አንተነህ ቸሬ
ኢትዮጵያ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በወራሪው የኢጣሊያ ጦር ላይ የተቀዳጀችው አንፀባራቂው የዓድዋ ድል የራሷን ነፃነትና ሉዓላዊነት አስከብሮ ከማስከበሩም አልፎ በመላው ዓለም በጭቆናና በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ይማቅቁ ለነበሩ ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ትግል መሰረትና ተምሳሌት መሆን የቻለ ድል ነው። ይህም ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና የተመዘገበ የታሪክ ክስተት እንዲሆን አስችሎታል።
የዓድዋ ድል በመላው ዓለም የሚገኙ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳ፣ ትግላቸውን ያጠነከረና ለስኬት እንዲበቁ ያደረገ የአሸናፊነት ምንጭ ስለመሆኑ የበርካታ አገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ በጥናቶቻቸውም አረጋግጠዋል።
በዓድዋ ጦርነት ላይ ብዙ ጥናቶችን ያደረጉትና ጽሑፎችን ያበረከቱት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሪ፣ የዓድዋ ድል፣ ነፃነትን አጥብቆ የሚሻ አዲስ የአፍሪካዊነት ስሜት እንዲጎለብት ማድረግ የቻለ ታሪካዊ ድል እንደሆነ ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አንፀባራቂ ድል የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች ምልክት መሆን የቻለ ወሳኝ ታሪካዊ ክስተት ነው። ጦርነቱና ድሉ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው ዓለምን ያስደነቀ ገድል መፈፀማቸውን ለመላው ዓለም ያሳዩበት በመሆኑ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው በጋራ ሆነው መታገል እንደሚገባቸው ትምህርት ሰጥቷል።
ፕሮፌሰር አየለ ‹‹The Victory of Adwa፡ An Exemplary Triumph for the Rest of Africa›› በሚለው ጽሑፋቸው የአምባሳደር ዶክተር ዘውዴ ገብረሥላሴን ሃሳብ ይጠቅሳሉ። አምባሳደሩ ስለጦርነቱና ድሉ በገለፁበት ማብራሪያቸው ‹‹የዓድዋ ድል የአውሮፓን ሰማዮች የሃዘንና የድንጋጤ ደመና ያለበሰ፤ በአንፃሩ በቅኝ ገዢዎች እየተበዘበዙ ለነበሩ ጭቁን የአፍሪካና የእስያ ሕዝቦች ደግሞ የነፃነት ተስፋን የፈነጠቀና የጀግንነት ወኔን ያላበሰ ደማቅ ድል ነው›› በማለት ይገልፁታል።
ከዚህ የአንጋፋው አምባሳደር ገለፃ መረዳት የሚቻለው የዓድዋ ድል ንዝረቱ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም እንደተሰማ እንዲሁም የድሉ ትሩፋቶች ለጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ትግል ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆኑና ትግሎቹም ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ የስኬት መንገድን የጠረጉ ታሪካዊ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ነው።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ከተቦ አብዲዮ የዓድዋ ድል ጥቁሮች በነጮች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጎናፀፉት ዓለም አቀፋዊ ድል በመሆኑ ትርጉሙ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ዓለም ትምህርት የሆነ ድል እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹የዓድዋ ድል ነጮችን ሁሉ ባሉበት ያስደነገጠና ‹አፍሪካ የጨለማ አህጉር ናት› ብለው ያሰቡትንና ያመኑትን አባባላቸውን እንዲቀይሩ ያስገደደና በአፍሪካ አዲስ ኃይል እየመጣ እንደሆነ ያስገነዘበ ድል ነው። ድሉ ለጭቁኖች በተለይ ለጥቁሮች ልዩ ትርጉም ያለው ታላቅ የመስዋዕትነት፣ የትብብርና የጀግንነት ገድል ነው›› ይላሉ።
እንደዶክተር ከተቦ ማብራሪያ፤ የዓድዋ ድል ለጭቁኖች የነፃነት ትግሎች ከፍተኛ ሚና ካበረከተባቸው የዓለም አካባቢዎች አንዱ የአሜሪካ አካባቢ ነው። በወቅቱ በአሜሪካ የጥቁሮች መብት የተከበረ ስላልነበር ድሉ ከፍተኛ እንድምታ ነበረው። ጥቁር አሜሪካውያን በትግላቸው ሂደት ብዙ ነገራቸውን ከኢትዮጵያ ጋር እዲያያዝ ያደርጉ ነበር።
በደቡብ አፍሪካም አፓርታድን ለመታገል በተደረገው ጥረት ኢትዮጵያ እንደነፃነትና ክብር ምልክት ተደርጋ ትወከል ነበር። ከ1896 እስከ 1897 ዓ.ም ድረስ ሩስያና ጃፓን ያደረጉትና በጃፓን አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጦርነት (Russo-Japanese War) ከዓድዋ ድል ጋር ተያያዥነት እንዳለውም በታሪክ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ዓድዋ ለመላው ዓለም ጭቁኖች የነፃነት ምልክትና የሞራል ምንጭ ሆኗቸዋል። በተለይ የአፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉ ትልቅ መሰረት የሆነ ድል ነው። የአፍሪካ አገራት ነፃ ከወጡ በኋላም የሰንደቅ ዓላማዎቻቸውን ቀለማት የወሰዱት ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት (አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ) ነው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization of African Unity) መመስረትም የዓድዋ ድል ውጤት ነው። ድርጅቱ እንዲመሰረትና መቀመጫው አዲስ አበባ ላይ እንዲሆንና የአፍሪካ አገራትም በዚህ እንዲስማሙ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረከተው ይኸው የዓድዋ ድል ነው።
ለድርጅቱ መመስረት ምክንያት የሆነው የፓን-አፍሪካ ንቅናቄ (Pan-Africanism) የተጠናከረውም በዓድዋ ድል ነው። ምንም እንኳን የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከዓድዋ ጦርነት ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም በዓድዋ የተገኘው ድል ግን የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል።
‹‹ጥቁሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ የዓድዋ ድል ትዝታና ስሜት ነበር›› የሚሉት ዶክተር ከተቦ፤ ‹‹ጭቁኖች ኢትዮጵያን የነፃነት ምልክትና የጥቁሮች ሁለተኛ ቤት አድርገው ነው የሚመለከቷት። ‹ኢትዮጵያ አገራችን ናት› ብለው ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር። የአፍሪካ የነፃነት መሪዎች (ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮበርት ሙጋቤ እና ሌሎችም) ኢትዮጵያን እንደሁለተኛ አገራቸውና ቤታቸው ነው የሚቆጥሯት።
ትግላቸውን የቃኙትም ከዚህ እሳቤያቸው አንፃር ነው። የነፃነት ትግላቸውን ባደረጉባቸው ጊዜያትም ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው የተለያዩ ድጋፎችን አግኝተዋል። ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ እንደነፃነት ምልክት መቆጠሯ በወሬና በንድፈ ሃሳብ የተገለፀ ብቻ ሳይሆን በተግባር የታዬና የተረጋገጠ መሆኑን ነው። የዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ የዓድዋ ድል ነው›› ይላሉ።
ስመጥሩ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ዊሊያም ኤድዋርድ ዱ ቦይስ ‹‹በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር የወደቁ ሕዝቦች ከዓድዋ ድል በመማር የነፃነት ትግሎቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በርትተው ለመታገል ቁርጠኛ በመሆን በነፃነት መኖርን ለድርድር እንደማያቀርቡት ለመላው ዓለም ማሳወቅ አለባቸው፤ ከኢትዮጵያ መማር ያለባቸውም ይህን እውነት ነው›› በማለት የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ትግል መነሻና ስንቅ እንደሆነ ለጭቁኖች መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አየነው ስለሺ በበኩላቸው የአብዛኞቹ የዓለም የጭቁኖች የነፃነት ትግሎች መነሻና የስኬት ምንጭ የዓድዋ ድል እንደሆነ ይገልፃሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፤ ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው ያደረጉት ትግል ስኬታማ መሆኑ ለሌሎች ሕዝቦች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል።
የዓድዋ ድል በሌሎች የዓለም አካባቢዎች የሚገኙና በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሥር የነበሩ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው በአንድነት መታገል እንዳለባቸውና ነፃነታቸውንም ማግኘት እንደሚችሉ ትምህርት መሆን የቻለ ታላቅ ድል ነው። ድሉ የትብብርንና የአንድነትን ውጤታማነት እንዲሁም ለነፃነት መስዋዕትነት መክፈል ታላቅ ክብር እንደሆነ ጭምር አሳይቷል። የነጮች የበላይነት ማክተም እንደሚችልም ያሳየና መንገድ የከፈተ አንፀባራቂ ክስተትም ነው።
በተጨማሪም ‹‹በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በላቲን አሜሪካና በእስያ የነበሩ የነፃነት ንቅናቄዎችም የተጀመሩትና ስኬትን ያስመዘገቡት የዓድዋ ድል በመላው ዓለም ከታወቀ በኋላ ነው።
ዓድዋ ላይ የተመዘገበው የኢትዮጵያውያን ድል በሌሎች የዓለም አካባቢዎች ለተደረጉ የነፃነት ትግሎች መጀመር ብቻም ሳይሆን ስኬታማ መሆንም መሰረት የሆነ ድል ነው። በአጠቃላይ የዓድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች የነፃት ትግል መሰረት የጣሉበት ፈር ቀዳጅ መስመር ነው›› ይላሉ።
ከድሉ በፊት ‹‹ኢትዮጵያውያን ኋላ ቀሮች ናቸው›› ብለው ያስቡ የነበሩ አካላት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት መስርተው የምጣኔ ሀብትና ወታደራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት ማሳየታቸውን የሚጠቁሙት አቶ አየነው፤ ይህም ድሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠረው ተጽዕኖ ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። የድሉ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና እንደታገኝ ከማስቻል በተጨማሪ ድሉ የጭቁኖች ትግል መመኪያና ምልክት ሆኖ እንዲታይ እንዳደረገም ይናገራሉ።
የዓድዋ ድል በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ለተደረጉ የነፃነት ትግሎች መነቃቂያ ከመሆን ባሻገር አገራት ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ በጭቁኖች ለተቋቋሙ ተቋማት መመስረትም ሚናው የጎላ ነው። ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization of African Unity – OAU) የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት (African Union – AU) ነው። ይህም የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የነፃነት ትግሎችና ከትግሎቹ መጠናቀቅ በኋላ የተመሰረቱ ተቋማት የዓድዋ ድል ደማቅ አሻራ እንዳረፈባቸው ጠቋሚ ምስክር ነው።
የ‹‹Roots of Rastafari›› መጽሐፍ ጸሐፊዋ ቨርጂኒያ ሊ ጃኮብስ የዓድዋን ድል ‹‹ኢትዮጵያ ዘረኛና ከፋፋይ የሆነውን የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ተግባርን በመቃወምና ድል በማድረግ የማይነቃነቅ ግዙፍ የክብር ማማ እንድትገነባና በድል የታጀበ ተጋድሎዋ ለሌሎች አፍሪካውያን የነፃነት ትግል አርዓያ እንድትሆን ያስቻላት ተምሳሌታዊ ድል›› በማለት ገልፀውታል።
የዓድዋ ድል በቅኝ ግዛት ሥር ወድቀው ለነበሩ የአፍሪካ ሕዝቦች የነፃነት ትግል ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው የነፃነት ትግሎቹ መሪዎች የነበሩና በኋላም አገሮቻቸውን በመሪነት ያገለገሉ አፍሪካውያን የትግል መሪዎች መስክረዋል።
የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንኩርማህ ‹‹ኢትዮጵያ ነፃ ከሆነች ሁላችንም አፍሪካውያን አንድ ቀን ነፃ እንደምንሆን አምናለሁ›› በማለት ነበር የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ትግል መጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረውና በአትዮጵያም ያላቸውን ሙሉ ተስፋ የተናገሩት።
የመጀመሪያው የጊኒ ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኮ ቱሬ ደግሞ ‹‹ … ኢትዮጵያውያን ታላቅ ሕዝቦች ናቸው። ጀግና አፍሪካውያን ናቸው። በጀግንነት ተዋግተው ነፃነታቸውን አስከብረዋል፤ ለመላው አፍሪካውያንም የነፃነትን መንገድ አሳይተዋል›› በማለት ለኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ለዓድዋ ድል አበርክቶዎች እውቅና ሰጥተዋል።
የፀረ-አፓርታይድ መሪውና የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪ በነበሩበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና እንደወሰዱ በታሪክ ተመዝግቧል። ‹‹ኢትዮጵያ ምንጊዜም በውስጤ ልዩ ቦታ አላት።
ወደ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ከመሄድ ይልቅ ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ የበለጠ ልዩ ስሜት ይሰጠኛል፤ አፍሪካዊ ወዳደረገኝ የማንነቴ ምንጭ እንደሄድኩ ይሰማኛል›› በማለት የተናገሩላት የዓድዋ ድል ባለቤቷ ኢትዮጵያ ለትግላቸው ያደረገችላቸው ድጋፍ ትርጉሙ ብዙ ነው። ምስክርነታቸውም ከዓድዋ ድል ታሪክ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
የማንዴላ ተተኪ ታቦ ምቩየልዋ ምቤኪም የዓድዋ ድል ለጥቁሮች፣ በተለይም ለአፍሪካውያን፣ የነፃነት ትግል ስለነበረው ፋይዳ ተናግረው አይጠግቡም። ‹‹የዓድዋ ድል ለትናንት ድሎቻችን ብቻም ሳይሆን ልናሳካቸው ላሰብናቸው አፍሪካዊ ዕቅዶቻችን ስኬት ታላቅ ስንቅ የሚሆነን አኩሪ ድል ነው›› በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ጃማይካዊው የፖለቲካ አክቲቪስትና የመብት ተሟጋች ማርክስ ጋርቬይ በንግግሩም ሆነ በጽሑፉ ላይ ሁሉ ‹‹በባርነት ተይዛችሁ በዘር አድልኦ በሽታ በተጠናወተው ኅብረተሰብ ውስጥ የምትኖሩ ጥቁር አፍሪካውያን በሙሉ ወደ አገራችሁ ወደ አፍሪካ፣ የነፃነት አገር ወደ ሆነችው አገራችሁ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ፊታችሁን ወደ ኢትዮጵያ መልሱ፤ ወደ ጥንት እርስታችሁ አፍሪካ ተመለሱ፤ ዘውዱን የደፋውን ጥቁር ንጉሥ ተመልከቱ፤ እርሱ አዳኛችን ነው›› ይል ነበር።
ሮበርት ኔስታ ማርሌይ (ቦብ ማርሌይ)ን ጨምሮ ስመጥር የኪነ-ጥበብ ሰዎች በልብሶቻቸውና በሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ላይ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ቀለማትን መጠቀማቸውና ከ30 በላይ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን አገራት ለሰንደቅ ዓላማዎቻቸው እነዚህኑ ቀለማት መምረጣቸው አጋጣሚ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዓድዋ ያስመዘገበችው ደማቅ ድልና አገሪቱና ድሏ የጭቁኖች መመኪያ በመሆናቸው ነው።
በአጠቃላይ የዓድዋ ድል ለጭቁን ሕዝቦች፣ በተለይም ለአፍሪካውያን፣ የነፃነት እንቅስቃሴዎች ሂደትና ስኬት ደማቅ አበርክቶ እንደነበረው ከአገራት መሪዎች፣ ከምሁራንና ከታዋቂ ሰዎች የተሰጡ ምስክርነቶች ያስረዳሉ። እነዚህ ስለዓድዋ ድል አስደማሚነትና ዘመን አይሽሬ አበርክቶዎች የተሰጡ ምስክርነቶች ኢትዮጵያ በዓለም የነፃነት ትግልና የጀግንነት ታሪክ የማይነቃነቅ ታላቅ የከፍታ ስፍራ እንዳላት የሚያረጋግጡ ዘመን ተሻጋሪ ማስረጃዎች ናቸው።
ዘለዓለማዊ ክብር ለዓድዋ ጀግኖች!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013