ዋ! …
ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ …
የስንኞቹ ባለቤት ብላቴን ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ናቸው።ታላቁ ባለቅኔ ለታሪካዊቷ ዓድዋ የጻፉት የግጥም መወድስ፣ የየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ውሎን በመገረም፣ በመደነቅ፣ ምናልባትም በመጨነቅ ያሳለፈችውን ዓድዋን፣ በተለይም ዓለምን ያስደነቀው የታላቁ የጥቁር ሕዝብ ድል ዋነኛ ምስክሮች የሆኑትን ተራሮቿን፣ በምናብ ያስቃኛል።
ውጊያው፣ ድሉና የተራሮቹ ምስክርነት
የዓድዋ ተራሮች የታላቁ ድል ዋነኛ ምስክሮች ናቸው።አዎ … ማርያም ሸዊቶ፣ እንዳ ኪዳነ ምሕረት፣ ሶሎዳ፣ ኤራራ … ተራራ ብቻ አይደሉም።ብዙ ሐዘን፣ ደስታ፣ ገድል … የተመለከቱና ምስጢሮችን የያዙ የዚያ አስደናቂ ውጊያና ድል ቋሚ ምስክሮች ናቸው።‹‹ማን ይናገር የነበረ፤ማን ያርዳ የቀበረ›› እንዲሉ፣ ከዓድዋ ተራሮች የበለጠ የውጊያውና የድሉ ምስክር ማን ሊሆን ይችላል?! አባ ጎራው በጀግንነት ተዋግተው ሲወድቁ፣ አባ ነፍሶ እንደ ተርብ እየተወረወሩ ጠላትን ሲያጋድሙ፣ አባ ሻንቆ ወራሪውን እግር በእግር እየተከተሉ ሲያባርሩት … የዓድዋ ተራሮች በወገኖቻቸው ጀግንነት ሲደነቁና ሲደሰቱ ነበር።እንደሰው አፍ አውጥተው መናገር ባይችሉ እንጂ ‹‹ዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፣ ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው›› ተብሎ የተገጠመው የእነርሱ ስሜት ሳይሆን ይቀራል?
ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ‹‹ልጆቼ ሆይ፣ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈፀምበት ቀን ነው፤ሂዱ ለአገራችሁና ለሃይማኖታችሁ ሙቱ›› ብለው ሲናገሩ ‹‹ፈጣሪ ሆይ፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ጠብቅ›› ብለው ፀልየው እንደሆነ መገመት የዋህ/ውሸታም ያሰኝ ይሆን?
አባ ጎራው ‹‹ከጀርባዬ ተመትቼ ከሞትኩ እንዳትቀብሩኝ፤ከፊት ለፊቴ ከተመታሁ ብቻ ቅበሩኝ›› ብለው ‹‹ስሸሽ ከሞትኩ ስጋዬን ለአሞራ›› ያሉበትን ፍፁም ጀግንነትና ቆራጥነት የተሞላበት ኑዛዜያቸውን ሰምተው በቆራጥነታቸው የተደነቁት እነዚህ ተራሮች፤ የአባ ጎራውን መውደቅ በተመለከቱ ጊዜ አዝነዋል።አባ ነፍሶ በአባ ጎራው ሞት ቢያዝኑም ምራቃቸውን ዋጥ፤ጥርሳቸውን ንክስ አድርገው ቦታቸውን ተረክበው የጠላትን ጦር በመድፍ ሲያጭዱት ባዩ ጊዜ ተራሮቹ ‹‹ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፣ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ›› ብለው ገጥመዋል።
የአባ ነጋን የጀግንነት ውጊያ ተመልክተው ‹‹ለእኛ አዲስ ሆነብን እንጂ የእርስዎ ጀግንነት’ማ በዶጋሊ፣ በኩፊት፣ በሰሀጢ፣ በጉንደትና በጉራዕ የታዬና የተመሰከረ ነው›› ብለው የተለመደውን ጀግንነታቸውን አወድሰዋል።የአባ ጎራውን መውደቅ ዐይተው የአባ መላን የአተኳኮስና የውጊያ ብልሃት ሲመለከቱ ሀብቴ የገቤ ተተኪ እንደሆኑ ተንብየዋል፤ትንቢታቸውም ተፈፅሟል።
የመነኮሳቱን ጸሎት፣ ግዝትና ማበረታቻ አሁንም በጽሞና ያዳምጡታል።የሊቀ መኳስ አባ ተምሳስ ‹‹ዉጋ! በርታ!›› የሚለው የነጋሪት ድምፃቸው ዛሬም ይታወሳቸዋል።የወራሪው ጦር ወታደሮች የኢትዮጵያውያንን ምት መቋቋም አቅቶት በዋሻ ውስጥ ሆኖ ‹‹እግዚኦ›› እያለ ያሰማውን ድምጽ በከፊል መጨነቅና በከፊል ተመስጦ አዳምጠውታል።
እነዚህ ተራሮች ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለኢጣሊያ ምርኮኞች ምግብና መጠጥ ሲያቀርቡ ተመልክተው ‹‹ጀግና ማለት እንደእኛ ነው! ለምርኮኛ ክብር የሚሰጥ!›› ብለው በወገናቸው ትህትናና ሩህሩህነት ተደንቀዋል፤ተገርመዋል።ንጉሰ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከጦር አዛዦቻቸው ጋ በመልዕክተኞቻቸው በኩል እየተገናኙ ሲመካከሩና ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ጦር ላነሰው ጦር ሲጨምሩ፤ሲያዋጉ ውለው ለዐይን ሲይዝ ወደ ድንኳናቸው ሲመለሱ አይተው ‹‹የዳኘው ጌታ! የኢትዮጵያ ልጅ!›› እያሉ አሞጋግሰዋቸዋል።
በግራ በኩል የነበረው ውጊያ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ቀጥሎ ስለነበር ኢትዮጵያውያን በጨለማው ሰዓት ከቀኑ ብሰው መዋጋታቸውን ተመልክተው የአድናቆታቸው መጠን ከከፍታቸው ሲበልጥባቸው ቅንጣትም ቅር አልተሰኙም።
ሽሽትንና ምርኮኛነትን እርም ያለና ‹‹ለጠላት እጄን አልሰጥም›› ብሎ ራሱን የሚሰዋ ወገን እንዳላቸው አስታውሰው የማቴዎስ አልቤርቶኒን መማረክ እንዲሁም የኦርስቴ ባራቴሪንና የጁሴፔ ኤሌናን ቅጥ ያጣ ሽሽት ሲመለከቱ ‹‹እግዚኦ ውርደት! እንደጓዶቻችሁ እንደቪቶሪዮ ዳቦርሚዳንና ጁሴፔ አሪሞንዲ ብትሞቱ ይሻላችሁ ነበር›› ብለው የወራሪውን ጦር አዛዦች መጨረሻ መመልከታቸውስ? ገፃቸው በወገንና በጠላት አስክሬን ሲሸፈን ሰቀቀኑ እረፍት ነስቷቸው ውሎ አድሯል።
ባለቅኔው
‹‹ በዳኘው ልብ በአባ መላው፣
በገበየሁ በአባ ጎራው፣
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው፣
በለው ብሎ በለው – በለው! ››
ብለው እንደፃፉት፣ ጀግኖቹ ‹‹በለው! … በለው! …›› ሲባባሉ የዓድዋ ተራሮች የጀግኖቹን የወኔ ድምፆች ሰምተዋል።ብርሃን ዘኢትዮጵያ ጦራቸውን ይዘው ተሰልፈው ‹‹በርታ! በለው! ድሉ የእኛ ነው›› ብለው ሲናገሩ እነዚያ ተራሮች ‹‹ጣይቱ ሆይ፣ እንኳንም የእኛ ሆኑ!›› ብለው ቀዝቃዛ አየር የሚነፍስበት የላይኛው አካላቸው ሳይቀር በኩራትና በደስታ ሞቅ ብሏል።
ምን ይህ ብቻ! ኢትዮጵያውያን ለክብራቸውና ለነፃነታቸው፤የወራሪው ተዋጊዎች ደግሞ ለአገራቸውና ለመንግሥታቸው ፍላጎት ሲሉ በላያቸው ላይ መውደቃቸውንና በጉያቸው ውስጥ መቀበራቸውን በሐዘን (ለወገናቸው) እና ‹‹እኛን አትዳፈሩ ብለን ነበር፤ይኸው እብሪታችሁ ሞታችሁን አፋጠነው፤እኛ በሰው ሞት የምንደሰት ባንሆንም በክብራችን ሲመጡብን ለወገን ሜዳ ለጠላት ባዳ እንሆናለን›› (ለወራሪው) የሚል ትርጉም ባላቸው ስሜቶች ታጅበው ተመልክተዋል።
የዓድዋ ተራሮች ስለውጊያውና ስለድሉ በቃላት የማይገለፁ ብዙ ታሪኮችንና ስሜቶችን አምቀው ይዘዋል።ለእነርሱ ብቻ ግልጽ፣ ለሌለው ግን ምስጢር የሆኑ በርካታ ታሪኮችና ስሜቶች!
የሎሬት ጸጋዬ ‹የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ፣
ታድማ በመዘንበልዋ፡፡
ዐፅምሽ በትንሳኤ ነፋስ፣
ደምሽ በነፃነት ሕዋስ፡፡
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ፣
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ፣
ብር ትር ሲል ጥሪዋ፣
ድው-እልም ሲል ጋሻዋ፣
ሲስተጋባ ከበሮዋ … ››
ገለፃዎች ከዓድዋ ተራሮች በስተቀር በቋሚነት የሚታወሱት በማን ነው?! የግጥሙን ስሜትስ ከእነርሱ የበለጠ ማን ያጣጥመዋል?! የሎሬቱ ስንኞች ዋናው ምስጢራቸው ፍንትው ብሎ የሚገለጠው ለተራሮቹ ነው።
ባለቅኔው ‹‹የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ፤የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ›› ብለው እንደተቀኙት ‹‹የኩሩ ትውልድ ቅርስና የኢትዮጵያዊነት ምስክር›› የሆነችው ዓድዋ፣ ቋሚ ቅርሶቿና ምስክሮቿ ታላቁን ድል የተመለከቱትና በድሉ ተገርመው እነርሱ ደግሞ ሌላውን የሚስገርሙት እነዚያ ተዓምረኛ ተራሮቿ ናቸው።
አዎ … እነዚያ የዓድዋ ተራሮች በመጨነቅ፣ በኩራት፣ በድንጋጤ፣ በሐዘን … ስሜቶች ውስጥ ሆነው ዓለም ዐይቶትና ሰምቶት የማያውቀውን የወገናቸውን የቆራጥነት፣ የጀግንነት፣ የውጊያና የድል ገድል ከመጀመሪያው እስከ ፍፃሜው ድረስ አይተዋል! የተመለከቱትን ሁሉ ይዘው ቆመዋል።
[እንዲያው ለመሆኑ ‹‹ዋ! … ያቺ ዓድዋ›› የተሰኘውን የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅንን አስደማሚ ግጥም ዓድዋ ተራሮች ላይ ወጥቶ አልያም ከተራሮቹ ግርጌ ላይ ሆኖ ድምጽን ዘለግ አድርጎ ማንበብ ምን ዓይነት ስሜት ይሰጥ ይሆን?! እነዚያ የድል ምስክሮችስ ምን ይሉ ይሆን? ምንስ ይሰማቸው ይሆን? ጋሽ ጸጋዬ ግጥሙን በየካቲት ወር 1964 ዓ.ም ዓድዋ ከተማ ውስጥ እንደፃፉት እንጂ በሚያስገመግመው ድምፃቸው ከተራሮቹ አናት ላይ ወጥተው አልያም ከግርጌያቸው ሆነው ስለማንበባቸው የነገሩን ነገር የለም።
ተራሮቹ ‹‹ተራራ›› ብቻ መስለውናል
ስለዓድዋ ድል ሲወራ የዓድዋ ተራሮች ፈፅሞ አይዘነጉም።ቦታዎቹ ካላቸው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንፃር ውጊያን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ተራሮቹን ቀድሞ መቆጣጠርና ይዞ መቆየት ትልቅ ጥቅም አለው።ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ይህንኑ የጦር ስልት ተግብረውታል፤ ቀድመው በጠላት ጦር የተያዙ ተራራዎችን በማስለቀቅ በጠላት ጦር ላይ ድርብ ድል ተጎናጽፈዋል።
ከላይ በጥቂቱ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የዓድዋ ተራሮች ብዙ ምስክርነቶችን በውስጣቸው ይዘዋል።ይሁን እንጂ እነዚህ ቋሚ ምስክሮች የያዙትን ታሪክ የሚዘክርና የሚያስታውስ መታሰቢያ አለመሰራቱ ከማስገረምም አልፎ ያሳፍራል።የካቲት 23 እየተጠበቀች በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የድሉን መታሰቢያ በተለመዱና አሰልቺ በሆኑ የሹማምንት ንግግሮች፣ ግጥሞችና መሰል መርሃ ግብሮች ‹‹ማክበር›› ልማድ ሆኖ ቆይቷል/ቀጥሏል።
ለግንባታው 10 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም በቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ አማካኝነት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዝግ የባንክ አካውንት ለመክፈት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመገኘቱንና ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነ ከመነገር በስተቀር የተሰማ ተጨባጭ ነገር የለም።
በዓድዋ እና አካባቢዋ ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ላይ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት በማካሄድ ዓድዋ እና አካባቢዋን ከ10 ተመራጭ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች መካከል አንዷ የማድረግ ዓላማ አለው ተብሎ የነበረውና ለታካዊቷ ከተማ አዲስ የምጣኔ ሀብት እድል ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ‹‹የዓድዋ ተራሮችና የዓድዋ ድል ቱሪዝም ፕሮጀክት›› ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በውል የሚታወቅ ነገር የለም።
ፕሮጀክቱ የሚከናወንበት አካባቢ ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ በተለይም ባለፉት አራት ወራት፣ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ መረጃ ለማግኘት እንኳ የሚመች አይደለም።የታላቁ ድል ምስክር የሆነችው ዓድዋ ብቻ ሳትሆን ጥንታውያኑ የሃ እና አክሱም ጭምር ተስፋ ጥለውበት የነበረው ይህ ፕሮጀክት የት ደርሶ ይሆን? ይህን ተስፋ ሰምተው የነበሩት የዓድዋ ተራሮችስ ምን ብለው ይሆን? ዓድዋን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረትስ የት ደረሰ?
ካሣ አያሌው ካሣ ‹‹ከዕለት ዝክር ወደ ቋሚ መዘክር መሸጋገር ያልቻለው ድል›› በሚለው ጽሑፉ፤ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህራንን ጥናት ጠቅሶ ‹‹ … ቀልብ ማራኪው የዓድዋ ሰንሰለታማ ስፍራ፤ ተፈጥሮ ካደለው ውበት በተጨማሪ የግዙፍ አፍሪካዊ ታሪክ ባለቤት ነው። እንደ አድማ በታኝ ፖሊስ እጅ ለእጅ ተያይዞ አድማሱን ከጥግ እስከጥግ የከበበው ማራኪው የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራራ፤ የካቲት 1888 ዓ.ም መላው የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ተምሳሌት የሆነውን አንፀባራቂ ጀብዱ አስተናግዷል … በጣም የተለየ መልክአ-ምድራዊ አቀማመጥ የተቸረው የዓድዋ ተራራ የጥቁር ህዝቦች የኩራት ቤታቸው እንደሆነ በቅኝ ገዢ ኃይላቱ ይታመናል። ማንም ቢመለከተው በተራራው የተለየ ተፈጥሯዊ ገፅታ ሳይደነቅ ማለፍ ይቸግረዋል። ይህ ተፈጥሮ የቸረችው ገፅታ ነዋሪው ስትራቴጂክ የሆነ የፀጥታና ደህንነት ክትትልና ውጊያ ለማድረግ የሚያስችለው ዕድል ፈጥሮለታል። በመሆኑም እራሱ የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራራ ኢትዮጵያ በጣልያን ወራሪ ላይ ድል ለመቀዳጀቷ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል … ›› ይላል።
እንዲህ ያለ አንፀባራቂ ድል የተመዘገበበት የዓድዋ ተራራ ዛሬም በድሉ ወቅት ከነበረው ገፅታው ብዙም እንዳልተቀየረ የካሣ ጽሑፍ ያብራራል። ‹‹ … ‹የጥቁር ህዝቦች ኩራት ቤት› የሚባል ስም የተቀዳጀ ግዙፍና ቀልብ ማራኪ ተራራ በእጇ የሚገኝ አገር የእጇን ወርቅ ከመዳብ ቆጥራዋለች። በታሪካዊ ሀብቷ መጠቀም ተስኗታል። በርካታ ጥናትና ምርምር ሊካሄድበት የሚችል ማዕከል የማቋቋም አቅም ያለው ዓድዋ፤ ትርጉም እንደሌለው ተቆጥሮ ተዘንግቷል። ቋሚ መዘክር ተገንብቶ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ የማስተላለፍ ሰፊ ዕድል በውስጡ አምቆ የያዘው ይህ ስፍራ፤ ዞር ብሎ ተመልካች እስካሁን አላገኘም። በጣም ብዙ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ሊፈልቁበት የሚቻለው የዓድዋ ድል ታሪክና የዓድዋ ቀልብ ማራኪ ሰንሰለታማ ተራራዎች የሚዳስሳቸው ብዕር አላገኙም። ሚዲያዎች በዓመት አንዴ የክብረ-በዓሉን ቀን አስመልክተው ‹‹ዓድዋ ዓድዋ…›› እያሉ ከመለፍለፍ በቀር ቋሚ አገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው በማስቻል ረገድ የተጫወቱት ሚና አናሳ ነው›› በማለት ካሣ የዓድዋ ተራሮች አስታዋሽ ማጣታቸውን አምርሮ ይተቻል።
ድምፃዊት እጂጋየሁ ሽባባው
‹‹ትናገር ዓድዋ ትመስክር አገሬ፣
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፡፡
በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን፣
ደግሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን፡፡
ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት … ››
ያለችው የተራሮቹን ስሜት (ቁጭትና ምስክርነት) ይመስላል።
ድሉ ትውልድ ተሻጋሪ ሆኖ የሚዘልቅበት ቋሚ ቅርስ ሊገነባለት ሲገባ፤ እስካሁን ድረስም ለዚህ ዕድል ሳይበቃ ቀርቷል። ያን ሁሉ ገድል የተመለከቱት ተራሮች ዛሬም ድረስ አስታዋሽ በማጣታቸው ትውልዱን በትዝብት (ኧረ እንዲያውም በንቀት) እየተመለከቱት ነው።‹‹ያለፈ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና መነሻቸውን የማውቁ ሰዎች ስር የሌለው ዛፍ እንደማለት ናቸው›› የሚለውን የማርከስ ጋርቬይ ሃሳብ እና ‹‹ያለፈ ታሪኩን እየዘነጋና እያጠፋ የሚሄድ ኅብረተሰብ፤ ከሌላው ብቻ ሳይሆን ከራስ ማንነቱ ተለያይቶ ይቀራል›› ሲል ሆብስ ባውን የተናገረውን ንግግር ተራሮቹ ለዚህ ትውልድ ደጋግመው እየነገሩት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013 ዓ.ም