ዝግጅትና ሎጂስቲክስ አቅርቦት በኩልም የነበረው መናበብ ለድሉ መገኘት ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው ያስረዳሉ። ሴቶች በቅብብሎሽ ግንባር ድረስ ዘምተው ምግብ አዘጋጅተው ወንዶችን እያበረታቱ ለድል ያበቁበት ስልትም በጣም የሚከበር፣ የሚደነቅና በታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ይነገራሉ።
አጼ ምኒሊክን ጨምሮ ሌሎቹን በማነሳሳት በኩል እቴጌ ጣይቱ ሚናቸው የላቀ ነበር የሚሉት አቶ ገዛኸኝ፤ የእርሳቸው ሚና ለበርካታ ሴቶች መነሳሳት ምክንያት እንደሆነም ይናገራሉ። ንግስቲቱ የነበራቸው ወኔ እና ተሰሚነትን ተጠቅመው በርካቶችን አነሳስተው ለድል የሚያበቃ ታሪክ መሥራታቸው ሁሉም በታሪክ ውስጥ የሚገዝፍ ሥራ ስለመስራታቸው ማሳያ እንደሆነ ያብራራሉ።
እንደ ምሁሩ ገለፃ፤ የዓድዋ ድል በሁሉም ዘርፍ በተደረገ የተቀናጀ ሥራ እና በተናበበ የተግባቦት ስልት የተከወነ ነው። በመሆኑም ታሪክ ዘለዓለም ሲዘክረው ይኖራል። ኢትዮጵያም ከጥቁር ሕዝቦች ሁሉ በተለየ መልኩ ተስላ በከፍታ ማማ ላይ እንድትቀመጥ ያደረጋትና በዓለም ታሪክም ያልተጠበቀ ለውጥ የተገኘበት እንደሆነ ይጠቁማሉ ።
የአሁኑ ትውልድም ከቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ጀግንነት የማስቀጠል አደራ እንዳለበት ይናገራሉ ። በተለይም ደግሞ ሀገር ፈተና ሲገጥማት በመነጋገርና ተግባቦትን በማስፋት፣ የዘመነ አሰራር በመከተልና የሀገርን ጥቅም በማስቀደም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ማድረግ የሚገባ ስለመሆኑ የአድዋ ድል ማሳያ እንደሆነም ይጠቁማሉ ።
ሀገሪቱን የሚመሩት መንግሥታት፣ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በዘመነ አጼ ምኒሊክ የነበረውን የአመራር ብልጠት፣ ለሀገር ህልውና ሲባል ልዩነቶችን ወደ ጎን የመተው፣ ሕዝቦች አንድነትና የሀገር ፍቅርን ምን እንደነበር ካለፈው ታሪክ ሊቀስሙ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ ። የሀገር ጥቅምን በማስቀደምና ልዩነቶችንም በመፍታት በጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ወደር የሌለው መፍትሄ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
በአሁኑ ወቅት ያሉ የታሪክ ምሁራን በዓድዋ ላይ የነበረው ታሪክ ፍንትው አድርገው ማሳየትና ትውልዱን ማንቃት እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ። ዓድዋ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የጭቁን ሕዝቦች ደማቅ ታሪክ መሆኑንም በተለያዩ መንገዶች ማሳየት ይገባል የሚል እምነት አላቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013