መርድ ክፍሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንበረ ስልጣኑን ከተቆናጠጡ ሶስት ዓመት ሊሞላቸው ነው። በእነዚህ ዓመታት ታዲያ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊነት በሄዱበት መድረክ አጉልተው ሲናገሩ ይደመጣል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ህዝብ በኩራት አንገቱን ቀና አድርጎና በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ እንዲንቀሳቀስ አበክረው ሲናገሩም ተደምጠዋል። በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው ንግግሮች ውስጥ ስለኢትዮጵያዊነት ከጠቀሱት የተወሰኑትን እንመልከት።
በበዓለ ሲመታቸው ወቅት የተናገሩት
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያና የዕሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ።
አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሃገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለሃገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። እንደገሀር ያለንን ሃብት አሟጠን ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም። መቆጨትም አለባችሁ።
ይሄንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ ሀገር አለችንና እውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሃገራችሁ መመለስና ሃገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን።
በውጭ ሃገራት ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩ በሃገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና ሃገራችንን በሙሉም መልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ
ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ብትሆንም ትፀንሳለች እንጂ አትወልድም፣ ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም፣ ማጎርመስ እንጂ ማጎልመስ አልሆነላትም። እንጀምራለን እንጂ አንጨርስም። ይህ ሾተላይ መለየት አለበት። ይህ አጨናጋፊ በሽታ ከውስጣችን ተለይቶ መውጣት አለበት። ይህ በሽታ ቂም ነው፣ ይህ በሽታ አልሸነፍም ባይነት ነው፣ ይህ በሽታ በቀል ነው፣ ይህ በሽታ መናቆር ነው፣ ይህ በሽታ የጅምላ ጥላቻ ነው፣ ይህ ሾተላይ ራሱን አደራጅቶ በመካከላችን ያለመደማመጥ፣ ያለመቻቻል፣ የባላንጣነት ግንብ ላለፉት 40 ዓመታት ሲሠራብን ቆይቷል።
ዛሬ ከታማኝ በየነ ጋር ስንተቃቀፍ የመጀመሪያውን መዶሻ ግንቡ ላይ አሳርፈናልና ይህን አጉዳይ፣ አጠልሽ ግንብ ጡብ ያላቀበለ፣ ብሎኬት ያላቀበለ፣ ሐርማታ ያላቀበለ፣ መክሰስና ከወንጀሉ ነፃ መሆን የሚችል አንድም በመካከላችን ስለሌለ ሁላችንም በርብርብ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት የገነባነውን ከፋፋይ የጥላቻ ግንብ ዛሬ ለማፍረስ ቃል እንግባ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረብ ኢምሬት
ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ በእምነት አስተማሪነት፣ በአገር መሪነት፣ በስነጥበብና በንግድ ሰፊ ቦታዎችን ይዘው መኖራቸው ይታወቃል። መሬቶቻችን ሲቆፈሩ የእኛ ቅርሶች በመካከለኛው ምስራቅ እና የመካከለኛው ምስራቅ ቅርሶች ደግሞ በእኛ ከርሰ ምድር ውስጥ ይገኛሉ። የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እንዲህ ከማደጋቸው በፊት ለስራ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዱ ነበር።
ዛሬም በየመንና በሶሪያ ባለው አሰቃቂ ጦርነት ዜጎቻቸው ሲበተኑ አገራችን ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ እየተቀበለቻቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከሶማሊያና ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ የጎረቤት ወገኖቻችን እናስጠልላለን።
በተለያዩ አገራት ተሰዳጅ ኢትዮጵያውያን ብንመስልም ታሪኮች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ሰጪም፣ ተሰዳጅ ብቻ ሳትሆን ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ የደግ ህዝቦች አገር መሆንዋ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ጊዜ ኃላፊ መሆኑን በመረዳት ከአንገታችሁ ቀና ብላችሁ ሂዱ። ዛሬም በኢትዮጵያዊነታችሁ ኩሩ። እመኑኝ ነገም እናንተም በቤታችሁና በድርጅቶቻችሁ ሌሎችን ቀጥራችሁ የምታሰሩ ትሆናላችው።
በዚህ ዘመን የአገራት ሀያልነት መወዳደሪያው እንደ ጥንቱ ዘመን በወታደራዊ ሀይል አይደለም። የመንግስታት ገናናነት ማሳያ የዜጎች የኑሮ ምቾት ነው። የቁስ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ብልፅግና ዛሬ ጭንቅላታቸውን ተጠቅመው የሀሳብ የበላይነት የተቆናጠጡ ህዝቦች የተፈጥሮ ሀብት ባይኖራቸውም በአዕምሮ መጥቀው ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌግራም ገፃቸው ካሰፈሩት
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት። ሐሳባችን፣ ሥራችንና ንግግራችን ሁሉ ታላቅነቷን የሚመጥን መሆን ቢችል መልካም ነው። ካልሆነ በኢትዮጵያ ሚዛን ተመዝነን እንቀላለን። ኢትዮጵያ መዝና ታላቅነቱን የመሰከረችለትን ማንም አያቀለውም። ኢትዮጵያ ያቀለለችውንም ማንም አያከብደውም።
ታሪካችን ይሄንን ይመሰክራል፤ ዛሬም እየመሰከረ ነው። ኢትዮጵያ ታላቅ ናት ስንል ከዜጎቿም፣ ከመሪዎቿም፤ ታላቅ ገድል ፈጽመናል ከሚሉ ሰዎች ሁሉ በላይ ታላቅ ናት ማለታችን ነው። በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ልሂቃን፣ የትኛውንም የተቀደሰ አጀንዳ አንግበው የተመሠረቱ ድርጅቶች፣ ሐሳብና ርዕዮተ ዓለሞች ሁሉም ከኢትዮጵያ በታች ናቸው።
ኢትዮጵያ በሺዎች ዘመናት ሠርተውና ተጋድለው ያለፉ መሪዎችና ዜጎች ድምር ውጤት ናት። ኢትዮጵያ – ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሰፍተውና ሞልተው የሚኖሩ፣ የሚሠሩና የሚጋደሉ ልዩ ልዩ ሕዝቦች ውጤት ናት። ታሪክ ያልመዘገባቸው፣ የታሪክ ድርሳናት የማያውቋቸው እልፍ አእላፍ ታሪክ ሠሪዎች በደምና በአጥንት፣ በላብና በወዝ በጽኑዕ መሠረት ላይ የገነቧት ሀገር ናት።
ግለሰቦች ለኢትዮጵያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤ የኢትዮጵያ ህልውና ግን በግለሰቦች አይወሰንም። ግለሰቦች ለክብሯ ሲሉ ደማቸውን ሊያፈስሱ፣ አጥንታቸውን ሊከሰክሱ፣ መስዕዋት ሆነው ሊያስቀጥሏት ይወስኑ ይሆናል፤ ነገር ግን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው የቤት እንስሳ፣ ለግለሰቦች ሲባል ሀገር እንድትሞት ወይም እንድትኖር ለድርድር አትቀርብም።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ታላላቅ ጀግኖች ነበሯት። በየጦር ሜዳው ታላላቅ ጀብዱ የፈጸሙ አርበኞች፣ በየእውቀት መስኩ አርቀውና አስፍተው የተመለከቱ አሰላሳዮች፣ በየውድድር ሜዳው አይበገሬነታቸውን ያስመሰከሩ ተፋላሚዎች፣ በሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አንቱታን ያተረፉ መሪዎች ከማህጸኗ በቅለዋል፤ ወደፊትም ይበቅላሉ።
ኢትዮጵያ እኛን እንጂ፣ እኛ ኢትዮጵያን አልፈጠርናትም። እኛ ከመፈጠራችን በፊት ኖራለች፤ ከእኛ መሐል አንዳችን ስለጎደልን አትጠፋም። እኛ በዘመናት መካከል ከመጡ አርበኞች፣ አሰላሳዮች፣ ተፋላሚዎችና መሪዎች እንደ አንዱ ነን። በተሰጠን እድሜ የየበኩላችንን ጡብ አስቀምጠን እንሄዳለን።
መጪውም የአቅሙን አክሎበት ይቀጥላል። በየትውልዱ አያሌ ዜጎችን እያፈራች መገስገሷን ትቀጥላለች። የትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” እያደረጋት ወደፊት ትጓዛለች። የእኛ ሚና ቀደምቶቻችን የጀመሩትን መልካም ተግባር አጎልብተንና አሳምረን ለመጪው ትውልድ ማቀበል ነው።
ከእኛ በኋላ የሚመጣውም ቅብብሎሹን ቀጥሎ፣ እኛ የጀመርነውን እያጎለበተ ያስቀጥላል። የሕዳሴ ግድብን ብንወስድ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ወሳኝ ፕሮጀክት አንዱ ነው። ያስጀመሩት መሪዎች ቢያልፉም ሕዝብና መንግሥት እየገነቡት ይገኛል።
ሌሎችም የተጀመሩ የመንገድ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመስኖ ግድብ፣ የኃይል ፕሮጀክቶችን ሕዝብና መንግሥት ካለፉት ተረክቦ አስቀጥሏቸዋል። ማን ጀመረው ከሚል ይልቅ ለኢትዮጵያ ምን ጥቅም ያስገኛል በሚል እየተፈተሸ መልካም የሆነው ሁሉ ጎልብቶ ይሻገራል፤ መልካም ሆኖ ያልተገኘውም ማንም ቢሠራው ጊዜ ራሱ ጥሎት ያልፋል።
የትኛውም ሀገር ከስልጣኔ ማማ ላይ የተቆናጠጠው በዚህ መልኩ ነው፤ ሌላ ተዓምር የለም። ሆን ብለን በክፋት ጥሩ ጥሩውን ብንደብቀው በጊዜ ሂደት መገለጡ አይቀርም፤ በተቃራኒው እኛ እስካለን በሚል ያገዘፍነው ጥቅም ሲታጣበት ጊዜውን ጠብቆ ይጣላል። ኢትዮጵያን ስንገነባ ይሄንን ሀቅ መገንዘብ ይገባናል።
መሪነት በአንድ በኩል ኃላፊነት ለመውሰድ የመቻል፣ በሌላ በኩል በፖለቲካ ትግል ውስጥ የማለፍ፣ አለፍ ሲልም የዕድል ጉዳይ ነው። ሌሎችም ዕድሉ ሲገጥማቸው፣ የፖለቲካው ሂደት ለዚያ ሲያደርሳቸውና ኃላፊነቱን ለመውሰድ ፍላጎትና ቆራጥነት ሲኖራቸው መሪ የማይሆኑበት ምንም ምክንያት የለም።
እየመሠረትነው ያለነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሪነት የፖለቲካ ሂደት ውጤት እንዲሆን የሚያደርግ ነው። የሀገሪቱ ሕግ የሚጠይቀውን ያሟላ፤ በምርጫ ያሸነፈና በፖለቲካ ሥርዓታችን ፍኖት የተጓዘ ኢትዮጵያዊ ሁሉ መሪ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ የሚጠርግ ነው። መሪነት ሥልጣን ሳይሆን ኃላፊነት፤ ገዥነት ሳይሆን አገልጋይነት፤ ድሎት ሳይሆን መስዋዕትነት ነው።
መሪ ከብዙ ኢትዮጵያውያን መካከል ሕግ እና የፖለቲካ ሥርዓቱ ዕድሉን የሰጠው አንድ ወሳኝ ሰው ነው። መሪዎችን ከዚህ በላይ አድርጎ መመልከት መሪዎችንም ኢትዮጵያንም ይጎዳል። ለመሪዎች ማሰብ፣ ለመሪዎች መጨነቅም መልካምና ተገቢ ነገር ነው። መሪዎችን ከኢትዮጵያ በላይ አድርጎ መመልከት ግን ስሕተት ነው። ኢትዮጵያ ወደረኞቿን በብዙ ግንባሮች ድል ነስታለች።
ለግላዊና ድርጅታዊ ጥቅማቸው ሲሉ ሊያጠፏት የተነሱት ሁሉም አሁን ተረት ሆነዋል። ከታሪክ የማይማሩ ሰዎች ዛሬም ሆነ ወደፊት መነሳታቸው አይቀርም፤ ዳሩ ግን እንደቀደሙት እብሪተኞች ተረስተው ይቀራሉ። በሚታየውም በማይታየውም ዘመቻ ሀገራችን ድል እያደረገቻቸው ትቀጥላለች። ያኔ ጠላቶቿ የሚቀራቸው ግንባር የውሸት ግንባር ብቻ ይሆናል። በእርግጥ ዘመኑም በተወሰነ ሳይረዳቸው አልቀረም።
ዐይናቸው እያየ ልባቸው በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የሚዋልልባቸው ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ጥንት ‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው› ይባል ነበር። አሁን ‹ጦር ከፈታው ውሸት የፈታው› ሆኗል። የውሸት ፋብሪካ ከፍተው፣ ውሸት እያመረቱና ውሸት እያሸጉ፣ በጅምላና በችርቻሮ ውሸት ሲያከፋፍሉ የሚውሉ የኢትዮጵያ የጎን ውጋቶች በዝተዋል። ዓላማቸው በሌሎች ግንባሮች ያጡትን ድል በውሸት ግንባር ለማግኘት፤ እግረ መንገዳቸውንም ትርፍራፊ ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው።
ለኢትዮጵያ መሞት የማይገኝ ዕድል መሆኑ እንደማይገባቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ለመግደል መነሣት የመጨረሻው ርግማን እንደሆነ አያውቁም። ሞት እንደሆን የማይቀር የሰው ልጅ እዳ ነው፤ ከሆነ አይቀር ለታላቋ ሀገር ለኢትዮጵያ ቢከፈል ትልቅ ክብር ነው። ኢትዮጵያ የተገነባችው በኢትዮጵያውያን ሥራ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን መሥዋዕትነትም ጭምር ነው።
የሐሰት አበጋዞች በሕይወት ያሉትን ገድለው የሞቱትን ሲያኖሩ ከርመዋል። ነገም አመል ነውና መቀጠላቸው አይቀርም። ኢትዮጵያውያን ግን የሚያዋጣን ለእውነት ስንል መኖር፣ በእውነት መንገድ መመላለስ እና እኛው ራሳችን እውነተኛ ሆነን መቆየት ነው።
የሐሰት ፋብሪካ በጅምላና በችርቻሮ የሚያቀርብልንን የውሸት ፕሮፓጋንዳ በሌለን ጊዜና ገንዘብ እየሸመትን፣ ስንወዛገብ በከንቱ የምንውልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። እንደ ሀገር ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን። መፈታት የሚገባቸው ቋጠሮዎች፣ መደፈን ያለባቸው ቀዳዳዎች፣ መሞላት የሚገባቸው ጉድጓዶች፣ መጠገን የሚገባቸው ድልድዮች፣ መገንባት የሚገባቸው ሥርዓቶች ተቆጥረው አያልቁም።
ያለንን ውድ ጊዜና ሀብት ኢትዮጵያን ለመለወጥ፣ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ፣ ኢትዮጵያን ለማስከበር እና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ብናውለው ይበጃል። ከዚህ የተሻለ ገንዘብና ጊዜያችንን ሊወስድ የሚገባው ምንም ጉዳይ የለንም።
የኢትዮጵያን ወንዞች ለማልማት እኛው ራሳችን የመስኖ ቦዮችን እንቅደድ እንጂ በተቀደደልን የወሬ ቦይ አንፍሰስ። ታላቋን ሀገር በታላላቅ ሐሳቦች ይበልጥ እናተልቃት እንጂ፤ በሐሳብ አንሰን፣ በወሬ ኮስሰን ሀገራችንን አናኮስሳት። ኢትዮጵያ መግዘፍ እንጂ አንሳ መገኘት አይመጥናትም። ለዚያም ሁላችንም በየተሠማራንበት ዘርፍ በዋዛ ፈዛዛ እንቁ ጊዜያችን ማባከኑን ትተን የሰለጠነችና ለሌሎች አርዓያ መሆን የምትችል ኢትዮጵያን ገንብተን ለልጅ ልጆቻችን እናውርስ!!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013