ጋሻው ጫኔ
የዓድዋ ተራሮች አፍ አውጥተው መነጋገር ጀምረዋል፡፡ መድፎች አጓሩ፣ መትረየሶች አሽካኩ፣ ጥይት ዘነበ፣ እሣት ወረደ፣ ጎራዴ ተመዘዘ፣ ጦር ተሠበቀ፣ እግረኛውም ፈረሰኛውም ወደጠላት ምሽግ ዘልቆ ገባ። ምድር ቀውጢ ሆነች፡፡ ወራሪው ጣሊያን ኪሣራ ከውርደት ጋር ተከናነበ፡፡ ኢትዮጵያ ክብርና ኩራት ተጎናፀፈች። አንፀባራቂ ድል ተቀዳጀች። ዘመን ተሻጋሪ ትውልድ አኩሪ ታላቅ ታሪክ ተጻፈ፡፡
አፄው ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት ብለው አዋጅ አስነገሩ። እንዲህም አሉ። “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ ሀገር አስፋፍቶ አኑሮኛል:: እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ:: እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም:: ደግሞ እግዚአብሔር አሣፍሮኝ አያውቅም:: ከእንግዲህም ያሣፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም:: አሁንም ሀገር የሚያጠፋና ኃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር:: አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሣልፌ አልሰጠውም:: ያገሬ ሰው እስካሁን አላስቀየምከኝም:: ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ:: ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ ፣ ለኃይማኖትህ ስትል በሐዘን እርዳኝ:: ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ:: አልተውህም:: ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም:: ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ::”
መላው ኢትዮጵያውያን በብርሃን ፍጥነት ያለአንዳች ልዩነት ለሀገሩ፤ ስለ ሀገሩ የያዘውን ይዞ፤ ባገኘው ነገር ሁሉ ዘመናዊውን የጣሊያን ጦር ሠራዊት ለመፋለም “ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ፤ ለአንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ!!” ማለት ጀመረ። እዚህም እዚያም ቀረርቶው፣ ሽለላው፣ ጃሎታው፣ መገናው ወኔ ቀስቃሹ ግጥም እንደ ክረምት ዝናብ በየጎራው፣ በየወንዙ፣ በየሸንተረሩ ይዘንቡ ጀመር። “እልም ካለው ጫካ እልም ካለው ዱር ሲያንጎራጉር ያድራል ከመውዜሩ ጋር!” ይል ገባ — የአበውና የእመው ጦር። “የማንን ሀገር ማን ይደፍራታል፤ የማንን መሬት ማን ይረግጣታል፣ አምበሣው ልጇ ያስከብራታል” እያለ በቁጭት በእልህ በማንደፍሮኝ የተንተከተከ የጋለ ወኔ ለማይቀር ሞት እየተባለ ይመሽ፤ ይነጋ ጀመር!!
አፄ ምኒልክ ውቅያኖስ ተሻግሮ፣ ድንበር ሠብሮ የገባን ወራሪ ጠላት ለመደምሰስ የክተት ጥሪ አውጀዋል። አዋጁም የንጉሡ ሣይሆን ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሀገራዊ ጥሪ ነውና! ከንጉሡ የተወዳጀውም ሆነ የተኳረፈው ሀገሩን ከጠላት ወረራ ሊታደግ ያረሰውን ሳይዘራ፤ የዘራውን ሳይሰበስብ ስንቁን ቋጥሮ በቀጠሮው ቦታ ወረኢሉ ላይ ከተመ። ጀግኖች አባቶቻችን ጎራዴ፣ ጋሻና ጦር ይዘው በሀገር ፍቅር፣ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት የጋመ ሥሜት ውስጥ ሆነው ተሠልፈዋል፡፡ ወራሪው ጠላት መድፍ፣ መትረየስ፣ ቦምብና የተለያዩ ቀላልና ከባድ መሣሪያዎችን ታጥቋል።
ሴት ወንድ፣ አራሽ ቀዳሽ፣ ተኳሽ፣ እረኛና የቤት እንስሳት ሣይቀሩ ሁሉም ወደ ዓድዋ አቀኑ። የመጨረሻው መጀመሪያ፤ የፍፃሜው ክብሪት ከሚለኮስበት አምባ ኢትዮጵያውያን ከተሙ — ዓድዋ። አዎ! በዚያች ሰዓት፣ ከዚያች ሥፍራ ተገናኝተው ፋሽስት ወራሪውን “ና ሞክረኛ!” ለማለት ተመሙ — አንድ መቶ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን። በራስ መንገሻ፣ በራስ አሉላና በዋግሹም ጓንጉል የሚመራው የኢትዮዽያ አርበኛ የጄኔራል ዳቦር ሜዳን ወራሪ ጦር ለመፋለም በአንድ የጦር ግንባር ተሠለፉ። በራስ መኮንንና በራስ ወሌ የሚመራው አርበኛ ጦር ደግሞ የጄኔራል አርሞንዴን ግንባር እንዲገጥሙ ከንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ተሠጣቸው። በፊታውራሪ ገበየሁና በራስ ዳምጠው የሚመራው የኢትዮጵያ አርበኛ ደግሞ አልቤርቶን ገጠሙት። አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ደግሞ በደጀንነትና ልዩ ልዩ ተግባራትን በመከወን ፍልሚያውን እየተከታተሉ፣ እየመሩ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲሰጡ የጦር ግንባር አሠላለፍ ዕቅድ ተግባራዊ ተደረገ። ሁሉም ለጠላት አጨዳ ወቅቶ ሊከምረው በየፊናው ተሠማራ – የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም፡፡
ኢትዮጵያውያን የተሰለፉት “ቆመህ ጠብቀኝ” በተሠኘ ጠበንጃ ብቻ በመሆኑ ንቀት አድሮበታል — ወራሪው ጣሊያን። ይሁን እንጂ እየፈላ የሚንተከተከው የፈረስ ጋላቢዎቹ የጥቁር አምበሶቹ ወኔ፣ ልባምነትና ፍጹም ጀግንነት ባለ ድል እንደሚያደርጋቸው አልተረዳም፡፡ ፊት ለፊት አፈሙዙን ወደ ኢትዮጵያውያን ደግኖ የሚንፈቀፈቀውን የመትረየስ ጥይት በደረቱ አብርዶ ሲወድቅ ሌላው ጀግና ኢትዮጵያዊ አንዱ በአንዱ ላይ እየተነባበረ ተንደርድሮ ሄዶ በጎራዴ የጣሊያንን ወታደር አንገት ሲቀላው ለወራሪው ታላቅ የሞራል ውድቀትና ሽንፈትን አከናነበ፡፡ ሠላቶው “ማማ ሚያ” (እናቴ) ማለት ነው ቢልም ወዴት…ወዴት ማን ሠምቶት…በሀገርና በእናት ድርድር የለም”ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ” እየመተረው፤ እየቀነጠሰው፤ እያጋደመው በጠላቱ ሬሣ ላይ እየተረማመደ ገሠገሠ፡፡ “ወደፊት ኧረ ወደፊት” አሉ ጥቁር አምበሶቹ፡፡ “ሠላቶ ገዳይ…ባንዳ ገዳይ…በዓድዋ ላይ!!”
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሆነው ተቃራኒው ነበር። ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ኃይል ቁርስና ምሣ ለማድረግ ወታደራዊውን ስሌት ቀምረው ይጠዘጥዙት ያዙ። ብዙም ሣይዘገይ አልቤርቶኒ ቁርስ ሆነ። ሽንፈትን ተጎንጭቶ ሠራዊቱ እንደ ገና ዳቦ ተፈረካክሶ የተሠለፈበትን የውጊያ ግንባር ለቀቀ፡፡ እግሬ አውጭኝ ብሎ ተፈተለከ። ብዙም አልቆየም — የምሣ ሰዓት እየደረሰ ነው። ተራው የጄኔራል አርሞንዴ ነበር። በጄኔራል አርሞንዴ የሚመራውን ዘመናዊ ጦር፤ ጎራዴ፣ ጦር፣ ጋሻ አካፋና መጥረቢያ የታጠቁት ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አርበኞች እንዳልነበረ አደረጉት። እዚህ ላይ አንድ ፍልሚያውን በብዕሩ ያስቀረ አውሮፓዊ ፀሐፊ ያሠፈረውን በእማኝነት ልጥቀስ — “…የኢትዮጵያ ሠራዊት ከቃልም በላይ ኃያል ነው። ጣሊያኖች ሽሽት ጠናባቸው…” ብሏል።
የሩቁን በውጅግራ እየጣለ፣ የቅርቡን በጎራዴ እየቀላ መገሥገሱን ቀጠለ — የኢትዮጵያ ሠራዊት። ሁሉም በየፊናውና በየግንባሩ እየተፋለመ ነው። የአልበርቶኒን ጦር ለቁርስ፣ የአርሞንዴን ደግሞ ለምሣው የሠለቀጠው የኢትዮጵያ ፋኖ፤ እግሬ አውጪኝ የሚለውን ቀሪ የጠላት ኃይል እየተከታተለ ይመትረው ይለቅመው ጀመር። ተራውን እየተጠባበቀ የቆየው ጄኔራል ዳቦር ሜዳም እምጥ ይግባ ስምጥ ጨነቀው። በመጨረሻም ደም አስክሮት፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እግሩ ወደወሰደው ፈረጠጠ። ግና ከኢትዮጵያውያን እጅ ለማምለጥ ከቶውንም አልቻለም። አይሞከርምም፡፡ ማን ለቆት? በዚህ ሁኔታ ለእውነት የተሠለፉት የያኔዎቹ እመውና አበው ከንቱ ሕልመኛውን የጣሊያን ጦር ከእኩለ ቀን በፊት ወደ “ነበርነት” ዓለም ቀየሩት። ጦርነቱ በግማሽ ቀን ውሎ ተገባደደ – የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም።
ውጫሌ በያኔው በወሎ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ሥር የምትገኝ፤ የአምባሰል ሠንሠለታማ ተራራ ወገብ ላይ የተቆረቆረች ትንሽዬ ከተማ ነች። የስምምነቱ 17ኛ አንቀፅ የአማርኛና የጣሊያን ትርጓሜው ታዲያ ለየቅል ሆኖ ብቅ አለ። ጣሊያን ስምምነቱን ለራሷ በሚመቻት መልክ ተርጉማ ኢትዮጵያን በማታለል ለተለያዩ የዓለም አገሮች ደብዳቤ ላከች።
በአንቀጽ 17 የሠፈረው ሐሳብ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የምታደርጋቸው ማንኛውም ግንኙነት በጣሊያን በኩል ብቻ እንደሆነ ይገልፃል። ታዲያ ይህን አሣሣች ቀጭን መልዕክት እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ አውስትሪያና ቤልጂየም አጨብጭበው ተቀበሉት። ኢትዮጵያ የጣሊያን ድርሻ መሆኗን አረጋገጡ። ሞስኮብ፣ ፈረንሣይና ቱርክ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርጉት ግንኙነትና ጥቅም ሲሉ ለመቀበል አቅማሙ።
ሁኔታው አፄ ምኒልክን አበሣጫቸው። በመታለላቸውም ተናደዱ፡፡ ጣሊያን የፈፀመችው ወንጀል መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ የጣሊያን ግዛት አለመሆኗን የሚገልጽ የእርምት ደብዳቤ እንዲጻፍ ለንጉሥ ኡምቤርቶ መልዕክት ላኩ። ዳሩ ግን ጣሊያን አውቃ የተኛች በመሆኗ የአፄ ምኒልክ መልዕክት ሊያስጨንቃት አልቻለም፤ ከመጤፍ ሣትቆጥረውም ቀረች። ጆሮ ዳባ ልበስ ያለችው ጣሊያን ነገረ ሥራ ያበሳጫቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሀገራቸውን ከወራሪው መታደግ እንዳለባቸው አመኑ። ሠራዊታቸው በአቅምና በሥነ ልቦና መዘጋጀቱን በመገንዘባቸው ለፍልሚያ ተዘጋጁ።
የያኔው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ በፍጥነት ሠራዊቱን በእጥፍ አሣድጎ መረብ ወንዝን ተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ ገሠገሠ። በርግጥ ከዚያ በፊትም ቢሆን ጣሊያን በበርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች ዘመናዊ ሠራዊቷን አሥፍራለች። አሁን እመውና አበው ባርነትን ከማይታገሱበት ደረጃ ደርሠዋል። ወሣኝ ለሆነው ታላቅ ፍልሚያ ተዘጋጁ። በእርግጥ ከዓድዋ በፊት ጦርነት አልነበረም ማለት አይደለም። ከዓድዋ በፊት በአምባላጌና በመቀሌ ውጊያዎች ተካሂደዋል። በጦርነቶቹ ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ያገኘውን ዓይነት ቦምብ በኢትዮዽያውያን ላይ የሚወረውረው የጣሊያን ወራሪ ጦር የግዛት ማስፋፋት ምኞቱን ተግባራዊ ለማድረግ መፍጨርጨሩን ተያያዘው። የፋሽስት ጣሊያን ጦር ዋና አዛዥና ናዛዥ የነበረው ጄኔራል ባራቴሪ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ተከፋፍለዋል የሚል የተሣሣተ ግምት ነበረው።
ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም ናኘ፤ ክብሯም ገነነ። በዚህም አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ዲፕሎማሲን በመምረጥ መወዳጀት ጀመሩ። እንደ ጀርመን፣ ቤልጂየምና ፈረንሣይን የመሣሣሉ አገሮችም ኤምባሴያቸውን በአዲስ አበባ ለመክፈት የቀደማቸው አልነበረም። እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን በምሥራቅ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ከያዟቸው አገሮች ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር ከኢትዮጵያ ጋር ለማካለል ስምምነት ተፈራረሙ። ኢትዮጵያ ከገዥዎች ጋር ድንበሯን ማስከበሯም ልዩ ታሪክ ሆኖ ተመዘገበ። አዳዲስ የሥልጣኔ ውጤቶችን እንደ ባቡር፣ ስልክ፣ መኪና የመሳሰሉትን የመጠቀም ዕድል አገኘች። ይህ ሁሉ የዓድዋ ድል ውጤት ነው።
ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካን ለመቀራመት በ1888 ዓ.ም በበርሊን ያካሄዱት ጉባዔ (የበርሊን ኮንፈረንስ) በመባል የሚታወቀው በአፍሪካ ቅኝ አገዛዝን አፀና። የዚህን ጉባዔ መንፈስ በተግባርና በአስተሳሰብ የታቃወመችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች።
የዓድዋ ድል በፈጠረው የነፃነት ትግል እንቅስቃሴ፤ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር በመጀመሪያ የተገላገለችው ጋና ነች። ጋና በ1959 ነፃ ወጣች። በዚያው ዓመትም ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረተች። ከ1950ዎቹ (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ነፃነታቸውን ያገኙ አገራት ቢኖሩም፤ በርካታ አገራት ነፃ የወጡት በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ነበር። ነፃነትን በመቀዳጀት የመጨረሻዎቹ ዚምባብዌና (በ1980) ደቡብ አፍሪካ (በ1994) ነበሩ። ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካም ሆነ ለዚምባብዌ ነፃነት አኩሪ ተጋድሎ አድርጋለች። በአጠቃላይ የፀረ – ቅኝ አገዛዝና የፀረ – አፓርታይድ ትግል መነሻ፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራሮች የተበሠረው አንፀባራቂ ድል ነው። የዓድዋው ድል የአፍሪካን የነፃነት ትግል መንፈስ ሲያቀጣጥል፤ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን በድንጋጤ አርበድብዷል። አንዳንዶች የአፍሪካን ታሪክ ለመረዳት የዓድዋ ድልን መረዳት ያስፈልጋል የሚሉትም ለዚህ ነው።
ጥቁር አፍሪካውያን የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ታሪክ (Pan-African History) ተደርጎ የሚቆጠረው የዓድዋ ድል በርካታ ስሜቶችን ይፈጥራል፡፡ በዚያ ተስፋፊነትና ወራሪነት እንደ ጀብድ ታይቶ የቅርምት አጀንዳ በገነገነበት ዘመን ፋሽስት ነጮች እንደምን የሽንፈት ፅዋን ተጎነጩ? የሚል ጥያቄ ቢነሣ አይገርምም፡፡ ስለዚህ የዓድዋ ድል መላው ጥቁር ሕዝብን በሐሴት ፀዳል እንዲፈካ አድርጓል፡፡ ነጮች በጥቁሮች ላይ ብቻ ሣይሆን፤ ጥቁሮችም በነጮች ላይ እንዴት የበላይ ሊሆኑ እንደቻሉ ድማሜ ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ምን ይህ ብቻ! የዚያ ትውልድ ድል የሚያስተላልፈው ቁም ነገር ምንድን ነው? የሚለው ሌላው መነሣት የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡
የዓድዋ ድል ከቃልነት የዘለለ ረቂቅ ትርጉም ያለው ሐቅ ነው። ስለሆነም የዓድዋን ድል ከጀግንነት፣ ጀግንነትንም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነጣጥሎ ማየት ይከብዳል። ኢትዮጵያዊነትና ጀግንነት ሁለት የማይለያዩ፤ እንደ ደምና ሥጋ የተዋሃዱ እውነታዎች ናቸው። ኢትዮጵያዊነትና ጀግንነት አይነጣጠሉምና!!
የዓድዋን ድል የድሎች ሁሉ ቁንጮ ብሎ መግለጽ ጥቁርን ጥቁር ወይም ነጭን ነጭ የማለትን ያህል ቀላል ነው። ይህ ሐቅ እንደ ኢትዮጵያዊው ግዮን (አባይ) ዝንተ – ዓለም ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ በከፍታ የሚኖር እውነታ ነው። ኢትዮጵያውያን እንዲህ የምንለው ድሉ ገዝፎ ውስጣችንን ስለደለለው አይደለም። በተግባር የተገለጠ እውነታ ስለሆነ ነው። ድሉ የገዘፈው የጥቁር ሕዝቦች ተምሣሌት በመሆኑ ብቻ ሣይሆን፤ የዓድዋ ገድለኞች ሰማይ ጠቀስ ተግባርና ኢትዮጵያዊነት የማይነጣጠሉ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው ነው።
እነ ቴዎዶር ቬስቴል፣ በርክሌይና ሪቻርድ ፓንክረስትን የመሳሰሉ እውቅ ምሁራንን ለዚህ እውነት በእማኝነት መጥራት ይቻላል። ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ካለም፤ ዓድዋንና የዓድዋን ጀግኖች ተጋድሎ አብጠርጥረው ስለሚያውቁት። ዓድዋ ቅኔ ነው፤ አዕላፍ ጥቁር ሕዝቦችን ለነፃነት ትግል ያነሣሣ ምትሃታዊ መልዕክት ነው። ያልተገመተ፣ ያልተጠበቀ ነጮቹ ሊያምኑትም ሆነ ሊቀበሉት ያልተቻላቸው፣ በእርግጥም ኃያልና ገናና ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል በወቅቱ በቅኝ ግዛት ሥር ሲማቅቁ ለነበሩ የካሪቢያን አገሮችና ድፍን አፍሪካን ለፀረ ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ (Pan-Africanism) በመቀሰቀስ ሚናው የላቀ ነበር። በመሆኑም የዓድዋ ድል የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ቋሚ ሐውልት ሆኖ ዝንተ ዓለም ይኖራል፡፡
እዚህ ላይ ቀደም ከተጠቀሱት ውስጥ የበርክሌይንን እማኝነት በጥቂቱ ላንሣ። የያኔዎቹ ዓርበኞች ጀግንነትና አልደፈር ባይነት ድንቅ ምትሃት የሆነበት ይህ ግለሰብ፤ የዓድዋን ጀግኖች በድፍረት ካሞካሹ ፀሐፊዎች መካከል አንዱ ነው። “ሃያ ሺህ ዘመናዊ ሠራዊት ያሠለፈው የጣሊያን መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር የሽንፈትን ጽዋ ተጎነጨ።…” ሲል ገልጾታል፡፡ ፀሐፊው በዚህ ብቻ አላበቃም። በማይነጥፈው ብዕሩ ፖለቲካና ታሪክ ማብቃቱን፤ በአፍሪካ ምድር አንድ ታላቅ ሕዝብ ብቅ ማለቱን ሐበሾች ከዘመነ ፍጥረት ጀምሮ ታላቅ ሕዝቦች መሆናቸውን እየጠቀሠ በስፋት ዘገበ። “የዓድዋ ድል የሁላችንም ምኞትና ኩራት ነው” ሲል ዓድዋንና የዓድዋ ጀግኖችን ገድል በብዕሩ አደመቀ፤ አወደሰ፤ አሞገሰ፡፡
ስለ ዓድዋ ገናናነት የተደነቀው በርክሌይ ብቻ አልነበረም። ድፍን ዓለም እንጂ!! ስለ ዓድዋ የሚዘክሩ በርካታ መጻሕፍት ተጽፈዋል። የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የሥነ – ማኅበረሰብ ልሂቃን፣ የጥበብ ወዳጆች ዓድዋን በተባ ብዕራቸው አሞካሽተዋል። ሆኖም ከድሉ ፋይዳ አንፃር ሲታይ የሚገባውን ያህል ተብሏል ማለት ግን አይቻልም። ድሉ ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያውያንና ለዘመናት በቅኝ ገዥዎች የባርነት ቀንበር ሥር ሲማቅቁ ለኖሩት ጥቁር ሕዝቦች ትርጉሙ የላቀ ነው። በአጠቃላይ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንጓዝ ካደረጉን ሀገራዊ ቅርሦች አንዱ ነው።
የዓድዋ ድል የተገዛ — አልገዛም፤ የተንበርከክ — አልንበረከክም ሙግትና ትንቅንቅ አውድ የወለደው የእኛነታችን መስታዎት ነው። አዎ! የተካሄደው ፍልሚያ ማንነታቸውን ላለማስደፍጠጥና ራሣቸውን ላለማጣት በቆረጡ ኢትዮጵያውያንና ባሕር አቋርጦ በመጣው ፋሽስት ጣሊያን መካከል ነበር። በዘመኑ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች በአፍሪካ ልዩ ሕዝቦች የሚያደርገንን ታላቅ ሥራ ከወኑ። ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነፃነታችንን አስከበሩ፡፡ ማንነትን ከመነጠቅ የበለጠ ቅጣት የለምና በዕድል ሣይሆን፤ በአኩሪ መስዋዕትነት የተገኘ ድል በመሆኑ ላቅ አድርገን ብናከብረው ተመፃደቁ የሚለን ከቶ ማን ይሆን? ኧረ ማንም!
ኮንትሮስኒ የተባለው ፀሐፊ የከተበው ምስክርነት ደግሞ እንዲህ ይነበባል፡፡ “…ሐበሾች ፍጹም ልበ ሙሉ ናቸው። ጀግንነታቸውን መካድ አይቻልም። በጎራዴ እና በሣንጃ ባለ መድፍ እና ባለ መትረየሱን የጣሊያን ሠራዊት ምርኮኛ አደረጉት…” ሲል በአግራሞትና በድማሜ ጽፏል። በትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜትና በአስደናቂ ጀግንነት አንድ በመሆን የተፋለመው የያኔው ትውልድ በቅንነትና በታማኝነት ተዋድቆ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ተስፋን ያጫረ ታላቅ ገድል አስመዘገበ። የድሎች ሁሉ የበላይ የሆነውን የዓድዋን ድል አበውና እመው ለሠንደቅ ዓላማቸው ክብር ሕያው መስዋዕትነት በመክፈል ከፍ…ከፍ አደረጉት። ኮርተው የኩራት መሠረት ሆኑን።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013 ዓ.ም