አስመረት ብስራት
«እቴጌ ጣይቱ – እቴጌ ብርሃን
ዳዊቷን ዘርግታ – ስማልኝ ስትል
ተማራኪው ጣሊያን – ውሃ ውሃ ሲል
ዳኛው ስጠው አለ – ሰላሳ በርሜል
እንደ ብልኃተኛ እናት – እንደ እመቤታችን
ሲቻለው ይምራል – የእኛማ ጌታችን »
እየተባለ በወቅቱ አዝማሪዎች የተገጠመላቸው እቴጌ ጣይቱ የዓድዋ ድል የእሳቸው ነበር ቢባል እንደማያንስባቸው በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሕግና የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ ይናገራሉ። አፄ ምኒሊክ ሰላማዊውን መንገድ ለመመልከት ጊዜ ሊወስዱ ማሰባቸውን የተረዱት እቴጌ በሚስጥር ጦር አሰናድተው በመጨረስ ጦርነቱን አይቀሬ እንዲሆን እንዳደረጉት ነው የሚናገሩት።
ሴቶች ብዙም ወደ አደበባይ በማይወጡበት ዘመን አንፀባራቂ ስራ የሰሩ፤ ሴቶች ከፊት መቆመን እንደሚችሉ ያሳዩ ጀግኖችም እንደነበሩ ታሪክን እያነሳሱ ያጫውቱናል። በተለይም ከአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በፊት እና በኋላ እቴጌ ምንትዋብ፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ በኢትዮጵያ የሴቶች ታሪክ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ያመለክታሉ።
በተለይ በቅርብ ጊዜ የነበሩት የሴት አርበኞች ብዙም እንደማይታወቁ የዘርፉ የታሪክ ምሁሩ አንሰተው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጐልቶ በወጣበት፤ ቀለም፣ ዘር፣ እድሜ፣ ፆታ፣ የቦታ አቀማመጥ ሳይገድበው በተካሄደው የዓድዋ ጦርነት ፋና ወጊ በነበሩት እቴጌ ጣይቱ አስተባባሪነት በርካታ ሴቶች የላቀ ተሳትፎ አበርክተዋል።
ለአገራቸው ነጻነት ከወንዶች እኩል ፊት ለፊት ከመዋጋት ጀምሮ ከሰራዊቱ በስተጀርባ በመሆን ስንቅ ያዘጋጃሉ፤ ያደርሳሉ፣ ዘመኑ ህክምና ያልተስፋፋበት በመሆኑ ቁስለኞችን በባህላዊ ህክምና እውቀት ያክማሉ የሚሉት ዶክተሩ ዓድዋ ያለሴቶቹ ተሳተፎ እውን ስለመሆኑ አጠራጣሪ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ይሁን እንጂ በርካታ ሴቶች በነበሩባቸው ዘመናት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምን እንደነበር አልተጠናም። ቢጠና ኖሮ ከወንዶች ያላነሰ፤ በብዙ መልኩ የበለጠ ታሪክ ያላቸው ሊኖሩ ይችሉ ነበር የሚሉት ዶክተሩ ለአገራቸው ነፃነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተው በታሪክ ብዙም እውቅና ካላገኙት ሴቶች መካከል የተወሰኑትን ለትውልድ ስንቅ ስለሚሆኑ ታሪካቸውን ማካፈል ወደናል። በቅድሚያ የጦርነቱ መሪ የእቴጌይቱን ታሪክ እናነሳሳ። የእቴጌ ጣይቱ የዓድዋ ገድል የሚጀምረው ለአድዋ ጦርነት መነሻ ከሆነው ከውጫሌ ስምምነት ነው። ነገሩ እንዲህ ነበር።
ኮንት አንቶኔሊ የውጫሌ ውል እርሱ እንደፈለገው እንደማይሆን እና 17ኛዋ አንቀፅ እንደተሰረዘ በሰማ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ እና አፄ ምኒሊክ በተቀመጡበት እልፍኝ ገብቶ የ17ተኛው ክፍል ተሰርዟል ተብሎ ተፃፈ በማለት አፄ ምኒሊክን ይጠይቃል። አፄ ምኒሊክም ሁለታችን አንተና እኔ ተነጋግረን አንተ ወደህና ፈቅደህ የተፃፈ ቃል ነው። ሌላ አልታከለበትም፤ ባስተርጓሚህ የተናገርከው ነው አሉት።
ከዛ ኮንት አንቶኔሊ እንዳልተሳካለት አውቆ የውሉን ወረቀት ቦጫጨቀውና ጦርነቱ እንደማይቀር ተናግሮ ከእልፍኝ እየወጣ እያለ “እቴጌ ጣይቱ ከት ብለው በመሳቅ የዛሬ ሳምንት አድርገው በዚህ የሚደነግጥ የለም ሂድ የፎከርክበትን አድርግ እኛም የመጣውን እናነሳዋለን እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው ከዚህ የሌለ አይምሰልህ። የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይደለም። አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፎከርክበትን በፈቀድህ ጊዜ አድርገው እኛም ከዚሁ እንቆይሀለን።” ይሉታል።
“ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም!! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” በማለት ፈፅሞ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንደማይደራደሩ መናገራቸውን ይናገራሉ። ይህ የሴቶችን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
እቴጌ ጣይቱ ሴቶችን በማስተባበር ትልቅ ስራም ሰርተዋል። እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ዘመቻ ወቅትም የራሳቸውን ጦር እየመሩ ዘምተዋል። ሴቶችን በተለያየ ዘርፍ በማሰማራት ሰራዊቱ ምግብ፣ ንፅህና፣ ህክምናም ሳይጓደልበት የተሟላ አገልግሎት እያገኘ እንዲዋጋ አድርገውታል።
ከጦርነቱ አስቀድሞ ሀገራችን ከ1880 እስከ 1884 ዓ.ም በነበሩት አምስት ዓመታት የከብት በሽታ ገብቶ ከብቶችና ሌሎች እንስሳት በማለቃቸው ገበሬው አርሶ ለማምረት ባለመቻሉ ሀገራችን ከፍተኛ የረሃብ ችግር ውስጥ መሆኗን በመረዳት ጣሊያን የኢትዮጵያ ሰራዊት በረሀብ ምክንያት እንደሚበተን ትልቅ ተስፋን አንግቦ እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር አልማው የመጀመሪያው ስንቅ የማቀበሉ ስራ በአግባቡ እንዲከናወን በማድረግ ሠራዊቱ በረሃብ ምክንያት እንዳይበተን ማድረግ መቻላቸውንም አስረድተዋል።
ጦርነቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ይደረግ ስለነበር በአንዱ አቅጣጫ የዘመተው አዝማች ድል አድርጐ እና ምርኮ ይዞ በመመለስ ሲፎክርና ሲያቅራራ ‹‹ድሉ ገና ንጉሡ ሣይመለሱ እዚህ ሆኖ መፎከሩ ምንድነው?›› በማለት እየተቆጡ ሲያበረታቱ እና ሌሎቹን አውደ ውጊያዎች እንዲያግዙ ሲያደርጉ ነበር። ጣሊያኖች ወደ መቀሌው ምሽግ በተሸሸጉ ጊዜም ይህን ሁኔታ የተገነዘቡት እቴጌይቱ የጣሊያኖችን የውኃ ምንጭ በራሳቸው ጦር በማስከበብ እና ምንጩን በማሳገድ ውሃ ሲጠማቸው ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉ አድርገዋል።
ይህ በመቀሌ የሚገኘው ምንጭም እስከዛሬ ድረስ ውሃ የሚያፈልቅ ሲሆን ለንግስቲቱ መታሰቢያነት ይሆን ዘንድ ‹‹ማይ እንስቲ›› ተብሎ ተሰይሟል። ትርጓሜውም የሴት ውሃ ማለት ነው። ሴቶች በጉልበት ብቻ ሳይሆን በጥበብ ድል መንሳት የሚችሉ መሆናቸውን ማሳያ ታሪክ ይሄንን ያሳየናል ይላሉ ዶክተር አልማው።
እቴጌ ጣይቱ የማይተካ ሚና ይኑራቸው እንጂ በጦርነቱ ወቅት በስራቸው ያስተባብሯቸው የነበሩ ከሀያ እስከ ሰላሳ ሺህ ተብሎ የሚገመቱ ሴቶችም በጦርነቱ ጉዞ ላይ ሆነ በጦርነት ጊዜ በየቀኑ ሰባትም ስምንትም ምጣድ እየጣዱ እንጀራ ይጋግራሉ፣ ጠላና ጠጅ ይጠምቃሉ፣ ወጥ ይሰራሉ፣ ግብር ያበላሉ፣ ቁስለኛ ያክማሉ፣ ውሃ ያጠጣሉ፣ በፉከራና በእልልታ ተዋጊውን ያበረታቱም እንደነበር የታሪክ ምሁሩ አስረድተው እቴጌ ጣይቱ እያንዳንዱን ስራ ለመስራት የሚችል ሙያተኛም ከሰራዊቱ እኩል ከማደራጀታቸውም በላይ ሰራዊቱን አጀጋኝ ወኔ የሚሞሉ አዝማሪዎችንም ይዘው ሄደው ነበር። እነዚህ እንስት አዝማሪዎች በመረዋ ድምፃቸው ያኔ የጠፋበትን ወኔ እየሞሉ ወደፊት ብለውታል።።
በአድዋው ጦርነት የኢትዮጵያ ሴቶች በአዋጊነት ተሳትፈዋል። ጦር መርተው፣ መድፍ አስተኩሰው፣ ወታደር አዘው አዋግተዋል፣ ቀን በውጊያ ማታ ከስንቅ ዝግጅት ሳይነጠሉ ረጅሙን የውጊያ ወራት አሳልፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አዝማሪዎች የደከመውን ጦር በቀረርቶና በሽለላ አቅሉን አሳጥተው በሞራል ጦርነቱን ያግለበልቡት እንደነበር ዶክተር አልማሁ ይናገራሉ። ሴቶች የማጀቱን ስራ፤ የአደባባዩን ጦር፤ የመዝናኛውን ሁሉንም አሟልተው ነው ጦርነቱን ለድል ያበቁት የሚሉት ዶክተሩ ከብዙው በጥቂቱ እቴጌ ጣይቱ እና ጀግኖች እናቶቻችን ለታላቁ የነፃነት ድል አድዋ ይህን አበርክተዋል። በአድዋ ድል ሌሎች ድልን የማያውቁትን የሚዘክሩትን ያህል ያልተወራለት ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው የሀገራችን እውነተኛ ድል ዓድዋ መሆኑን ዶክተር አልማው ተናግረዋል።
ከዶክተር አልማው ሀሳብ በተጨማሪ ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ ነውና ነገሩ ታሪክ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ ከጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ ከሚለው መፅሐፍ በገዛ አይናቸው አይተው በፅሁፍ ካኖሩልን በተወሰነ መልኩ እነሆ ብያለሁ።
ተኩሱ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት የጀመረ እስከ አራት ሰዓት እንደ ሐምሌ ዝናብ አላባራም። ድምጹም በኖህ ጊዜ ሰማዩ ተነድሎ መሬቱን አጠፋው እንደተባለው ይመስላል እንጂ በሰው እጅ የተተኮሰ አይመስልም። መድፉም ሲተኮስ ጢሱ የቤት ቃጠሎ መስሎ ይወጣ ነበር። ከዓድዋው ጦርነት እጅግ ጥቂቱን ጻፍኩ እንጂ፣ አይኔ ያየውን ጆሮዬ የሰማውን በሙሉ መጻፍ አይቻለኝም።
በዚያን ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በግንባራቸው ተደፍተው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው፣ ድንጋይ ተሸክመው እያዘኑና እየተጨነቁ ወደ እግዚአብሔር ሲጮሁ በንጉሠ ነገሥቱ ግቢ ላይ የመድፍና የነፍጡ አረር እንደ ዝናብ ወረደበት።
እቴጌም ጥቁር ጥላ አስይዘውና አይነ እርግባቸውን ገልጠው በእግራቸው መሄድ ጀመሩ። ሴት ወይዛዝርቱ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ልጅ ወይዘሮ ዘውዲቱና ደንገጡሮች እቴጌን ተከተሏቸው።
የኋላው ደጀን ጦር እንደመወዝወዝ ባለ ጊዜም፣ እቴጌ አይዞህ! አንተ ምን ሆነሃል! ድሉ የኛ ነው! በለው! አሉት። በዚያ ቀን እቴጌ ጦራቸውን በግራና ቀኝ አሰልፈው የሴቶችን ባህሪ ትተው የተመረጠ የወንድ አርበኛ ሆነው ዋሉ። የእቴጌ ጣይቱ መድፈኞች እቴጌ ከቆሙበት በስተቀኝ ሆነው መልሰው መላልሰው በመተኮስ በመሃል ሰብሮ የመጣውን የኢጣሊያ ጦር አስለቀቁት። በዚህም ጊዜ የኢጣሊያ ሰራዊት ሽሽት ጀመረ።
እኛም ለጊዜው የፊተኛው ጦር ድል ሲሆን፣ የጦርነቱ መጨረሻ መስሎን ደስ አለን። ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ የፊተኛውን ጦር አባራሪውን ተከትለው በሩን አልፈው በዘለቁ ጊዜ እንደገና የኢጣሊያ ጦር እንደ ቅጠል ሆኖ ተሰልፎ ቆየ። ተኩሱም ከፊተኛው የበለጠ ሆነ።
አጼ ምኒሊክም ጦር ጨምረው ወደፊት ወደ ተራራው ከተጓዙ በኋላ ከበቅሎ ወርደው በዋሻው ውስጥ በነበረው ሁለት ሺ የሚጠጋ የኢጣሊያ ጦር ላይ አስር አስር መድፍ ሲጥሉበት በዋሻው ውስጥ የነበረው የጣሊያን ሰራዊት እግዚኦ ብሎ ጮኸ።
የአጼ ምኒልክ ታዛዥ አባ ተምሳስ የንጉሠ ነገሥቱን ጥላ ይዞ ነጋሪት እያስመታ፣ አይዞህ በርታ! እያለ ሲያዋጋ ዋለ። እቴጌ ጣይቱም መጀመሪያ ድል ባደረጉበት ቦታ ቁመው ለተጠማውና ለቆሰለው ውሃ ሲያጠጡ ዋሉ። እንኳን የኢትዮጵያ ሰው፣ የኢጣሊያ ቁስለኞችም የእቴጌ ውሃ አልቀረባቸውም። ሴትነት ጅጋኔም ርህራሄም መሆኑን እቴጌ ያጠየቁበት ተግባራቸው መሆኑን ያሳዩበት ነው።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ሳይመለሱ በርካታ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከግንባር መመለስ ጀመረ። ይሄኔ ንጉሠ ነገሥቱ ሳይመለሱ እንዴት ትመለሳላችሁ፣ በሉ ምርኮኛና ቁስለኛውን እዚህ እየተዋችሁ ወደ ግንባር ተመለሱ ብለው እቴጌ አዘዙ።
የእቴጌ እህት ወይዘሮ አዛለች፣ ሰው የማረከውንና ቁስለኛውን ይዞ ሲመለስ ባየች ጊዜ፣ ንጉሥህን ጠጅህን ጮማህን ትተህ ወዴት ትመለሳለህ? እያለች ለፈፈች። የምኒሊክ ደግነት እንኳን ወንዱንና ሴቱን መነኩሴውን ጭምር አጀገነው። እቴጌ ጣይቱና አብረዋቸው የነበሩ ሴቶች ያለስራቸው ታላቅ ስራ ሲሰሩ ውለዋልና፣ ታሪካቸውን ጽፌ አልጨርሰውም።
ንጉሠ ነገሥቱ ሳይመለሱ ቀኑ እየመሸ በመምጣቱ፣ እቴጌ ምነው ጦሩ አልተፈታም እንዴ? የሚል መልዕክት ወደ አፄ ምኒሊክ ላኩ። አፄ ምኒሊክም በግራ ሲተኮስ እሰማለሁ እንጂ በዚህ ያለው አልቋል ብለው መልእክተኛ በመላክ ወደ ሰፈር ተመለሱ።
እቴጌም የንጉሠ ነገሥቱን መመለስ ባዩ ጊዜ ላይን ድንግዝግዝ ሲል ከጦር ሰፈራቸው ተመለሱ። በድንኳናቸው በመግባት ዙፋናቸውንና መከዳቸውን እጅ ነስተው በዙፋናቸው ላይ ተቀመጡ። በጦርነቱ መሃል እንዳልዋሉና እንዳልነበሩ ሆነው ተገኙ። ድንቅ ሴት።
ሀገራችን ከአውሮፓዊያኑ ቀድማ ሴትም ወንድም እኩል መሆኑን ያበሰረች፣ በመሪነት ሴቶች ከፊት ይቆሙ እንደነበረ የሚያሳዩ ታሪኮች አሉን። የታሪክ ድርሳናትን ስናገላብጥ ልብን የሚሞሉ ድሎች ባህል ፍቅር የተሞላበት ሆኖ እያለ ከሰለጠኑት የቀደምነው እኛ ስለምን ይሆን ወደኋላ የተመለስነው ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ወንዱም ሴቱም ደማቸውን ያፈሰሱላት ለአንድነቷ የህይወት ወጋ የከፈሉላት መሆኑን ልብ ያለው ልብ ይበል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013