መርድ ክፍሉ
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ብዙ ታሪክ አለው። ኢትዮጵያዊያን ነጻነታቸውን ያወጁበት እና ለጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን ድል ያስመዘገቡበት ዕለት ነው። የዚህ ታሪክ መነሻ ታዲያ ይህ ነበር። ጊዜው አውሮፓውያኑ አህጉረ አፍሪካን ለመግዛት በእጅጉ የሚመኙበት፣ያሻቸውን ለማድረግም የሚቋምጡበት ነበር።
በኢትዮጵያ እና በጣልያን መካከል ግንቦት ወር 1881 ዓ.ም አንድ ስምምነት ይፈረማል። ይህም ሃያ አንቀጾችን የያዘ እና ሁለቱ ሀገራት ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር የፈረሙት ስምምነት ነበር።
ስምምነቱ ታዲያ የውጫሌ ውል ስምምነት ይባላል። ይህ ስምምነትም ለሁለቱ ሀገራት በሚያመች መልኩ በአማርኛ እና በጣሊያንኛ ቋንቋ ተፅፎ የተዘጋጀም ነበር። የታሪኩ መነሻ የሁሉ ነገር መጠንሸሻ ከዚህ ጀመረ። የጣሊያን መንግስት በውጫሌው ስምምነት በኩል ኢትዮጵያን እንደፈለገ ለማድረግም ተመኘ።
በስምምነቱ አንቀጽ 17 ላይ በጣሊያንኛ ትርጉም የተቀመጠው ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ለሚኖራት ጉዳይ ሁሉ የጣሊያን መንግስት አጋዥነት መቀበሏን እንደተስማማች ተደርጎ ነበር የተጻፈው።
በአማርኛ የተጻፈው ደግሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ለሚኖራት ጉዳይ የጣሊያንን መንግስት የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባት የሚገልፅ ነበር። የዚህ ትርጉም ታዲያ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ኢትዮጵያ በተጨባጭ የጣሊያን ረዳትነትን መቀበል እንደምትፈልግ የሚያሳይ ነበር። የዚህን ትርጉም ስህተት የተረዱት ቀዳማዊ አጼ ምኒልክ ስምምነቱን አለመቀበላቸውንም በይፋ ለአውሮፖ ሃያላን አስታወቁ።
ትርጓሜውን በማሳሳት ሆን ብላ የፈጸመችው ጣሊያንም ወደ ኢትዮጵያ ጦሯን ማስገባት ጀመረች። ጦሯንም በኢትዮጵያ አራቱ አቅጣጫዎች 20 ሺህ ወታደሮችን አሰማራች። በኢትዮጵያ በኩልም በአፄ ምኒልክ መሪነት የክተት አዋጅ ታወጀ ህዝቡም ተነሳ። በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ ለጥቁሮች ነጻነት የሆነ ዓለምን ያስደነቀ ዜና ተሰማ።
ኢትዮጵያ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ወራሪውን ጣሊያንን ድል በማድረግ አኩሪ ታሪክ አስመዘገበች። ዛሬ 125ኛው የዓድዋ ድል በዓል እየተከበረ ይገኛል። በዚህም በዓድዋ ጦርነት ወቅት በጀግንነት የተሰውና ዳር ድንበር ያስጠበቁ የጦር አበጋዞችን እናስታውሳለን።
ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራ)
የንጉሰ ነገስቱ የመሀል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ ከጣልያኖች ጋር በተደረገው በሁሉም ጦርነት የተመሰከረላቸው ጀግና ነበሩ። የአምባላጌውን ምሽግ በመስበር በጣሊያን ላይ የመጀመሪያውን የድል ደውል ያሰሙት እና ዋናው የድሉ ባለቤት እሳቸው ነበሩ። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የዓድዋ ድል ጉልህ ድርሻ አለው። በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ። የዓድዋ ጦርነት የተጀመረው በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከማለዳው ነበር።
ውጊያው ከጠዋቱ 11፡30 ላይ በአራት ጄኔራሎች የሚመራው የጠላት ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ ፣ በዋግሹም ጓንጉል ፣ በራስ ሚካኤል እና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ። ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት የገጠሙት በእንዳ ኪዳነ ምህረት በኩል የመጣውን እና በጄኔራል አልበርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ነበር። በጦርነቱ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሰራዊቶቻቸው በመለየት ጎራዴያቸውን መዘው በዋናው የትግል አውድማ፣ በተፋፋመ እና በቀለጠው ውጊያ ላይ ተወርውረው ገቡ።
ዘለው እንደገቡም ከጀግናው ጓደኛቸው ከቀኝ አዝማች ታፈሰ ጋር እየፎከሩ የጠላትን አንገት በጎራዴ ሲቆርጡ እና ሲገነድሱ ቆይተው ከርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ። ሌሎችም አዝማቾች እና መኮንኖች እንዲሁም ተራ ተዋጊዎች ሞተዋል። ዓድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አጽማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወሰደ።
በቃል ኪዳናቸው መሠረት ከሰባት ዓመት በኋላም አፅሙ በትውልድ አካባቢያቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አረፈ። ከዓድዋ ድል በኋላ በጃንሜዳ የጦር አበጋዞች በፈረስ ሲያልፉ የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት አፄ ምኒልክ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱም ይነገራል። ምንጭ፡- ተክለጻዲቅ መኩሪያ እና ሌሎችም
ራስ አሉላ አባነጋ
ራስ አሉላ የተወለዱት በ1840 ዓ.ም ተምቤን ውስጥ ዙቅሊ ሚካኤል በተባለ ቦታ ነው። አሉላ የገበሬ ልጅ ናቸው፤ የመሳፍንት ዘር የላቸውም። አባታቸው እንግዳ ቁቢ አሉላን ጨምሮ ሌሎች ልጆቻቸውን ራስንም ሆነ ሀገርን ከጥቃት መከላከል እንዴት መማር እንደሚቻል ያስተምሯቸው ነበር። አሉላ ግን ከሁሉም የላቁ ነበሩ። አሉላ በልጅነታቸው በዙቅሊ ሚካኤል ደብር ከመምህር ወልደጊዮርጊስ ዘንድ ሐ ይማኖታዊ ትምህርት ተምረዋል።
ኢትዮጵያን የመውረርና ቅኝ ግዛቷ የማድረግ ሕልሟን ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ኢጣሊያ በየካቲት 1888 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችውና እጅግ አሰቃቂ ሽንፈትን በተከናነበችበት የዓድዋ ጦርነት ላይ አኩሪ የጀግንነት ታሪክ ከፈፀሙት ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች መካከል አንዱ ራስ አሉላ ነበሩ። ራስ አሉላ በጦርነቱ የጀኔራል ቪቶሪዮ ዳቦርሜዳን ጦር በመደምሰስ የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ከሌሎቹ ወራሪዎች በበዛ መልኩ ክንዳቸውን ደጋግሞ እንዲቀምስ አድርገውታል።
ራስ ሚካኤል
ከዓድዋ ቀደም ብሎ የመጀመሪያው የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት አምባላጌ ላይ ህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም ተካሄደ። አምባላጌ ላይ የራስ መኮንን፣ የራስ ሚካኤልና የራስ መንገሻ ጥምር ጦር ለሁለት ሰዓታት ያህል ተራራውን ከቦ ከተዋጋ በኋላ የጣልያንን ጦር ድባቅ መትቶ መሪውን ሜጀር ቶሰሊን መግደል ችሏል። እንደ ጆርጅ በርክሌይ ገለጻ ራስ ሚካኤል በአምባላጌው ጦርነት ላይ 15 ሺ ጦር በማሰለፍ አኩሪ ተጋድሎ ፈጽመዋል።
በዓድዋው ጦርነት በጄኔራል ኦሬስቴ ባራቲየሪ ዋና አዝማችነት የተመራው የጣልያን ጦር በሶስት አቅጣጫ ነበር ወረራ የፈጸመው። ጄኔራል ዳቦር ሚዳ በቀኝ በኩል የዘመተውን ጦር ሲመራ አልበርቶኔ የግራውን ግንባር መርቷል። የመካከለኛው ግንባር ደግሞ በአሪሞንዲ ነበር የተመራው። አራተኛው የጄኔራል ኤለና ጦር ደግሞ ተጠባባቂ እንዲሆን ተደርጓል።
በኢትዮጵያ በኩል ወደ ዓድዋ የዘመቱትን የጦር አዝማቾችና ያዘመቱትን የሠራዊት ብዛት ስንመለከት ከንጉሠ ነገሥቱ በመቀጠል ሁለተኛ የሚባለውን ሠራዊት ይዘው የዘመቱት ራስ ሚካኤል ናቸው። የጣልያን ጦር የካቲት 22 ቀን ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ሊነጋጋ ሲል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዓድዋ ጦር ግንባር ደረሰ። ከደቂቃዎች በኋላም ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ በዓለማችን ታሪክ ላይ ደማቅ አሻራ ጥሎ ያለፈው ታላቁ ጦርነት ተጀመረ።
በዚህ ጦርነት በመካከለኛው ግንባር ራስ ሚካኤል ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከጠላት ጦር ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው በአሪሞንዲ የተመራውን ጦር ድባቅ መትተዋል። መሪው ጄኔራል አሪሞንዲም በጦርነቱ ተገድሏል። የራስ ሚካኤል ሚና በዚህ የተገደበ አልነበረም። ከዳቦር ሚዳ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሲፋለም የነበረው የራስ አሉላ ጦር ከፍተኛ ጫና ላይ ስለነበር አፄ ምኒልክ የራስ ሚካኤል ጦር ወደ ስፍራው ሄዶ እገዛ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጡ። በመሆኑም የተመደበበትን የመካከለኛውን ግንባር ኃላፊነት ከተወጣ በኋላ ከዳቦር ሚዳ ተናንቆ የነበረውን የራስ አሉላን ጦር ለማገዝ ወደ ግራ ግንባር ተንቀሳቀሰ።
በመጨረሻም ሁሉም የኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች ግንባር በመፍጠር ፊታቸውን በአልበርቶኔ ወደሚመራው የግራ ግንባር አዞሩ። የሚካኤልም ጦር እንዲሁ። ጥምር ጦሩ እኩለ ቀን ላይ ሙሉ በሙሉ የጣልያንን ጦር ደመሰሰ። መሪውን አልበርቶኔንም ማረከ። ጦርነቱ በግማሽ ቀን ውስጥ በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ሲጠቃለል ሀምሳ ስድስቱም የጣልያን መድፎች፣ በርካታ ከባድና ቀላል መትረየሶች እንዲሁም ጠመንጃዎች ተማርከዋል። ከእነዚህም የተወሰኑት በራስ ሚካኤል የተማረኩ ሲሆን ከፊሎቹ በደሴ ሙዚዬም ይገኛሉ።
ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ
የኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ ሲነሳ፤ በግንባር ቀደም ከሚጠቀሱት መካከል ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉት ጦርነቶችም፤ መድፉን ወደ ጠላት ወረዳ ተኩሶ… ጠላትን የሚያርበደብድ ጀግና ናቸው። በተለይም ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር ባደረገችው የ1888 ዓ.ም. ጦርነት ወቅት፤ በመቀሌ፣ በአዲግራት እና በዓድዋ ተራሮች መድፉን ጠምዶ፤ የጣልያንን ጦር ከርቀት በመምታት ዝናን ያተረፈ ጎበዝ ተሰኘ። በማዕረግ ላይ ሌላ ማዕረግ ተጨምሮለት… ደጃዝማች ተብሎ ስማችው በወርቅ ቀለም ከተጻፈላቸው ጀግኖች መካከል አንዱ ሆኖ ተጠራ።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. የዓድዋ ጦርነት እለት…. የጦሩ ዋና ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው በጦርነቱ ላይ ሲሰው አጼ ምኒልክን ጨምሮ ብዙዎች አዘኑ። በዚህን ጊዜ ምኒልክንም ሆነ ህዝቡን ለማጽናናት፤ “ገበየሁ ቢሞትም ባልቻ አለልዎ” ለማለት ጭምር እንዲህ ተባለ። ገበየሁ ቢሞት፣ ተተካ ባልቻ፤ መድፍ አገላባጭ፣ ብቻ ለብቻ። ተብሎ ተፎከረ።
ባሻ አውዓሎም ሐረጎት
ባሻ አውዓሎም ሐረጐት ካልተዘመረላቸው የዓድዋ ጀግኖች አንዱ ናቸው። ባሻ አውዓሎም በኤርትራና በትግራይ የሚመላለሱ ነጋዴ ነበሩ። ቀደም ሲል ራስ አሉላ ጣሊያኖችን እየሰለሉ እንዲነግሯቸው፣ የኢትዮጵያን ጦር ምስጢር ደግሞ አሳስተው እንዲጠቁሟቸው ከባሻ አውዓሎም ጋር ተስማምተው ነበር።
በዚህ መሠረት፣ ባሻ የኢትዮጵያ ጦር ከኪዳነ ምህረት ገሠሦ ጀርባ ባለ ተራራ ላይ መመሸጉን ለጣሊያኖቹ ይነግራሉ። ስለዚህ ጀኔራል አርሞንዲ ጦሩን እየመራ ኪዳነምህረት ገሠሦ ተራራ ላይ ይመሽጋል። በዚህ ጊዜ እነ ራስ አሉላ በጀርባው ቆርጠው ገብተው መድፍ ሲተኩሱ ከዓድዋ 10 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ መሆኑን አርሞንዲ አያውቅም ነበር። ስለዚህ፣ ለተቀረው ጦር “ገብቻለሁ” ሲል በተመሳሳይ ሰዓት ከሦስቱም አቅጣጫ ተኩስ ተከፈተበት።
እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና የማይሸነፍ የሚመስለው የአውሮፓ ቅኝ ገዥ በጦርና በጐራዴ የተሸነፈበትና የተዋረደበት በመሆኑ ክብር ተሰጥቶት ለቀጣዩ ትውልድ ታሪኩ በክብር መሸጋገር አለበት። የምኒልክ ጦር ጣልያን ከምሽጉ እንዲወጣ የተዘየደው ነገር በኢጣሊያኖች የሚታመን የኢትዮጵያ ሰው በኩል የተሳሳተ መረጃ በማቀበል ከምሽጋቸው ወጥተው ውጊያውን እንዲጀምሩ ማድረግ ነበር። ይህንንም ለጀግናው የጦር አለቃ ራስ አሉላ አባነጋ አማከሩና ራስ አሉላ ቀድሞ ለራሳቸው እና በኋላም ለጣሊያን ስለላ ይሰሩ የነበሩ አውዓሎም የተባሉ ነጋዴ ጣልያንን መረጃ እንዲያስቱ በእርቅ ከአፄ ምኒልክ ጋር እንዲገቡ ተደረገ።
አፄ ምኒልክም ይቅርታ አድርገውላቸው እቴጌ ጣይቱም በእህል ውሀ ሰበብ “አውዓሎም ይህ የምትበላው እንጀራ ቁርባን ነው” ብለው በአፄ ምኒልክና በመኳንንቱ የተዘጋጀውን ወጥመድ እንዲፈጽሙ አስማሏቸው።
ለጣሊያኑ ጄነራል ‘ኢትዮጵያኖች በእለተ እሁድ ቤተክርስቲያን የመሳለም ልማድ ስላላቸው፤ የካቲት 23 ሰንበትም ብዙው ወታደር አክሱም ፅዮን ለመሳለም ስለሚያቀና የቀረውም ምግብ ፍለጋ በመበተኑ ንጉሠ ነገሥቱ ብቻቸውን ይሆናሉ በጠዋት ማጥቃቱ ቢጀመር ድሉ ያለምንም ጥርጣሬ የጣሊያን ይሆናል” ብሎ አሳመነ።
በዚህም የጠላት ጦር ንጉሠ ነገሥቱን ብቻቸውን ሊወጋ ቋምጦ ሲገሰግስ ከዓድዋ ሠፈር ተቃረበና ጠዋት በአሥራ አንድ ሰዓት ርችት አሰማ። የምኒልክም ሠራዊት አድፍጦ ሲጠባበቅ አድሯልና አፀፋውን መለሰ። በዚህ ጊዜ አፄ ምኒልክ የዓድዋን ጦርነት ከፈቱ። ጦርነቱ ሲፋፋም አውዓሎምና ጓደኛው ወደ ወገናቸው ጦር ሲቀላቀሉ ያየና ነገሩ የገባው ጄነራል “አውዓሎም አውዓሎም” እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምተው “ዘወአልካዩ እያውዕለኒ” ብለው አፌዙበት። (በዋልክበት አያውለኝ እንደማለት ነው) ውጊያም በግማሽ ቀን ተጠናቆ ቀኑን ሙሉ ምርኮና አስክሬን ሲሰበሰብ ውሎ ከምሽቱ በአሥራ ሁለት ሰዓት ድሉ የኢትዮጵያ መሆኑ ታወቀ።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013